May 26, 2014

አባቴን ያጣሁበት 23ኛ ዓመቴ

#አባቴን ያጣሁበት #23ኛ ዓመቴ
እናንት ጸሐፊዎች ላይ ላይ ስለሚታየው ነገር ከምትጽፉ የግለሰብን ስሜት ብታንጸባርቁ ሙያው ያድጋል..አለኝ አንድ የዚህ ባለታሪክ ባለቤት፡፡
“ጸሐፊ”? ብዬ በማቅማማት ታሪኩን ሰማሁት!! እውተኛ ነው….

‹‹አባቴን ያጣሁበት 23ኛ ዓመቴ››
TesfaBelaymeh
አስተምራለሁ፤ የተማሪዎች ዝቅጠት እኔንም ስለሚያስጠይቀኝ ሌት ተቀን እማስናለሁ፤ የደሜን ወዝ እንደማልወደው ሁሉ ሥራየንም እንዲያስጠላኝ እየተፈታተነኝ ሥለሆነ፤ የሁለንተናዬ መዝገብ እንዳይዘጋ ስማስን 23ኛ ዓመቴ ዛሬ ደፈንኩ፡፡
በሰልፍ ሜዳ ላይ፤ ጥቋቁር  ጸጉሮች ጣል ጣል ባደረጉበት፤ የእድሜ ትኩሳት በጠበሰው አይን፤ የዓመታት ክምር የገመደው ክትፋት በግንባሩ ላይ ተስሏል፡፡ እኔም በዚህ እድሜዬ እንዲያ ሽበት ጣል ጣል ያደረገብኝን ምክንያት በኋላ እነግራቹሃለው፡፡ እርሱ ዋት ነኝ ሲል እኔን እያስረጀ ነው፡፡ትልቁ ሽበታም ሰውዬ የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር መሆኑ ነው!! በጡረታው ሰዓት ምን ይሰራል? ብዬ ሳስብ እና የቤቱን ጓዳ ሳልመለከት መፍረድ እንደሚያስኮንነኝ ስለተረዳሁ፤ ተቆጠብኩ፡፡ በቤት ውስጥ ያሉ የልጅ ልጅ ነፍሳት ምን በልተው ያድራሉ?
 የርዕሰ መምህሩን ፊትና ጀርባ ሳሰላስል የግንቦት 20 መፈክር ከእሳቸው አፍ ሲወጣ፤ በዚህ በሽምግልና ወረታቸው /ይቅርታ/ ወራታቸው እንዲህ የሚንተገተግ ልሳን ስሰማ ደነቀኝ! እኔ ይሄው ግንቦት በጠባ ቁጥር፤ ዕድሜየን እገብራለሁ፤ ጸጉሬን አሸብታለሁ፤ እድሜዬን በሙሉ የምቆጥረው የኢህአዴግ በዓል፣ ደርግ የወደቀበት፣ ጸረ- ህዝብ መንግስት የተገረሰሰበት .. እየተባለ ሲለፈፍ ነው፡፡ ወይ እኔ እድሜየን ማክበር መቁጠር/ማቆምም አለብኝ፡፡ አሊያም ግንቦት 20ን መደገፍ!!?? እንዴት ነው…. እድሜ መቁጠርን የምናቆመው? እንዴትስ ነው ግንቦት 20ን መደገፍ የምችልው?
እድሜን ከመቁጠር ለማቆም የሚረዱ መንግዶችን ሁሉ ሞክሬያለሁ፤ የመጀመሪያው ራስን ማጥፋት ነው-አይሆንም! ቀጥሎም ይህንን ወር ጥሎ መጥፋት ነው- አይሆንም! አገር ጥሎ መጥፋት- ይህም ቢሆን ግንቦት የትም አገር ላይ የምትገኝ ወር ፤ 20ም የትም ቦታ የምትገኝ ቁጥር፡፡ ታዲያ ይህቺን ቀን እንደምን ተደርጎ አለመቁጠር ይቻላል? ምነው ይህቺን ቀን ጠላሃት ልትሉኝ ትችላላችሁ!? 23 ዓመት ይዤው የነበረውን ቁስል አሁን ላወጣው ነው!!  ከእናቴ የሰማሁትን እንዲህ ነው…
አባትህ በሻለለቃነት ማዕረግ ፤ የደርግ ባለስልጣን ነበር፡፡ኢሰፓ አልነበረም፡፡ ግንቦት ወር 1983 ገንጣይ አስገንጣይ የሚላቸውን የሰሜን አመጸኞች ለመግታት ሲል እንኳን የወታደር አለቃን የዩኒቨርሲቲ ተማሪችን ማሰለፍ ግድ ሆኖበታል!! አባትህም ወደ ደብረታቦር ከሄደ ሰነባበተ፤ ጦርነቱ አይሏል… በዜና የምንሰማው መርዶ፤ ከየቦታው የሚሰማው የመድፍ እና የጥይት ጩኸት እንኳን እርጉዝ ጠንካራ ወንወድንም ያንበረክካል፡፡ ግንቦት 13 ሁሉም ነገር ሲያበቃለት፤ የአባትህ ሞት ተሰማ… እኔንም ጽንሱ ተቆጣኝ… የአባትህን ሞት ስሳማ እንባዬ ወደ ውጭ ሳይሆን ወደ ውስጥ አነባሁት፤ የጸጉር ሽበት ምክንያት የእናቴ የውስጥ እንባ ነው! የአንዱ ውልደት ለአንዱ ሞት ነውና አባትህን የተላቀቀው ነፍስ ወዳንተ መጣ፤ አንደተን ወለደ፡፡ አለችኝ!!

ግንቦት 20 የእናቴ የውስጥ እንባ ምክንያት፤ ለኔም የሽበት መንስዔ ፤ ያለድሜዬ ከአገር እና ከዘመን መሸሸጊያ ፤ የአባቴ ሙት አመት መታሰቢያ ጠላ እና እንጀራ የምሸከምበት፤ ወንድሙን ገድሎ የሚፎክረውን ወንድሜን የምሰማበት… 23ዓመት የተጠመደ ቀንበር!!
 ግንቦት 20 ለኔ??

 በዚህ በዓል ላይ የታላቁ ሽበታም ስውዬ የመፈክር ጩኸት ግርም እያለኝ ነው፡፡ ይሄ ሰውዬ በግምት የ65 ዓመት ዕድሜ  አዛውንት ይሆናሉ… ከዚህ መንግስት ጋር ያላቸው ግንኙነት የእድሜያቸውን ሲሶ ብቻ ነው… ያውም በቀደሙት ስርዓቶች ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ይሳተፉ እንደነበር አጫውተውኛል!! ያለፉት ስርዓቶች በተለይም ከዚህ የቀደመው ከዚህኛው ስርዓት ጋር በርዕዮተ አለም ቅርጽ እንደማይገናኙ ራሱም መስክሮልኛል፤ የዚህ ስርዓት ደጋፊም እንዳልሆነና ፈጽሞ እንደማይደግፈው በተደጋጋሚ ገልጾልኛል!! ታዲያ ይኼ ሁሉ መፈክር ከየት እየወጣ ነው?

ይህ በተጨማሪ የእድሜዬንና የዘመኔን ሽሽት የፈጠረብኝ ነው! ግንቦት 20 ሲመጣ እየሸበትኩ ነው፤ የአባቴን ገዳይ ሽለላ እና ፉከራ እየሰማሁ ነው!! ስትፎክሩ የአባቴን  ሞት እየዘፈናችሁበት ነው…. 

No comments: