Mar 29, 2014

ሔዋን የመጀመሪያዋ ባርያ ነች!

                                                                                                                                                                                    ተስፋ በላይነህ
ሔዋን የመጀመሪያዋ ባርያ ነች!

ፕሮፌሰር መስፍንን እናውቃቸዋለን፤ ጽሑፎቻቸውን ለበርካታ ዓመታት ሲያስነብቡን እውቀት በፈቀደላቸው ሰፊ ውቅያኖስ ውስጥ እየዋኙ ጨልፈው ከሚሰጡን ጭልፋ ውሃ ስንጠጣ ኖረናል፤ እየጠጣንም ነው፤ አስትንፋሳቸው እስካለች ድረስ ማጠጣታቸውን የሚያቆሙ አይመስሉም፡፡ከ30ሺ ቀናት በላይ ስትንቦገቦግ የኖረች እና ያለች እስትንፋስ የተፈጠረችበትን አላማ አልሳተችም… እስትንፋስ ይስጣቸው….!

ሆኖም አንድ ግለሰብ ከእውቀት ባህር እየጨለፈ ሲያጠጣ ሌላኛው ግለሰብ የሚቀበለውን መጠጥ እንዳለ ሊጋትአይገባውም፡፡ የባርነት አነሳሱም ይህ ነው!! አሰስ ገሰሱን መጋት/ጠበቅ ይበል/ የባርነት አነሳስ እና መንገዱ ነው!                                                                                       
ለምን ብሎ ሳይጠይቅ ‹‹ተቀባይ›› ፍጥረት በባርነት ቀንበር ጥማድ ውስጥ እንዳለ ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ 
‹‹እምቢ›› ባይነት ለአምላክ ሳይሆን ለፍጡራን ሆኖ እንደ እውቀት ደረጃ እና አስተሳሰብ ልቀት ብስለት ሚዛናዊ ለሆኑ መልሶች መገዛት አለብን…


ፕ/ መስፍንም በፋክት መጽሔት ቁጥር 38 መጋቢት 2006 ዓ.ም ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? ሲፈቅድ ወይስ ሲፈቀድለት?” 
በሚል ርዕስ አንድ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ በሁለተኛ ክፍልም አስነብበውናል፡፡ ጽሑፉ ለወ/ሮ መስከረም/የፋክት መጽሔት አምደኛ/ መልስ ሆኖ የቀረበ ነው፡፡ 
በበኩሌ በማጠቃለያ ሃሳቡም ሆነ በርዕሱ ጭብጥ ተስማምቻለሁ፡፡የጎረበጠችኝ ሃሳብ ግን አለች፡፡ 
ብዙውን ጊዜ የሰው ሃሳብ ላይ የምንወስደው ነገር ሁሉ እንዳለ መዋጥ እንደሌለብን ከላይ የገለጽነው በመሆኑ፤ ፕሮፌሰር መስፍን ‹‹እንዲያውም ከዚህ በፊት እንደጻፍሁት ሔዋን የመጀመሪያዋ አብዮተኛና የነጻነት እናት ነች ለማለት ይቻላል›› ተብሎ የተገለጸው ሃሳብ ወደ ሌላ ጭብጥ የሚወስደን በመሆኑ የግል ምልከታየን ለመሰንዘር ተገደድሁ፡፡

የፕሮፌሰር ጽሑፍ ባርያ በራሱ ፈቃድ እቅመ ቢስነቱን ተቀብሎ የሚኖር ከሆነ እና በቀጣይ ለሚደርሰው ችግር 
እና የጭቆና ግፍ ሁሉ ተጠያቂ ገዥውን ጌታውን ብቻ ተጠያቂ አድርጎ የሚኖር ከሆነ ሎሌነቱ የመነጨው ራሱ ባስቀመጠው “እሺ ባይነት” የራስ ድካም መሆኑን ማመን እንዳለበት ለማስረዳት የተቀመጠ ሃሳብ ነው፡፡ እውነትነት አለው፡፡ ለውጥ ሁልጊዜም የሚጀምረው ከውስጥ ነው-በፈቃድ፡፡….
ሔዋን የነጻነት አርበኛ ሆና ልትቀርብ የቻለችበት ሃሳብ በሚገባ ሊጤን የሚያስፈልገው አደገኛ አስተሳሰብ ነው!! ከዚህ በፊት አንድ ጸሐፊ ዲያቢሎስን ‹‹የመፈንቅለ መንግስት አለቃ›› ብሎ በማሞካሸት ያቀረበውን ሐሳብ በውሥጡ የያዘውን መርዝ ለመፈተሸ ሞክሬ ነበር/ይስማዕከ ወርቁ/ ፡፡ 
በ‹‹ሳታኒዝም›› እምነት መሰረት ዲያቢሎስ አምላክ ሆኖ የሱ ጠበቃዎችም ‹‹አምላክ ነን›› ለሚሉት መብታቸው ሆኖ እንደሚቀጥል የነጻነት አምላክ የሰጣቸው ምርጫ በመሆኑ ለመፍረድ አንሸነጋገልም፡፡ “አማልክት ትሆናላችሁ” የሚለው የውድቀት አነሳስ ለባርነት መነሻ እና መንገድ መሆኑን ከሚያምኑት ምዕመን በመሆኔ ግን የሔዋንን የነጻነት አርበኝነት አጥብቄ እከራከራለሁ፡፡ ከፕ/ር መስፍን ጽሑፍ ጋር  የቀረበው ስዕል /የተበጠሰ ሰንሰለት በጸሐይ ብርሃን የታጀበ/  ከሔዋን ‹‹እምቢ ባይነት›› በስተጀርባ የተገኘው ብርሐን ነው ወይንስ ጨለማ?ብለን እንድንጠይቅ ያስገድደኛል፡፡

በእየሱስ ክርስቶስ ትምህርት ተለክፎ/ ተመስጦ/ እውነትነትን አምኖ በዚህ ክበብ ውስጥ ሆነን ግን 
‹‹ዲያቢሎስን የመፈንቅለ መንግስት አለቃ›› ብሎ ማሞካሸት
 ፤ ኄዋንን ‹‹የነጻነት አርበኛ›› እና ‹‹አብዮተኛ›› ብሎ ማስቀመጥ አደገኛነቱን ልንገነዘበው የሚገባ ይመስለኛል፡፡


ሲጀመር ሔዋን በራሷ ፍላጎት ነበር እንዴ የ‹‹ነጻነቱን›› መንገድ መርጣ የወሰነችው? ይህ አስተሳሰብ አንድም ሔዋንን ከጀርባዋ የነበረውን አለማስታወስ አሊያም ከጀርባዋ የነበረውን ማወደስ ነው፡፡
ከዚህ በተረፈ ግን ባርያ ነጻ የሚወጣው ራሱ ፈቅዶ እንጂ ሌላኛው ‹‹ባርያ›› ባስቀመጠለት የባርነት መንገድ አይደለም… የሔዋን ‹‹ነጻነት›› መንገድ እና ‹‹አብዮተኝነት›› ዋናው ትልቁ ‹‹ባርያ›› ባስቀመጠላት ሌላኛው የባርነት ቀንበር ወጥመድ የተገኘ ጥልቅ ባርነት ነበር…! በባርነትም እንዳልነበረች…. የነበረችበትን የ“ቅድመ ርግማን” ሕይወት የባርነት አድርጎ መውሰድም ጭምር ነው!! በሚገባ ይፈተሸ፡፡ እርግጥ ነው በሌላኛው ምልከታ አጮልቀን ስናይ የሚያስረዳን ፍቺ እናገኝ ይሆናል ሆኖም ለሁለት ጌታ የሚገዛ ባርያ የለም በሚለው መርህ መሰረት ሔዋን የመጀመሪያዋ ባርያ ናት! ነጻነት እዳ የሚሆንበትም መንገድ አለ፡፡ ነጻነት ዕዳ የሚያስከፍል መንገድ ማስከተል የለበትም፡፡ ነጻነት ሌላ የጭቆናን ስርዓት እና ባርነትን ካስከተለ በምን መንገድ መው አብዮተኛ የሚያስብለው? የቆየው ባርነት ሌላ አስከፊ ባርነት ከመዘዘ የመጀመሪያው የነጻነት መንገድ ከባርነት ውጭ ምን ስያሜን ሊያስገኝ ይችላል?
“ሔዋን ሲነገራት የማትሰማ የመጀመሪያዋ ሰው ናት!” የሚለው አባባል ሐቅ አይደለም ብሎ የሚከራከር ሓሳብ አልያዝኩም፤ ለባርነት የመጀመሪያዋ ሰው እና ለነጻነት የመጀመሪያው ሰው ብሎ በማቅረብ  የተደባበሰውን ሌላኛው ሐቅ መደምሰስ አይቻልም፡፡ የሔዋን ዘር የተጨቆነ ነው ብሎ በማሰብ መላውን የሔዋንን ዘር ማካተት የመጀመሪያዋን የሔዋንን ‹‹እምቢ ባይነት›› /ለሌኛው እሺ ብሎ ሎሌ መሆንን በመቀበል/ ታሪክ የሚሽር በመሆኑ ፕ/ር ለመሞገት የተነሱበት ሐሳብ እንደሆነ ከጽሑፋቸው ለመረዳት እንችላለን፡፡
የዮሴፍ እጮኛ ማርያም የመጀመሪያዋ ለአምላክ የተመረጠች ሰው ነች /ልብ በሉ ሴት አላልኩም / ሰው ነው ያልኩት፡፡ ቀዳሚው አዳም እንዳለ ሁሉ ተከታዩ አዳምም አለ፤ የእጸ በለሷ ሔዋን እንዳለች ሁሉ የእጸ ህይወቷ ሔዋንም አለች፡፡ ይህንን ፕ/ር መስፍን ሳይረዱት ቀርተው ነው ብዬ ልገምት አልችልም፡፡ ክርስቶስን ያውቁታል እና፡፡ ሔዋንን የመጀመሪያ አብዮተኛ ያሉበትም ማዕዘን የማይካድበት ምልከታ እንዳለ ሆኖ ነጻነትን ለማግኘት ሲባል ብቻ ግን የትኛውንም የታሪክ ተሞክሮ ለነጻነት ተምሳሌትነት ማቅረብ በከፍተኛ ደረጃ የሚጣረስ ሐሳብ ነው፡፡ አንባቢያንም ይህንን አይነት ‹‹ውስጠ ወይራ›› አመለካከት እንዲያመዛዝኑ እና አበጥረው እንዲመለከቱ ለማሳሰብ ያክል ነው፡፡ “ሔዋን ሲነገራት የማትሰማ የመጀመሪያዋ ሰው ናት!” የሚለው አባባል ባሏን መርዝ አብልታ ነጻ የምትወጣ ሴትን ከማበረታታት ተለይቶ የማይታይ ሐሳብ ቤላኛው ጥግ ታይቶኛል፡፡ በትህትና ነጻ መውጣት ይቻላል-በትዕቢትም፡፡ በብዕር ነጻ መውጣት ይቻላል- በሰይፍም፡፡
ማርያም በትህትና ነጻ የወጣች የመጀመሪያዋ ሰው ስትሆን ሔዋን በትዕቢቷ ‹‹ነጻ›› የወጣች ሰው ናት…
ከሁለቱም ሔዋኖች የነጻነት ምርጫ የተገኘው ነጻነት የሚያሳየን ውጤት አመዛዝነን መወሰን የኛ ምርጫ ነው፡፡  ለምርጫ ያክል የሁለቱም ነጻ መውጣት ቀርቦልን ቢሆን ያስማማን ነበር፤ እኔም የኋለኛዋን ሔዋን ነጻ መውጣት መንገድ የምከተል እና ፕሮፌሰር መስፍንን ለዘመናት ሲታገሉለት የነበረውን ‹‹ጴጥሮሳዊነት›› መንፈስ ከኢትዮጵያዊነት ወኔ ጋር አጣምሬ የምከተል ሰው በመሆኔ ነጻ መውጣት የምንችለው- ነጻነት ማግኘት የምንችለው ሰዎች/ጨቋኞች/ በሚሰጡን የነጻነት መንገድ ሳይሆን በፈቃዳችን በመሆኑ፤ የምንደውሰደውን የነጻነት መንገድ በጥንቃቄ ልንፈትሽ እንደሚገባ ለማስጨበጥ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአለም ላይ እየተሰበከ ያለው ‹‹ነጻነት›› /ፍሪደም/ በጥንቃቄ ሊፈተሸ ይገባል፡፡ ዘፋኟ ማዶና ለነጻነት ‹‹ስትዘምር›› ከየትኛው ‹‹ጌታ››? እና ከየትኛው ‹‹ባርነት››? የሚለው ጥያቄ ሊከተል ይገባል፡፡ ወደ ዝርዝሩ አልገባም፡፡
ዋነው ቁም ነገሩ ነጻነትን በሃይልም/በአመጽም/ በፍቅርም/በትህትናም/ ማግኘት እንደምንችል መተማመኑ ላይ ሆኖ በሰብአዊነት መንፈስ ውስጥ ሆነን በትህትና የምናገኘውን ነጻነት፤ በፖለቲካ ትግል የምናገኘውን ነጻነት፣ በሰላማዊ ትግል የምናገኘውን ነጻነት እንደ መጀመሪያ እና ዋነኛ የባርያ ፈቃድ ውሳኔ አድርገን መውሰድ ላይ ብናተኩር የሚል ሐሳብ ለመያዝ ነው!! በዚህ ድምዳሜ ሔዋን የመጀመሪያዋ የነጻነት አርበኛ ልትባል አትችልም፡፡

“ሔዋን የመጀመሪያዋ ባርያ ነች የሚለው አስተሳሰብ” ፤ “የመጀመሪያዋ የአለም ህዝብን ለባርነት ቀንበር አስገባሪ ሰው” መሆኗ በሚለው ቢለወጥ፤  ሆኖም ግን መላው የሰው ልጅ/ የሔዋን ዘር/ በሙሉ እንዳይወቀስ የመጀመሪያዋ ትክከለኛው የነጻነት መንገድ ተምሳሌት የተባለችውን ብናስቀምጥ፤ የተሻለ እና ተመራጭ ምክር ከምንወዳቸው ፕ/ር እጠብቅ ነበር፡፡ አንድም በዚህኛው ጥግ ሳይመለከቱ ወይንም በቀጣይ ክፍል ሊያብራሩት አሊያም ‹‹የአመጸኛው ጌታ›› ሎሌ ሆነው የመረጡት አስተሳሰብ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ከሁለተኛው ክፍል ላይም አልተጠቀሰም፡፡
 የነጻነት አምላክ ፈጣሪም በሰጣቸው ነጻነት መሰረት የፈለጉትን ጌታ መምረጥ እንደሚችሉ እና ሔዋንን እንደ መጀመሪያዋ አብዮተኛ ተቀብሎ መከተል የገዛ ፈቃዳቸው መሆኑን እየጠቀስኩ ለጋራ ነጻነት እታገለላሁ፡፡  ለነጻነት እታገላለሁ!! ለነጻነት የነጻነት መንገዴ የገዛ ፈቃዴ ነው!! ሔዋን ግን የገዛ ፈቃዷ እንዳልነበር ዘፍጥረት አስቀምጦልናል፡፡ የሔዋን ነጻነት የተሰበከው በዲያቢሎስ ሲሆን፤  የመጀመሪያ ባርያ ሆና ያገለገለችም ሔዋን በመሆኗ፡፡ ሔዋን የመጀመሪያዋ አመጸኛ  የመጀመሪያዋ ‹‹የባርነት›› ፈር ቀዳጅ የሆነች የሰው ልጆች እናት ናት!! የመጀመሪያዋን ሔዋን ተከትለው ነጻነትን የሚሰብኩልን ሔዋኖች ከተፈጠሩ ዲያቢሎስ ጭፍሮቹን ያበዛል፡፡ ሁለተኛዋ ሔዋን ለመላው ሰው ዘር ነጻነት ተምሳሌት ለመሆን የምትችል ፈርጥ ናትና ሔዋኖችንም ሆኑ አዳሞች መላው የሰው ዘር የሚደሰትበት ነው፡፡ ሔዋን ግን የመጀመሪያ ባርያ ነበረች፡፡ ቸሩ ቸር ያቆየን!   

No comments: