Feb 13, 2013

ለነይስማዕከ እና መሳዮቹ የተጻፈ ጥያቄ-ለምን ያወናብዱናል?






ይድረስ ለበዕውቀቱ ስዩም እና ለይስማዕከ ወርቁ- 
                          በሌላችኹበት!
                 ጥቁር እና ነጭ :- የቄሳርን ለቄሳር!
       በተስፋ በላይነህ
     ስነጥበብ እጅግ በጣም የተሰወረውን የውስጥ ስሜት ነግሎ በማውጣት እግር አልባውን እንኳ ክንፍ እስከመስጠት የሚያስደርስ ፀጋ ፤ በሀሳብ በምናብ ምናኔ ወደ ፊት እና ወደኋላ መብረር የሚያስችል ክንፍ አለው፡፡ በየዘመናቱ ስነ-ጥበብን ያስተዋወቁ ሰዎች ብቅ ብለዋል:: እንደዘጋቢያቸው ወይም መስካሪያቸው  የፈረጠመ ጡንቻ አማካኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተትረፈረፈ ሲሰማና ሲታይ እናያለን፡፡ በየጊዜው የሚነሳው ትውልድ እያነሳ ይጥለዋል፡፡ ነገር ግን በጊዜ  ብዛት  አያረጅም፤ በዘመን ኮፈን አይጣልም፤ በወቅቶች መፈራረቅም አይጠወልግም ::  እንደወይን እየጣፈጠ እንደንስር ሀይሉን እያደሰ ዘመኑን ይዋጃል:: የትውልዱ ስልጣኔ ሲዋዥቅ አብሮ ሊዋዥቅ ይችላል፤ የትውልዱ ስልጣኔ ግን ሲያድግ ክፍ ይላል ስለቱም ሊጨምር ይችላል::
       ከኢራን/ፋርስ/፣ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅ ከግሪክ፣ ከራሺያ፣ ከእንግሊዝ፣ ከጀርመን፣ ከአየርላንድ ከሊቢያ፣  ከናይጀሪያ እና ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በርካታ የስነ-ጥበብ ፈርጦች ተከስተዋል:: ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው እንደመስካሪያቸው ጡንቻ አማካይነት ብዙ ሊባልላቸው ይችላል:: እንደሚጮኽላቸው (መስካሪዎች) የጩኸት ሀይል ስማቸውም ሊገን ይችላል:: ሼክስፒርን ስናይ እንግሊዞች ባለቸው ሀይል የራሳቸውን የመመስከርና የመንዛት ችሎታ መሰረት ብዙ ተብሎለታል:: እንደራሻዊው ደስቶቭስኪ ደግሞ የነበራቸውን የመጠቀ የስነ-ጥበብ ሀይል በመስካሪያቸው እንደሌሎች ሳይጮኽላቸው ስራቸው ገኖ ሊታይም ይችላል:: የአንዳንድ ሰዎች የስነ-ጥበብ ስራ ስራው በራሱ ባለው ጩኸት መቃብር ፈንግሎ ሊወጣ ይችላል:: ብቻ እውነተኛ እና ሀይል ያለው ስራ ይሰራ እንጂ ቀኑን ጠብቆ መታየቱ አይቀርም:: አሁን ያለንበት ዘመን የመረጃ ዘመን በመኾኑ በ‹‹ቲፎዞ›› በጩኸት ለዕይታ የሚቀርቡ ስራዎች በርክተዋል :: ጯኺ ከሌለ ስራ ተቀብሮ ሊቀር ይችላል:: መስካሪ የሌለው ዳኛ ለፍርድ እንዲሚቸገር ጩኸት የሌለው ድምጽ እንደማይሰማ ኹሉ በየጊዜው የሚወጡ የጥበብ ሰዎች  ጯኺና መስካሪ እያጡ ሲቸገሩ እናያለን::
       የቁራ ጩኸት እንደተባለው አላስፈላጊ ምስክር (የማስታወቂያም ስራ የገቢ ምንጭ መሆኑ ከታወቀ ወዲህ) ጩኸት የማይገባቸው ስራዎች በማስታወቂያ ሰሪው ሀይል ብቻ ገነው ሲወጡ ይታያሉ:: እነዚህንም ገንዘብ ዋናው መሰረታዊ ነገር  እየሆነ ገንዘብ የሌለው የስነ-ጥበብ ሰው በችጋር ሲሰቀይ የምናየው ሀቅ ነው:: በዚህ አጋጣሚ በጩኸቱ ስራ የተሰማራችሁ ሰዎች ያልተዘመረላቸውና ያልተጮኸላቸው  ሰዎች ነገር ግን ምጥቀትን የያዙ ስራዎች ብትፈልጉ መልካም ነው::
       እንግዲህ አንድ የስነ-ጥበብ ሰው የፈለገውን የተሰማውን በስነ-ጥበብ ሀይል ከባህሩ ዋኝቶ፤ ከጠፈሩ ተንሳፍፎ፤ ከምድሩም ተዋህዶ የቀዘፈውን የቀዳውን የተመለከተውን እንካችሁ የማለት መብትም ግዴታም አለበት::  ወደዋናው ነጥብ ለመምጣት ያነሳሳኝ በአሁኑ ሰዓት ያለው አንባቢና የጥበብ ተመልካች የሚሰማውን የሚያነበውን የስነ-ጥበብ ፈጠራ ከምን ማዕዘንና እይታ ተመልክቶ እያጣጠመ እንደሚገኝ በማገናዘብ ነው:: ስለተጮኸላቸው ወይስ ስራቸው ስለጮኸ? ምላሹን ለርስዎ! ለዚህም ሀሳብ ዋና ተጠቃሽ የስነ-ጥበብ ሰዎች በእውቀቱ ስዩምና ይስማዕከ ወርቁ ናቸው::
       አንድ ሰው የፈለገውን የማምለክ ያሻውን ጎራ ወግኖ መጻፍ የተፈጥሮ መብቱ ነው፡፡ እግዚአብሔርን አለማምለክም ሰይጣን ይሻለኛል ብሎ ካሰበም መብቱ ነው:: የአመላለክ ስርዓቱን የእይታ ጎኑን በፈለገው መልኩ የማቅረብ ሙሉ መብት አለው:: ታዲያ እዚህ ላይ ግን ችግር ውስጥ የሚገባው አንባቢው የሁለቱን ጽንፎች በሚያስተውልበት ጊዜ የመለየትና የአንዱን ጎራ ( የሚያምንበትን) ሃሳብ ለይቶ ግልጽ የሆነ ውሳኔ እንዲሁም መረጃ የማግኘት ሃላፊነትም ግዴታም ስለሚኖርበት ነው:: አንባቢው ተመልካቹ የሚያነበውንና የሚያየውን ሀሳብ በጥንቃቄ አጉልቶ ማየትና ሊደርስ የሚችለውን ጫና ገምቶ ብቁ የሆነ አንባቢ መኾን ይጠበቅበታል:: ባየኋቸውና በገኘኋቸው እንዲሁም በነበብኳቸው የስነ-ጥበብ ፈጠራዎች ምን አገኘሁ? ምን አጣሁ? ምን ለየሁ? ምን ጎደለው? ብሎ ካልጠየቀና ካልመረመረ ይህ አንባቢ ሰው ሳይሆን እንስሳ ነው፡፡ ወይም አሻንጉሊት አሊያም ተንቀሻቃሽ መሳሪያ (ሮቦት):: ይህ ደግሞ ብዙ ማንበብ ይጠይቃል ብዙ መረዳት ይጠበቃል:: ግልብ ኾነን የምናነብ ከሆነ ጥራዝ-ነጠቅ ከሚባለው ፈርጅ ውስጥ እንመደብና መነጠቃችን አይቀርም:: በዚህ መሰረት ከላይ የጠቀስኳቸውን ስመ-ጥር የስነ-ጥበብ ሰዎች ስራዎቻቸውን በማየትና አንባቢው ላይ እየደረሰ ያለው መወናበድ ሀሳብ ለመስጠት ነው:: ብዙም የተለየ ሃሳብ የመጠቀ አስተሳሰብ ይዤ ሳይሆን በመሰለኝና በተረዳሁት መጠን የቀረበ ነው፡፡
       በእውቀቱ ስዩም እና ይሰማዕከ ወርቁ አንድ የሚያመሳስላቸው የጋራ መነሻ ብዬ የምገምተው ነገር ሁለቱም ምናልባት የቅኔ ትምህርት (የአብነት ትምህርት) እንዲሁም የመለኮታዊውን ክበብ ቀዝፈው የመጡ መኾናቸው ላላቸው ወቅታዊ ስብዕና እና የስነ-ጽሁፍ ፈጠራ አጋዥ መሆኑን የምንስማማበት ሀሳብ ይመስለኛል:: በእውቀቱ ስዩም በ 1995 ዓ/ም ያነበቡኳትን የግጥም መድብል ስራዎቹን ያወኩበት ወቅት ነበር:: ‹‹ኗሪ አልባ ጎጆዎች›› የተሰኘቸው ይቺ ስራ ማንም ሳይጨኽለት በራሷ ያላት ሀይል ላነበባት ትልቅ ድምጽ የነበራት ስራ ነበረች::
         “ግጥም የሕያው ስሜቶች ምስክርነት እንደሆነ እናምናለን ምናባዊ መገለጥ እንደሆነም እናምናለን ለአያቶቻችን ከመለኮት ጋራ የሚያገናኝ መሰላል ለአባቶቻችን የአብዮት ሰይፍን የሚስል ሞረድ ለእኛ ፍለጋ/ኅሰሳ/ መኾኑን እናምናለን… እያለ መክሊት…መኾኑን በማመን ሀሳቡን ይጀምራል:: በግሌ ከነበረኝ የግጥም ፍላጎት ከእድሜም አንጻር ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የግጥም መድብል በመያዝ በወቅቱ ስፍጨረጨር የነበርኩትን ጨቅላ እኔን ግጥም ትግል አለመኾኑን በእወቅቱ ስዩም አበሰረኝ:: በሶስት ብር ከ ሀምሳ የተገዛቸው የሎሬት ባለቅኔ ፀጋዬ ገ/መድህን ‹‹እሳት ወይ አበባ›› የግጥም መድብልን ተውኳት፡፡ በዘመኑም በእውቀቱ ስዩም አዲስ ምዕራፍ ከፈተልኝ:: ደጋግሜ አነባቸዋለሁ በቃሌ እደግማዋቸሁ :: በወቅቱ ገጣሚው በዝና ስለማይታወቅ በቃሌ የያዝኳቸውን ግጥሞች ጓደኞቼ ደብተር ላይ በመጻፍ እኔን ያደንቁ ነበር፡፡ የእኔ እየመሰላቸው ግጥም እንደሚችል መስክረውልኝ ነበር፡፡ ከጊዜ በኃላ ግን ገጣሚውም በስፋት ሲታወቅ በዛን ወቅት ያስተዋወኳቸው ግጥሞች የእኔ አለመኾኑን ከተረዱ በኋላ እንኳን ያለጊዜው ግጥሞችን በማወቄ አድናቆት አድርሰውኛል:: እንግዲህ እኔ እንዲህ የተደነቅኩ ዋና ገጣሚው ምን ያክል እንደሚደነቅ መገመት ቀላል ነው::
 በላዔ ሰብዕ፣ መልካ ሕይወት፣ ዘመን ሲታደስ፣ ሞኝ ፍቅር፣ መሄጃው የታለ፣ ብታውቂ፣ ጣይና አንሺ ፣ ጥጡና ፈታይዋ፣ ፍካሬ እውነት፣ መለየት፣ ይስጥሽ ወንዝነት መመኝት..ወዘተ የመሳሰሉ ግጥሞች የጨቅላነት እድሜዬ ስሜታዊ እንዲሆን ተፈጥሮን በተለያዩ ማዕዘኖች እንድመለከት የረዱኝ ግጥሞች ናቸው፡፡ በሕይወት ዘመንም አንድ ነገር መፈለግ እንዳለብኝ ያስተማሩኝ ስንኞች ነበሩ::  በእያንዳንዱ ግጥም የነበሩ የስዕል መግለጫዎች በራሳቸው የገጣሚውን ሌላኛው የስነ-ጥበብ ገጽታ የሚያመላክቱ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት በወቅቱ ገጣሚውን በግሌ በአንደኝነት የስነ-ጥበብ ጎራ ለማስቀመጥ አስችሎኛል::
   በ90ዎቹ የነበረው የሰው የማንበብና የመጻፍ ባህል በመጠኑም ቢሆን የተዳከመበት ወቅት ነበር ለማለት እደፍራለኹ:: ከዚያም ይኸው ጸሐፊው ‹‹በራሪ ቅጠሎች›› በሚል ያቀረባት የጋርዮሽ ስራ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሚወጡት አጫጭር  ልብወለዶችወግና  መጣጥፎች የተለየ አድናቆት እንድንሰጥ አስገድደውኛል፡፡ ‹‹እንቅልፍ እና ዕድሜ›› ከ97ቱ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማያያዝ የተጻፈው ድርሻም አጠር ያለ ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጠው ሥራ ነበር:: በግጥም መደብል ሀረግም ‹‹የእስት ዳር ሃሳቦች›› የተሰኘችው የግጥም ስራ እንደቀዳሚዋ ባትሆንም የበኩሏን ድርሻ አበርክታለች:: በተጨማሪም ‹‹መግባትና መውጣት››   በቀልድ እያዋዛ ያቀረበው ሐሳብ የሚደነቅ ነበር:: ሆኖም በእነዚህ አመታት ውስጥ በጸሐፊው የስነ-ጥበብ አስተሳሰብ አብሮ መጓዝ የሚያስጠይቅ መኾኑን ልብ ይበሉ:: በብዛት ፍለጋ ላይ የኾነ ጸሐፊም መኾኑን ራሱ መስክሯልና-ለእኛ ፍለጋ/ኅሰሳ/ መኾኑን እናምናለን… አያቶቻችን ከመለኮት ጋር ለአባቶቻችን የአብዮት ሰይፍ ብሎ ለራሱ ግን ገና ፍለጋ ብሎ መጻፉን አንረሳም፡፡ እንግዲህ ገጣሚው ፈልጎ ፈልጎ ምን እንዳገኝ በስራዎቹ የምንመዘግነው ይኾናል፡፡
  ከአንድ ግጥም ወዳጅ ወዳጄ ጋር ስለግጥሞቹ ስንወያይ ገጣሚው በስሜታችን የሌለን በሕይወታችን ያላገጠመንን የኑሮ ክስተቶች ሆነን እንድንገኝ የማድረግ ኃይል አለው:: ይህም ማለት ለምሳሌ ‹‹ዕረፍቴን አሥሣለሁ›› የሚለው የግጥም ሐሳብ ብሩኩ ወዳጄ ባልኖረበት እና ባላጋጠመው የሕይወት ገጠመኝ ውስጥ እራሱን እንዳገኘው -ሳይከፋው እንደከፋው፤ ሀዘን ሳይሰማው እንዳዘነ፤ ምንም ዓይነት በፍለጋ ሕይወት ውስጥ ሳይኖር ብዙ ነገር እንደፈለገና ፈልጎም እንደዋተተ ሲነግረኝ ያለውን የስነ-ጥበብ ኃይልና ጫና ለመረዳት ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ ሰለዚህ የዚህን ገጣሚ ዱካ መከተል ግለሰቡ በኖረበት ስብእና መጓዝ ስለሚያመጣ አንባቢዎች በጥንቃቄ እንዲያነቡና እንዲገነዘቡ ወደሚመክር ጭብጥ እናመራለን:: ጻሐፊው ያሻውን ይጻፍ የማገውን ይተንፍስ አንባቢ ግን በአፅዕኖት በዐርምሞ እና በማስተዋል እንዲያነብ ይመከራል::
ልክ እንደመናፍቅ-ቀኖና እንደጣሰ- እምነት እንደ ካደ
ከቀኖች ሰልፍ ውስጥ- ማን ገዝቶ ለየው- ሰናበት ወዴት ሄደ?
ዕረፍት የት ገደመ- ወዴት ተሰደደ?    እያለ ይቀጥላል፡፡
በእኔ በኩል በወቅቱ በታላላቆቹ መጽሐፍት ላይ ( ቁርዓን እና መጽሐፍ ቅዱስ) ትኩረቴን ሰጥቼ ስለነበር እራስን ፈልጎ ማግኘት የቀለለበት በመኾኑ የሌሎችን የግለሰብ አስተሳሰቦች መረዳትና ማስተዋልን አግኝቼአለሁ:: ገጣሚውም ከእነዚህ መጽሐፍት ብዙ የቀዘፈ መኾኑን ተረድቼአለሁ::ለጸሐፊያንም የአስተሰሰብ ሞገድ ኃይል የሚረዱ መጽሐፍት መኾናቸውን አንብበው ከሚረዱትና ለአንባቢያን ከሚያቀሩቡት ጸሐፊዎች ሀሳብ መረዳት ይቻላል:: በዚህ ወቅት ‹‹ዴርቶጋዳ›› የተሰኘ መጽሐፍ ለገቢያ ሲቀርብ በተለይ ወጣቱ መጽሐፍ ይዞ መታየትንና ወደ መጽሐፍ ማንበብ ዝንባሌ መከተሉ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አብዮተኛ ነበረች:: ከተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች አነጋገሪ አወያይ ትውልድ ወደ መጽሐፍ ማንበብ ባህል እንዲመለስ ማድረጓን አልክድም:: ጸሐፊው ይስማከ ወርቁም ይህን የአብዮት እሳት ማቀጣጠሉ ያስመሰግነዋል:: በጊዜው ይህን መጽሐፍ ያላያዘና ያላነበበ ኢትዮጵያዊ እስከማይባልበት ደረጃ መድረሱ መጽሐፉን ያለውን ኃይል ያሳየ ነበር፡፡ በተለይ እስከ 80 ገጽ ያለው ፈጠራ እጅግ ውብ ነበር:: በ‹‹ሆሊውድ›› የጥበብ መስኮት የሚወጡት ፈጠራዎች ትውልዱን አጥምደውት ስለነበር ጸሐፊው ያቀረበበትን ገጽታ ይህንን ያመላከተ መኾኑን እርሱ ነው የጻፈውን? ብለው የጠየቁ አንባቢያንም አልታጡም:: በበኩሌ አፍሪቃዊ መሆን ኢትዮጵያዊ መሆን ብሎም ከአብነት ትምህርት መውጣት ይህ ስራ ቀላል እንደሚኾንለት እተማመናለሁ:: ይህንንም  መጽሐፍ ተከትሎ የወጣው የግጥም መድብል ‹‹የወንድ ምጥ›› የተሰኘች ሥራ በተለየ መልኩ የስነ-ግጥም   ሰይፉን የሳለበት ፤የግዕዝ እና የቅኔ ችሎታውን ያሳየበት፤ ድርሻውን  የተወጣበት ስራው ነበር:: ‹‹ሰቆቃወ ቂል›› የተሰኘችው የግጥም ስንኝ በተለየ አፅንዖት ነበር የተመለከትኳት ምን እንኳ ከግል ሕይወቴ ጋር የሚያገናኛት ሐሳብ ባትሰንቅም በስነ-ጥበብ ኃይል  ግን  በገጣሚው ሐሳብ ስር መደቆሴ አልቀረም:: የወንድ ምጥ የተሰኘው ረዥም ግጥም በራሱ ልዩ አፍሪቃዊ እንባን የተላበሰ፤ የአፍሪቃዊያን ታሪክና ህዝቦች ኑዛዜ፤ ጩኽት እንዲሁም ምጥ ነበር:: ምናልባት ርዕሱ ከወንድ ምጥ ይልቅ ‹‹ወንድ ሲማጥ›› የሚለው የሚወክለው ሆኖ አግኝቼዋለሁ:: በሰው ሐሳብና ስም አጠራር ጣልቃ መግባት ባይመከርም፡፡
  እንግዲህ ስለ ሁለቱ የስነ-ጥበብ ሰዎች የነበረኝን ከበሬታና ልሰጥ የሚገባኝን አድናቆት በዚህ እያበቃሁ ከዚህ በላይ ማወደስና ማመስገን ወደ አምልኮት ጎራ ስለሚመደብ አቆማለሁ:: ብዙ መውደድና ብዙ ማፍቀር እንደ አርጤምስ እጣ ፈንታ ስለሚያመራ:: አርጤምስ የምትወደውን ልጇን በማጣቷ በተቀረፀ ሀውልት ስታመልከው ተገኘች፡፡
       በሁለቱ የስነ-ጥበብ ሰዎች ያየሁት ትልቁ መመሳሰልም የቅኔ ገበታን የጠገቡ የመለኮታዊውን ውሃ የጠጡ መኾናቸውን ከላይ ጠቅሼአለሁ:: በእነዚህ መብል እና መጠጥ ውስጥ ግን ሁሌም መደናገርና ወደ ውስጥ በገቡ ቁጥር ለተለያዩ ጥያቄዎች የሚጋብዙ ሐሳቦች ስላሉ ሁለቱ ጸሐፊዎችም የዚህ እጣ ፈንታ ሰለባ መኾናቸውን ተገንዝቤአለሁ:: በዚህ ፍለጋ ወቅትም ወደ አንዱ ተጠግቶ ማመን አላየሁባቸውም በብዛት ግን እያሞገሱና እየደገፉ ያሉት የጭለማውን ጥግ (ሰይጣንን ወደመደገፍ) መኾኑን በጻፏቸው ጽሑፎችም ሆነ የግጥም ስንኞች ማየት ይቻላል:: ለምሳሌ በእውቀቱ ስዩም ‹‹መልክአ እናት›› የሚለው የግጥም ስንኝ ከጌታ እናት ከማርያም ጋር የተዛመደ ውዳሴ እሱን ለወለደችው እናቱ መስጠቱ:- ሰላም ለኪ  ለአይኖችሽ፤ ለከንፈሮሽ፤ ለጣቶችሽ በማለት ያወድሳል:: እናትን ማመስገን ማወደስ ባልከፋ ነገርግን ‹‹አንቺ ከሴቶች ተለይተሸ የተባረክሽ ነሽ›› ለተባለላት የጌታ እናት የተሰጠውን የመንፈስ ቅዱስ ምስክር ለእናት መስጠት አምልኮ ነው! ምዕመናን የማርያምን ምስጋና የሚያቀርቡት የወለደችውን ጌታ ለማመስገን መኾኑ አይካድም:: እዚህ ላይ ገጣሚው ያመሰገነው እናቱን ቢኾንም በተዘዋዋሪ ግን እሱን የወለደች በመኾኗ ራሱንም እያመሰገነ መኾኑ በድብቅ ታይቶኛል:: እንግዲህ ትልቁ ችግር ከቅኔ እና ከመለኮታዊው ኃይል ያገኙትን ጥበብ ለራስ ጥቅምና ሸቀጥ ማዋል ህዝብንም ማወናበድ መወላወል በመኾኑ አንባቢ ልብ እንዲል የሚመመክር ሐሳብ ነው የያዝኩት፡፡ ከአንዱ አንዱን መለጠፍ ለአንድ የተሰጠውን ሌላኛው መስጠት አንባቢን ግራ ያጋባል:: ምን አልባት በሁለቱም ወገን ኾነው ለሚያነቡ ሰዎች ወይንም ሁለቱንም ለማያውቅ አንባቢ ተራ ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ አንድን ወገን አጥብቆ ለያዘ ግን ለሁለት ጌታ መገዛት አትችሉም የሚለውን ቃል የሚያፋርስ በመኾኑ ጥቁሩን ከነጭ ብርሃንን ከጨለማ ማቀላቀልና መለጠፍ አይቻልም:: የቄሳር ለቄሳር ነውና!
  ይስማከ ወርቁም በ‹‹ወንድ ምጥ›› ስራው የወደድኩለት የግጥም ስንኝ ‹‹ሰቆቃወ ቂል›› በስንኞች መዳረሻው ላይ ‹‹የልቤ ዳጎን›› እያለ የገለጻት ሴት ከትክክለኛ የጣዎት አምልኮ የማይለያይ ሐሳብ በመያዙ በ ዜሮ የሚያባዛ ቃል ነው:: በዚህ መደብል ላይ ‹‹ሰይጣን የታደለው›› ብሎ ያቀረበው ግጥም ምናልባት ወደ ጨለማው ንጉስ ማዘንበሉንና መከተሉን የሚያመላክት ግጥም ነው፡፡ ‹‹ሪቢ›› ብሎ ያቀረበው ግጥም ‹‹የቀንድ አውጣ ኑሮ›› በተሰኘችው መድብል ‹‹ኦላ ረቢ ክርስቶስ ውረድ ከጫንቄዬ ውረድ›› እያለ ያቀረበው ሐሳብ መቶ በመቶ የሚያመልከውን ያሳየበት አረጋጋጭ ስንኝ ይዟል:: ያሻውን ማምለክ የፈለገውን መከተል የግሉ ምርጫ ተፈጥሯዊ መብቱ  መኾኑን ገልጸናል ነገር ግን አንዱን ከአንዱ መለጠፍ የጠራ እምነት እና አመለካከት አለመያዝ ትልቁ ችግር መኾኑን ለማስገንዘብ እወዳለሁ:: ሰይጣንን መከተል በብዙ ጊዜ በፍርሃትና በመጠራጠር ስለሚኾን እርሱን የሚከተሉ ሰዎች ሙሉ በሙሉ አምነው ተደግፈው ሲከተሉ አናያቸውም የ‹‹መንፈቅለ መንግስት አለቃ!››  የሚሉት አምላካቸው ዲያቢሎስ  አንድን ነገር ፈንቆሎ የመጣ ተቋውሞ የተጣለ በመኾኑ ይህንን ገዥ መከተል ሁልጊዜም ሲዋትቱ ሲቅበዘበዙ መኖር ነው፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ሙሉ በሙሉ ቆርጠው አምነው የማይታዩት:: ከወንድ ምጥ የግጥም መድበል ውስጥ ‹‹የአፈ ጉባኤው መዶሻ›› ግጥም በውስጡ በቀላሉ ሊታይ የማይችል ሐሳብ አለው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ ሰዎች መልዕከት ምዕራፍ 8 የተጠቀሰውን ሐሳብ በመውሰድ በቀጥተኛ ሐሳብ ‹‹በፓርላማ ለሚያንቀላፉ የህዝብ እንደራሲዎች›› ብሎ ያቀረበ ሲሆን ሌላው የማይታየው ሀሳብ ግን አፈገባኤውን እንደ አብ ( አባት እግዚአብሔር) መዶሻውን ደግሞ እንደ ወልድ ( ክርሰቶስ) አድርጎ ያስቀመጠ የሸፍጥ ሐሳብ ነው፡፡ ሐዋሪያው ጳውሎስ በመልዕከቱ የሚያጸድቅ ማን ነው? የሚኮንንስ ማን ነው? ብሎ የመሰከረውን የኢየሱስ ክርሰቶን ስም መዶሻ ብሎ መሰየሙ ለፈራጁ ይቀመጥ፡፡ መፍረድ ለርሱ የተሰጠ በመኾኑ ራሱ አምላክ የሚፈርደው ይሁን!
       መዶሻ የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል
       የሚያጸድቅ መዶሻ ነው የሚኮንንስ ማን ነው
        ……..ይልቁንስ…………
       ጉልላታችን ያነጸው ካስማ ማገር ያፋቀረው
      ወፍጮ ከመጅ የሚወቅረው በአፈ ገባኤ ቀኝ ያለው
      እኛ እኛን የሚወቅረው መዶሻው ነው::›› በማለት በውስጥ ሐሳብ ስራውን ይሰራል፡፡ ለግልብ   ለአንባቢያንም የማይታይ ሐሳብ ይዟል ::የመጽሀፍ ቅዱስን የጳውሎስ መልዕክት ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ 8 ከቁጥር 33 ዠምሮ ያንብቡ፡፡
   የ‹‹ቀንድ አውጣን›› ኑሮ የግጥም መድብል በተደጋጋሚ ሳነብ አምላኬን አምስገኜአለሁ፡፡ ጥቁርና ነጭ አይንን በመስጠቱ እንዲሁም ብርሃናዊ ልቦናን በመቸሩ ይህን ግልብ ጥቁርና ነጭ አለም በሚገባ እንድመለከት አድርጎኛል:: አምላክን በአርአያው በአምሳያው እኛን መፍጠሩ የገረመው ይህ ፀሐፊ የአምላክን ህልውና በሚዳፈር መልኩ ሲያቀርበው ተመልክቼለአሁ:: ቆንጆ ናት ብሎ ያቀረባትን ሴት አምላክ እሷን ከመሰለ ቆንጆ ነው ብሎ ማቅረቡ አንድን ፍጡር ከፈጣሪዋ ማስበለጥ የቀረበበት አምልኮ መኾኑን ተረድቼአለሁ:: በተከርቸም ስራው ላይም በመግቢያው ያስቀመጠውን የአንድ ጀብደኛ ሰው ዐባባል ተርጎሙ ማስቀመጡ ከፈጣሪው ጋር የተጣላ መኾኑን የዚህን መግቢያ መጽሐፍ እንድታነቡት እመክራለኹ፡፡ አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር የሚለውን - ምንማችን ሆይ በምንም የምትኖር ምንምህ ትምጣ…እያለ ይጠርቃል፡፡ ፈጣሪ የፈጠራቸውን ሲያሰቃይ እኔ ግን በፈጠራዬ  ያስቀመስኳቸውን ገጸ-ባሕርያት አላሰቃይም በማለት ከፈጣሪ ጋር ሲግደራደር ማየቱ ከአባታቸው ከዲያቢሎስ የወረሱት ትዕቢት በመኾኑ አዲስ ነገር አይደለም፡፡
   ተመስገን ደሳለኝ ‹‹የመለስ አምልኮ›› በሚል ርዕስ ያስነበበን ጽሑፍ አንድ ግለሰብ ሊሰጥ ከሚገባው ስም በላይ ከሄደ አምልኮት መሆኑን በመግለጽ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩት የመጽሐፍ ቅጂዎች አመላካች ናቸው:: በስነ-ጥበብ ዘርፍ ያለውን የተጋነነ አምልኮ ሊያሳየን የሚችል አንባቢ /ጸሐፊ/ እንዲሁም ሃያሲ ያስፈልገናል:: ለዚህ ነው ህዝቡ የሚያመልከው አጥቶ የሚጨብጠው ጠፍቶበት ሲቅበዘበዝ የሚታየው፡፡
    ‹‹የእግዚአብሔር እና የብሔር ብሔረሰቦች ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ አንደ ታቡ/Taboo/ ነው፡፡›› በማለት አቶ በእውቀቱ ስዩም አቅርበውልናል፡፡
 Taboo የሚለውን ቃል ኮንሳይንስ ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት
taboo (also tabu) a social or religious custom placing prohibition or restriction on a particular thing or person. Adj. prohibited or restricted by social custom. designated as sacred and prohibited. Place under such prohibition. . / forbidden ፡፡ አማረኛውም (የተከለከለ ነገር እያደረጉት የማይናገሩት) በሚል ይተረጉመዋል፡፡ በእውቀቱ ስዩም በአንድ መጣጥፉ ያስቀመጠው ኢትዮጵያ ውስጥ ሰለ እግዘአብሔርና ስለ ብሔር ብሔረሰቦች የሚያወራ እንደ Taboo ይታያል ብሎ ማስቀመጡ በጣም የሚያሳዝን ሐሳብ ነው፡፡ ቆፎው የተነካበት ንብ ሆ! ብሎ ቢዘምት የንብን ቀፎ መንካት Taboo ነው ብሎ መውሰድ ምነኛ ሸፍጥ ነው? ምንም እንኳ ከንብ የበለጥን ፉጡሮች ብንሆንም እግዚአብሔር ሲነካብን ግን ዝም ማለት አንችልም:: ምንም እንኳን እንደ ንብ በመርዝ መናደፍ ባይኖርብንም በጥበቡ ኃይል መመስከርና ሰላማዊ ጣፋጭ ቃሉን       (ማሩን) መስጠት ይጠበቅበናል፡፡ ቡጥጫና ቁንጥጫ ማስከተል ባይጠበቅብንም ፤ እንደ ንብ መርዝ ማስከተል ባይመከርም የቃላት ሰይፍን ይዘን በመንፈሳዊ ጦር መዋጋት አለብን፡፡ በመዳረሻ ሓሳቡም  ሰው በብሔር ተከፋፍሎ ከሚጣላ ሳይንቲስቶች እንኳ ከአሳ-ነባሪ የመጣን ነን ብለው በሚያስተምሩን ሰዓት ሰው በተራ ነገር ሲጎነታተል ማየቱን አዝኗል፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ሰው በዘር በቀለም በሃይማኖት በጎሳ ሊተነኳኮስ አይገበም፡፡ ከሰውነት በታች ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ከአሳ-ነባሪ መጣን የሚል ወገን፡፡ በእግዚአብሔር ለሚያምኑት እግዚአብሔርን መንካት ብሎ  በTaboo መጣጥፍ ያቀረበቀው ያልበሰለ ሓሳብ አስቂኝ ነበር፡፡  አዋቂዎች ነን ባይ ነገርግን ያላዋቂዎች ጅራፍ ነው፡፡
      ሰላማዊ እውነት የያዘ የስነ-ጥበብ ሓሳብ ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም ለመቀበል ዝግጁ መኾን አለብን፡፡ ይህም የሚኾነው አንባቢው ሲበራከትና፡፡ በረጋ መንፈስ መመርመር የሚችል አንባቢ ሲገኝ ነው፡፡ ብዙ የሚያነብ ሰው በብዙ ይፈተናል፡፡ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን፤ ጨርቅም እንዱሁ በእሳት ይለያልና፡፡ ለአንባቢዎች  የተተወ የቤት ስራ ይሆናል፡፡ አገራችን በብዛት ያጣችው ይህንን ነው፡፡ ብዙ አንባቢያን ሊኖሩ ይቻላሉ፡፡ አስተዋይ አንባቢ ግን ጥቂቶች ናቸው፡፡ ጥቂት ጸሐፊያን አሉን፤ ጥቂት አስተዋይ አንባቢያንም አሉን፡፡ ጥቂት አስተዋይ ሃያሲያንም አሉን፡፡ ብዙ ሳያነቡና ሳይጽፉ ነገር ግን በጩኸት ብቻ የበዙ ጸሐፊያን-አንባቢያን ከበዙ ችግር ነው፡፡ አስተያት መቀበል የሚወዱ ጥቂት ጸሐፊያን አሉ፡፡ ብዙ ጥቂቶች ደግሞ ከበዙ ችግር ውስጥ መግባታችን አይቀርም፡፡
       ስለዚህ አንባቢያን በምናነብበት ወቅት እንጠይቅ፡፡ ከተለያዩ ማዕዘናት በማየት እናንብብ፡፡ የተጻፈውን ነገር በውል እንለይ፡፡ ጥቁርና ነጩ ሳይምታታብን በሚገባ ተጠንቅቀን እናንብብ፡፡ ስንጽፍም እንዲሁ፡፡ ጸሐፊያን በምትጽፉበት ወቅት ጥቁርና ነጩን እየለያችኹ እንድትጽፉልን እንማጸናለን፡፡ ይህ ካልኾነ ግን በመሀል ቤት የሚወቀጠውን ህዝብ እናስብ፡፡ ጎርፍ ጠራርጎ ይወስዳል እንደሚባለው፡፡ ላለመወሰድ መሰረት መያዝ ነው ጎበዝ! በቲፎዞና በጩኸት የሚኖር ህዝብ ከበዛ በተፅእኖ የሚኖር ትውልድ ይበረክታል፡፡ ታላቅ ክሽፈት!
      ‹‹እሳት ወይ አበባን›› የተረዳኹባት ጊዜ ደርሶ መቸም በተውሶ የሄደ መጽሐፍ አይገኝምና ለመግዛት ዋጋ ከማይፍቁ መጽሐፍ አዟሪ ወዳጆች ጋር ተገናኘኹ፡፡ ‹‹አለች›› አለኝ፡፡ ዋጋ ስጠይቃቸው 3ከ50 ሲሉኝ በጣም በመደሰትና በመገረም 3ብር ከሃምሳ ስትሸጥ ነበረች መጽሓፍ በዚህ ኖሮ አቀበት በኾነበት ጊዜ በዋጋዋ መገኘትዋ ደንቆኝ ብሬን ሳወጣ፡፡ ተሳለቁብኝ! አልገባኝም ነበር ለካስ 3ከ50 ያሉኝ ‹‹ሶስት ሞቶ አምሳ ብር ነበር!›› አበስኩ ገበርኩ!....
   ተመልሼ የቀንድ እወጣ ኑሮን መተንተን ዠመርኩ፡፡ ‹‹የማርያም መቀነት›› የምትል ስንኝ አበረታታችኝ፡፡ ‹‹ረቢ›› ለሚለው ልላኛው ግጥምም መልስ ምቴን ለጋኹ፡፡ ጥቁርን ከነጭ እንድለይ የጥቁርና የነጭ አምላክን አመሰገንሁ!  አንባቢ ሆይ ጥቁርና ነጭ አይን እንዳለኽ ኹሉ ለህሊናህ ጥቁርና ነጭ መነጽር በማበጀት ወደ መረጥኸው መንገድ ሂድ፡፡ ይስማዕከ በዣንቶዣራ መጽሐፉ ስለ ፍሪሜሰን ለመተንተን ሞክሯል፡፡ ዋነኛ መለያቸው ጥቁርና ነጭ ምንጣፍ መኾኑን አላስቀመጠልንም፡፡ እነዚህ ሚስጥራዊ ቡድኖች Yes, lucifer is god, and unfortunately Adonay is also God, for the eternal law is that there is no light without shade, no beauty without ugliness, no white without black, for the absolute can only exist as two gods, darkness being necessary for light to serve as its foil, as the pedestal is necessary to the statue, and the brake to the locomotive..". በማለት ማመናቸውን አልተረዳኸውም ወይም የዚህ አስተሳሰብ ቀንበር ስር ነህ! ለሁለት ጌታ ግን  መገዛት አትችሉም፡፡ ብርሃን ከጨለማ ሕብረት የለውም፡፡ የቄሳርን ለቄሳር የእግዚአብሔረን ለእግዚእብሔር!  ቸሩ ቸር ያቆየን…             
 ላኦ ቢረ*ን ሰም-

ኦላ ረቢ ብለህ ገጠምክ ተባለ አሉ
ከጫንቃዬ ውረድ በቃኝ አልክም አሉ
ይስማህ አሜን ብለህ ጠንክረህ በቃሉ
ሸምተህ አትርፈህ እድሜህን በሙሉ..
ሁሉን ያዬህ መስሎህ ዝነኛ መባሉ..
               ያንስታይ ተወካይ
የጲላጦስ ወገብ-የሌጊዮን ደዋይ
  የማሳሳት ቀመር-የሐሰት ተጋዳይ                
የተጣለው ኮከብ-የክደት ተከታይ
በምን እንወቅህ-የጥበብ ወላዋይ?
ለምነሽ ለምነሽ ስትኖሪ ስታታ
ሲጠፋሽ መንገዱ ስታጪ ገላጋይ
ወይ ያዙኝ ልቀቁኝ ሳይገድሉ ነኝ ገዳይ…
እሱ ንደው ከሃሊ ሁሉን ታጋሽ ከላይ
ምንም አያልቅበት
ምኑም አይጎድልበት
አንተ ብን አባይ*
ይከብራል ይነግሳል በምድር በሰማይ..!
ድንቄም አባራሪ
10 አባራሪ
ሁሉን እይዛለሁ
ሁሉን አውቃለሁ ባይ
ተመለስ! ተመለስ! አንዱን ይዘህ አሳይ፡-
ህዝቤም ስታዳምጥ ሰሙን ከወርቅ ለይ!
እጅግ በጣም የተሳሉ ልኂቃን እየመጡብን ነው፡፡ የማርያም መቀነት ይላሉ- ፍጡርን በፈጣሪ ያመሳስላሉ…ኦላ ረቢ ረቡኒ(መምህርን) ይሰናበታሉ፤ ቃሉን ደግሞ ይጠቅሳሉ ሃይሉን ግን ይክዳሉ! እባካችሁ አንዱን ያዙና እንለያችሁ በመሐል ቤት አላዋቂ አበዛችሁ…

               *ላኦ ቢረ- ኦላ ረቢ
                                          *አባይ (ወንዙና ሚዛኑ) - አባይ ወንዝ፤ አባይ ሚዛን፡፡

1 comment:

Unknown said...

መለኮት የሁሉም ፈጠራ ምንጭ መሆኑ የታወቀ ነው ። የሀገራችን ደራስያንም ይህንን እውቅና መስጠታቸው ተገቢ ነው ማለት ይቻላል። በእውቀቱ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው አስተያየት ይበል ልክ ነው የሚያሰኝ ነው።