Oct 15, 2013

Why the Ethiopians are migrating? ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ?



ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ?
ተስፋ በላይነ

  
 በዚህ ርዕስ ላይ ለመጻፍ እነሳሳና ለዚህ ምክንያት ተብለው የሚነሱትን ዋና ዋና ነጥቦች ግልጽ ስለሆኑ ለመጻፍ እሰንፋለሁ፡፡
  ከጥቂት ወራት በፊት መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ የሚድያ ሽፋን ሲያገኝ ተመለከተናል፡፡ በመንግስት ሚዲያ የሚቀርቡት ሃሳቦች ደግሞ የልብን እንደማያደርሱ ከተገነዘብን ቆይተናል፡፡ የባስ ብሎም ወገናዊነት የሚንጸባረቅባቸውን ሃሳቦች ማሰራጭት እና ከተጠያቂነት ለመዳን ጥረት ሲደረግም በተደጋጋሚ እያየን ነው፡፡
  ታዲያ ይህንን ነገር ስመለከት በተደጋጋሚ እኔ ከማስባቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ጋር የሚስማሙ  ምክንያቶች ማግኘት ስላልቻልኩ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡ /በተለይ “ሶስት ማዕዘን” ተሰኘ ፊልም ካየሁ በኋላ ምንም አይነት ለስደት ምክንያት ባያቀርብም/ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ አረብ አገራት የሚሰማው ዜና እንድጽፍ አስገድዶኛል፡፡
አንዳንድ የመንግስት ተቀናቃኝ የሆኑ የፖለቲካ ቡድናት የውስጤን ሃሳብ ሲጋሩ “የመንግስት ተቀናቃኝ ነኝ እንዴ?” ብዬ ራሴን ጠየቅሁ፡፡
  የመንግስት ተቀናቃኝ ከመሆን የመንግስት ደጋፊ መሆን በብዙ እጥፍ እንደሚሻል መጠራጠር የለብንም፡፡ ያ መንግስት ግን መሰረታዊ የህዝብ ጥያቄዎችን የማይመልስ፣ መሰረታዊ የህዝብ ችግሮችን የማይፈታ እና የህዝብን ድምጽ በፍላጎት የማይቀበል ሆኖ ሲገኝ የዛ መንግሰት ደጋፊ መሆንም እንደሌለብን መጠራጠርም የለብንም፡፡
  የመንግሰት ተቀናቃኝ/ ተቃዋሚ/ መሆን ማለት የሌላ መንግሰት መሆንን የሚሻ ተቀናቃኝ ቡድን /ተቃዋሚ ፓርቲ/ አባል መሆን ማለት ነውን ? መልሱ ነውምም አይደለምም ሊሆን ይችላል! ይህ ጉዳይ ሌላ ርዕስ ስለሚፈልግ ወደ ጎን እንተወው፡፡
ኢትዮጵያዊያን ስለ ምን ይሰደዳሉ?
  ህዝብ፣ መሬት እና መንግስት አገርን ይመሰርታሉ፡፡ የአንድ አገር ህልውና የሚጠበቀው በህዝቦቿ፤ ለህዝቦቿ፣ በመቴቷ ለመሬቷ በመንግስቷ ለመንግስቷ ብቻ ነው፡፡ መንግስት  ለህዝብ ሲቆም፤ መንግስት ለመሬት ሲቆም እና መንግስት በመንግስትነቱ ገደቡ ተወስኖ ህዝብን ማገልገል ከሆነ ተግባሩ ይህ አገር ሰላማዊ ሁኔታ ላይ ይገኛል ሊባል ይችላል፡፡
ህዝብ ሰላም ሲሆን፤ ህዝብ መሬትን ሲወለድበት፣ ሲያድግበት፣ ሲወድ፣ ሲያገለግል፣ ሲሞትበት የአባቴ የእናቴ መሬት ብሎ ከደም እና ከአጥንቱ ጋር ሲዋሃድ አገሩን እያሳደገ ወገን ዘመዱን እና መላ የሰው ዘርን እያከበረ እየተከበረ የህይወትን ትርጉም ሲያጣጥም በአገር የመኖርን ጥቅም እና ውለታ ሲረዳው ፤ አገሩን ለማቅናት ያለግዳጅ ሲረባረብ፤ በፍትሃዊ መንግሰት አስተዳደር ስር ሆኖ ሲተዳደር ፤ አገር አለኝ ሲል ትክክለኛው አገራዊ ስሜት ላይ ይደረሳል፡፡ የከበደ ሚካኤልን “ተረትና ምሳሌ” ን ማንበብ በቀላሉ ሊሰርጽ የሚችል ትምህርት ነው/
ስለዚህ በእነዚህ ምክንያቶች በመነሳት ኢትዮጵያን /አገር/ ይህን ትውልድ /ህዝብ/ እና ልማታዊ መንግስታችንን እንደ መንግስት በመውሰድ ያለውን እውነታ በቀላሉ ልንረዳው እንችላለን፡፡
ኢትዮጵያ፡- ከዘመናዊ ት/ት መጀመር እና መስፋፋትን ምክንያት በማድረግ ኢትዮጵያኖች ወደ ውጭ የትምህርት ዕድል ማግኘት በመቻላቸው ኢትዮጵያ የውጨውን ዓለም ለመቃኘት ችላለች፡፡ ምናልባትም በኢትዮጵያ የነበሩ አንዳንድ የሚስዮናዊያን ተቋማትም የኢትዮጵያን ዜጎች በመጠኑም ቢሆን ወደ ውጭ የማስውጣት እና የማስተማርን እድል ችረዋል፡፡  እነ ፕሮፌሰር ታምራት አማኑኤል፣ እነ ከንቲባ ገብሩ፣ እነ ኦኔኒሞስ ነሲብ / መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የተረጎመ/ እነ አለቃ ታዬ እና መሰል ሰዎች የሚስዮናዊያን እጅ ይዘው የውጭ ትምህርት እንዳገኙ ይታወቃል፡፡ በትምህርት እድል ያገኙትም እነ ሀኪም ወርቅነህ እሸቴ/ ከመቅደላ ጦርነት በህጻንነቱ የተወሰደ/ እነ አለቃ ታዬ- የኢትዮጵያ ህዝብ ታሪክ በመጽሐፍ ያሳተመና በጀርመን ሀገር የግዕዝ መምህር የነበረ/ ፤ እነ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረ እየሱስም/ የመጀመሪያዋ “ልብወለድ” የምትባለዋን “ጦብያ” ን የጻፈ / እነዚህ የውጭውን አለም ለመመልከት እድል ካገኙት የሚጠቀሱም ናቸው፡፡ እነ በጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለ ማርያም/በ1923 ህገ መንግሰት ሲረቀቅ የተሳተፈ/ ፤ እነ ግዛው ዳኜ /ዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታል ሲቋቋም የረዱ/ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝም/በመርከብ ተደብቆ ወደ ኦስትርያ  የሄደ ሀኪም ቢሆንም በፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ የሚያጠነጥን መጽሐፍ ጽፏል- አጤ ምኒልክና ኢትዮጵያ (1912) እና መንግስት እና የሕዝብ አስተዳደር-1916/ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
 ወደ ውጭ መሄድ ለኢትዮጵያ ጥቅም እና ለግለሰቦች እድገት መሻሻል እንዲሁም የንቃተ ህሊና ማደግ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የተሻለች አገር ለማድረግም ያደረገው ጥረት ከፍተኛ ነው፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም በተለያዩ ጊዜያት የውጭ ትምህርት ያገኙ ኢትዮጵኖች እንደነበሩ እናያለን፡፡ ውጭ የሚሄዱት ተሰደዱ ማለት አንችልም፡፡ በአለም ዙርያ ባህል፣ ጥናት፣ ሃይማኖት ጥበብ እና ስልጣኔ መለዋወጥ የሚጠቅም ነው፡፡ ምንም እንኳ በሀገር ውስጥ ተሻለ የሚባል መንገድ፣ ተሻለ የሚባል መጫሚያ፣ ከውጭው አለም ተሻለ የሚባል የኑሮ ደረጃ እንዳልነበረ ቢታወቅም ወደ አገር መመለስና አገርን ማገልገል የኢትዮጵኖች የውስጥ ፍላጎት ነበር፡፡ ማንም ሳያስገድዳቸው እና ሳያማክራቸው በውስጣቸው የታተመው የኢትዮጵያዊነት ደም እና መንፈስ እንዲመለሱ ውጭ ሄዶ ተምሮ መምጣት እና አገርን ለመጥቀም እንዲያስቡ አድርጓቸዋል፡፡
የአጼው ስርዓት ሲያከትም፤ “አብዮቱም ሲፈነዳ”፤ ኢትዮጵያም ከምዕራባዊያን /ከአሜሪካ/ ጋር በፖለቲካ ልዩነት ሲነጣጠሉ ፤ “ሶሻሊዝም” /ሕህብረተሰባዊነት/ የኢትዮጵያ መተዳደሪያ ቀኖና ሆኖ ሲለፈፍ፤ የውጭ ትምህርት ወደ ሶሻሊስት አገሮች መሆኑን አስታኮ ወደ ኩባ፣ ራሽያ እና ምስራቅ ጀርመን ለትምህርት የተላኩት ኢትዮጵያኖች ቁጥር ቀላል አልነበረም፡፡ በዚህ ወቅትም አባቴ ወደ ጀርመን ሄዶ የትምህርት ጊዜውን እስኪያጠናቅቅ “አገሬ መች ይሆን የምገባው?” እያለ ሌት ተቀን ሲያስብ እንደነበር አጫውቶኛል፡፡ ይህ ከየትም የተገኘ አይደለም፤ ከመሬት ፍቅርከህዝብ ፍቅር  ከመንግስት ፍቅር በአጠቃላይ ከአገር ፍቅር የተገኘ በዋጋ የማይታመን ፤ በስሌት የማይቀመር መታደል ነው!
  በጣም ከሚገርመኝ ታሪክ ውስጥ እና መታሰብ የሚገባው አንድ ነገር አለ፡፡ የንጉሱን ከስልጣን መውደቅ ተከትሎ በተፈጠረው የፖለቲካ ድርብርብ፤ ከተለያዩ አገራት በርዕዮተ አለም መርፌ ተወግተው ወደ ስልጣን መንበር ሲቀራረቡ የ “ያ ትውልድ” አባላት እርስ በርስ ተበላልተዋል፤ በጠበንጃ እና በሃይል ያሸነፈው  የስልጣን መንበሩን ሲቀማ ሌሎቹ ተሰደዱ! /ንጉሰ ነገስቱም በ1928 የኢጣልያን ወረራ ወቅት ለ5 ዓመት መሰደዳቸውን አንዘነጋውም፡፡/
  እስከ 1966 ዓ.ም ድረስ አንድም ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ውስጥ “ስደተኛ” ተብሎ የተመዘገበ እንደሌለ የሚነገር ሲሆን ህንዳዊያን ወደ አሜሪካን አገር የመግባት እና ዜግነት ለማግኘት ኢትዮጵያ ድረስ መጥተው፤ አማርኛ አጥንተው በስመ ኢትዮጵያዊነት ያገኙ እንደነበር ስንሰማ በ40 ዓመታት ውስጥ ከየት ወደየት እንደደረስን ቀጥተኛ ማመላከቻ ነው፡፡ “የሶሻሊዝም” አቀንቃኝ የነበረው ኮ/ል መንግስቱም መሰደዱን ሳይገለጽ የሚታለፍ አይደለም፡፡/
  የህዝብ ፣የመንግስት እና አገር ስሜት እየተዳከመ በሚመጣበት ሂደት ውስጥ ስደት፣ ሙስና፣ ስንፍና አድር ባይነት እና ግዴለሽነት ይስፋፋሉ፡፡
ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት አሁን እንደ ማእበል የሚናወጠው እና እንደ ጎርፍ የሚጥለቀለቀው የህዝብ ስደት እንዲህ እንዲህ እያለ አሁን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የእነዚህም ምክንያቶች ከላይ ለማየት እንደሞከርነው ሶስቱ መሰረታዊ ምክንያቶች ማለትም የመሬት አልባነት ስሜትየህብዝ ክብር እና ኩራት እንዲሁም የመንግስት ፍትሃዊ አስተዳደር መደብዘብ የአንድን ሀገር እድገት ደረጃ እና ህልውና ይቆጣጠራሉ፡፡
  የምጣኔ ሐብት እድገት ቁጥር ያለ መሬት ክብር እና ፍቅር፤ የምጣኔ ሐብት እድገት ቁጥር ያለ ሰብዓዊነት ክብር እና ቦታ፤ የምጣኔ ሐብት እድገት ቁጥር መረጋታት ባልታየበት ሕዝብ፤ በሚሰደድ፣ በሙስና እና የሰውአዊነት ክብር ባላታየበት አገር ውስጥ የህዝብ ድምጽ በታፈነበት አገር ውስጥ “እድገት አስመዘገብን”  ቢባል እውነት ከውሸት ጋር ተመራርዞ አመትን በቁጥር ከመጨመር ውጭ ምን ሊፈይድ ይችላል?
  በሀገር ውስጥ ያለው የተቋማት አሰራር ድክመት፣ የሰው ልጅ ገንዘብን እንደ ብቸኛው የህይወት መሰረት አድርጎ በመውሰድ፣ በፖለቲካው ስርዓት ያለው አለመግባባት እና መሰል ምክነያቶች ኢትጳያዊያንን እንዲሰደዱ ከሚያደርጉ ምክንያቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስንቶቹ ለቀቁ? ለአገርህ ብቻም ሳሆን ለህሊናህ ደፋቀና እያልክ ስትሰራ የሚደመጠው እና የሚመሰገነው አሸርጋጁ በመሆኑ ስደትን ካባባሱት ነገሮች የሚጠቀስ ነው፡፡ አየር መንገዱ ከሚያገኘው ገቢ አንጻር የሚከፍለው ክፍያስ ተመጣጣኝ ነው? ስንት ሀኪሞቻችን…ስንት ምሁራኖቻችን…ስንት ሴቶቻችን…ስንት ወጣቶቻችን በስጋም በነፍስም የሚሰደዱት ለምንድን ነው?
  ሕጻናት የአገር ፍቅር ምንነትን ሳይረዱ፤ ለህዝብ ክብር እና ፍቅር እንደ እናት ጡት ወተት ሳይጠቡ ካደጉ፤ በመሬታቸው አፈር ረጭተው፣ የአያት አባቶቻቸውን ወግ እና ታሪክ እየሰሙ ለማሻሻል በተስፋ ካላደጉ፤ ህዝብም በሚያስተዳድረው መንግስት ላይ ተስፋ እና ፍቅር ካጣ በስጋም በነፍስም የሚሰደድን ህዝብ ማቆም ማለት የሚዘንብን ዝናብ እንደማስቆም ነው፡፡ የሚናወጥን ማዕበል እንደማብረድ ነው፡፡ የሚጥለቀለቅ ጎርፍን እንደመገደብ ነው፡፡
  ባለንበት ዘመን አገራችን የመሬት አልባ ትውልድ፣ የህዝብ አልባ ትውልድ እና የመንግስት አልባ ትውልድ በመፈጠራቸው ኢትዮጵያኖች ይሰደዳሉ፡፡ መሬቱ ያው ነውና ልንወቅሰው አንችልም፡፡ ህዝብም የሚመራው በመሪው እና በመንግስቱ ነውና ህዝብ እና መንግስት ወቀሳውን ይወስዳሉ፡፡      
  ኢትዮጵያ ወስጥ ደግሞ ተሰሚነት እና ሃይል ያለው ህዝብ ሳይሆን መንግስት ስለሆነ ለኢትዮጵኖች መሰደድ ምክንያት መንግስት ሃላፊነቱን እና ወቀሳውን ይወስዳል ማለት ነው፡፡ መንግስቴ ሆይ አገራችን ህዝብ አልባ፣ መሬት አልባ እና መንግስት አልባ እየሆኑ ስለሆነ እባክህን ስለ ኢትዮጵያ አምላክ ብለህ…
ቸሩ ቸር ያቆየን!


No comments: