Oct 20, 2013

ከታሪክ በስተጀርባ የሚደረግ ሴራ-በኢትዮጵያ





‹‹ከታሪክ በስተጀርባ የሚደረግ ሴራ››
"በኢትዮጵያ የንብ ቀፎ ውስጥ እንደልብ መግባት እና የመውጣት መብት የሚፈልጉ ሁሉ ሊከፍሉት የሚገባ ዋጋ መኖሩን ሊያውቁ ይገባል"
ጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድ-ጠ/ሚኒስትር፡፡
በተስፋ በላይነህ
  ታሪክ የሌለው እንሰሳ ነው፡፡ ሰው ደግሞ እንሰሳ አይደለም፡፡ የአንድ ማህበረሰብ የዛሬ ውሎ፤ የዛሬ ህልውና፤ የዛሬ ገጠመኝ ለነገው ትውልድ መሰረት ነው፡፡ ታሪክ የትውልድ መሰረት ነው፡፡ ባለ ታሪክ ትውልድ ሲመሰገን ይኖራል፡፡
 ታሪክ በአሸናፊዎች እጅ መጻፉ ዛሬ ላይ የተደረገውን እውነታ የመቀየር ሃይል ባይኖረውም፤ ለነገው ትውልድ ግን የማሳሳት፣ የማጣመም ሴራ፣ የማወናበድ ቅጥፈት ሊፈጸም ይችላል፡፡ እየተፈጸመም እያየን ነው፡፡
  ታሪክን ወደ ኋላ ተመልሰን የምንቀይረው ሳይሆን የምንማርበት የምንሻሻልበት ክስተት ነው፡፡ ታዲያ የዛሬዋ ቀን እውነተኛ መረጃ ለነገ ትውልድ በታሪክ መድረክ ስትቀርብ ያላትን ጥቅም በዋጋ መተመን አይቻልም፡፡ ሆኖም የድርጊቶች መዝገብ አያያዝ ጥንቃቄ የተሞላበት፤ ሁሉንም ማዕዝናት ያስተዋለ ሆኖ መቅረብ አለበት፡፡
  ሁሉንም ማዕዝናት የምንለው በትክክለኛነት የተደረገበትን እውነተኛ ዘገባ በማቅረብ ተያይዘው ሊቀርቡ የሚችሉ ሃሳቦችን አብሮ በማቅረብ ታሪክ አንባቢውን ከአድሎአዊነት እይታ ነጻ ኢንዲሆን ከመርዳቱም በተጨማሪ ለታሪክ ተቀባዩ ተፈጥሮአዊ የህሊና ፍርድ ለመስጠት ያስችለዋል፡፡
  ሁሌም ታሪክን ስናነብ ከባለታሪኩ በስተጀርባ ያለን ሴራ፣ ሸፍጥ፣ ውስብስብ አሻራ እንዲሁም ተሸናፊ አካላትን ብናስታውስ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡ በአንዳንድ ምሳሌዎች ከተላያዩ የታሪክ ክስተቶች ቅንጭብ ቅንጭብ በማድረግ፤ በመታዘብ ምን ለማለት እንደፈለግሁ ለማስረዳት እና ጭብጥ ለማስያዝ እሞካራለሁ፡፡
 ልጅ ተፈሪ፣ ቀጥሎም ራስ ተፈሪ፣ ከዛም ደጃዝማች፣ ከዛ ንጉሰ ነገስት የሆኑትን አጼ ኃይለሥላሴ ባለረጅም እድሜ የስልጣን ቆይታ፣ በአለም አቀፋዊ ሰመጥር፣ ዝነኛ ገዥ ነበሩ፡፡ በ37 ዓመታቸው ወደ ስልጣን በትር ሲሾሙ ከጀርባ ስንት ሴራዎችን እንዳለፉ አለማሰብ ይከብዳል፡፡ በተጠቀሰው ዕድሜያቸው ለንግስና ሲበቁ በተመሳሳይ የዕድሜ አመት ቁጥር ለስልጣኑ ታላቅ ተቀናቃኝ የነበረውን ልጅ እያሱን አንዘነጋም፡፡ በዚሁ ተመሳሳይ አመት በቁጥር በ37 ዓመት የሞተውን ልጅ እያሱን ከስልጣኑ ዙፋን ስር ሆኖ ሲያቃስት ይታየኛል... ከንጉሱ ዙፋን ስር ያልተሰማ ድምፅ አለ!
  ከነጋድረስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ የአጼ ምኒልክ ወቀሳ ደብዳቤ ጀርባ ምን አለ? አያቱን በአጼ ዮሐንስ ጦርነት ያጣው ይህ ብላቴና በምጽዋ አድርጎ ወደ ኦስትሪያ/ጀርመን ሲያመራ ከዛም ከህክምና ትምህርት መልስ የሀገር ግልጋሎት፤ ከዛም የጻፈው መጽሐፍ የጀርባ ትርጉም ምንድን ነው?
 የእንግሊዝ ኢትዮጵያን በፋሺስት መወረር ምላሽ፤ የአምስት ዓመት ቆይታ ውሳኔ፤ ንጉሰ ነገስቱን አጅቦ ውጊያ በማድረግ ‹‹ከጎን ነበርን›› ርዳታ ጀርባ የተጠነሰሰልን ሃሳብ ምንድን ነው? የአሜሪካ ኤርትራን ከእንግሊዝ አስተዳደር ተላቅቃ ወደ እናት ሀገር መዋሃድ ትስስር ጀርባ ሲጠና ምንድን ነበር?
የፖርቺጋሎች እርዳታ ለልብነ ድንግል፤
የቴምፕላሮች የላሊበላን ማጀብ፤
የአቡነ ተክለ ሐይማኖት የቃልኪዳን ስምምነት በዛጔ እና በሸዋ የስርወ መንግስት ሽግግር፤
የራስ ሚካኤል ስሁል እና የጀምስ ብሩስ ወዳጅነት፤
የአጼ ዮሐንስ እና የናፒር ስምምነት ከተክለ ጊዮርጊስ ጋር፤
የእንግሊዝ ሚሲዮናዊያን ተግባር በአጼ ቴዎድሮስ ዘመን፤
ራሽያ ኤርትራን በሞግዚትነት ለመያዝ መሯሯጥ፤ብዙ ብዙ…
  ዛሬ እየበላን ነው፡፡ ዛሬ እየጠጣን ነው፡፡ ዛሬ ሞቅ ያለ ትዳር፣ ላቅ ያለ ዝና፣ የካበተ ሀብት እና የተደራረበ የእውቀት ሽሚያ ወረቀት፤ ለንዋይ ሸክም እየተጋን ነው፡፡ ጥሩ ነው! ለዛሬ መትጋት በጎ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ በነገ አይን ስትታይ፤ ዛሬ ትላንት ስትሆን እና ከትውልድ ትውልድ ተላልፋ ታሪክ ሆና "ታሪክ" መባል ስትጀምር በትውልዱ ዓይን ሚዛን ስትታይ ለፍርድ የማየስቸግር፤ ትውልድ ሊኮራበት የሚገባ ተግባር ፈጽመን ሰንገኝ "ዛሬን" በትክክል እንደኖርናት የሚያስመሰክር የስኬታማ ትውልድ መገለጫ ነው፡፡
 ታሪክን ማጥናት ታላቁም ጠቀሜታ እዚህ ላይ ነው፡፡ ዛሬን ለመገንባት፣ ዛሬን ለመጠቀም፣ ከትላንት ለመማር፣ ስህተትን ላለመድገም፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ እና ለሚመጣው ትውልድ መልካም እና የተሳካ “ባለታሪክ” “ባለ ሀገር ዜጋ” ለመፍጠር ይጠቅማል፡፡ ይህ በኢትዮጵያችን አለ ወይስ የለም? ይህ ጥያቄ የማይቀር ነው፡፡ ያውም በብዙዎች ባልተስተካከለ አይን፣ ባልተቃና ህሊና ለሚተረከው የኢትዮጵያ ታሪክ፡፡ አንድ መጻሐፍ ላይ አጼ ቴዎድሮስ ራሳቸውን በሽጉጥ አልገደሉም የሚል መረጃ ያቀረበ ጽሑፍ ሳይ፣ ፋሲል ግንብ በኢትዮጵያኖች አልተሰራም፣ ላሊበላንም እኛ አልወቀርናቸውም እና መሰል ሁለት ጽንፍ ሀሳቦች በተደጋጋሚ ይሰማሉ፡፡
 የኢትዮጵያን ታሪክ በስፋት እና በጥልቀት ለማጥናት አስቸጋሪ የሚሆኑበትን ምክንያቶች ማቅረብ ቀላል ነው፡፡ በርካታ ምክንያችን ማቅረብም ይቻላል፡፡ ታሪክ በአሸናፊዎች መጻፉ፣ በጠላት እጅ የገቡ እና ለጠላት ሴራ ውጥን ሆን ተብለው የሚሰናዱ መረጃዎች መሰራጨት፣ ዜና መዋዕል ጸሐፊዎች ሚዛናዊ እይታ እና የተቃና ህሊናን አለመጠቀም፣ የጦርነት ብዛት፣ በጦርነትም ብዛት የሚለዋወጡት መንግስታት ያለፈውን ታሪክ ማናቋሸሽ እና እኔ ብቻ ትክክል ነኝ ማለት፣ የሰፊው ህዝብ በታሪክ ታሳፊነት ድርሻ ማነስ፣ የትምህርት አለመስፋፋት፣በታሪክችን የመለኮታዊ ሃይል ስፍራ መንሰራፋት እና ገዥዎቻችን እኔን የተቀባውት ከላይ እንጂ የተቀባሁት በህዝቡ አለመሆኑን መደንገጋቸው እና መሰል ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
  በመለኮት ሃይል መቀባትን የሚያምነው ህዝብ አምላኩ ለህዝቡም መቆሙን፣ ነገስታቱን የቀባው አምላክ ህዝቡንም እንደሚወድ እና እኩል አድርጎ ማየት እንደሚችል የሚነገዘብ ህዝብ ነገስታቱን መጠየቅ ባይችል እንኳ አምላኩን በውስጥ ጸሎት፣ በቅን ልቦና እንዲሁም አልተገለጠልኝም የሚለውን የነገስታትን አገዛዝ ስርዓት መርምሮ መጠየቅ ግን ይችላል፡፡ መቃወምም ይችላል፡፡ እንደውም ነገስታትን ከመጠየቅ አምላክን መጠየቅ በላቀ ደረጃ ተስማሚ እና ለውጥ አምጪ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
 እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ግን አሳዛኝ ህዝብ ለማይት አልታደልንም፡፡ በመቶ አመት ታሪክ ውስጥ ሶስት ዋና ዋና መንግስታት ተለዋውጠዋል፡፡ ከአሁኑ ዓመት ወደ ኃላ ስንመለስ 1905ን እናገኛለን፡፡ ዘመነ መሳፍንቱን ተክቶ ታለቁ ቴዎድሮስ ተነሳ፡፡ ከድንኳን ድንኳን፤ ከቦታ ቦታ እንደተንከራተተ ዘመኑ ወደኋላ እርሱ ግን ወደ ፊት ሆነና ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ…
ከዛም አጼ ዮሐንስ ሲተካ በሚገባ ሳይረጋጋ እና ዙፋኑን በቅጡ ሳያጣጥም ከአንደኛው ጦርነት ወደ አንደኛው ሲመላለስ በመረጠው ሌላኛው ጦርነት አንገቱን ሰጠ፡፡ ከዚህ በኋላ የሚመጡት ነገስታት ከነርሱ የተማሩ ይመስላሉ፡፡ ቢያንስ በጦርነት ራሳቸውን አልሰጡም...! አጼ ዮሐንስ በወሰዱት አንድ የታሪክ ክስተት ከተከታያቸው ወራሴ መንግስት ሳያገኙት አልቀሩም፤ አጼ ምኒልክ ከጣልያኖች ጋር ለጊዜውም ቢሆን የተስማማው እና መሳሪያ ማግኘት ከዛም አጼ ዮሐንስ መጎዳታቸው፤ አጼ ቴዎድሮስ ላይም የተሰራው የእንግሊዞች መሳሪያ ጦስ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አጼ ምኒልክም የተስማማ እና የተረጋጋ አጨራረስ አላጋጠመውም፡፡ ለዛች መከረኛ ዙፋን ርብርቦሽ ሚስጥራዊ ሞትን አስከትሏል፡፡ አቤቶ      /ልጅ/ እያሱም በቅጡ የንግስና ስርዓትንም ሆነ የአመራር ጊዜን ሳያሳይ ከጦርነት ጦርነት ሲሸሽ፣ ከእስር እስር ሲያመልጥ ሰሚ እንዳጣ አልቃሽ የሚደርስለት አጥቶ አሟሟቱም ሳያምር ሄደ፡፡ ለሶሰት ከፍተኛ ባለስልጣናት የተጋባችው ዘውዲቱም ከንግስት ሳባ ቀጥል ብቸኛ ንግስት ተብላ መቀባቷ ነበር ለውጡ፡፡
 ንግስናን ያገኛሉ ከተባሉት ተጠባባቂዎች አንዱ የነበረው የጣይቱ ብጡል የወንድም ልጅም ራስ ጉግሳ ወሌ በኋላ በአንቺም ጦርነት ደሙን አፈሰሰ፡፡ ንግስተ ነገስት ዘውዲቱም በዚሁ ጦርነት ባጣቸው ባሏ ምክንያት እርሷም ተከተለችው፡፡ ተከታዩ የዙፋን ባለቤት ተፈሪ ሆነ፡፡  
  ተፈሪ ከ13 ዓመቱ ጀምሮ በሀረር ከአባቱ ብዙ ልምድ እና የወደፊት እጣ ፈንታውን የሚያደላድል ዕድል ማግኘቱ ግልጽ ነው፡፡ በንግስት ዘውዲቱ ስር እንደራሴ /አልጋ ወራሽ/ በመሆን ሲሾም አውሮፓን የጎበኘበት አመታት ለዙፋኑ መሰረታዊ ጥቅም ሳያገኝ አልቀረም፡፡
  ምዕራባዊያኑ ሁሌም አብረውት ነበሩ ማለት ግን ይከብዳል፡፡ ጣልያን ታላቅ ወረራ እና ስደት አስከትላበታለች፤ እንግሊዝ የራሷን አሻራ አኑራለች፤ ሌሎቹንም ብናይ ለረሳቸው ጥቅም እንጂ ለሌላም ስምምነት ውስጥ እንደማይገቡ አስመስክረዋል፡፡ /ንጉሱ ከአሜሪካ ጋር ለዓመታት ወዳጅ ለመሆን ቢጣጣርም በ1966 ላይ ግን ሲጠሯት አቤት ለማለት አቀረቀርች... /
 ራስ ተፈሪ  ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሆነ በኋላ ግማሽ ምዕተ አመት ወደ ሚጠጋ ጊዜ ኢትጵያን ገዝቷል፡፡ እነ አባወቃውን፣ እነ ራስ ጉግሳ ወሌን፣ እነ ደጃዝማች ባልቻ ሳፎን እና ሌሎች ለስልጣኑ መንገድ በቆረጣ የሚታዩትን ያስወገደው በጦርነት፣ በእስር፣ እና በብልጠት ነበር፡፡ የአድዋው አርበኛ ባልቻ ሳፎ /አባ ነፍሶ/ ግን ያሳዝናሉ፡፡ 
  እንዲህ እንዲህ እያለ ቀ.ኃ.ሥ አምስት አመት በስደት ከዛም ከድህረ ፋሺስት መልስ "ኢሊሙኔሽን" በሚሉት የስልጣን ዘመን የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት ሊሆን አልቻለም፡፡ 30ዎቹ እነ ሲቪሊያ ፓንክረሰትን፣ ኩዋሜ ንክሩማን እና ማርከስ ጋርቬይን አልከለከለንም፡፡ ፓን አፍሪካኒዝም ተጠነሠሠ፡፡ ስልጣን እንዲህ በቀላሉ ሊገኝ? አርበኛው ወደቀ... ገበሬው አመረረ... እናት አለቀሰች... እማማ ኢትዮጵያ ደም አነባች! አይ አንቺ ሀገር..! ንጉሱም ለመሰደድ የበቁ የመጀመሪያ ስደተኛ ሊባሉ ሊያስችላቸው ይችላል፡፡ ለሊግ ኦፍ ኔሽን ያሰሙት ጩኸት ሰሚ ቸጣ!  “እንግሊዝን ያመነ ጉም ዘገነ” መሆኑን ሳይረዱ ተወዳጁ፡፡ ዘላቂ ግን አይደለም፡፡ ዘላቂ ፈጣሪ ብቻ ነው!
  ከዛም አሜሪካ ተራዋን ያዘች፡፡ ኤርትራም ለመዋሃድ "ሙከራ" አደረገች፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ አየች! መፈንቅለ መንግስትም ተሞከረ አንድም ብቻ አይደለም ሁለት ሶስቴ፡፡ የ53ቱን ግን የሚያክል አልነበረም፡፡ ያም ዙፋኑን ሊያነቃንቀው አልቻለም፡፡ 13 ዓመት መጠበቅ ግድ ይላልና፡፡ ከተለያዩ የጦር ቦታዎች በተውጣጡ ወታደሮች ደርግ ብቅ አለ፡፡ ለኢትዮጵያ “ያለምንም ደም የሚል” መፈክር ቢያሰማትም ደሙ ግን አሁንም ሊያቆም አልቻለም፡፡ የ59ኙ የግድያ ፍርድ እና የሌ. ጀ አማን አንዶም አሰቃቂ ግድያ ይህች አገር ምን ይሆን የራቃት ያስብላል፡፡
  የኢትዮጵያ ህዝብ ደሙ ፈሰሰ፣ የኢትጵያ እናቶች እንባ ተረጨ፡፡ ወደ ሰማይ ተረጭቶ ቢሆን ፈጣሪ ሰምቶ ታላቅ መሪ ያስነሳልን ነበር፡፡ እንባው ወደላይ ይሁን ወደታች የተረጨው ስላላይን ቀጣዩን መሪ ታላቅ መሪ ለማለት ተቸገርን፡፡ ታሪክ ይፋረደዋል!
 ፈጣም ሀዝቡን ከልብ አልለመናችሁኝም ብሎ ይሁን ለፈተና አስቦት ባልታወቀ ምክንያት የፈጣሪን እና የእምነትን ህልውና ጉድ ለሚያስብል ዙፋን ኢትዮጵያ ታጨች፡፡ ጉድ ተሰማ፡፡ ጉድ ተባለ፡፡ ስደት ከኋለኛው ጨቋኝ ከተባለው መንግስት በተለየ መልኩ መንገዱን ቀየሰ፡፡ ይሄው ስደት እስካሁን አልተገደበም፡፡ ኢትዮጵያ!!
  ቀ.ኃ.ሥ ተያዙ፡፡ በሚያሻማ አሟሟት ተሰናበቱ፡፡ ኢትዮጵያ ኃይለ ሥላሴ፤ ኃይለ ሥላሴ ኢትዮጵያ እንዳልተባለ እርሳቸው ሲሄዱ ኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ቀጠለ፡፡ ህዝብ ይሄዳል፣ ትውልድ ይተካካል ኢትዮጵያ ግን አለች-ትቀጥላለች-ትኖራለች!
  የአሟሟትን ክብር እንኳ እንደዚያ ሲያሞካሹ የነበሩት ንጉሰ ነገስቱ በወጉም አልተቀበሩ፡፡ ሞተዋል ከተባለ በኋላም እንደገና የቀብር ስነ-ስርዓታቸው ይደረጋል ብሎ የገመተ አልነበረም፡፡ የጊዜ ባለቤት ፈጣሪ ግን አሳየን፡፡ በተከታዩ መንግስት የቀብር ስነ-ሰርዓት ተደረገላቸው፡፡ ይህ ታዲያ የታሪክ መልስ አይደለም ትላላችሁ? ታሪክ ፈራጅ ነው፡፡
 ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ተቧደነች፡፡ ያንን ጉድ ያስባለ ጦር ሃይል ገረሠሠች፡፡ 17 ጊዜ 70 ይቆያል የተባለ ዙፋን ለባለተረኛው ማስገደድ አለበት፡፡ 1983፡፡ ኮ/ልመንግስቱ ኃ/ማርማያም ተሰደዱ፡፡ በወግ እንኳ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ አልሸኛቸውም፡፡ ያው ታሪክ ፍርዱን ሊሰጥ ግድ ነው!
ህገመንግስት፣ የራስን መብት መወሰን፡፡ ኤርትራን “አዲዮስ!” አስባለን፡ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ፤ የተማሪዎች ደም...  ቦናፓርቲዝም፣ አብዮታዊ ዴሞካራሲ፣ ምርጫ 97ን ይዘን ቀጠልን፡፡ ፓራለማው ከንጉሰ ነገስቱ ባልተለየ ድባብ የአንድ ሃሳብ የበላይነትን አጠናከረ!
  ሶስቱ መንግስታትን ማወዳደር አይቻልም፡፡ ዋይኒ ሩኒን ከፒተር ቼክ፤ ሊዮኔል ሜሲን ከፔርሎ፤ ኔይማርን ከዚነዲን ዚዳን ጋር  ማወዳደር ይቻላልን? አይቻልም! ሶስቱም በተለያየ ቦታ የሚዳኙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሶስቱም ግን ኳስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሶስቱም ደግሞ መሪዎቻችን ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ/ አፄው እና ኮረኔሉ/ ስለስልጣን ዘመናቸው በቀላሉ የማያልቅ ዘገባ ለማስተባበል ሞክረዋል፡፡  እንደ እኔ እንደኔ እነርሱን ከመቀውቀስ ኑዛዜያቸውን በማንበብ ታሪክ የሚነግረንን ፍርድ ማየቱ የሚቀል ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን እና የመሬት ባለቤት ሆነ? ይሄንን አይን ይፈርዳል!
  ከእያንዳንዱ የታሪክ ክስተት ጀርባ ታላቅ ሚስጥር አለ፡፡ ታላቅ ትምህርት አለ፡፡ የነገ ተስፋ አለ፡፡ ከታሪኩ የማይሻሻል ህዝብ ከእንሰሳነት አይለይም፡፡ ታሪኩን የማየያይ ህዝብ ሰው ነኝ ብሎ ሊያወራ አይጋበዝም፡፡ ብዙ አሳልፈናል፡፡ ብዙ አይተናል፡፡ ብዙ ለመማር እድል አግኝተናል፡፡ ከዚህ ካላተማርን ግን ሰው መሆናችንን ክፉኛ ያስጠረጥራል፡፡ አባቶቻችን ስልጣንን የገነት በር አደረጉት፡፡ ይዘውት ሲሄዱ ግን አላየንን፡፡ ልናይም አንችልም! አባቶቻችን በዘር፣ በቀለም፣ በጎሳ ተናንቀው እንደሆነ እኛው በዚህ መዘውር የተቃኘን ከሆንን አጥቶቻቸውን ቀስረው ባጠጠጡት ጥርሶቻቸው ይሳለቁብናል! ለመዋይት እና ችግርን በሰላም ለመፍታት ስልጣኔን ካልተማርን ካለፉት አልተሻልንም፡፡
  ዛሬ ትነጉዳለች! ነገ ትተካለች! ታሪክ ይጻፋል፡፡ ታሪክ ሰሪ ትውልድ ሲመሰገን ይኖራል፡፡ ከየትኛው መደብ ነን? ዛሬ ምን እየተሰራ ነው? ከታላቁ የህዳሴ ግድብ በስተጀርባ ምን አለ? ከታለቁ መሪያችን ሞት በስተጀርባ ምን ይገኛል? ከባለ ራዕዩ መሪ ራዕይ ስር ምን ትንቢት አለ? ሃይል እና ስልጣን የእግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህች መሬት አንገታቸውን የሰው፣ ደማቸውን ያፈሰሱ፣ ስጋቸውን የቆረሱ፣ አጥንታቸውን ያደቀቁ ይፋረዳሉ! ንግስት ሳባ ልትፈርድ ትነሳለች! ጥበበኛው የኢትዮጵያ አምላክም ይፋረዳል! ከታሪክ በስተጀርባ ያለን ነገር እናስተውል፡፡ የዚህ ጽሑፍ አላማው አንድ ነው፡፡ ታሪክን እንወቅ፡፡ በታሪካችን በሰላም እና በቀና መንፈስ እንወያ፡፡ ከታሪክ ማወቅ ውስጥም፤ ከታሪከ መማር ይከተላል፡፡ ከታሪክ በስተጀርባ ያለን ሴራንም ያስመረምራል፡፡ ታሪክ ሰሪ ትውልድ ያደርገናል! ታሪክ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል፡፡                                                 ቸሩ ቸር ያቆይን!

No comments: