ይሕንን ማን አደረገ?
በታሪካዊው በአጼ ፋሲል ግንብ
ውስጥ እያንዳንዱን ክፍሎች ስመለከት፤ በተለይ በጠላት የደረሰውን ጣራ ስመለከት ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ኃይል ሆነኝ!
በጣም ለማደንቃቸው ጸሐፊያን፡፡ ወደዱም ጠሉም፤ አወቁም አላወቁም በኔ ላይ ይሕንን አድርገዋል፡፡ እነዚህና በዘመኖቻቸው ብቅ ያሉ ዘመዶቻቸው ፡- ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም፣ ሙልጌታ ሉሌ፤ አለማየሁ ገላጋይ፣ ኤፍሬም ስዩም እና አሌክስ አብርሃም!! በቅ/ተከተል ፡- በ “ሰው” ዊነት፣ በትጋት፣ በታሪክ ምጥቀት፣ በቅኔ/ፍልስፍና፣ በፈጠራ፡፡ የእነዚህ ውህደት ይሕንን አደረገ፡፡
#ተስፋ #በላይነህን
የስንዴ ዘር ውስጥ እንክርዳድ
አለ፡፡ የስንዴ መንግስት እንዳለ ሁሉ የእንክርዳድ መንግስትም አለ፡፡ ስንዴ ህዝብ እንዳለ ሁሉ፤ እንክርዳድ ሕዝብም አለ፡፡ የመከር
ጊዜ ሲመጣም ስንዴውን ከእንክርዳድ እንደሚያበጥረው የታወቀ የተፈጥሮ ህግ፤ የእናቶቻችንም ልማድ ነው፡፡ ስንዴ በጎተራ ይቀራል፤ እንክርዳድ በነፋስ ይ..ጣ..ላ..ል!
ከመጽሐፍት ሁሉ እጅግ የገነነ፤
በመታተተም ብዛትም ሆነ በብዙሃን ልሳናት በመተርጎም፤ ለሰው ልጅ መለያዬትም ሆነ አንድነት ፈር ቀዳጅ፡፡ ይሕ መጽሐፍም በኔ ላይ
ይሕንን አደረገ፡፡
ሥለምን “ሴቶቹ” ጠሉት? ሥለምንስ
“ካህናቱ” ዘጉት/ዘነጉት? ሴቶቹ ካህናት መሆን ካልቻሉ፤ ካህናቱም መግለጥ ከተሳናቸው… ሥለምን እንዲህ ሆነ? ይሕንንሥ ማን አደረገ?
ወደ ኋላ ወደ 17ኛው መቶ ክ/ዘመን
ተሻግረናል! ጠላት ይሕችን አገር በተደጋጋሚ ሊበታትናት፤ ሊቆራርጣት፤ የራሱን ሐሳብ ሊዘራባት፤ መሬቷን ሊያርሰው ይፈልጋል፡፡ አደረገም!
እስኪ አሁን ደግሞ ወደ ኋላ
አንድሺህ አመት ደግሞ እንመለሥ፡፡ ከአስራ ሰባተኛው ክ/ዘመን ወደ 7ኛው መቶ ክ/ዘመን፡፡ ይሕች አገር ህዝቦቿ የቀይባሕር ነፋስ
የተነፈሱ፤ ፈረሶቻቸውን ቀይባሕር ያጠጡ፤ የብሔረ ነጋሽን ቆላማ እና ደጋማ ደረቅ እና ነፋሻማ አየር የቀዘፉ ናቸው፡፡
አሁን ደግሞ ወደ ፊት እንሂድ፤
ዘመኑን ቁጠሩና ድረሱበት፤ ሆኖም ግን አሁን ላይ እንገኛለን፡፡ ከ7ኛው ክ/ዘመን ወደ 21ኛው ክ/ዘመን፡፡ በ17ኛው ክ/ዘመን ተገንብተው
በነበሩ የኪነ-ጥበብ ትሩፋቶች ውስጥ ባንደኛው፡፡
ጣሪያው ፈርሷል፤ ሬሳ የወጣበት
የሚመስለው እልፍኙ፤ እስትንፋስ አልባ ፍጡር የሚመስለው ግንቡ፤ ሰው አልባ ቤት፤ እግር አልባ ፈረስ መስሏል፡፡ ሽኮናው እንደተሰነጠቀ
ፈረስ፤ ለእርድ እንደተቀጠቀጠ ወይፈን/ጃንደረባ/ የስነ ልቡና ጽልመት
ተከናንቧል-ቤቱ፡፡ ይሕንን ማን አደረገ?
‹‹… በእርሻው መካከል ዘርን የዘራ ሰው ትመስላለች፡፡ ሰዎቹ ሲተኙ ጠላቱ መጣና በስንዴው
መካከል እንክርዳድን ዘርቶ ሄደ፡፡ ስንዴውም በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ደግሞ ያን ጊዜ ታዬ፡፡ የባለቤቱም ባሮች ቀርበው፡
ጌታ መልካምን ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልንበርህምን? እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? አሉት፡፡›› እርሱም… አሁን እኛ የምንጠይቀውን ጥያቄ መልሥ ሠጠበት…/ወደ ኃላ እንበላበታለን/!!
ይህን የቆምኩበትን ጣሪያ ማን
አፈረሰው? አሁን የቆምኩበትን ህንጻ ማን ገነባው? አሁን የቆምኩበትን ህንጻ ሕይወት ማን ነጠቀው? በውስጡ የነበሩ የዝሆን ጥርስ፣
የአልማዝ እና እንቁ ጌጣጌጦች፣ የውድ ሽቱ ዕቃዎች፣ ሥልጣኔዎች፣ ሰረገላዎች፣ ከእነዚህም ሁሉ በላይ የዚህን ቤት ‹‹ሰው አልባነት
ጠኔ›› ማን አሰለጠነው? ይሕንንሥ ማን አደረገ?
የጥበብ ጠያቂዎች ይህንን ይጠይቃሉ!
ዕድሜ ዘመናቸውን የሚኖሩት ሲጠይቁ ነው! የትናንትናውን ጥያቄ ፈጽመው አይጠይቁም፡፡ በነጋ በጠባ፣ ወፍ በጮኸ ቁጥር ግን አዲስ
ጥያቄዎችን ከፀሐይ ጨረር እንደ ቅጠሎች ይመገባሉ! ጠቢባን ይጠይቃሉ፡፡ ይሕንን ማን አደረገ? እያሉ…!
ፈረሶቻችን ወዴት ለገሙ? የሚከንፉበት
ረጃጅም ክንፎች ወዴት ተሰበሩ? ልጓም አልባ ምናባቸውስ የት ተወሳሰበ? የቀይ ባሕር ውሃሥ እንዴት የሙት ባሕር ሆነ? ይሕንንሥ
ማን አደረገ…? እያሉ ይጠይቃሉ!
በ17ኛ መቶ ክ/ዘመን የአጼ
ፋሲል ንግስና ኢትዮጵያን በሯን ዘግታ እንድትቀመጥ፤ የቀይ ባሕር ግዛቷን እንድትከልል ሆነ፡፡ መተማንም የንግድ መዓከልነቷን አጠናከረ፡፡
አሁን ግን ይሕ ሕንጻ ጣሪያ አልባ ሆኖ ይታያል- ያንጠባጥባል! ያፈሳል! ሕይወት አልባ ሆኗል! የሚሞቀው የሚደምቀው የነግስታት
ቤት ጣሪያው ተነስቷል! ይሕንን ማን አደረገ?
ጣልያን ይሁን ሱዳን ይሁን ቱርክ
ይሁን ግብጽ ይሁኑ ፖርቹጋሎች አሊያም እንግሊዝ ይሕንን አደረጉ!
የነገስታትን ርስት ወረሱ፣ ጣሪያ አፈራረሱ… የቀይ ባሕርን በፈርኦን በትር/በሙሴ ያይደለ/ ጣኦት ከሁለት ከፈሉ፡፡ ነገስታትም እጃቸውን ታጥበው ተመለሱበት፤ ከዛን ቀን ጀምሮ
ቀይ ባሕርን አልተሳለሙትም፡፡ ፈረሶቻቸውም ቀስ በቀስ ልጓሞቻቸቸው ጠበቁ፤ ክንፎቻቸውም ረገፉ፤ በእግሮቻቸውም ተደፉ፤ አፈር ላሱ…
ይሕንን ማን አደረገ?
ሥለ እርሻው ስንዴ እና እንክርዳድ
እንመለስ፡፡ መምሕሩን ጌታ መልካም ዘር በእርሻህ ዘርተህ አልነበርህምን?
እንክርዳዱንስ ከወዴት አገኘ? ብለውት ነበር፡፡ እርሱም ምን አላቸው? እርሱም፡- ጠላት ይሕን አደረገ! አላቸው፡፡
ጠላት ይሕንን አደረገ!! ጠላት
ምን ያደርጋል? ጠላት ቤት ያፈራርሳል! ከርስት ያስነቅላል! ልጓም ያጠብቃል!! ነጻነት ያሳጣል!! ጠላት ጣሪያ ያፈራርሳል- ታሪክ
ይገድላል- ጠላት ወደ አምላክ ያስጮሃል!!
‹‹ባሮቹም፡- እንግዲህ ሄደን ብንለቅመው ትወዳለህን? አሉት፡፤ እርሱ ግን፡- እንክርዳዱን
ስትለቅሙ ስንዴውን ከእርሱ ጋር እንዳትነቅሉት አይሆንም፡፡ ተውአቸው እስከ መከር ጊዜ አብረው ይደጉ በመከር ጊዜም አጫጆችን፡-
እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው እሰሩ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ እላለሁ አለ፡፡›› እንክርዳዱን አስቀድማችሁ ልቀሙ በእሳትም ለማቃጠል በየነዶው
እሰሩ ስንዴውን ግን በጎተራዬ ክተቱ… አምላክም ይሕንን ያደርጋል!!
No comments:
Post a Comment