Feb 25, 2013

ምልክአም -ሰይፈ ነበልባል_Abe Gubiegna To the prime minister

Writer Abe Gubegne 1925-1972



















ምልክአም -ሰይፈ ነበልባል
ጠ/ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሊያነቡት የሚገባ መጽሐፍ፡፡

   የስነ-ጥበብ ሀይል ያለፈውን የታሪክ ክስተት በጊዜ ርቀት በቦታ ርዝመት ሳይስተጓጎል ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ዕይታን የማበርከት ጸጋ እንዳለው በተለያዩ የስነ-ጥበብ ሰዎች ስራ አይተነዋል፡፡ ለምሳሌ ብንጠቅስ ሎሬት ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህን የአጤ ቴዎድሮስንና የአቡነ ጴጥሮስን መራራ ሰዓት ተረድቶ በነርሱ ቃናና ልሳን የተነገረ እስኪመስል ድረስ አቅርቦልናል -ነፍስ ይማር! በጊዜው የሚገኙ የስነ-ጥበብ ሰዎችም ጊዜውን በሚገባ እያዩ ፣ የህዝቡን የውስጥ ችግር እያደመጡ ሊተነፍሱልን ይገባል፡፡ ከዚህም አልፎ በዛሬውና በትናንቱ በጊዜ ክስተት የተፈጠሩትን አጋጣሚዎች ለነገው ትውልድ የማስተላለፍ የማሳየትና ቢቻል ደግሞ እሰዬው ነው፡፡ ዛሬ ላይ ሆነው ነገን ማየት የሚችሉ የስነ-ጥበብ ሰዎች የነብይነት ጸጋ የተላበሱ እንዲመስሉ ያደርጋቸዋል:: ይህንን ጽሑፍ እንድ ድፍና በነበረበት ዘመን ነገን ማየት የቻለ ‹‹ነበልባል›› ጽሑፊ አቤ ጉበኛ አንዱ ነው ፡፡   አቤ ጉበኛ (፲፱፻፳፭ / ባሕር-ዳር አካባቢ፣ ይስማላ ጎጃም ተወለደ - ፲፱፻፸፪ / አዲስ አበባ ላይ አረፉ-ህይወቱንና ታሪኩ የምገልጽበት ጽሑፍ ባለመሆኑ የሰራቸውን የስነ ጥበብ ስራዎች በመጥቀስ የዚህ ጽሑፍ ርዕስ ወደ ኾነችው ስራው እሻገራለሁ መስኮት (ግጥምና ቅኔ)፤እሬትና ማር (ግጥምና ቅኔ)፤ከልታማዋ እኅቴ (ልብ-ወለድ)፤ምልክዐም ሰይፈ ነበልባል (ልብ-ወለድ)፤አንድ ለናቱ (ታሪካዊ ልብ-ወለድ)፤የረገፉ አበቦች (ልብ-ወለድ)፤ከመቅሰፍት ሠራዊት፥ ይጠንቀቅ ሰውነት (ተውኔት)፤ቂመኛው ባሕታዊ (ተውኔት)፤የሮም አወዳደቅ (ተውኔት)፤የራሔል ዕንባ (ተውኔት)፤የደካሞች ወጥመድ (ተውኔት)፤አልወለድም  (ልብ-ወለድ)፤የዓመፅ ኑዛዜ (፲፱፻፶፭ ..) (ልብ-ወለድ)፤The Savage Girl 1964 ... (እንግሊዝኛ)፤Defiance 1975 ... (በእንግሊዝኛ)፣ የፓትሪክ ሉሙምባ አሳዛኝ አሟሟት…ይገኙባቸዋል፡፡
       በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ንጉስ ነገሰት ዘ ኢትዮጵያ በ 34 ኛው ዘመነ መንግሰት የታተመችው ምልክአም ሰይፍ ነበልባል መጽሐፍ የወደፊቱን ያየችና በተግባር ሊሰራባት የምትችል መጽሐፍ ናት፡፡
       ይህችን የ 170 ገጽ መጽሐፍ በልጅነት እድሜዬ ባያትም የተረዳኋትና በጥንቃቄ ያነበብኳት ግን በቅርቡ ነው፡፡ አቤ ጉበኛ ለእውነት የታገለ ፀሐፊ መኾኑን በስራዎቹ ማየት እንድንችል ያስመሰከረ ጥበበኛ ነበር፡፡ የስነ-ጥበብ ሰዎች በፖለቲካው ዘርፍ እውነትን ይዘው ባላቸው ፈጠራ ህዝቡን ሊያነቁት ይገባል፡፡ እንደ ጥንቶቹ  ዜና መዋዕለ ፀሃፊዎች በጠጅና በጉርሻ እየተደለሉ የንጉስን እንጂ የህዘቡን ድምጽ ( ጩኸት ) የማያሳሙ ከሆነ ለህሊናቸው ውርደት ለስማቸው ግርዶሽ ማስቀመጣቸው አይቀርም፡፡
  የስነ-ጥበብ ሰዎች በመንግት ደረጃ ያላቸውን ሃይልና በህዝቡም ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ባደጉ አገሮች ማየት ቀላል ነው፡፡ በመንግስት የተወደዱ የስነ ጥበብ ሰዎች በህዝቡ ዘንድ ሲወደዱ አናይም በህዘቡ ዘንድ የተወደዱ ሰዎች ደግሞ በመንግሰት ዘንድ እንደማይወደዱ የምናየው ሀቅ ነው፡፡ በሃገረ አሜሪካ በ 2008 የፕሬዝዳንት ኦባማ ‹‹በሊንከን ሜሞሪያል›› ሰፊ ስፍራ ለተሰበሰቡት ዜጎች መንግስትንና ህዝቡን ወክለው የቀረቡት ዘፈኞችና ተዋንያን ነበሩ፡፡ ሥነ-ጥበብ ምን ያህል ትልቅ ስፍራ ትልቅ ኃይል ያላት ሥጦታ መኾኗን ያስመሰከሩበት ዝግጅት ነበር፡፡ / በነገራችን ላይ የስነ-ጥበብ ሰዎችም የፖለቲካው አስተሳሰብ ተመሳሳይ ኾኖ በመገኘቱ ነበር ህብረት የፈጠሩት/
      እንግዲህ አቤ ጉበኛ በፃፉት ምልክአም ሰይፍ ነበልባል የተባለች አጭር ፈጠራ ስራ ያዘለችው ቁም ነገርና ምክር ከአንድ ህገ-መንግስት ጋር አባሪ ሆና የምታገለግል መጽሀፍ መኾኖን በ 10 ጣቴቼ መመስከር እችላለሁ፡፡ ጥያቄዬም ጠ/ ሚኒስቴራችን ይህችን መጽሐፍ አንብበዋታል? ካነበቡትስ እንዴት ይመለከቱታል?

  መጽሐፉ በመቅደም ክፍሉ ዓላማችን የቸገራት ምንድነው? ምግብ ? ልብስ? ቤት? አዎን በሙሉም ባይሆን በከፊል የነዚህ ነገሮች ችግር አለባት በማለት ይጀምራል:: ሲቀጥልም ሰው እንዴት አድርጎ ራሱን ብቻ እንደሚያጠቅም ከማሰብ ይልቅ እንዴት አድርጎ ከወንድሞቹ ጋር በሰላም መኖር እንዲችል ጨምሮ ቢያወቅ ይበልጥ በተደሰተ  ነበር፡፡ በማለት ዘመን የማይሽረውን ምክሩን ያስነብበናል፡፡ እያንዳንዱን አንቀጽ ማስቀመጥ መጽሐፉን መገልበጥ ቢኾንብኝም አንቁፆቹ የያዙት ፍሬ ሃሳብ ግን ልቀቁኝ ልቀቁኝ አያሰኙም፡፡ በተቻለኝ መጠን አጠር አጠር ያሉትን ለማቅረብ እምክራለሁ፡፡
      የመጽሐፍ ዋና ጭብጥና ሃሳብ የሚያወራው ስለ አንድ ምልክአም ስለተሰኝ ጠ/ሚኒስተር ሲኾን ጠ/ሚኒስተሩ ወደሞት ያሻገረውን ሰዓት በማስቀመጥ ለህዝቡ የሚያስተላልፈውን ምክር በመለገስ ይጀምራል፡፡ ይህች አለም ለእውነተኞች እንደማትመችና እውነተኞች በዚህች ምድር ለረዥም እድሜ እንደማይቆዩ በነኬኒዲ ጋንዲ ፣ ሊንኮን ሌሎችን ታላላቅ ሰዎች በመጥቀስ ይህንንም ጠ/ ሚኒስትር ምልክአምን ሞት በበለጠ በማቅረብ እውነታውን ያጠናከርልናል፡፡
      ይህ ደራሲ ጽሑፉን ፈጠራ ቢለውም ከአንዳንድ በዕውቀት ከነበሩ ሰዎች ጋር በመጠኑ ይመሳሰላል በማለት በመግለጽ ያለውን የስነ-ጥበብ ኃይል ተጠቅሞ የጠ/ ሚኒስትሩን ስራዎች በልብ-ወለድ መልክ እያዋዛ ያቀርብልናል፡፡ እንዲህ ነው እንጂ የጥበብ ሰው!
       ጠ/ ሚኒስትሩ ሕይወቱ ለማለፍ በተቃረበችበት ሰዓት ለምክትል ጠ/ ሚኒስትሩ እና ለሌሎችም ሚኒስትሮች በሚያደርገው ጥያቄና መልስ ይጀምራል፡፡ ሚኒስትሮቹ የሚጠይቁትን ጥያቄ ሰላማዊና ለሌሎች በማሰብ በቀረብ ሃሳብ እየመለሰ ስራውን እስከ እለተ ሞቱ የሚሰራበትን ሁኔታ ያስገነዝበናል፡፡ ከአንዳድ ቃለ-ምልልሶች በኋላም በሕግ ስም የሚጻፍም ወንጀል በነጻነት ስም የሚመጣ ባርነት በጽድቅ ስም የሚሰራ ኃጢያት ፣ በርኅራሄ ስም የሚሰራ ጭካኔ ዓለምን ምን ያህል እንደሚጎዳት እወቁ ሟቾች መኾናችሁን ልታውቁ እንደሚታወቅ ሁናችሁ ራሳችሁን አታታሉ እውነትኛ ነገር ቢክድም ከእውነትነቱ አያልፍም ራሰን በሀሰት ቢያታልሉት እውነት የተደበቀውን ምስጢር ትገልጠዋለች ራሳችሁን ነፃ የምታደርጉት በእውነት እንጂ በውሽትአይደለም በማለት እህ! ምን ያለ ሰላማዊ ሞት ፍቅርን እስከ ሕይወት ፍፃሜ ሳያጡ መሞት ምን አይነት ከፍተኛ ዕድል ነው! ነፍሱ ከስጋው በመለየት የፅሑፍ ስራው ይጀምራል፡፡ መሞቱን ወደ መጨረሻ ብቻ አስቀምጦ ‹‹ትራጀዲ›› የሚሉትን የስነ-ፅሑፍ ዘርፍ አልተጠቀመም፡፡ ምናልባት ትራጄዲ ቢኾን ከመጽሐፍ ጭብጥና ምክር ይልቅ አንባቢው በልቅሶና በስቃይ እንዳይጎዳበት ያደርገበትን ዘይቤ ወደጀዋለሁ፡፡ መሞቱን እያወቅን የምናነበው ስራ በቀጥታ ትኩረታችን ከሚተርክልን ጭብጥ በመኾኑ የመጽሐፍን አላማ በሚገባ የያዘች ስራ ነች፡፡
      ንጉስም የቀብር ስነ-ስርዓቱን ለማሰጀመር በሚያደርጉት ንግግር ይቀጥላል፡፡ የንግግራቸውም ሃሳብ የጠ/ ሚኒስትሩን ስብዕናና ተግባር የሚገልጽ በመኾኑ ጠ/ ሚኒስትሩን በሚገባ እያውቅናቸው የምንሄደው ከተለያዩ ሰዎች ጋር የተናገሩትንና በተለያዩ ስፍራዎች በፓርላማ  በአለማቀፋዊ ስብሰባዎች በሚያደርጓቸው ንግግሮች ይህንን ነበበልባል የተባለ ጠ/ ሚኒስትር በቅርበት እንደናውቀውና እንድንመኘው ያደርገናል፡፡
      በምዕራፍ 2 ክፍልም ጠ/ ሚኒስትሩን አጭር የህይወት ታሪክ ይገልፅልናል፡፡ የተማሩበትን ት/ቤት የትምህርት አቀባባላቸውንና ያደረጉትን ፖለቲካዊ ትግል ከቀድሞ ጠ/ ሚኒስተር ጋር ሊያመሳስላቸው በመቻሉ አቤ ጉበኛን የወደፉቱን ተመልካች ፀሐፊ ሊያስበለው የሚችል ገጽ ነበር፡፡ ኾኖም አቤ ጉበኛ በጽሑፍ የገለፀው ጠ/ ሚኒስተር በኢትዮጵያ ምድር ተከስቶ ቢኾን ኖሮ ይህች አገር ትክክለኛውን መሪ አገኘች የሚያስብል የታሪክ አጋጣሚ ይኾን ነበር፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ የሞቱተም ሥልጣን የውጡትም በተቀራራቢ ዕድሜ በመኾኑና የነበራቸው ተናግሮ የማሳመን፤ የዕቅድ አወጣጦች ፤ በህዝብ ዘንድ አመኔታና ቅርርብ አሁንም ይህንን ምናባዊ ጠ/ ሚኒስትር እንዲንፈልግ ያደርገናል፡፡ ‹‹ሞት ወቃሽ አያደርገን›› የሚሉትን የአባቶቻችንን ባሕል በማስታወስ ሥራዎችን ግን ማሰብና ማወደደር ከአባቶች መንገድ መውጣትን አይፈጥርብንም፡፡ ስለዚህ ይህንን መጽሐፍ አንብበን የቀድሞውን ጠ/ ሚኒስትር የሚወክል መጽሐፍ ነው? አይደለም! ለማለት የየራሳችንን ውሳኔ እንስጥበት፡፡ ለኔ ግን ጎልቶ የታየኝ ይህንን መጽሀፍ ያሁኑ ጠ/ ሚኒስትር አንብበው ራሳቸውን እንዲገመግሙና በህይወት እያሉ የተሰጣቸውን ትልቅ ዕድል ተጠቅመውበት እንዲያልፉ ሀሳብ ለመጠቆም ነው፡፡ ባለፈ ታሪክ ከመከራከር ላለንበት ጊዜ ቦታ መስተት ጠቃሚ መኾኑን በመረዳት፡፡
   መጽሐፍ ይቀጥላል ህዘብ ሲያለቅስ የተለያዩ መፈክሮችን በመያዝና የተለያዩ ታላላቅ ሰዎች ሀሳባቸውን በግጥም ሲገለጹ ያስነብበናል፡፡ በምዕራፍ 3 ላይ ጠቅላይ ሚኒስተር ምልክአም በጠቅላይ ሚስትርነታቸው ዘመን ከተነገሯቸው ንግግሮች አንዳንዶቹ በማለት ስልጣን በተረከቡበት ቀን በፓርላማ ያደረጉትን ንግግር ያስነብበናል፡፡ በዚህም ንግግራቸው ወቅት የመሪዎች ስም ከህዝብ በበለጠ ታወቆ መሄዱን፤ ስለ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ያላቸውን አቋም በማተኮር ሃሳባቸውን ይገልጹበታል፡፡ በምዕራፍ 4 ደግሞ ጠ/ ሚኒስተር ምልክአም የመሪነታቸውን ስራ እንደጀመሩ ያዘጋጁትን የልማት ዕቅድ ባቀረቡ ጊዜ ይደረጉትን ንግግር ያቀርብልናል፡፡ እድገት የሚመነጨው ከመልካም አስተዳደር ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው እድገት ደግሞ የስም ብቻ ዕድገት አይደለም የአቶሚክ ቦምብ መስራት፤ ሮኬቶች ሰርቶ መተኮስ ፤የጠፈር ላይ አካላትን መመርመር የሚባሉት ከፍተኛ ጉዳዮች ለጊዜ ከደረጃችን በላይ ስለሆኑ አሁን የምንፈልገው የምንችላቸው ጥሩ ያገራችን ህዝብ ሁሉ በቀላል ሊሰራቸው የሚችላቸውን ስራዎች በተፋጠነና ጠቃሚ በሆነ መንገድ ሰርተን እንድንበለጽግ ነው፡፡ ከአቶሚክ  ቦሞብ ይልቅ ዳቦ ብዙ ፈላጊ አለው፡፡ በማለት ያስቀመጠው ሃሳብ በይበልጥ የሚሰመርበት ኾኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ከቤተ-ክርሰቲያንና ከልሎች ሃይማኖት መሪዎች ጋር ያደረጉትን ምልልስ፤ አገር ውስጥም መሰራት ስለሚገባቸው ፋብሪካዎች፣ መንገዶች፣ ባንኮች ፣ እርሻ ንግድና ሌሎችን ልማታዊ ስራዎች በመተንተን እስከ ገጽ 49 ድረስ ንግግራቸውን ይቀጥላሉ፡፡ በገጽ 49 ላይም ከምክር ቤቱ አባላት የቀረቡለትን ጥያቄዎች የሰጧቸው መልሶች በሚል ርዕስ አሁንም እስከ ገጽ 56 ጽፏል፡፡ ስለካፒታዝምና ሶሻሊዝም ርዕዮተ አላማት ሁለቱም ለኛ በቀጥታ እንዲልተፈጠሩ የነርሱን አስተሳስብ ገልብጦ መጮህ የማሚቶ ስራ መሆኑን እየገለይቀጥላል፡፡ የኢምባሲ ደረጃዎችን የዲፕሎማቲክ ግንኙነት መክፈትና ኢንተርናሽናል ስብሰባ ማብዛት ፣ ሹማምንትን መኪና እየገዙ መስጠትና ልዩ ልዩ ጉርሻ ማብዛት ፤ የሚነስትሮችን፣ የጀኔራሎችን፣  ወደ ውጭ የሚላኩትን መልዕክቶተኞች ቁጥር በመቀነስና ለማንኛውም ትርፍ የምናወጣውን ገንዘብ ሁሉ ያለምህረት መቀነስ አለብን በማለት ይጠቅሳል፡፡ ጠንከር ያለ ሀሳብ የሚሰነዘርበት   ምዕራፍ አምሰት በህዝቦች መካከል የተከሰተውን ብጥብጥ የዘርና የሃይማኖት ክፍልል በማስቀመጥ ህዝቡን የሚመክርበት ክፍል ነው፡፡ በጣም ይገርማል! በምዕራፍ 6 ስለ በዓላት ቀናተ አከባበር ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት አስደሳች ነበር፡፡ ከሰራተኞችና ከአሰተዳደሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይትም የዚሁ ምዕራፍ አካል ነው፡፡ በሰላማዊና በወታደራዊ አገልግሎት መንግስታቸውን ለሚያገለግሉ ሰዎች መልካም አኗኗር የተዘጋጀ ዕቅድ በሚል ርዕስ ደንቦች በዝርዝር ቀርቦ ስለ ባልና ሚስት ትዳርና ፍቺ  ህጎችን ጨምሮ ስለ በጎ አድራጎት አቋም የቀረበ እቅድን በመያዝ የህገ-መንግሰት አባሪ ለመባል የሚስችላትን ሃሳብ ይዛለች የሚለውን የመጀመሪያ አንቀጽ ሃሳቤን ይደግፍልኛል፡፡ ወደ ምዕራፍ ዘጠኝ ስንገባ ታላቁን የኤስቫኖስ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ኢንስቲቱት መርቆ በከፈተ ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ምልካም ያደረገው ንግግር ይቀርብልናል ቀጥሎም በገጽ 130 ላይ ታላቁን የመንፈሰዊ ት/ት ቤቶች አካዳሚ ተመርቆ ሲከፈት ጠ/ ሚኒስትሩ ያደርጉት ንግግር በማለት በዘመናችን በየቀኑ እየተራመደ በሚገኘው የሳይንስና የቴክሎጂ ውጤት አድናቆቱን የጨረሰው ነፍስ ፤ ሪቂቅና ስውር ቢሆንው የመንፈስ ሀይል  የሚገኙትን ከፍተኛ ነገሮች ለመረዳት ሲቸገር ይገኛል ለዚህ ዋናው መድሃኒት መንፈሳዊ አሰተማሪዎች የመንፈስ ምስጢር ላይ ላዩን  ብቻ ሳይሆን ውስጡን ጠለቅ  አድርገው ተረድተው መገኘታቸው ብቻ ነው ይላል፡፡
   የመንፈሳዊ እምነቶች ፍፁም ተቃራኒ የሆነው የማቴሪያልዚም አምልኮ የሰዎችን  መንፈስ እየደከመ በሄደበት በአሁን ጊዜ የሃይማኖት ሰዎች ደግሞ እርስ በርሳቸው እየተጣሉና እየተናናቁ ሲገኙ የእግዚአብሔር አምልኮ  እንዲይጠፉ የሃይማኖት ሰዎች ሁሉ ልዩነታቸውን በመዘንጋትና በአንድ ላይ  በመሰለፍ እንዲሰሩ የሚድረግ አላማ እንዳለሁ ማስቀመጡ ፍንትው ያለ  የመጪውን ጊዜ ያስተዋለበት ጥበብ ነበር -አቤ ጉበኛ!
ወደውጭ አገርም በመሄድ ያደረጓቸው ንግግሮች ቀርበዋል:: በብዙ መንግስታት መሪዎች በመንግሰት አንድነት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ያሰሙት እጅግ ከፍ ያለ ንግግር በጣም አስገራሚ ነበር::   የመንግስታቱን ድርጅት የወቀሱበትና የመከሩበት ተሰምሮበት ተደጋግሞ ሊነበብ የሚገባው የመጸሐፉ ትልቅና አስደሳች ክፍል ነው፡፡ ስለ ሶስተኛው የአለም ጦርነት ሳይቀር ሀሳብ የተሰነዘሩበት ሲሆን ደራሲውን ትንቢት ተናጋሪው ጸሀፊ ያስባለው ነው:: በዚሁም ክፍል በጣም የሚገርመው እና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምዕራፍ 11 ሲሆን “ታላቁ ጭቅጭቅ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሀሳብ አለ:: በተፈጠረው የመልካም አስተዳደረር ስርዓት ህዝብ ሀሳቡን በነፃነት የሚገልጽበት መድረክ በመፈጠሩ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ግለሰቦች የሚፅፉት በፕሬሱ ከመውጣቱም ባሻገር ህጉ በራሱ ትልቅ አስተማሪ ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ እየሰሩ ባሉበት ወቅት እንኳ አንዳንድ ግለሰቦችና ተቃዋሚ ቡድኖች ያሻቸውን ይጽፉ ነበር:: ይህም በገጽ 152 ላይ የተቀመጠው ጽሁፍ ያስረዳል:: “ የአህያ ልጅ በህዝብ ረኝነት ላይ” በሚል ርዕስ ስር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የሚያወግዙና የሚሰድቡ ወገኖች ሃሳባቸውን በነፃነት ሲገልጹ እናያለን:: አንዳንድ ወገኖችም ለምን አታስቆማቸውም? ለምንስ ይሳደባሉ? መታገድም አለባቸው ብለው በሚጠይቁበት ሰዓት የቀረበላቸው መልስ ለመሪዎቻችን የሚመክር ጭብጥ አለው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲህ ይላሉ:: …ስንት ታላላቅ ሰዎች የተጋደሉበትን የሀሳብ ነፃነትን ያህል መሳሪያ በምቀኝነት በቆሻሻ ነፍስ ሲጨማለቅ ማየት ያሳዝናል:: የማንም ሀገር መሪ እንዲያደርገው ለብልግና ብቻ የተቋቋሙ ጋዜጦችን መዝጋት እችል ነበር:: ነገር ግን ያዘጋጂዎቻቸውንና ፀሐፊዎቻቸውን ታናሽ ሰውነት በየቀኑ ከመግለፃቸው በቀር እኔም ሆነ ሌሎች የስራ ጓደኞቼ ለመረጠን ህዝብ የምናበርክተውን አገልግሎት ሊያሰናክሉ ሰለማይችሉ ዋጋ የሌለውን ጩኸታቸውን እንደቀጥሉ ከመተው የተሻለ እርምጃ አላደርግም:: ህዝብ ራሱ ይፍርድባቸው! በማለት ያስቀመጠው ዘመን ተሸጋሪ አስተምህሮት ሊታሰብበት የሚገባ ርዕስ ነው:: ሌላኛው ወገንም ተቃዎሚዎች ለጻፉት ሃሳብ ምላሽ በመስጠት  እውነት ሲረጋገጥ እናያለን::
ከአምባሳደሮችና ከውጪ አገር ቡድኖች ጋር በመመሳጠር  በአገር በቀል ባንዳዎች የመግደል ሙከራ ደርሶበት በህዝብ አንድነትና በተወካዮቹ እርዳታ ሴራው ይከሽፋል፡፡ ህዝቡም ለባንዳዎቹ ያለውን ተቃውም በሰልፍ ያስማል፡፡ ኾኖም ራሱን ደብቆ የማይኖረው መሪ ከማንም ህዝብ ተደብቆና ተሯሩጦ መንገድ አዘግቶ በውድ መኪናዎች የማይሯሯጠው ጠ/ ሚኒስተር ከአንድ ትንሽ ሰርግ ግብዣ ተገኝቶ በቀረበለት መጠጥ ውስጥ በተደረገች መርዝ ጤናው ይታወካል፡፡ በጣም የሚገርመው ግን እንዲዚህ ታሞ ወድቆ ህዝብ ሲተራመስ “ቀስ ብላችሁ ሰርገኛው የተከራየውን እቃ እንዳይበለሹበት በጥንቃቄ ስብሰቡለት በማለት ወደ ሆስፒታል ተወሰዶ ወደ ምዕራፍ አንድ ሁነት ይመልሰናል፡፡
      ፀሐፊው የእውነት ሰዎች ክርሰቶስ በ33 ዓመቱ መስቀሉ እነ ጋንዲ ሊንከን በግፍ መሞተቸው አነ ኔሮን የገዙሽ እነ ሂትለር የፈነጩብኝ የወንበዴዎች የግፈኞች አለም ! ድሮስ ለደጎች መች ትሆኚ !  ወንበዴ አለም  !  ርጉም አለም  ! በማለት የዚህ አለም ተጨባጭ ሁኔታ በማሳየት ያጠናቅቃል ::
      በጣም አስገራሚና አስተማሪ ልትነበብ የሚገባት ታሪካዊ መጽሐፍ መሆኗን ሳንረዳ አንቀርም:: እውነተኛ ጠቅላይ ሚነስትር የምንፈልግባት ድርሳን በመሆኗ በቀጥታ ለአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን በመጋበዝ ላለንበት የዲሞክራሲያዊ ግንባታ ይመች ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥያቄ በመጠይቅና መልስም በመጠበቅ ህገ- መንግስታዊ መብቴን በማስጠበቅ ፅሑፌን አጠቃልላለሁ ::
     ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለ ማርያም ደሳለኝ ይህችን መፅሐፍ አንብበዋታል ካነበቧት መቼ እና የት ካነበቧትስ በኃላ ምን ተሰማዎት በልብ ወለዱ የቀረበው የፈጠራ ጠቅላይ ሚነስትር እርሶዎትን ሊወክል ይችላል መልሶዎትን በጉጉት እጠባበቃለሁ :: ቸሩ ቸር ያቆየን!

No comments: