May 25, 2014

የአሉላ ምድር!!

የአሉላ ምድር!! 
ዓብይ ርዕስ፡- የአሉላ ምድር!!

ዑሥ፡- የዮቶር፣ የካሌብ፣ የአርማህ፣ የላሊበላ፣ የታጠቅ፣ የበዝብዝ፣ የአሉላ የጃገማ….. የዕልፍ ነፍሳት ጩኸት!!
 ((ተስፋ በላይነህ))
እንዲህ የተንጣለለ ቦታን የያዘ ፤ የተባዘተ የጥጥ ፈትል ክምር ሰፊ… ከምንጠብቀው በላይ ሰፊ… ሆኖ የሚታየኝ ምንድን ይመስላቹሃል?  ዋጋው ለአንድ ሰፊ ቃዳ የጥጥ አዝመራ ጉልጎላ ለሚውሉ እልፍ ሰራተኞች ‹‹ደመ››ወዝን ለሶስት ወር የሚከፍል ነው፡፡ ነገሩ ምን ይመስላቹሃል? ---አልጋ ነው!  ዙፋን!!
እዚህ ከተንጣለለ ሰፊ ሜዳ ላይ ይተኛሉ…ከአልጋው ስር ተሰንቅረው የሚገኙት ስብርባሪ አጥንቶችን ማለሳለሻ ነው…ማድቀቂያ!
ይህ ከአንድ ዋንጫ በላይ በስፍር የማይሞላ መጠጥ ስንት ነው…?  ቅላቱ …?  ጎምዛዛነቱ… ፍስሃው….?  ይህ ሁሉ የነፍሳትን ደም ማስታገሻ ጽዋ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ ሳስብ ካለፈው ይልቅ የዛሬው፣ ከዛሬው በይበልጥ የሚመጣው የታሪክ ድርሳን በእጅጉ ያምማል! ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ አጨፋጫፊ፣ አጨራራሽ፣ አዋራጅ ክስተቶችን እንዳስተናገደቸው ሁሉ…፤ በጠራ ሰማይ ላይ ጨረቃን፤ በዋልድባ ዘፈንን የሚያስታውሱን የስቅታ ብቅታዎች አይጠፉም፡፡ ከጥንት እየጀመርን ብናወራው ተረት ተረት እየመሰሉ መንጎዱን ተያይዘውታል… ይነጉዳል ሰዓቱ… ይፈራረቃል ወቅቱ… ይደራረባል መዓልቱ… አበቅቴው ላይጎድል ይሞላል፣ ላይሞላ ይጎድላል…! ይዘንባል መዓቱ… የባለታሪኮቹ አጥንት ስብራት የተከሰከሰውን ያክል ወደ አመድነት እየተለወጠ ነው፡፡ የፈሰሰውም ደም የአለማት የነዳጅ ዘይት ቅሪት ከመሆኑ በፊት ከእያስጴድ በተሰራ ዋንጫ ውስጥ ተቀድቶ መጠጣት አለበት…!! ይጠጣል እንደጉድ!!!
እናንት እንግሊዞች የፈለጋችሁትን ካስፈጸማችሁ መጠቀሚያ ካደረጋችሁን በኋላ ኦና ዘግታችሁን ትሄዳላችሁ… ብሎ ለታሪክ ፍርድ የተወው ቱርክ-ባሻ የቁቢ ልጅ ከድሃ ገበሬ የተወለደው አሉላ ነበር፡፡/ቃላት ተቀያይረዋል/   
ያ ጣልያናዊ ኢትዮጵያን ለማሸማገል የተመረጠው ሽማግሌ ይዞት የመጣው ጀነራል ንጉስ ምኒልክን በድንኳን ውስጥ ሲያገኛቸው ከንጉሱ አጠገብ ለነበረው አንበሳ አልነበረም በብርክ የሰገደው… ለጥቁሩ ንጉስ ለጥቁሩ አንበሳ እንጂ! ልብ በሉ ያ ነጭ ‹‹በድንኳን›› ውስጥ ለነበረ ጥቁሩ ንጉስ ነው የሰገደው!!
አሁን የአሉላ አጥንት ወደ ብስባሽበት እየተቀየረ ነው… ግድ ነው! የተፈጥሮ ግድ ነውና! ሸዋ እና ትግራይ እንዲያ እንዳልተገፋፉ ኢትዮያ አንድ ልታደርጋቸው የታሪክ ክስተትን ለገሰች፡፡ አድዋ ላይ ታየች!
አሉላ ለባህር ምድር፣ ለዳር ድንበር፣ ለአገር ፍቅር እንዲያ ሲሰባበር… አሁን እንዲህ ስንፈረካከስ አጥንቱ እንዴት ያለ ሲቃን ዝማሜ እያስወጣ ይሆን??  እንዴትስ ያለ ሙሾ እያስወረደ ይሆን?? አጥንት ሙሾ አያስወርድም ልትሉኝ ትችላላችሁ?? ተለያይተናል! የሙታን አምላክ የለኝም! የኢትዮጵያ ጀግኖች ህያዋን ናቸው!! በህያዊነታቸው ህላዌ ከማንባታቸው በቀር!!
በዶጋሌ ምድር እንዲያ እንደ እቶን በሚንቀለቀለው የምደር አሸዋ ሰመለላለስ የነበረን ጀግና ሐውልት በቦታው አፍርሶ ለደንበር ወራሪ ሰርጎ-ገብ ሐውልት ማቆም ምን ይባላል? የዘርዓይ ድረስን ማንነት አወናብዶ ለግፈኛው ግራዚያኒ ሐውልት ኢፍታሃዊነት ልሳን ከየት ያጣል?
ልብ በሉ! መንግሰቱ ኃይለማርያም በግዞት ይገኛል… የአሉላን ሐውልት ያሰራው እርሱ ነበር፡፡ የአሉላን ሐውልት አስፈርሶ የጣልያንን ሰማዕታት ሐውልት ያስገነባው ነጻ አውጪ አሁን የድል በዓሉን እያከበረ ነው!! የኢትዮጵያ ጠላት ማን ነው? ወዳጇስ?
የአጥንቱ ጩኸት የማን ነው! የተንጣለለው አልጋ ለማን ነው?  የፈሰሰው ደም የማን ነው?  የሚረጨው ወይን የማን ነው!! እነዚህ እኮ አማልክት ናቸው!! ደምን ወደ ወይን ቀይረዋል…!! ወይን ወደ ደም የቀየረውን እነርሱ ግን ደምን ወደ ወይን ቀይረዋል!!
መሰረቱ ጥልቅ ነው…ከአዳም እንዳንጀምረው ያልተጨበጠ የአማልክት አፈ-ታሪክ ነው!! የመሰከረው ብዙ ነው!! ኄኖክ መስክሯል!! ኖህ መስክሯል!! አብርሃም ከሳራ በኋላ ኢትዮጵያዊት አግብቷል…ዮሴፍ ተቀምጧል!! ሙሴ ተምሯል!!
የአለም ህግ መስራች ሙሴ፤ በህዝብ አስተዳደር እንዲያ ቁም ስቅሉን ሲንገላታ ኢትዮጵያዊው ካህን ዮቶር ነበር የሰማመረው፡፡ የዕብራዊያን ነጻነት መሰረት የኢትዮጵያ ምድር ነው!! የኩሽ ርስት ነው!!
የጥበብ ጥማት በዚህች ምድር ነው!! የአዜብ ንግስት ከምድር ጥግ ጥበብን ሽታ የተጠማች ናት፡፡ ለጥበብ ምስክርነትም ለፍርድ የምትነሳ!! ሳባ ርስቷ በአሉላ አጥንት በአሉላ ደም ወደብ ነው!! ዛሬ አሉላም ያለቅሳል.. ሳባም ትጮሃለች… ጥበብም ይጠማል!!
ቅረቡ ወደ ዘመን…ጥረቡ ሐውልት… ትከሉ ድንጋይ…ድንጋይም ሰው ሆኖ ሕይወትን ይሰብካል!! ክርስቶስ ሲወለድ የአለም ጠላት አስቀድሞ አማልክትን አሰባስቦ ለጥቃት ሲሰባሰብ… የክርስቶስ መሸሸጊያው የኩሽ ምድር ነው!!
ክርስትና ከመሰረቱ ወደ ዓለማት የተሰበከው በኢትዮጵያዊው አለቃ በንግስት ህንደኬ ጃንደረባ አማካኝነት ነው፡፡ ምስጢር አለው!! ሳውል ‹‹ጳ›› ውሎስ ሲሆን ምስጢር አለው!!
የመጀመሪያው ክፍለዘመን ታላቅነት፣ የጥቁር ህዝብ መሰረት፣ የንግስና ስርዓት በአሉላ ምድር ለአለም ተመስክሯል!
እስልምና ከመሰረቱ ሲጠነሰስ፤ የመሸሸጊያ እና የመጠለያ ባላደራ የአሉላ ምድር ናት!! እዩት ላሊበላን ከምድር ብቃይ ነፍሳት አልተወቀረም ተብሏል! የሰማያት ውዳቂዎች ገነቡት ተብሏል!! ለትውልድ አደራነት ቅርስነቱ ተቀምጧል፡፡ ልሳኑን ጨርሶ ለዘመናት ይጮሃል…!
እዩት የብራና ክምር የ ((ዓ)) ለማትን ምስጢር ከድሞ ሲያቀያይድ!! እዩት ደግሞ በእቶን እሳት ሲንቀለቀል፤ እዩት ደግሞ ያ ሁሉ ብራና ሲቃጠል ፤ ሲጉዋዝ ሲዘረፍ፤ ምስጢር ተመጽዋች ሲያደርገን!!
ዩዋቸው እነዚያን ሴቶች ዓለምን በፍርድ ሲያስደምሙ እነ ንግስት እለኒ ምንትዋብ…. እዩት የኢትዮጵያ መሰረት ወደ ነበረው ሲስፋፋ… እዩት ታጠቅ ካሳን የኩሽ ምድር አፈር ሲያሰክረው… እዩት ጠላት እርስ በርሳችን ሲያተረማምሰን… እዩት!!
እዩት የካሳን ጉርሻ… እዩት ተስፋ ማጣት…ሲያደርግ ባዳ!! እዩት ዩሐንስን ከአሉላ ምድር እስከ ገላባት በርሃ ሲመላለስ… እዩት አንገቱ ሲበጠስ…እዩት የዮሐንስ አጥንት ሲጣራ!! እዩን እኛ እዚህ ስንነካከስ!!
መረብ ጣጣዋ አላለቀም!! የአሉላ ምድር መሰረቱን አልያዘም! ጠላት ሐውልት ቆሞለታል… የአሉላ ምድር በእንክርዳድ ተሞልታለች!! በጠላት ተወርራለች… አርበኞች አጥንታቸው ተከሰከሰ… ደማቸው ፈሰሰ… ጠላት አጥንታቸው ላይ ድብን ያለ እንቅልፍ ለመተኛት አልጋ ያሰማምራል… ደማቸውን ለመጠጣት ዋንጫ ያጋጫል!! ጃገማ ኬሎ ተቀምጦ ሐሞቱን ያፈስሳል!! አሉላ ግን ይመለሳል…
---የአሉላ ምድር!!
   ተስፋ በላይነህ


No comments: