Feb 13, 2013

ለመክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ



የክሽፈቶች ክሽፈት(6)

ክሽፈት…
ገንዘብ ሲኾን ጌታ
ጌታ ሲኾን ገዥ
ገዥም ሲኾን ጨቋኝ
ክሽፈት…
ትዳር ሲሆን ግዞት
ግዞት ሲኾን ምሬት
ምሬት ሲሄድ ስርቆት
ክሽፈት…
ጎሳ ሲሆን ዋና
የሰው ልጅ ፈተና
ጠባብ ሲሆን ሃሳብ
ሃሳብ ሲኾን ሰበብ
የሰው ዘር ሲጠና
ትውልድ ሲያጣ መና
ህይወት ሲያጣ ቃና
በችጋር በስቃይ መሬት ስትኾን ኦና
ፍቅር ሲቀር መና…
ክሽፈት…!
አንዱ ሲንፈላሰስ
በሊሞዚን ዝና
በካዲላክ ወገን በፖርሹ ሲዝናና
ሌላው በባዶግሩ ለከርሱ ሲናና
ልዩነት ሲሰፋ-በህዝብ ሃብት-በወንጀል ሲነግስ በሙስና
የክሽፈቶች ዋና…!

ክሽፈት ማለት ግዞት
በመንፈስ ልቦና በህሊና መሞት፡፡
መታሰር በደዌ መተብተብ በጠኔ
እጅ እግር ተይዞ ማጣት ትግል -ወኔ፡፡
ክሽፈት መዋዠቅ ነው መንደርደር ቁልቁለት
እንዳይመለሱት ልጓም አትቶ መቅረት…
አለመማር ክሽፈት ከኖርንባት ትላንት
እድገት አለየማት ታሪክ ሲሆን ተረት
                  -ተረት ሲሆን ቅዠት፡፡
ክሽፈት ክሽፈት ክሽፈት…
በቀደመው ግዛት ሲታጣ ነጻነት
በጎሳ በድንበር ሲበዛ ጦርነት
ያያቶችህ አለት ሲናጋ መሰረት
ያባቶችህ መንገድ ሲደገም ስህተት
        የነገ ማንነት ራዕይህ ሲሞት
የማክሸፊያው ቁልፉ ጠፍቶብን መዋትት፡፡
የክሽፈቶች ክሽፈት፡-
                           ትላንት-ዛሬ-ነገ መንደርደረ ቁልቁለት
                         ነገ-ትላንት-ዛሬ መሸከም ያን ዳገት!

የስኬቶች ስኬት
በታሪክ በወኔ አልበገር ማለት
ለክብር ለኩራት መሞት ለነጻነት..
ካገዛዝ ጭቆና ለስልጣን መታገት
ሰው በህግ ሰው ለህግ ስርዓት መገዛት፡፡
ዜጋ በነፃነት በልቦና መዝመት
በስራ በኑሮ ተሻሻሎ ማየት
ችጋር ከምድረ-ገፅ እስኪጠፋ መትጋት
በሰላም በፍቅር መገዛት ለእውነት፡፡ 
                                               ለፕሮፍሰር መስፍን ወልደ ማርያም2005

No comments: