May 19, 2014

የጎንደር ከተማን በጨረፍታ

የጎንደር ከተማን በጨረፍታ 
ከክፈፍለል 1
ፒያሳ

እንደተለመደው የአንዳንድ ከተሞችን ቅኝት ስንቃርም፤ ከኋላ ታሪክ ባለመጀመር ከነገውም ከዛሬወም፤ ከዛሬውም ከትላንቱም እየጨራረፍን እንተይብ፡፡
ነገ ወይንም ከዓመታት በኋላ በአካባቢያችን የብአዴን ጽ/ቤት ለመስሪያ ቤትነት የሚያውለውን ህንጻ ያስገነባል፣ ምናልባትም 2008 አሊያም 9 …. የጎንደር ረፈራል ሆስፒታልም ይጠናቀቃል፡፡ ሌሎችም...

አዚህች ላይ ግን ሳልጠቅስ ማለፍ የማይቻለኝ አንድ ክስተት አለች፡፡ በአካባቢያችን የብአዴን ጽ/ቤት አዲስ ለሚያስገነባው ህንጻ መሰረት ሲቆፈር ያወጣውን አፈር መሀል መንገድ ላይ መዘርጋቱ ነዋሪዎችን አስደምሟል፡፡ ለልማት ሲባል አይደለም ተለዋጭ ያለው መንገድ ይቅርና ተለዋጭ የሌለው መንገድም ሊዘጋ እንደሚችል በተደጋጋሚ አይተናል፡፡ ልማታዊ መንገስት ሁልጊዜም ከፊ ለፊቱ የሚየታየው ልማት እንጂ ጥፋት ስላልሆነ ለልማት ሲባል የሚጠፉት ነገሮች በሙሉ ልማታዊ ናቸው፡፡ ስለዚህ ልማቱን ለማፋጠን ወደፊት!!

አስተዳደር በሚባል ቦታ አሁን አዳዲስ ሕንጻዎች በቅለዋል፤ አጼ ቴዎድሮስ ቢነሱ ጎንደርን ያውቋታል ሲባል የነበረው አሁን ተረት እየሆነ የመጣ ይመስላል፤ ለውጦች አሉ!! የውስጥ ለውስጥ መንገዶች በኮብል ስቶን ተነጥፈዋል፡፡
ዳሽን ቢራ በከተማዋ ከተተከለ ጀምሮም የጠጭዎች ቁጥር እና የውስጥ ለውስጥ የድራፍት ቤቶች መበርከት ይስተዋላሉ፡፡ ከተማውም ዳሽን ዳሽን ይላል፡፡ በታሪካዊ ቅርስነት እየተመዘገቡ ያሉት ህንጻዎች ከዳሽን ቢራ ጋር ያላቻ ጋብቻ ፈጽዋል፡፡
በየመንገድ ዳሩ የተገነቡት የቆሻሻ መጣያ ቅርጫቶ በዘመናዊ መብራት አሸብርቀው መታየታቸው ያስደስታል፡፡ በከተማዋ የህንድ የሕይወት ተሞክሮ ፈጠራ የሆኑን ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች አኩኩሉ የሚጫወቱ ይመስላሉ፤ ከቦልኮ ፒያሳ ከፒያሳ አራዳ እና ወደ ተለያዩ መዳረሻች ቤት ድረስ አገልግሎት በመስጠት ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ….

ወደ ቡልኮ አካባቢ የአቅም ግንባታ ቢሮ የነበረ እና አሁን የሲቪል ሰርቪስነት የጠቀየረ ቢሮ ከዓመታት በፊት የአንዲት አሜሪካዊት ቤተመጽሐፍት ነበር ቢሉኝ ተገረምኩ፡፡
በከተማው ውስጥ የንባብ ባህል አይታይም፡፡ ፑል ቤቶች፣ ጫት መቃሚያ ቤቶች፣ ሺሻ ቤቶች፣ ፕለይ ስቴሽን ቤቶች፣  የአውሮፓ እግር ኳስ ማሳያ ቤቶች፣ ቡቲኮች፣ ካፌዎች፣ ድራፍት ቤቶች፣ የጀበና ቡና ቤቶች እና መሰል ጎጆዎች  ኑሮን ማሸነፊያ በሮች አሏቸው፡፡
በተለይ በተለይ እኔን በሚመለከቱኝ ጉዳዮች ላይ ላተኩር፡፡ አካባቢያችን ለመኖር ምቹ ይሆን ዘንድ የሰብአዊነታችን ሚዛን እና የአስተሳሰብ ልቀት ድርሻች ሊታከልባቸው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ የግልና የቤትንጽህና፣ የመንገድ ዳር እግረኛ መንገዶች፣ የመኖሪያ ቤት የግቢ አጥሮች፣ በየጊዜው የሚቆፋፈሩት መሄጃዎች፣ የመጠጥ ውሃ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የንባብ ቤት፣ የሲኒማ ቤት፣ የቲያትር ቤት፣ የስፖርት ማዕከል፣ የቀበሌ ስፖርት ውድድሮች፣ የት/ቤቶች አወቃቀር እና አቋም፣ የመስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ፣ ሆስፒታሎች፣ ታሪካዊ ቅርሶች፣ የህዝቡ የኑሮ ሁኔታ፣ የደስተኛነት መጠን፣ የአመለካከት፣ በከተማው ውስጥ ያለው ተሳትፎ እያልን ልንጠቃቅስ የሚገባቸው አበይት ጉዳዮች ይኖራሉ፡፡

 አንድ መንግስት እነዚህን ነገሮች አሟቲ ሲገኝ ስራውን በትክክል እየተገበረ ነው ብለን አብረን ልንተባበረው እና ለንደግፈው አልፎም የአገራዊነት ስሜት ተሰምቶን አሻራችን ልናስቀምጥ የምንችልበትን አጋጣሚ ሊመቻች እንደሚገባ የምንስማመበት ሀቅ መኖሩ ሙሉ በሙሉ ያስማማናል! ይህ ነገር በከተማዋ አለ ብሎ ማሰብ ለነዋሪዎቿ የምንተወው ጉዳይ ቢሆንም፤ እንደነዋሪነት እና አሻራን ለማስቀመጥ የተመቻቸ ሜዳ አለ ብሎ መገመት ይከብደኛል፡፡ ችግሩ ከማን እንደሆነ ግልጽ አልሆነልኝም፡፡
እዚች ከተማ ጥርሳቸውን ነቅለው፣ተክለው፣ በየሰፈሩ ተጠራርተው፣ የቀለም ትምህርት ተምረው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡና ተመርቀው የወጡ ተወላጆች በ90በመቶ በላይ እዚህ አይገኙም፡፡
ከየትኛው ትውልድ መጀመር እንዳለብኝ ማሰብ ቢቸግረኝም ከተማዋ ከታሪካዊነቷ አንጸር ታሪካዊ ስብዕናዋን ይዛ እየተጓዘች ነው ብሎ ማሰብ በቀላሉ የሚታለፍ አይፈለም፡፡ አዳዲስ ህንጻዎች ተገንብተዋል፣ አዳዲስ የጎብኝ መዳረሻ ሎጆች፣ ሆቴሎች፣ ፔንሲዮኖች ተሰርተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ሩቅ ቦታ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ቦታዎች አሁን ለኑሮ ተስማሚ የሆኑ ስፍራዎች ሆነዋል፡፡ ቀበሌ 18ን መጥቀስ በቂ ነው፡፡

ከዩኒቨርሲቲው አካባቢ በተለምዶ ጂቲዜድ እየተባለ የሚጠራው ስፍራ የተገነቡት ቪላ ቤቶች አሁን ተፈላጊ እና ውብ ህብረትን የፈጠሩ መኖሪያ አካባቢ ሆነዋል፡፡ በየቀበሌው አሮጌ እና እየፈራረሱ የነበሩ ቤቶች አሁን በሊዝ እየተሸጡ መኖሪያ ቤት፣ ሆቴል እና ፔንሲዮን እየሆኑ ነው፡፡
በዋናነት ከተማዋ ለኑሮ ምቹ፣ ህዝቡ የተረጋጋ መንፈስ፣ አልፎ አልፎም የእረፍት ጊዜያትን በጋራ የሚያሳልፍበት ቦታዎች፣ አዕምሮውን ሊያድስ የሚችልበት ስፍራ፣ ታሪኩን ባህሉን እና ጥበባዊ እድገቱን ሊያሻሽል የሚችልበት ተጠቃሽ ስፍራ ከእድገቷ ጋር መረሳታቸው በግሌ የሚያሳዝነኝ ብቻም ሳይሆን ለማንኛውም ተወላጅም ሆነ ለከተማ አስፈላጊ ናቸው ብሎ የሚያስብ ሰው የሚያስቆጭ ነው፡፡
በከተማዋ የተቋቋመው ቆሻሻ አስወጋጅ ድርጅት ይበል የሚባል ስራ እየሰራ እንደሆነ መካድ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ግን በተለያዩ ስፍራዎች ቆሻሻዎች በየጊዜው እየተወገዱ ምትክ አፋጣኝ ስራ ስለማይታይባቸው ለእይታ ውበት ማራኪነትም ብቻ ሳይሆን የሚፍሩት ጠረን አካባቢውን ጥሩ አየር እንዳንተነፍስ እንደ ጋሬጣ መሰንቀራቸው ነው፡፡ አንድ ከተማ ለኑሮ ተስማሚ መሆን ከሚጠበቅበት መገለጫ አንጻር የቆሻሻ ነገር በዋነኛነት የሚጠቀስ ነውና!  

የኔነት ስሜት እየተሰማው የሚኖር ነዋሪ ሊፈጠር የሚችለው በከተማዋ ውስጥ ተጠቃሚ የሞሆንበት፣ የሚውልበት፣ የሚዝናናበት፣ ከውስጥ ስሜት አንጻር ደስታን እና ትውስታን እየፈጠረበት የሚኖር ሰው ሲኖር ነው፡፡ ይህ አለ ብዬ መገመት ይከብደኛል፡፡ የዚህም መሳያ  ምልክቱ ነዋሪየሆነ ሰው ተወልዶ አድጎ ት/ት ከተማረ በኋላ ስፍራውን ለቅቆ መሄዱ እንደከፍተኛ ድመግብ መዳረሻ መታየቱ ነው፡፡ ወጣቱ በከተማው ውስጥ የኔ የሚለው ነገር አለ? አብዛኛው ወጣት የራሱ የሆነ ቤት፣ ትዳር ልያዝ ቢል የራሱ የሆነ ንብረት እንዲሁም መሰረታዊ ፍልጎቶች አሉት?

በከተማዋ አንድ ወይንም ሁለት /3/ ቤተ መጽሐፍት አሉ ፡፡ በአልማ የተሰራ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በቅርብ የተሰራ ከከተማዋ የእግር ኳስ ሜዳ አጠገብ የሚገኝ ነው፡፡ ህዝቡ የማንበብ ባህሉ እጅጉን የወረደ ነው፡፡ ይህ በጎንደር ከተማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገሪቷ ከተሞች የሚስተዋል ነው፡፡
አሁን ኑሮን ለማሸነፍ የገንዘብ ክምችት በዋነኛነት የተያዘ የአገሪቷ ፓሊሲ መሆኑን ሳንረዳው የቀረን አይመስለኝም፡፡ ሩጫው ገንዘብ ማካበት፣ ገንዘብ መያዝ፣ ይዞ መገኘት በሚለው ብሂል መሰረት ሁሉም መሯሯጡ ይታያል፡፡ ህዝቡ ስራ ላይ ሲረባረብ ማዬት ያስደስታል፤ ኑሮን ለመሻነፍ ሊታገል ማየት ትልቅ ዕድገት ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ሩጫ ግን ማንነትን በመርሳት፣ ታሪክን በመተው፣ ባህልን በመቅበር፣ አዕምሮን በመዘንጋት፣ ቁሳዊነትን ብቻ በማስተጋባት የምንረባረብ ከሆነ ከተማዋ በቁስ ብቻ የምትሞላ ይሆናል፡፡ የሚኖርባት ገንዘብ ያለው ብቻ ይሆናል፡፡ አንድ ግለሰብ በግል ልዝናና፣ መንፈሴን ላድስ፣ ውስጤን ላዳምጥ፣ የልብ ትረታየን ልስማ ብሎ ቢያስብ የት ይሄዳል?

ጎንደር ‹‹የ44 ታቦታት›› መቀመጫ ስትባል እንሰማለን፡፡ አርባ አራት አድባራት አሉ ማለት አይደለም፡፡ ----
ገነት ተራራ/ በቆዬ አጠራሩ ‹‹ትግሬ መጮሂያ›› ቦታ ሄዶ ለመቀመጥ እና ራስን ለማዳመጥ ሙሉ በሙሉ ተመራጭ ነው ብዬ አልገምትም፣ በተራራው ላይ የጎሃ ሆቴል እና በቅርብ የተከፈተው ላንድ ማርክ ሆቴል ይገኙበታል፡፡ ምናልባትም ወደ እነዚህ ቦታዎች ሁደን እንዳንዝናና ጎሃ ከመራቁም ባሻገር ለነዋሪው የሚመጥን አገልግሎት ይገኝበታል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ዋጋው ሰማይ ነው፡፡ ሄዶ ለመመለስም ቋሚ መመላለሻ የለም፡፡ መሸት ካለም የጸጥታ ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡

አሁን በተከፈቱት ሆቴሎች ከሞላ ጎደል በእያንዳንዱ ማለት ይቻላል የነጻ ኢንተርኔት አገልግሎት አለ፡፡ እኔ ከምጠቀምባቸው እና ከማውቃቸው ሆቴሎች ውስጥ ማለትም ዋሊያ ካፕራ፣ ዞዝ አምባ፣ ፎገራ ሆቴል፣ ኤጂ ሆቴል፣ ታየ በላይ ሆቴል፣ ሎጅ ፋሲል፣ ላንድ ማርክ በቅርብ የሚገኙ እና የነጻ ኢንተርኔት ግልጋሎት የሚሰጡ ናቸው፡፡ ምናልባትም 85 በመቶ በግብርና ለሚተዳደር የኢትዮጵያ ህዝብ የኢንተርኔት አገልግሎት መበራከቱ የእድገት መለኪያ ነው ብየ በማቅረብ አልመጻደቅም፤ ሆኖም ግን የመበራከቱን ጉዳይም አልነቅፈውም፡፡

ለመዝናናት የት ይሄዳሉ?  ይቀጥላል….

No comments: