እመጓ-ዝጎራ እና መርበብት!
(ተስፋ በላይነህ)
ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴ ሥራዎቹን እነሆ ብሎናል፡፡ ሶስት መጽሐፍትን ከ2007 ዓ.ም እስከ 2010 ዓ.ም፡፡ በጭብጥ እና በመቼት አደራደራቸው፤ በገጸ ባሕርይ አወቃቀራቸው ዋና ትክተታዊ ነጥባቸውን ሳይለቁ፤
አንድ የድርሰት ሰው እንደ “ፈጣሪ” ሊታይ ይችላል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ አልቦ-ሥጋማ ፍጥረቶችን ያበጃል፡፡ ከሸክላ ባይሆንም ከምናባዊ እስትንፋስ ብቻ፡፡
ተደራሲያኑ በምናባቸው ያይዋቸዋል፡፡ በምናብ የማሳየት ብቃቱ ከፈጣሪው አገላለጽ ጋር ይቆራኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ይስማዕከ ወርቁ በአንድ መጽሐፉ የገለጸውን ስናስብ ሐሳባችንን ያጠነክርልናል፡፡
ይስማዕከ እንደሚለው “እኔ ፈጣሪ ነኝ፤ ነገር ግን እንደ ታላቁ ፈጣሪ ፍጡሮቼን አላሰቃይም”፤ ፈጥሮ የሚያሰቃይ ፈጣሪ አምላክነቱን የሚያጠያይቅ ሐሳብ ይዞ ራሱን ከምድር ፈጣሪ ጋር ሲያወዳድር ተመልክተነዋል፡፡
ይሕ በእንዲህ እንዳለ፤ ይስማዕከ ወርቁ እና ዶ/ር ዓለማየሁ ዋሴን ልናነጻጽር የምንችልባቸው ገጠመኞች የዶ/ር ዓለማየሁ3ኛ መጽሐፍን ‹‹መርበብት››ን በማነብበት ሰዓት ወደ ሐሳቤ አንዣበበ፡፡
ዶ/ር ዓለማየሁ በሶስቱም መጽሐፍት “ሲሳይ”ንፈጥሮታል፡፡ ሲሳይ በተለይም በሙያ ተሳትፎው ከፈጣሪው(ከደራሲው) ጋር መቀራረብ ስለሚታይበት ሲሳይን እና ዶ/ር ዓለማየሁን መለየት መክበዱ አንድን አንባቢ አያስነቅፈውም፡፡
በሶስቱ መጽሐፍት ውስጥ የምናገኜው “ሲሳይ” ይዞት የመጣውን ገጸ ባሕርይ /ውክልና/ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በሶስቱም ስራዎች የቀረበውብን ሲሳይ ወጥ የሆነ ምሥሱን እናገኝለት ይሆን? በቤተሰብኃላፊነቱ፣ በሙያ ሥነ-ምግባሩ፣ በችሎታው፣ በሥንፍናው፣በጉብዝናው፤ በእምነቱ…?
ሶስቱም መጽሐፍት ምሰጢር ናቸው፡፡ የአጻጻፍ እና የትረካ ፍሰታቸው፤ ከስሜት ጋር የተያያዙ ልብ አንጠልጣይነት ልማዳቸው፤ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ በርካታ ገጾችን እና“ካልጨረስኩህ አልለቅህም” አይነት ጣዕማቸው ተመሳሳይነታቸውን ያቀራርበዋል፡፡
እላይ ይስማዕከ ወርቁን የጠቀስኩት ያለ ነገር አይደለም፡፡ በተለይ በዶ/ሩ ሶስተኛው መጽሐፍ “መርበብት” እና በይስማዕከ “ክቡርድንጋይ” በ8ኛ መጽሐፉ (ይመስለኛል) መካከል የተሳሰረውን "የጭብጥ መስመር" ለመለየት እና ተቃርኖአቸውን ለመመመልከት ስለፈቀድሁ ነው፡፡
ይስማዕከ “ክቡር” ሲል የሚጠራውን “ድንጋይ”፤ ከዲያቢሎስም ይሁን ከማይታይ “መንፈስ”፤ “ጥበብ”ን እና ልማትን እንዲሁም ሥልጣኔን የምናገኝ ከሆነ፤ “ክቡሩን ድንጋይ” /ጥንቆላ ድግምት../ የሙጥኝ ልንል እና ለንገለገልበት ይገባል ባይ ነው፡፡
ሰለሞን ጠቢቡ ይጥቀምበት ነበር የሚባለውን መናፍስትን የማስገዛት“ጥበብ”ን ጨምሮ፤ ይስማዕከ አይኑን እና ምላሱን ሳያሽ በመናፍስት "እገዛ" የሚገኙ ጥበቦችን መጠቀም እንዳለብን አጥብቆ ሲመክርተ
መልክተነዋል!!
ዶ/ር ዓለማየሁ በሶስተኛ መጽሐፉ ይዞት የተነሳው ሐሳብ በዚህ "መረብ" ዙሪያ የሚያውጠነጥን ነው፡፡ በሐሳብ ይዘታቸውን መመሳሰላቸውን ጠቅሰን መናፍስትን ለጥበበብ "መጠቀም አለብን" ወይንስ "የለብንም" ወደሚለው ክርክር መግባታችን የሚቀር አይመስለኝም፡፡
ምንም እንኳ የማይታዬውን ይቅርና የሚታውንም ለማመን ለተቸገረ የአሁን ትውልድ ይሕ ጉዳይ ከጸጉር ሥንጠቃ አነሰ የሚባለውን “የመካከለኛው ዘመን ኢትዮጰያ ርዕዮተ ዓለም ግብግበ”ን ማስታወሱ አይቀርልንም፡፡
የሰው ልጅ መንፈሱን ሲክድ፤ ከነፍሱ ጋር ሲጣላ የማይታዩ ፍጥረታትን መካዱ እና ከማይታዩ ፍጥረታት ጋር መቆራረጡ የማይቀር ነው አይቀርም፡፡
ከነፍስ ጋር መቆራረጥ የሚታየውን ዓለም ቁርኝት ማዛባት ነው ብዬ እወስደዋለሁ፡፡ በመንፈስ እና በነፍስ
ጠንካራ ግለሰቦች ሲኖሩን የሚታየውን አሜኬላ የማሽቀንጠር፤ የሚታየውን አረንቋ የማጽዳት እና ወደ ምድራዊ ሥልጣኔ የአብሮነት ልምምዳችን የሚያሳልጥልን ለሰው ልጅ ብቻ የተሰጠ ጸጋ-በረከት ነው፡፡
የሚታዩ ፍጥረታት (ሰውን ጨምሮ)፤ መሬቱ፣ ውሃው፣ ጫካው፣ ሰማዩ፣ ኣራዊት ለማዳው፤ ማዕድኑ፤ ተራራው፣ ዋሻው ወዘተውጋር የምናደርገው ትስስር በውስጣችን ባለው “ዓለም” ልክ የሚሰፈር ይመስለኛል፡፡ አንድ ማሕበረሰብ አካባቢው ውስጥ ያለውን የሚታይ የሚዳሰስ የሚጨበጥ ጸጋ ለመጠቀም፤ አግባብነት እና ሕግአዊነት ባለው መስፈሪያ የሚመዝናቸውሆኖ ሲገኝ ውጤቱ በጅምር አስተያዬትም ሆነ በአጠቃቀም ደረጃ "ሰው" የመሆንን ክቡር መልዕክት አመላካች ናቸው፡፡
አግባብነት ሥንል ከሥር መሰረቱ ሁሉን አቀፍ የሆነውን የነገሮች አፈጣጠር ሥልት ከነምክንያቱ ማጤንን ያመላክታል፡፡ ሥልት ክህሎትን አውቀትንን/ጥበብን ይጠይቃል፡፡
ሕግአዊነት ሲባል ደግሞ መዳረሻ ሚዛኑን ያመላክተናል፡፡ መፍትኄአምጥተናል…? እኩልነትን አስፍነናል…? ሕያዊነትን ገንብተናል…? መተካካትን አስፍነናል…? ወዘተ እያልን ማብራራት እንችላለን!
ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው/ራሳችንን ስንመዝነው/ የሁለንተናችን አስተያዬት እና አጠቃማችን በድርጊት እና በውጤት ደረጃ እኛነታችንን ይገልጻሉ፡፡ በመርብብት መጽሐፍ በተደጋጋሚ ሲገለጽ የምናስተውለው እና ስንፈትሸው መዳረሻው ለአካባቢያችን የምንሰጠውን ትኩረት በመፈተሸ ምን ላይ እንዳለን ማሳየት መቻሉ ነው፡፡
ይሕንን ሐሳብ ለማጠናከር መርብበት መጽሐፉም ይሁን ያለፉት ሥራዎች ይሕንን ጉዳይ ሳያነሳው ያለፈበት ምዕራፍ አይኖርም፡፡
ሲሳይ በውጭም ይሁን በአገር ውስጥ በየትኛውም ገጠመኝ ይሁን ክስተት ኢትዮጵያን ያስባል፡፡ በውጩ ካለችው ኢትዮጵያ ውስጥ በውስጡ የበቀለችው ኢትዮጵያ ሰፊ ምድርናት፡፡ ጥልቅ ዋሻ ናት፡፡ ትልቅ ክምር ናት፡፡ አያልፋትም፡፡ ያለፋታል፡፡ በግልብ አያያትም:: ይጠልቃታል:: ይጠይቃታል፡፡ ይመክራታል፡፡ ይመሰክርላታል፡፡ ያፍርባታል፡፡ ያርፍባታል:: ይኮራባታል፡፡ ያለቅስባታል፡፡ ያለቅስላታልም…!
ምናልባትም የደራሲው የሙያ ተሞክሮ ለዚህ ሁሉ ሐተታ "ምንጭ" ሊሆን ይችላል ብለን መገመት እንችላለን፡፡ ሆኖም በሙያው እጽዋት ጋር የተቆራኜው ሲሳይ፤ ባሕሉን፣ ሐይማኖቱን፤ መንደሩን፤ ውሃውን፤ ቅርሱን፤ ፖለቲካውን ሕዝቡን በሚመለክት በየዘርፉ እንደ ሙያው የተካነበት ይመስላል፡፡
በየመሃሉ ወቅታዊ ውዥንብሮችንም አያልፋቸውም፡፡ ሊፈትሻቸው፣ ሊያርማቸው፣ ሊጠግናቸው፣ ሲመሰጥባቸው እናስተውለዋለን፡፡ በጥብቅ ይታገላል… እንደዜጋም እንደ ምሑርም፡፡ ከአንድምሑር የሚጠበቀውን ሁሉ በማድረግ ጥጉን ይዞ በጠራራ ጸሐይ ፋኑስ ያበራውን ፈላስፋንም እንድናስታውስ ያስገድደናል፡፡
በመርበብተ-ሰለሞን “ጥበብ” እንጠቀምበት ወይንስ አሽቀንጥረን እንጣለው…? ይሕ ጥያቄ ለይስማዕከ ወርቁ እና ለዶክተር ዓለማየሁ የሚቀርብ ይሆናል፡፡
ሁለቱም የየግላቸውን መዳረሻ በመጽሐፍቶቻቸው አሳይተውናል፡፡ የማይታየውን እንኳ ማመን እና መቀበል ላቃተው ትውልድ እኚህ ግለሰቦች ምንአይነት መልክ ይኖራቸዋል? የሚለው ራሱን የቻለ ርዕስ ቢሆንም፤ ያገባኛል/ይመለከተኛል የሚለው ትውልዱም የትኛውን መዳረሻ ሊዘግን ይችላል..? በምን አይነት መስመርስ ሊቀበለው ይችላል…? አቀባበል እና አጠቃቀሙስ በምን መልኩ ይወሰናል…? እንጠቅምበት/አንጠቀምበት የሚለውስ በየትኛው መመዘኛ ታይቶ ነው…? የሚሉ መሠል ጥያቄዎች ለእያንዳንዳችን የሚተዉ ይሆናሉ፡፡
በ316 ገጾች የተቀመጠው “መርበብት” በሁለቱ መጽሐፍቶቹ ጋር ተመሳስሎውን እና መለያየቱን ተሸክሞ፤ የውጭውን ዓለም ምልከታ በንጽጽር ሲያቀርብልን አናስተውላለን፡፡ እንደ ሲሳይ አመለካከት አብዛኛውን ገጠመኝ ከአገሩ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማወዳደር ይቀናዋል፡፡
በአገር ውስጥም ቢሆን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ወቅታዊ ትኩሳት እና አጠቃላይ ገጠመኞች ትኩረትን አግኝተው ተዳስሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ይስማዕከ ወርቁ እና ዶ/ር ዓለማየሁ አንድ ምንጭ የቀዳቸው ሁለት ወንዞች ናቸው፡፡ በግራ እና በቀኝ ትይዩ ሆነው የሚፈሱ፡፡
ከምንጩ ለመጠጣትም ሆነ በወንዙ ለመፍሰስ የአንባቢ ድርሻ ይሆናል፡፡ "ምንጩን አያሳጣን" ብቻ ነው የዘወትር ፀሎታችን..!
መልካም ንባብ!!
No comments:
Post a Comment