Jul 25, 2013

የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት




Prof_Mesfin-wolde maRiyAm
“የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት” የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የመጨረሻ ቃል?

እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ሉቃስ ፯፡፴፪

ተስፋ በላይነህ

  ሰሞኑን የክረምቱ ብርድ ሃይሏል፡፡ ዝም ላለ ህዝብ “ሬሳ ያስመስላል”፡፡ ሌሊቱንም የሚዘንብባቸው ቀናት በዛ ይላል፡፡ የሌሊት ሰላም ይናፍቃል! ጸሐፊዎቻችንም መጽሐፍ እያወጡልን ነው፡፡ መሪዎቻችንም ዝም ላለው ህዝብ ህግጋት እያወጡልን ነው፡፡ በዚህ አመት በርካታ መጽሐፍት የወጡ መሰለኝ፡፡ በርካታ ህግጋትም ጭምር፡፡  የባለፈውን ዓመት መጽሐፍት አሰባስቦ ያስተዋወቀን የዛጎል ቤተ መሐፍትን አመስግኑልኝ፡፡ እንዳለ ጌታ ከበደ ነበር አስተባባሪው፡፡ ባለፈው ዓመት መሪዎቻችን በሞት መተካካት ላሳየን ሞትን አስታውሱልኝ! ሞት ግን አይመሰገንም፡፡ ሞት ሲከበር  ካየን ግን ቆየን፡፡

 ዘንድሮ ጥቂት የማይባሉ መጽሐፍት ወጥተውልናል፡፡ መጽሐፍ አዙዋሪዎቻችን ተሸክመውት የሚዞሩት ነገር ያሳዝኑኛል፡፡ ህዝቡም ተሸክሞት የሚዞረው ሸክም ያሳምመኛል! አንዲት መጽሐፍ ለማንበብ ተሸክመን መዞር  የከበደን ሰዎች እጅግ በዝተናል፡፡ አንዲት እንጀራ ለማግኘት የምንንከራተት ሰዎች ተበራክተናል! በረከትም አጥተናል! መጽሐፍ አዟሪዎቻችን ግን በጀርባም በፊት ለፊትም ይዘውታል፡፡ ተሸክማ ይዞራሉ! መሪዎቻችን እንጀራ መሬቱን ተሸክመውታል! ተሸክመናቸው እንኖራለን!

 ከአንዳንድ መጽሐፍ አዟሪዎች ጋር የመግባባት እድል አጋጥሞኛል፡፡ በእውነት ያስደስታሉ፡፡ መጽሐፍ ከሚያነብ ሰው ጋር ማውራት እንዴት ደስ ይላል? ምንም በሃሳብ ባንግባባ የሌላውን መጽሐፍ ሃሳብ በማምጣት ያግባባናል፡፡ አንባቢ በሃሳብ ያፋጫል፡፡ ጦር መወራወር፣ ሰይፍ መማዘዝ የለም፡፡ በሃሳብ ብቻ መወያየት፡፡ ይህ ትልቅ ስልጣኔ ነው! ሰው ማለት ይኼ ነው! ከመሪዎቻችን ጋርም የመተዛዘብ እድል አጋጥሞኛል፡፡ ከመጽሐፍ አዟሪዎች ጥፍር እንኳ አይደርሱም! መሪዎች ያነባሉ/ ንብ ማንባት/ ፡፡ መጽሐፍ አዟሪዎች ያነባሉ/ ንባብ/ ባ ሲጠብቅ፡፡ አሊያም ያነባሉ እንባ!/ ባ ሲላላ/ ይህ ኢትዮጵያ ነውና!

 ታዲይ በዚህ ክረምት ሰሞኑን ከእጄ የሰነበተች መጽሐፍ “መልክዐ ስብሐት” ትሰኛለች፡፡ በዓለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት የተሰናዳቸው ይህች መጽሐፍ ስለ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር ማንነት የ27 ሰዎች የግል ዕይታን አቅርቦልናል፡፡ የሃሳቡን አምንጪ ዓለማየሁ ገላጋይ አመስግነናል፡፡ መልክአ እና መልክዐ አንድ ናቸው? ሕያው ስብሐት /ገጽ 129/ ፣ ጋሽ ስብሐት አንድም ሶስትም ነው! /ገጽ 256/ እንዲሁም ስብሐት ለአብ /260/ ርዕስ አሰጣጣቸው ከመስመር ያለፈ ኾኖ ታይቶኛል!

  ሰው የግል አስተሳሰቡን ይዞ በተወሰነለት የእድሜ ገደብ የኪራይ ምድሩን ለቅቆ ሲሄድ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የማንነቱ አሻራ ተተክሎ ይቀራል፡፡ ዘላለማዊ ሰው የለም፡፡ በኖረበት ዘመን “ሰው” ለመኾን ግን ያደረገው ሙከራ ማንነቱን ይገልጸዋል፡፡ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር የራሱ የሆነን ማንነት ይዞ የኖረ መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቀዋለን፡፡ ስለ ስብሐት ለአብ የምንነጋገርበት ሃሳብ ባለመኾኑ በዚሁ ልተወው እና “ሰው መኾን” ወደ ሚለው ፍሬ ሃሳብ አመራለሁ፡፡

ሰው እና ሞት የሚባሉት ነገሮች አይነጣጠሉም፡፡ እየኖርን ሰው ለመሆን እንጥራለን፡፡ ሞት ግን አይቀርልንም፡፡ ስለዚህ ለማይቀርልን እጣ ፈንታ ከመጨነቅ ወይንም ከመታገል በተሰጠን የመኖር እጣ ፈንታ መታገል ይበጀናል፡፡ ትግል ሰው ለመሆን! በተወለድንበት መሬት የምንሞትለት ዓላማ አለን፡፡ የምንሞተውም ለዓላማችን እና ለማንነታችን ነው! ማንነት ምንድን ነው?

 መልክአ/ዐ ስብሐትን እያነበብኩ “የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት” የምትል አንዲት ጥሑፍ አገኘሁ፡፡ እጅጉን ከማረኩኝ ጽሑፎች ተርታ መድቤያታለሁ፡፡ ከባድ ሃሳብ እና ከባድ ሸክም ለዚህ ትውልድ ያዘለች ነች!

  በዚህ ዓመት በቁጥር መግለጽ ባልችልም በርካታ መጽሐፍት ወጥተዋል፡፡ ኧረ ለመኾኑ በየጊዜው የሚወጡትን መጽሐፍት የሚመዘግብ አካል ማን ነው? ምናልባት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር? መጽሐፍ አዟሪዎች…? መሪዎቻችን ድህነት ቅነሳ ላይ ናቸው ብዬ ነው፡፡  አላውቅም…! መጽሐፍ ሳይቆጥሩ ድህነትን መቀነስ ድሀን ለመቀነስ ይመስለኛል፡፡ /በነገራችን ላይ በፓወር ግዕዝ አማርኛን ሲተይቡ ኮምፒውተር ላይየጥያቄ ምልክትን በቀጥታ ማግኘት ስለማይቻል ኹሌም እናደዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያኖች መጠየቅ አይወዱም ተብለን ይኾን?/

  ከትንሽ የመጠን እና የገጽ ብዛት ያላት የደሳለኝ ዳቼ ፡ የመለስ አስተምህሮተ ጥቅሶች መጽሐፍ እንስቶ እስከ ዘውዴ ረታ የአጼ ኃይለሥላሴ ታሪክ ትልቅ መጽሐፍት ታትመው ወጥተውልናል፡፡ በብዛት አነጋጋሪ የነበረች “መክሸፍ እንደ… ኢትዮጵያ ታሪክ” ትመስለኛለች፡፡

  የስብሐት ለአብን መልክ ያሳየችን መጽሐፍ ለየት ትላለች፡፡ ባለፈው ዓመት በሞት የተለየንን ስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን ለማስታወስ የተጻፈች ነች፡፡ አስታውሱ “በሞት የተለዩንን ለማስታወስ…!”

ታዲያ ይህችን መጽሐፍ እያነበብኩ መሃል ላይ ከግል ጡመራ ሰሌዳ ያገኘኋት ጽሑፍ ሃሳቤን ይዛው ሄዳለች፡፡ “የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት” ብዙ እንድናስብ የምታደርግ አጭር ጽሑፍ፡፡

 ሰው ሲሞት በሌሎች ዘንድ ማንነቱን ማስተዋስ እና ስራዎቹን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፍ የተለመደ ነው፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይ ስብሐት በህይወት እያለ አስነብቦናል፡፡ መሰል፡፡ ኢህአዴግንም ከስሶልናል! /ጥያቄ ምልክት ስላጣኹ ነው!/ መልክዐ ስብሐት ከሞት በኋላ በተለያዩ ሰዎች ዘንድ የተውጣጣ ሃሳብ ነው፡፡

 ሰው በህይወት እያለ “የተውጣጣ ሃሳብ” ሲያገኝ ደስ ይላል፡፡ ምናልባት ስብሓት በህይወት እያለ ብዙ ተብሎለት እርሱም ብዙ መልሷል፡፡ መታደል ነው በህይወት እያሉ ጣጣን ጨርሶ መሞት…! ስንቶቻችን

 ሳንሞት ጣጣችንን ጨርሰናል? ስንቶቻችን ጣጣችን ከህይወታችን በልጦብናል? ስንቶቻችን ህይወት ጣጣ ሆኖብናል? የምንኖረው የምንሞተውስ ለምን ጣጣ ነው? መሪዎቻችንም በማውጣጣት ሃሳብ ቢያምኑ ምንኛ መታደል ነበር ጥያቄ ምልክት፡፡ ከቃል አጋኖ ጋር፡፡

  ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ሳስብ የኢትዮጵያን ታሪክ በልዩ አይን እንድመለከት እና በተፈጠረው ታሪክ አጋጣሚ ከስህተት መማር ወይንም ከስኬት መሻሻልን እንድወስድ ያስገነዝበኛል፡፡  መጽሐፍትን ጽፈዋል፡፡ ሃሳባቸውን ያለ ፍረሃት ለዘመናት ገልጸዋል፡፡ እውቀት የእድገት መሰረት መሆኑን አበክረው አስረድተዋል፡፡ ጦርነታ ትልቁ ጠላታቸው ነው፡፡ ባንዳ ኮርቶ አርበኛ ሲሰቃይ እና ሲረክስ ሲያዩ እርር ድብን ይላሉ፡፡ መንፈሳዊነት መሳሪያቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት መገለጫቸው ነው፡፡ ጣጣቸውን ጨርሰዋል!  ልብ በሉ የህይወት መሰረቱ ጣጣን መጨረስ ነው!

 የስልጣን ጥማት አለባቸው እያሉ የሚያስወሩ ቡድኖች አሉ፡፡ ስልጣን የሚፈልግ ሰው እንዲህ እውነትን ብሎ ሙጭች አይልም! ጣጣ አያበዛም! ስልጣን የሚፈልግማ ወላወይ በመኾን ባለተረኛን መንግስት ከነታሪክ ስህተቱ አሜን ብሎ መቀብል ነው፡፡ ስልጣን ፈላጊ ናቸው ብዬ መቀበል አልችልም፡፡ በደርግ ዘመንም «ታዲያ እኛን ምን አድርጉ ትሉናላችሁ፣ መሳሪያው ያለው እናንተው ጋ አይደለም እንዴ?» የተባለን አባባል ወደ “በለው፣ ጨርሰው” አስተሳሰብ በመለጠፍ “ስም የማጥፋት” ወንጀል ሲሸመት አይተናል፡፡ የሁሉንም የግል ማንነት ለፈጣሪ ፍርድ እንስጥ፡፡ ነገር ግን የእኚህን ሰው ማንነት በሚገባ አውቆ ፍርድ ከመስጠት በፊት የጻፏቸውን መጽሐፍት አንብበን እንዲሆን የግል ምስክርነቴን አስተላልፋለሁ፡፡

 በእጄ ከገቡ መጽሐፍት “አትላስ” ስለ ኢትዮጵያ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ በስዕል ይዘረዝራል፡፡  እንጉርጉሮ  በ1967 ዓ.ም የወጣ የግጥም መድብል ነው፡፡ እውነትም እንጉርጉሮ! በተለይ በመቅደሙ ላይ የተቀመጠው ሰሜት ነኪ አገላለጽ ለብቻው ነው፡፡ እውነት ፕሮፌሰሩ ስሜትን ‹‹የማንጎርጎር›› ስጦታ አላቸው፡፡    ከቆሜ አየዋለሁ እስከ ህያው ኢትዮጰያ የተቀመጡት ግጥሞች ለስሜት ከስሜት የቀረቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከየት ወዴት…? ደግሞ 1986 ዓ.ም የወጣች ስትሆን ትንሽነቷ ቶሎ ቶሎ ጨርሱኝ ግን ደጋግሙኝ ደጋግሙኝ ትላለች! ከነፍጠኛ አተረጓጎም እስከ ጴጥሮሳዊነት አመለካከት ውስጣዊ መንፈስን የሚነካ ግሩም ጭብጥ ይዛለች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅርን የገለጸበት መንገድ ማንም አልገለጸበትም፡፡ መስፍን ወልደማርምም ኢትዮጵያዊነትን የገለጹበት አገላለጽ ልዩ ነው፡፡  የክደት ቁልቁለት ሁለት መጽሐፍን ይዟል፡፡ ገረፍ አደረግሁት ግን አላነበብኩትም፡፡  አገቱኒ  ሌላኛው ለየት ያለ አቀራረብ ያለው መጽሐፍቸው ነው፡፡ የህይወት ታሪካቸውን ለመጠቆም ሞክረውበታል፡፡  ታሪክ የለኝም! ብለው ይነሳሉ… አንድ “ወሬኛ ናቸው” ብሎ የመለሰላቸውን ሰው በቁጣም አልተቀበሉት! አዎ ወሬኛ ነኝ ብለው ይመልሱና ወሬ ሃሳብ መግለጽን ከያዘ፣ እውነተኛ እና በእውቀት ከተደገፈ ወሬ ከብረት እንደሚበልጥ ያስረዱታል፡፡ በመጠኑም ቢሆን የልጅነት ጊዜያቸውን አስቃኝተውናል- በአገቱኒ ተምረን ወጣን፡፡ ክፉ ቀን ደግ ነው! ምርጫ 97ን እና የኢትዮጵያን የወደፊት ሁኔታ ለማመላከት የቀረበ ጭብጥ ወደ መጨረሻ እናገኛለን፡፡ “አደጋ ያብዣበበበት አፍሪካ ቀንድ” ይከተላል፡፡ ስለ አፍሪካ ቀንድ የኋላ ታሪክ ፣ ያለበትን ሁኔታ እና የወደፊት እይታ ለማመላከት የቀረበ መጽሐፍ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በ20 ዓሜ,ት ውስጥ ከ 5 ሀገራ ወደ 10 ተሸጋግሯል፡፡ ስለ አረብ አገራትም ብዙ ጽፈውበታል፡፡

  ከዛም በያዝነው ዓመት መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንደርሳለን፡፡ መጽሐፉ መታተም የነበረበት ቀድሞ ቢኾንም ጊዜውን ጠብቆ 2005 ወጣ፡፡ ብዙዎቹን አነጋግሯል፡፡ ያስቆጣቸው ነበሩ! ሃሳቡንም የተጋሩትም በርካታ ናቸው፡፡ “የከሸፈ ታሪክ እንጂ ታሪክ ይከሽፋል…?  በሚል አገላለጽ የተጀመረው ሃሳባዊ ውይይት ያስደስት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንዲህ በሃሳብ ብንወያይ፤ የሃሳብ የበላይነት ባህል አድርገን ብንቀጥል ልዩ ነበር፡፡ ያም በጊዜው ከሸፈ!?

  ለዓመታት በመጽሔቶች እና በጋዜጦች በበርካታ ሃሳቦች ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን አስነብበውናል፡፡ አሁን ደግሞ በወርድ ፕሬስ እና በዘመነኛው ፌስ ቡክ ገጽ አልተለዩንም፡፡ እድሜ መጨመር ቢቻል ለእርሳቸው በጨመርኩ ያልኩበት ቀን ነበር፡፡ ነገር ግን የእድሜ ባለቤት ፈጣሪ ነው! እድሜና ጤና እንዲሰጣቸው መለመን የእኔ ፈንታ፡፡ ታዲያ በዚህ ክረምት አንድ ጽሑፍ በድረ ገጽ እንደ ተለመደው አስቀመጡ፡፡ ከአድን ጊዜ በላይ አንብቡኝ አንብቡኝ ይላል፡፡ የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት አስተማሪ ጽሑፍ ነው፡፡ እንድታነቡልኝ እጋብዛለሁ! ሳንሞትም ሳናኖርም ኖረንም ሞተንም የምንሸከመው ጥሑፍ፡፡

ታዲያ ሞት የሚባለውን ነገር በዚህ ጽሑፋቸው መግለጻቸው የመጨረሻ ቃል!? ብዬ እንዳስብ አደረገኝ! ጽሑፉን አንብቤ ስጨርስ ለሰዓታት ስሜቴ ይርገበገብ ነበር! እውነት ምንድን ነው? መኖር ምድን ነው? የምንሞተው ለማን ነው? እየኖርን መሞት እንዴት ያለ ክፉ ደዌ ነው? መሬት ምንድን ነው? ኮምፒውተሬን ወደ እንግሊዝኛ ለወጥኩና ብዙ ጥያቄ ምልክቶችን አስቀመጥኩ…!

ሰው መሆኔ ቀርቶ፣- አስከሬን ስባል፣

እወቁልኝ ይህን ብቻ፣- የገባኝን ያህል

ሞክሬ ነበር ሰው ለመሆን፤

ኑዛዜ ከምትል አንዲት የግጥም ስንኝ ቀንጨብ አድርገው በለሆሳስ ሹክ አሉኝ፡፡

መሬት አልነበረኝም በሕይወቴ

መሬት አልፈልግም፤ አሁን በሞቴ

አቃጥሉልኝ ሬሣዬን፤

አመድ እስኪሆን፤

አዋሽ ውስጥ ጨምሩልኝ አመዴን፤

አመዴ

ከአዋሽ ይቀላቀል ከዘመዴ

ይቺን አትንፈጉኝ አደራ

አመዴ እንኳን እንዲኮራ …

 ይህ ግጥም የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ከምናለቅሰው በላይ የሚያስለቀስ አባባል ነው፡፡ በስሜት አልቅሻለሁ!

  ሬሳ የማቃጠሉ ተግባር በቁሙ የተጎዳውን ደሀ ሲሞት ደግሞ መድረሻ እንዳያሳጣው የደሀ ሬሳ ለማቃጠል የሚያስፈልገው ወጪ ‹‹ድህነትን ለመቀነስ›› ከሚለው በጀት ወይም እርዳታ ቢወጣ ችግሩን ሁሉ ያቀላጥፈዋል፤ ደሀውም እየተደሰተ ይቃጠላል ወይም ችግሩ አብሮት እንደሚቃጠል እያወቀ ይደሰታል። ይኸኛው ደግሞ ይገርማል፡፡

ሰው እየኖረ ሲሞት ያሳዝናል፡፡ ለአኗኗሩም ሳይጨነቅ ለአሟሟቱ ይጨነቃል፡፡ ለምን ለሰውነቱ ሳያስብ ለበድን ሬሳው ያስባል!?  

ሰው እየኖረ ቢስማማ፣ ቢረዳዳ፣ ቢከበር፣ ቢከባበር፣ ቢደሰት እድል ፈንታው ነበር፡፡ አምላክ በምድር ሁሉን መሬት ሰጠን! ነገር ግን በመሬቱ ሰው ከሰው ሲበላለጥበት አንዱ ሲጨፍርበት እንደኛው ይኮራመትበታል፡፡ ድሀው መሬቱን ሲልስ ‹‹ሀብታሙ›› ጫማው ይላስበታል…. የሚትበት መሬት እና የሚሞትለት መሬት ማጣት አለመታደል ነው!  

  የምድሩ መሬትስ አልኾነም ፈጣሪ ግን ነፍሳችንን በግዛቱ ያድርግልን! በዚህች መሬት እውነትን ያለ፣ እውቀትን ያለ፣ ሃቅን ያለ፣ ሀገርን ያለ፣ መሬትን ያለ በመንፈስ ድሀ ሲኾን ታዝበናል፡፡ በመንፈስ ድሀ መኾን ብጹዕነት ነው! በህይወት ሳለን መስማማት፣መሰማማት ያሻለናል! በህይወት ሳለን መደጋገፍ መተቃቀፍ ይበጀናል! በህይወት ሳለን መከባበር መመካከር ይቀልለናል! እኚህን የሞራል አባት ግን አልሰማናቸውም! አልተመከርናቸውም! አልዘሀርናቸውም! አላከበርናቸውም፡፡ ከሞቱ በኋላ ሙሾ ማብዛት ግብዝነት ነው! ከተሞተ በኋላ ነጋሪት መጎሰም ለማደንቆር ነው! በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 7፡ 32 /፯፡፴፪/ የክርስቶስ ቃል ትዝ አለኝ፡፡

እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም

  ድንጋይ ከመኾን ይሰውረን! ፈጠሪ ሰው አርገን! ፈጣሪ ለመሬት ልሳን ያድርገን! የኢትዮጵያን ልሳን የሚሰማ መሪ ላክልን! ፕሮፌሰሩንም የሰማቸው የለም! እርስዎ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ አያፍሩም ኢትዮጵያም እርስዎን ስላፈራች አታፍርም፡፡ ልሳኗ ነበሩ! ሰሚ ግን አልነበረም…

ቸሩ ቸር ያቆየን!


No comments: