Jul 31, 2013

… and be sure your sin will find you out! Num: 32:23






ደወል!

… and be sure your sin will find you out! Num: 32:23

If you do not do well, sin lies at the door. Gen 4:7

…ኃጥያታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ…ዘኁልቅ 32፡23

ተስፋ በላይነህ

“አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ፡፡ ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡ ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ፡፡ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፡- ለምን ትናደዳለህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢያት በደጅ ታደባለች ፈቃድዋም ወደ አንተ  ነው ፡- አንተ ግን በእርስዋ ንገስባት፡፡” ዘፍጥረት 4፡2-7

   አ. ማ፡ አጽህኖተ ማስታወሻ /P.S- Post script/ አንተ ግን ግን በእርስዋ ንገስባት! ነገር ግን ቃየን በኃጥያት ላይ መንገስ አልቻለም፡፡ ወንድሙን  ጠራውም ወደ ሜዳ ወሰደው፡፡ አቤልንም ገደለው፡፡ የመጀመሪያው ግድያ ተፈጸመ፡፡ በንዴት በቅናት ተነሳስቶ ወደ በቀል አመራ፡፡ ኃጥያት ላይ መንገስ አልተቻለም፡፡ ለኃጥያትም ተገዛ! ማንም አላየኝም ብሎ አስቦ ነበር፡፡ የኅሊናው ደወል ግን ይጮሃል! እግዚአብሔርም “የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል፡፡” አለው፡፡  ቃየን ተረገመ፡፡ ተቅበዝባዥ ኮብላይ ኾነ!

 ቃየንም ለእግዚአብሔር መለሠ  አለውም፡- “ኃጥያቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት፡፡ እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ ከፊትህም እሰወራለሁ በምድርም ላይ ኮብላይ ተቅበዝባዥ እሆነለሁ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል፡፡” ሲል ተናዘዘ፡፡ ይህ የህሊና ደወል ነው፡፡ ኃጥያት ትከታተለናለች!

  ሰንቶቻችን በህሊና ደወል ተቅበዝብዘናል? ስንቶቻችን ኮብልለናል? ስንቶቻችን ደወሉ ይጮኽብናል? ከተጫማነው ጫማ እሰከ ተከናነብነው ልብስ፤ ከያዝነው የኪስ ስልክ እሰከ ምንዘውረው መኪና… ስንቶቻችን ለኅሊና ነጻነት እንኖራለን? የኅሊና ደወል ከሐዲስ ሳህሌ- ከሱጴ ቦሮ ምድር! /በዓሉ ግርማ/

ደወል-1

  ወድ መባል የሚያንስበትን ‹‹ካዲላክ›› መኪና ይነዳል… ገንዘቡ በየት በኩል… እንዴት አድርጎ… በመቼ እንደገባ ለማስታወስ ጊዜ አጥቷል… ባማረው መንገድ እንደ ጉድ ይነዳዋል… ወደ ተቀጣጠረበት ጎዳና እያመራ ነው… መኪናውን ‹‹ፓርክ›› ለማድረግ አልተቸገረም…በጣም የተከበረ ነው! አንዲት ጥላሸት የተቀባች የምትመስል ሴት… በሚንቀጠቀጥ እጇ ለልመና ዘረጋች… አለማዬት ቢችል መታደል ነበር… አለማየት ግን አይችል!፡ አለመስማት ቢችል ግልግል ነበር…! አይን ቢታወር… ጆሮ ቢደፈን ግን ከኅሊና ደወል ማምለጥ አይቻልም! የሚነዳው መኪና የተገዛው ከዚህች አዛውንት ጎሮሮ ተሰንቅሮ እንደኾነ ኅሊናው ብቻ ያውቀዋል! ድሀ ሲያይ ያንገሸግሠዋል፡፡ ደወል..!

ደወል-2

  የማይፈልገው የስልክ ጥሪ ነበረበት… ስልኩን ማጥፋት ግድ ሆነበት፡፡ አጠፋ…! አገር ሰላም- ታክሲ ውስጥ ገባ፡፡ ወደ ማምለጫው ስፍራ እያመራ ነው፡፡ ባልጠበቀው መልኩ የስልክ ደወል ይሰማል… ማመን ግን አልቻለም፡፡ የስልኩ ጥሪ ልክ የራሱን! ልቡ ደነገጠ… ኪሱ ውስጥ ገባ፡፡ ስልኩ ‹‹ኦፍ››  ነው፡፡ ወዲያውኑ ግን ሌላኛው ሰው ‹‹ሄሎው›› አለ፡፡   እፎይታ! የሌላ ሰው ስልክ ነበር፡፡ መንገዱ ለጊዜው ሸሸ… አዕምሮው ሰላም ግን ማረፍ አልቻለም! ከኅሊና ደወል ማምለጥ አይቻልም፡፡ ደወል…!

ደወል-3

በጫት ቤት ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ በጠራራ ፀሐይ ቤታቸው ደምኗል፡፡ በጢስ ታፍኗል፡፡በለጋ ወጣትነት እርጅና እና ተስፋ የመቁረጥን “ጸጋ ለብሰዋል”፡፡ በጢስ ውስጥ መተያዬት ቢከብድም፤ በድንግዝግዝ ይደባበቃሉ፡፡ ድብብቆሽ! እየመሸ ሄደ፡፡ መብራት ይብራ ተብሎ በራ፡፡ ደነገጠ፡፡ ድንገት የሚያውቀው ሰው እንደዳይኖር በጣም ሰጋ! ትልቅ ስጋት፡፡ በፍጥነት የበራ አይኑን አሽከረከረ፡፡ የሚያውቀውን ሰው ፍለጋ፡፡ ሁሉንም አማተረ፡፡ ተመስገን! የሚያውቀው ሰው የለም፡፡ ድንጋጤው ሸሸ፡፡ ውፍ!! ሲጋራ በላይ በላይ! የኅሊናው አባቱ ግን ተደነቀሩበት…! የስጋ እናቱ ተላተሙበት…! ሌላ የማይሸሹት ድንጋጤ…! የማያመልጡበት ጩኸት! ደወል…!

ደወል-4

‹‹ከፍቅረኛው›› ጋር ይዝናናል፡፡ በልዩ ስፍራ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ልጅቷ የባለጠጋ ልጅ ናት፡፡ ባለጠጋ ቤተሰቦቿን ተማምኖ በትዳር ሊተሳሰር ይፈልጋል! “ሃብት እና ባለጠግነት ከአባቶች  ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት” የሚለውን አባባል ከተረት ለይቶ አላየውም፡፡ ከእግዚአብሔር ያገኛት ሴትማ ገንዘብ ፍለጋ…ባለጠጋን ፍለጋ ሸሽታዋለች! አሁን ያለው ከማያውቃት ሴት ጋር ነው! ባለጠጋ ለመኾን…! በበቀል ሀሳብ እርሱም ሊበቀል ይሁን… ያጣውን ለማግኘት… ከባለተረኛ ልጃገረድ ጋር ተቀምጧል፡፡ ያሉበት መዝናኛ ራድዮኑ ተከፍቷል...! ፍቅረኞች ይገባበዙበታል…! “ፍቅር እና ገንዘብ” የሚል ሃሳብ ለውይይት ቀርቧል፡ የመረጋጋት ስሜት አይታይበትም…! ይቅበዘበዛል…! መወያያ ርዕሱ ‹‹ምቹ›› አልሆነለትም፡፡ በጣም ረዘመበት… የ 5 ደቂቃ ንግግር ለዚህ ብላቴና ዝንት አለም ሆነበት! አንቆራበጠጠው…! አንገሸገሸው…! “ኤጭ!” ብሎ ጮኸ፡፡ “ምንው?” አለች ‹‹ፍቅረኛው›› “አይደብራቸውም እንዴ? ቀኑን በሙሉ አንድ ርዕስ ብቻ መጮኽ?” ሲል ተደመጠ፡፡ የተረዳው አልነበረም፡፡ “ኧረ” አለች በመገረም፡፡ “ እኔ ደግሞ አልሰማሁትም ነበር፡፡” ስለ ምን ነበር ዝግጅቱ ስትል መለሰችለት፡፡ ራድዮኑን ማንም የሚሰማው የለም… የሚጮኸውም ራድዮኑ አልነበረም፡፡ ደወሉ ከውስጥ ነው! ከኅሊና ደወል ማምለጥ ዘበት ነው!

ደወል-5

  ከቤተ ክርስትያን አገልግሎት ከራቀ ዘመናት ነጎዱ…! የቅዳሴ… የማሕሌት… የሰዓታት… ዜማ ከሩቅ ይሰሙታል…! ከአሃዱ/ከእሁድ/ እስከ ሰኑይ/ሰኞ/ ደወል አልጠፋም፡፡ ደወል ለእግዚኦ… ደወል…ለቅዱስ ቅዱስ! የቤተ ክርስትያኑን ደወል ሰምተው “አሐዱ” ለማለት ሲሯሯጡ ይመለከታል፡፡ ባለፉት የጉብዝና ጊዜያት ይህንን ደወል የሚደውለው እርሱ ነበር…! ሙዳይ ምጽዋት ወደ ግሉ ካዝና አድርጎ ከተያዘበት ዕለት ጀምሮ ከቅጥሩ አርባ ክንድ ማለፍ ተስኖታል…! እንደ ንዑስ ክርስትያን ለመሳለም… በረከት ሊሳተፍ ቀረብ ሲል መጽዋቾች  የሚጥሉት ሙዳይ ሳንቲም በተቀበለ ቁጥር ጩኸቱ አላስቆም፣ አላስቀምጥ፣ አላስቀርብ ስላለው እግሬን ይስበረው ብሎ ቀርቷል፡፡ በርቀት ደወሉ ይሰማው ጀመር…! ከቤተክርስትያን ደወል ሽሽት…! ሀገር ተሻገሮ… ወንዝ አቋርጦ… ወዝ ወደ ሚቆረጥበት መንደር ተሳፈረ… እዚህ ደወል የለም! እዚህ አሐዱ..እግዝኦ…ቅዱስ ቅዱስ የለም፡፡ ለርሱ “ረብሻ” የለም! ጸጥታ! ሰማዩ በጠራ ቁጥር፤ ከዋክብት በተደረደሩ ቁጥር፣ ጸሐይ በጠለቀች ቁጥር… ወፎቹ ሲንጫጩ ግን ከኅሊናው ደወል ማምለጥ አልቻለም! ከውስጠኛው ደመል ለመራቅ የት ይግባ? የዚህኛው ደወል የባሰ ነው!

ደወል-6….ደወል-7…8….9

  ባለስልጣኖች ለህዝብ ይደሰኩራሉ… በርካታ አዋጆችን ተንተርሰዋል…! ረዣዥም የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ከትረዋል…! “ሙስናን እንዋጋ…!” በትልቁ ተጽፏል… የኅሊናው ውጊያ ግን ከተለጠፈው ደርቷል፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላት፤ የማትታይ ኅሊና ግን በየጊዜው ትደውላለች…! ትላልቆቹ የማስታወቂያ ሰሜዳዎች የውስጣቸውን ጩኸት ለማካካስ የተሰቀለ ነው፡፡ ኅሊና ካልፀዳ… ወሬ ቢንጋጋ ምንም ጥቅም አለው? የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ሙስናን ሊያቆሙት አልቻሉም፡፡ ማቆሚያው የውስጥ ሰሌዳ እንጂ መች ከውጭ ነው? …

 ሰዓሊው ሳያስበው የለቀለቀው ‹‹አብስትራከት›› ስራ በታዳሚዎቹ ተደንቆለታል…! ተጨብጭቦለታል፡፡ ነገር ግን ለርሱ ምጸት ሆኖ ይሰማዋል፡፡ በስንት ምርቃና እንደተገኘ… ለምን እንደሳለው፣ እንዴት እንደሳለው  እርሱ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ጥበብ የጫት ውጤት ሲኾን አይወድም! ግን እንጀራ ከጥበብ በለጠች! ደወሉ ከቀለማቱ ጋር ተዋህደው በጠበጡት! …

  የሚጠጣው ውድ ‹‹የአልኮል›› መጠጥ ለመለኪያ የተከፈለባት ዋጋ የእናቱን ማጀት ትሞላለች፤ የልጆቹን ወተት ታነጣለች… ግን በላይ በላይ ይታዘዛል! የውስጡ ደወል ስካር እና ‹‹የሞንታርቦው›› ድለቃ እየመሰለው “ድገሚ!” እያለ ያስቀዳል… ቆነጃጅትን እያሻሸ ይጋብዛል…! ሲነጋ ከስካር ሲተያይ… ከድለቃው ሲለያይ ደወሉ ግን አልተለየውም! ህመም…

  ብዙ ‹‹ዕልፍ›› ደወሎች፡፡ ብዙ ሺ ጩኸቶች ተረግጠዋል! ብዙ እውነቶች፣ ብዙ ሃቆች፣ የስንቱ ደም ይጠራናል፣ የብዙ ንጹሃን ነፍሶች በእስር ቤት ታጉረዋል፡፡ ደወሉ አላረፈም! ጊዜው ለፀፀት፣ ለይቅርታ እና ለንስሃ ነበር፡፡ ይቅር ሳንባባል ጊዜው ይነጉዳል…! በሕይወት መቆየት ከኅሊና ንጽህና ለመፈወስ ነው፡፡

  ኅሊናን ሳንንከባከብ፤ ኅሊናን ሳናስተምር፣ ኅሊናን ሳናዳምጥ- ፖሊሲ-ስትራቴጂ- ትምሕርት- ሚዲያ-ደንብ… ሁሉ መደበቂያ ናቸው፡፡ ህጻናት ከስር መሰረታቸው የኅሊናን ምንንት ሳይገነዘቡ፤ ኅሊናን እየደለሉ፤ በቁመት ብቻ የሚያድጉ ከኾነ በኋላ የሚለጠፍላቸውን መመሪያ እና ደንብ ለማንበቢያ ብቻ እንጂ ለመተግበሪያ ቦታ የላቸውም፡፡ በኅሊና ደወል ጩኸት ሳይሆን በኅሊና እጦት ተጠምተዋል፡፡ የኅሊና ዋጋ አልተነገራቸውም እና! ህጻናት የከደበ ሚካኤልን ተረትና ምሳሌን እንኳ እንዲያውቁት እየተደረገ አይደለም፡፡

  ልቡሰ ጥላችንን ባዶ እያደረግን መኖር ‹‹ፋሽን›› ሆኖ ተዋህዶናል፡፡ /ልቡሰ ጥላ፡ የዳኛቸው ወርቁ አደፍርስን ያስታውሷል/  አዕምሯችን ለወረት የሚታክት ሲሆን ከሰውነት ሚዛን እወጣን ነው፡፡ አንዴ ቆም ብንል፤ ደወሉን ብንሰማ ይበጃል!

  ራስን መሸወድ፣ ራስን ማሳመን፣ መሸንገል እና መደለል የሚቻልበት ዘመን ደርሰን ይኾናል፡፡ በዘመናት የማይለወጠው፤ ሰማይ ምድር ቢያልፉም ቃሉ ግን የማይልፈው፤ ልናመልጠው፣ ልንሸገው፣ ልንክደው፣ ልንደበቀው አንችልም! ደወሉ እርሱ ነው፡፡ ደዋዮቹ የእርሱ ናቸው፡፡ ነጋሪቶቹ፣ ሙሾዎቹ፣ እምቢልታዎቹ፣ ዋሽንቶቹ ይጮኻሉ… አንዴ ቆም ብለን ልናደምጥ ይገባናል! ለይቅርታ እንድንዘጋጅ፡፡ ይቅርታ ደግመን እንዳንሳሳት ቃል መግባት ማለት ነው፡፡

ቃየን እና አቤል አንድ ቢሆኑ ይህ ሁሉ አይደርስም ነበር፡፡ አሁን በእኛ መካከልስ ሰንት መለያየቶች ነግሰዋል፡፡ ስንት ተቃውሞዎች ተበራክተዋል….ስንት ደወሎች…? አንድነት ርቆናል! ማናለብኝነት፣ ማሽሟጠጥ፣ ማፌዝ ተስፋፍተዋል፡፡

  ለኃጥያት መገዛት በስንፍና፣ በንዴት በቂም በበቀል ሊሆን ይችላል፡፡ ከኃጥያት መሸሽ ይበጅ ነበር፡፡ ለኃጥያት ግን ከተገዛን የኅሊና ደወሉ አያድርስ ነው! ተመልሶም እንደሚያገኘን አንጠራጠር፡፡ ንጹህ ኅሊና ዕረፍት ነው! ካሆነ ግን ማምለጥ አይቻልም፡፡  መጽሐፉም እንዲል “… እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ ኃጥያታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ!” ዘኁልቅ 32፡23፡፡

ቸሩ ቸር ያቆየን!



 
 

No comments: