የጤዛ ተስፋ
ጤዛን ተመስለው ለመትነን ተቋጥረው፤
ተውበናል ብለው ለመጥፋት በርትተው፤
ጦርንም ሰድረው ለመክፋት ጀግነው፤
ፋኖስንም ንቀው
ጠፈርንም ክደው ለመውደቅ ቸኩለው፤
እመኑን ይሉናል በጤዛ ማንነት
ውቅያኖስን ስለው!
***---***---***
ትላንት ነበር ሰኞ
ሳላውቀው አለፈ ያ ልጁ ማክሰኞ
ነጎደ ሰዓቱ፣
ከነፈ መዓልቱ፣
አበቅቴው አይሞላም ዘመነ ስሌቱ
ይመጣል ይተካል “አዲሥ ነኝ!”
እያለ ይደርሳል ዕለቱ፡፡
ዛሬ ቅዳሜ ነው! ጥቢ ነው ወራቱ
በውሻ ውውታ በጉጉቷ መርዶ ታጅቦ
ሌሊቱ
ተተካው ይለናል በማለዳ ወፎች
በንጋት ብስራቱ፡፡
***----***---***
የትላንቱ ሳይሆን ታድሶ የመጣው
ተሸሎ የወጣው በጎህ ተስፋ ያለው
የባሰ “የነጣ” ምስኪን “ባዶ”
ቀን ነው፡፡
ይሄዳል ይመጣል ፤ ይወርዳል
ይወጣል
ጊዜ ባዶ ሸራ፤
ወጣሪ የሌለው፤ ቀለም አልባ
ስዕል ትርጉም የለሽ ስራ
ብራናውም ሌማት -አብሮ ተወጥሮ
ብዕር አልባ ፊደል- ለቅሶና መከራ…
እኛን ሊለቀልቅ እኛን ሊሞነጭር
እኛኑ ሊጽፈን
ከጥቁር ጠጉር ላይ ነጭ ቀለም ስሎ ያለቀን አስረጀን!
ባዚም መንፈስ ቅዠት ህይወትን
አስውሎ
በንዋይ ትኩሳት በበለሱ ጣዕም
በክደት አስምሎ
ቁጭ ላለው አለት በሚቃመው ሬት
ተብትቦ አባብሎ
ሰላም ነው ይለናል በወሬው በዜናው
ቀላምዶን አታ’ሎ፡፡
***----***---***
ከጠይም ቆዳ ላይ የማይነበቡ
ፊደል የሌላቸው
ጨ..ምዳዳ ጽሑፎች በክታብ ተከትበው
በጥቁር ጠባሳ ወግ ባጣ ንቅሳት
በሃሞት ጠንቁለው
በልብ ሲቃ ህመም በህሊና ግዞት
ወገቡን አጉብጠው
ተራመድ ይሉታል መሄጃንዳለው
ሰው…!
መሪ በሌለበት አገር በሌለበት
ህዝቡም በታመሰው
“ተራመድ!” ይሉታል ተራመድ
ወደፊት እረኛ ‘ንደሌለው….!
በቀኝ የሚቆሙ ጻድቃን ነጭ ለባሾች
በጎች ናቸው ብለው፡፡
***---***---***
አለም ለፍየሎች ለቅጠል በጣሾች
“ስዕሉ ጥሩ ነው!” “ፊደሉም
ማለፊያ!” ለሚሉ ተንታኞች
ላድር ባይ አቀንቃኝ ላጨብጫቢ
ዳኞች
ለነዚህ ብቻ ነች…
ግማታቸው ከርሱ ቦርጫቸው ለሰፋው
ሕሊናን ደፋፍኖ ረግጦ ላሰረው
ሰውነትን ንቆ አውሬነት ለያዘው፡፡
***----***---***
አይ አለም…. !
ወደ ኋላ ባዶ ወደፈትም ሲኦል
የተሳለው ስዕል የተጻፈው ፊደል
ለማንም አይገባ -ለማን አይገመድ -ለማን ሳይፈተል
ሞት የሚባል `መልዐክ` መጥቶ ይወስደዋል
ለማይገባ ፊደል ለማይገባ ስዕል
ለስር ያቀርበዋል፡፡
ብራና ለሌለው ሸራው ላልተሰፋ
ሲኦል ለሚባለው ለዛ ክፉ ተስፋ!
ወርውሮት ይመጣል -ሌላኛውን
ዝናብ በሰው ላይ ሊያከፋ!
ለባለተረኛው “ታሪክ አልባ ትውልድ”
ጤዛውን ሊያካፋ…
የጤዛ
ተስፋ!
No comments:
Post a Comment