Feb 5, 2013

መክሸፍስ እንደ እኔ…ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እና በዲያቆን ዳንኤል ክብረት


መክሸፍስ እንደ እኔ…
በተስፋ በላይነህ
      በፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም እና በዲያቆን ዳንኤል ክብረት መካከል የቀረበው የብእር እሰጣ ገባ እና አስተያየት ቅብበሎሽ በዲሞክራሲያዊ ስርአት ውሰጥ የተለመደና የሚጠበቅ በመሆኑ ጦር ከመማዘዝ ብዕር ተቀሳስሮ ወደ አንድ መምጣት ይደገፋል፡፡ ሆኖም  ምሑራዊና ምክንያታዊ አልፎም ትህትናዊና  ሀሳቦችን በመያዝ ሌላኛውን አካል ማለትም አንባቢውን በማያስፈራና ነገም እኔም ብፅፍ…… ብሎ ለሚያስብ ሰው አበረታች ምልልስ እንዲሆን እንሻላን፡፡ ሁሉም የሚፅፈው የሚያነበውና  ሀሳብ የሚቀባበለው ይህቺን አገር ለማስተባበርና ሰላማዊ የተሻለች ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመገንባት ነውና፡፡    
      መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ የተሰኘውን የፕሮፌሰሩን መፅሐፍ ባየሁበት ጊዜ በወቅቱ  ለኢትዮጵያ ስልጣኔ ውድቀት ተጠያቂ ማነው? ተብሎ ለቀረበልኝ ጥያቄ መልስ በምፈልግበት ወቅት የወጣ በመሆኑ ለተፈጠረው አጋጣሚ የአጋጣሚዎች ባለቤት የሆነውን ፈጣሪ አመስግኛለሁ፡፡ በጓደኞቼ ዘንድ ለውይይት ለቀረበ ሀሳብ ይህች አገር ለምን ኋላ ቀረች? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት በሰፊው ተወያይተናል፡፡ አንዱ -የቤተክርስቲያን ውስጣዊ እራር ድክመት፤ሌላኛው -የጦርነቶች ብዛት፤አንዱ -የዘር ልዩነት እና ጠባብ አመለካከት እንዲሁም የመንግስት አወቃቀር ድክመትና የስልጣን ጥማት ከገደብ አለመኖር በማለት ሀሳቦች ተሰነዘሩ፡፡ ስለዚህ የፕሮፌሰሩ ሀሳብ (ሳነብ እንደገባኝ) የምንግዚየውም ትውልድ ጥያቄ ነው፡፡ ለምን ከሸፍን?
      በሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 384 ረቡዕ ጥር 08 2005 ዕትም የወጣውን የዲያቆን ዳንእል ክብረት ፅሑፍ ባየሁበት ጊዜ ግራ ተጋባሁ፡፡ በቀረበው አስተያየት በቃላት አገላለፅ መፃሀፉን ለመተቸት የተሞከረና የዲያቆኑ ሀሳብ ትክከለኛውን የተረዳሁትን የመፅሐፉን ሀሳብ ሊገልፅልኝ ስላልቻለ በኔ በቃላት ድክመትና በአስተያየት ምጥቀት ማነስ በሚል ለዲያቆኑም ካለኝ ቦታ በመነሳት ለመወሰን አልቻልኩም፡፡ ሆኖም በመጠያየቅና በመወየወየት ብዙ ይገኛልና ከጓደኞቼ ጋር በተደረገው ውይይት አንድ ሀሳብ ያዝን፡፡ የሚገርመው ፕሮፌሰሩ በወርድ ፕሬስ ድህረ ገጽ የሰጡትን ምላሽ በምናይበት ጊዜ እና ተወያይተን ከያዝናቸው ሀሳቦች ጋር መቀራረባቸው ነው፡፡ በዚህም መሰረት ለጋዜጣው አስተያየት ለመስጠት ወሰንን፡፡
      ዲያቆን ዳኒኤል በትጋት እየሰራ ያለ ሰው ነው ብለን መናገር እንችላለን፡፡ የተለያዩ መፅሀፍትን በአግዮስ አሳታሚ ድርጅት ስር እያቀረበ ለአንባቢያን የአስተሳሰብ ስፋት እየሰራ ይገኛል፡፡ በግሉ ባለው ጦማር (ብሎግ) አማካኝነት ወጣቱ በተወሰኑ ማህበረሰባዊ ድህረ-ገፆች ብቻ ተጠምዶ እንዳይውል ማድረጉ ያስመሰግነዋል፡፡ፕሮፌሰሩም ካላች የጊዜ ትልቅ ስጦታ ጋር በመታገዝ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የነበራቸውን የካበተ ለምድ በህብረተሰባዊት ኢትዮጲያ መንግሰትአስተዳደር የነበራቸውን ቦታና ከ80ዎቹ ወዲህ በመሩት መስሪያ ቤት በግሌ ያደረጉትን የህይወት ጉዞ ጥንካሬና ትግል ሳላደንቅ ማለፍ አልችልም፡፡ በእውነት እንደዚህ የኢትጵያን ታሪክ ከተለያዩ ማዕዘናት (ምንጮች) በማየትና በመረዳት የሚያደርጉትን ሙሑራዊ ትንታኔ የእውቀትና የስልጣኔ ፍለጋ እንዲሁን የክሽፈት ፍለጋ አደንቃለው፡፡ በአሁኑ ሰዓት አንዲህ እያነበበ የቁጭት ምሑራዊ ትንታኔና እይታ እያቀረበ የተሻለች ክብሯን ና ማንነቷን የጠበቀች ኢትዮጵያን ለመፍጠር (ለማምጣት) የሚተጉ ሙህራን ቢኖሩና ቢበራከቱ እውነት የዚህችን አገር ህልውና በገሀድ እየተለወጠ ማየት በተቻለ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር 80ዎችን የእድሜ ቁጥር አልፈዋል እሳቸውን የሚተካ ሰው አለን? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ሌሎችም የታሪክ ፀሐፊዎች ተንታኞችና ተቆርቋሪዎች እንዳሉ ሳንዘነጋ  እንደዚህ ለዘመኑ ቅርብ ሆነው ድምፃቸውን እያሰሙ ሀሳባቸውን ሊለግሱን ይገባለል፡፡
      ዲያቆን ዳንኤል እጅግ በስራ የተጠመደ ሰው መሆኑን ተመልክቻለው፡፡በራሴም ላይ ደርሶ አይቻለሁ፡፡በቅርብ ቀን ያሳተምኳትን መፅሐፍ አስተያየት በመፈለግ መፅሐፌን በመስጠትና በኢ-ሜልም መልዕክት በመላክ ሙከራ አድርጌያለሁ፡፡ የኢ-ሜል መልዕክቱ አንድ አመት ቆይቶም ማየት አልቻለም፡፡ መፅሐፉንም በቅርብ ከሰጠሁት በኋላ በተነጋገርንበት ወቅት የተቀበልኩት ሀሳብ መፅሐፉን አንብቦታል ብዬ መቀበል ግን አልቻልኩም፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የስራ ብዛትና ውጥረት መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ስለዚህ ዲያቆኑን ከመውቀስ አይዞህ በርታ ያሉትንም ክፍተቶች በሚገባ በማየት ጠንክር ከማለት ውጭ ትህትናዊ ምክር ከመለገስ በቀር አንዳችም ጠንከር ያለ ሀሳብና አሉታዊ ምላሽ ለመስጠት እቸገራለሁ፡፡ ሰው በፍቅር ብቻ ይማራልና!  ኢትዮጵያ ለዘመናት ያጣችው ምክርን ሀሳብንና ስልጣንን በፍቅር የሚሰጥ ሰው ነው፡፡
      ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያ ከሳባ መንግሰት እስከ ኢህአዴግ የመጣችው በአፈ ሙዝ ቀሰራና አንዱ በአንዱ ላይ ሲዘምት ሲሸፍት ሀሳቡን ሲያጣጥል መንገዱን ሰርዞ በራሱ ሲተካ በየጊዜው የተፈጠረችው ኢትዮጵያም አዲስ የቤት ስራ በሚሰሩ ነገስታት ስለተሞሸረች ነው፡፡ የቀደመ ክብሯን ይዛ መቀጠል ባለመቻሏ የከሸፈ ታሪክ ብለን እንድናስብና እንድንጠይቅ አስገድዶናል፡፡ በአውነት የነበረንን ስልጣኔና ቀደምትነታችን ዛሬ ባለማየታችን ይህ ትውልድ ለውጥ ከሌለም የሚመጣው ትውልድም ጥያቄ ማቅረቡ አይቀርም፡፡
      ወደ ዋናው የግል ሀሳብ ስንመጣ ይህ ትውልድ የሚለው መልስ ሊሆን ይችላል፡፡ ታሪክ ሰንሰለት ነውና በጊዜ ሂደት ተፈጥሯዊ ቅብብሎሽ እዚህ ደርሰናል፡፡ ስለዘህ ያለፈውን ከመውቀስ የፈሰሰ ወተት አይታፈስም በሚለው አባባል መሰረት የፈሰሰ ወተት ለማፈስ ከመሞከር ዛሬ የያዝነውን ወተት እንዳይደፋ ማድረግ ብቸኛ አማራጭ  በመሆኑም ለዚህ ትውልድ የተሰጠ አደራ ነው you cannot reverse the past but you can Learn from it (ያለፈን ታሪክ መመለስ አይቻልም ከታሪክ ግን መማር ይቻላል)ነውና ቁምነገሩ አሁን ማድረግ ያለብን ካለፈው መማርና የዛሬዋን ኢትዮጵያን ይዞ ለነገ ማስተላለፍ ይሆናል፡፡ ስለዚህ መክሸፍስ እንደ እኔ ወደሚል ሀሳብ የተነሳሁበትም በአሁኑ ያለው ትውልድ (እኔን ጨምሮ) ለሚቀጥለው ትውልድ ታሪክ ሰርቻለሁ ወይ ብለን በመጠየቅ ከሰራን ጥሩ ካልሰራን ግን ከሽፌያለሁ?
ለጓደኞችም የምመልሰው ነገርም ይህን ይሆናል፡፡ ለዚህች አገር ኋላ መቅረት የትናንቶቹን ተጠያቂ ከማድረግ የታሪክ ቅብብሎሹን ለመቀጠልና የከሸፈ ታሪክ አባል ላለመሆን መኖር ይመስለኛል መፍትሔው፡፡
ታሪክ ሰንሰለት ነው ሲባል ያንዱ ህልውና ላንዱ መሰረት መሆኑን በቀላል ምሳሌ እንመልከተው፡፡ የዲም ላይት አምፑልን እንውሰድ፡፡ መነሻውን የሃይል ምንጭ ይዘን በተያያዘው ገመድ እያንዳንዱ አምፑሎች ይበራሉ፡፡ ባላቸው የቀለም ልዩነትም የሚፈጥሩት ውህደት የዲምላይቱ ውበት ነው፡፡ በዚህ መካከል ግን በተወሰኑ ቦታዎች የማይሰሩ አምፑሎች ካሉ ብልሽቱ ለጠቅላላው ዲምላይት የሚፈጥረውን ክስተት ወይንም ተጽዕኖ መገመት አይከብድም፡፡ እንግዲህ ከፕሮፌሰሩ መፅሐፍ የተረዳሁት ይህንን የተበላሸ መስመር በታሪክ ክስተት ውስጥ ፈልጎ ትምህርት መውሰድ፡፡ የከሸፈ የታሪክ ቦታን በመፈተሽ የሚፈጠረውን ተደጋጋሚ የነገ ብልሽት አስተካክሎ የታሪክ ህብረ ቀለሙን ማስዋብ ነው፡፡ መፅሐፉን የተረዳሁትና መፅሐፉም እየጠየቀ ያለዉ ይህንን ነው፡፡ በአድዋ ጣልያንን በእግር ያለጫማ ድል አድርገን ከ40 ዓመት በኋላ በማይጨው ግን እኛ ያው እነርሱ በላይ በታች፡፡ ለምን? መክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ…
በዚህ ትውልድ የምንገኝ ሰዎች ለታሪክ ምን እያበረከትን ነው? ለዚህች አገር ምን እሰራን ነው? ጥንታዊት ኢትዮጲያን እያስታወስን የነበረንን ቀደምትነት ባሕል ስልጣኔ እያስታወስን ምን እበረከትን ነው? በታሪክ ውስጥ ትልቁ ክሽፈት በመንፈስ መሞት ነው፡፡ የምናው የምንሰማው የምንለብሰው የምናወራው እኛን እኛን ካልሸተተ ይህ ትልቅ ክሽፈት ነው፡፡ በዘመናችን የሚቀርቡት የስነ-ጥበብ ስራዎች እኛነታችንን ፈልገው ታሪካችንን አነፍንፈው በዘመኑ እይታ ካላቀረቡልን እየከሸፍን ነው፡፡ ቢነገር ቢሰማ የማይጠገብ ታሪክ ባለቤት ነን፡፡ ሊያስተምሩን ሊለውጡን የሚችሉ አጋጣሚዎች ሞልተው ተርፈውናል፡፡ ብቻ እነዚህን ክስተቶች ፈልጎ በረቀቀ ስነ-ጥበብ ሙያ እያዋዛ የሚቀርብ ነው ያጣነው፡፡ በጊዜያችን ገንነው ከወጡት ሙዚቀኞች የአቶ ካሳሁን ልጅ አንዱ ነው፡፡ በተረዳው መልኩ ሰላማዊ ነው ባለው የግል አረዳዱ የኢትዮጲያን ታሪክ በስነጥበቡ ዘርፍ እያሰማን ነው፡፡ ሁሉም የስነጥበብ ባለሙያ ታሪኩን እያነበበ ስሕተቶችን ወደ መማሪያ ሃሳብ እየለወጠ ቢያቀርብ ይህ ሰው ስለእውነት እያበራ ያለ ሰው ነው፡፡ ታሪካችንን በሚገባ ብናነብ ከትክክለኛ ምንጭና ሚዛናዊ ከሆነ እይታ ብንመለከት ብዙ አስደሳች አኩሪና አስተማሪ ሃሳቦች ይገኛሉ፡፡ እያሳሳበን ያለው ያንጆሊና ክሳት የሮኒ ስብራት… ብቻ ከሆነ ግን ከሽፈናል፡፡ ጌትነት እንየዉ በአንድ ወቅት ያቀረበልን ግጥም አሁን ተጠናክሮ የሚታይ አቀራረብ ነው፡፡ ህንደኬ በተሰኘ የቴአትር ስራው ለመግለጽ ተሞክሯል፡፡ ብዙ ህንደኬዎች ያስፈልጉናል፡፡ በስጋ እየሞትን በመንፈስ እንዳንሞትን እንዳንከሽፍ እንንቃ! የሎሬት ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህንን ሃሳብ ቀንጨብ በማድረግ ልሰናበት፡፡

ይድረስ ወገን ከኛው ለኛ
አበቅቴ ዉሉን አልሳተም፣ ፅዋህን ተቀበለኛ!...
ህዝብ መርተን ያለአላማ፣ ያለማተብ ያለሃይማኖት
በአምባገነንነት ዕብሪት፣ ያለዲሞክራሲ ፍኖት
ጠመንጃ ነክሰን በመግደል፣ ጠመንጃ ነክሰን በመሞት
ፍቅር ፈርተን ሰላም ፈርተን
አንድነታችንን ቀብረን፣ ተስፋችንን አጨልመን
የነፍስን አንደበት ዘግትን
የልጆቻችንን ተስፋ፣ እምቡጥ ሕልማቸውን በልተን
ሳይነጋ እየጨለመብን፣ ሳንጎለምስ እያረጀን
የስጋችንን ጨርሰን፣ በመንፈስ እየሞትን ነን፡፡…

No comments: