Feb 12, 2013

About Professor Mesfin Wolde Maryiam Book Articlle

ታላቅ ክሽፈት
ከስህተት መማር ከክሽፈት መዳን ነው!
በተስፋ በላይነህ
በዕለተ እሁድ ከብሔራዊ ቲያትር የፕሬፈሰሩን መክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ መጽሐፍ አስተያየትና የውይይት መድረክ ዝግጅት ተከታትለን ስንወጣ ለጋዜጣ ንባብ ጊዜ ሰጥተን በዕለቱ የሚወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ በገጽ 36 ቅጽ 18 ቁጥር 25/1334 እሁድ የካቲት 03/2005 በክፍል አንድ ዕትም ሥለከሸፈው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ጥራዝ አንዳንድ ነጥቦች በሚል ርዕስ በአቶ ተስፋዬ ንዋይ የቀረበ ፅሁፍ ላይ ትኩረቴን ሰጠሁ፡፡ ምክንያቱም የወጣሁትም ከዚህ ዝግጅት በመሆኑና ክሽፈት የምትባል አማርኛ ሰሞንኛ ከመሆኗ አንጻር በየመጠጥ ቤቱ ፣ ጸጉር ቤት ስጋ ቤቶች የመነጋገሪያ ሀሳብ ከሆነች ትንሽ ሰንበትበት ብላለች፡፡ በተለያዩ ጋዜጦች መጽሄቶችም ላይ የአምድ የጋራ መለያ ሆናለች፡፡ መጽሐፍ አዘውታሪ በሆኑ ሰዎች ዘንድም “ባክህ ከሸፈሃል” አንተነህ የከሸፍክ ሲባባሉ እንሰማለን፡፡ በዕለቱም ብሔራዊ አካባቢ የነበረው ሰው ይህችን መጽሐፍ ያልያዙት በዕለቱ የነበሩት የብስክሌት ተወዳዳሪዎች ብቻ ናቸው ብየ መግለጽ ምን ያህል ሰው ይዞት እንደነበር የሚያመለክት ግነታዊ ሃሳብ በመሆኑ አንባቢያን ይረዱኛል፡፡
አርዕስቱን ስመለከት የከሸፈው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ” ጥራዝ አንድንድ ነጥቦች በማለቱ የመጽሑፉን ግድፍቶች ሊናገርና መጽሐፉ የታዩበትን ሕፀፆች ለማውጣት የተጻፈ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ይህም ያየበትን ማዕዘን ለማየት ስልፈለግሁ ጓጓሁ፡፡ ሆኖም ጥራዝ በማለቱ የያዝኩትን መጽሐፍ ጥራዝ ብሎ መግለጽ ትንሽ ግራ አጋብቶኛ፡፡ ምናልባት ጥራዝና መጽሐፍ አንድ ከሆኑ የአማርኛ መምሕሮቼን ለመጠየቅ እገደዳለሁ፡፡ አቶ ተስፋዬ ንጉሴ ለምን ይህንን መጽሐፍ ጥራዝ አሉት? በማለት ጠየቅሁ፡፡ ወረድ ብሎም መነሻ ብሎ የጀመረውን አገራችንን የአጭር ታሪክ ማንበቤን በመጠራጠር ወደ ኋላ ተመለስኩ፡፡ የጸሐፊውን ስምና ርዕሱን በሚገባ አየሁ የአገራችንን አጭር ጊዜ ታሪክ ሃሳብ ስደጋግመው እንዴት የኢትዮጵያ አጭር ጊዜ ታሪክ ተባለ? ሆ! ገና ከአርዕሠቱና ከፅሑፉ መጀመሪያ አንቀጽ መጀመሪያ መሰመር ጥያቄ ከጀመርኩማ ወደ 26 የሚጠጉ አንቀፆችን በማነብበት ወቅት ምን ያክል እንደሚያጠይቅ በመገንዘብ ለገዛሁት ጋዘጣ ዋጋዬን ለማግኘት ማንበቤን ቀጠልኩ፡፡
እያንዳንዷን መስመር በማየት ሃሳብ ከሰጠው ምናልባት ውድ ጊዜዬን ወድ ሰዓቴን ጨንቅላቴንና የዚህ የጋዜጣ አምድ ገጽ ላለማባከን ባጭሩ ለማስቀመጥ አገደዳለሁ፡፡ እርስዎም መጽሐፉን ሳያነቡ ይህን አስተያዬት እንዳያነቡት እመክራለሁ፡፡
አቶ ተስፋዬ ንጉሴ አይደለም ከርስዎ ፅሁፍ አይደለም ከፕሮፌሰሩ መጽሐፍና ከሌሎችም ታዋቂ መጽሐፍት ቀርቶ ከታላላቆቹ መጽሐፍት ሳይቀር ስህተትና ሊያጋጩ የሚችሉ ሀሳቦችን እንፈልግ ብንል ሊያገኙ እንደሚልችሉ አይጠራጠሩ፡፡ ስናነብ የተልባ ፍንጣሪ በሚባል ዘይቤ የምናነብ ከሆነ ትልቅ ክሽፈት የሚያስከትል በመሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ለማመላከት እወዳለሁ፡፡ እረስዎም በፕሮፈሰሩ መጽሐፍ ላይ ያደረጉት የተልባ ፍንጣሪ አይነት የንባብ ዘይቤን መጠቀምዎትን ጽሑፍዎትን አንብቤ ስጨረስ የተረዳሁት ውሳኔ ነበር፡፡
እርስዎ በጠቀሱት ሃሳብ እንኳን በ2 ተኛው አንቀጽ ‹‹በሚገባን ቋንቋ አቅርበውልናል›› ማለትዎትን ለመሰንጠቅ ልሞክር፡፡ ቋንቋ በግዕዝ በዓርብኛ በጽርዕ በሌላም በሌላም ቢቀርብልን እኳን የተጠቀሱትን ቋንቋዎች የሚችሉ ሰዎች ይገባቸዋል፡፡ ቋንቋን ቀለል ያለ አገላለጽ፤ ቀለል ባለ ሀሳብና ግልጽ በሆኑ አማረኛ ቃላት አቅርበውልናል ቢሉ ኖሮ ያስመሰግንዎት ነበር፡፡ ለእያንዳንዱ መሰመር credit እየሰጠሁ ያለውን ችግር ልፈልግ ካልሁ ከየአንዳንዳችን የሚገኝ ድክምት ነው፡፡ አርስዎም ጽሁፎትን በዚህ አይነት ሀሳብ እንዳነብ አድርገውኛል፡፡ በነገራችን ላይ እርሰዎ እያልኩ የጻፍኩ በአለም ለየት ከሚያደርጉን ባህሎቻችን የማያውቁትን ሰው ማክበር ፣ታላላቆችን ማክበርና ትሕታናዊ ሀሳቦችን ለማስተላለፍ ያስተማረችኝን እምዬ ኢትዮጵያ በመሆኗ ነው፡፡ እርስዎ ግን (የጥራዙ) ጸሐፊ መስፍን ወልድ ማርያም ናቸው ብለው ሲገልጹ አገር ያወቀውን ፀሀይ የሞቀውን ማዕረጋቸውን እራሳቸው አልጠቀሱትምና እኔም አልጠቅሰውም ማለትዎ አሳዝኖኛል፡፡ እርሳቸው የፕሮፍሰርነት ማዕረጋቸውን ለገበያ ማውጣት አለመፈለግና ሌላም የግላቸው ምክንያት ይኖራቸዋል፡፡ ባጠቃላይ ፅሁፍዎት ነገር ፍለጋ /ውስጠ ወይራ/ መሖኑን በመገንዘብ ንባቤን እንዳጠናክር አድርጎኛል፡፡ የተደጋገመ ጭንቁርቁር ሃሳቦችን በማየቴ አዝኛለሁ፡፡
እራሳቸው አላስቀመጡትምና እኔም አላስቀምጥም ማለት ኢትዮጲያዊነትን ገደል የሚከት ልምድ በመሆኑ ይታረሙ፡፡ ስናነብ የመጽሐፍን ጭብጥ እየፈለግን መጽሐፉን ሀሳብ ሚዛናዊ በሖነ አዕምሮ ብንፈልግ ብዙ መማር እንችላለን፡፡
ቀጠለ በ3ኛው አንቀጽ ላይ ኢትዮጵያ ማነች ተብሎ ለቀረብ ጥያቄ መልስ ይሉንና፡- አገር ነች፡፡ በማለት ይመለሱልንናል፡፡ ኢትዮጵያ አገር ነች የሚል መልስማ አይደለም እርስዎ የማይናገሩት ድንጋዮች እንኳ ይመሰክራሉ፡፡ አቶ ተስፋዬ ንጉሴ ማናቸው? ተብሎ ቢጠየቅ ሰው ናቸው፡፡ ተብሎ መመለሱ እንኳን እኛ በመንገድ የሚያልፍ ውሻ እንኳን ያውቀዋል፡፡ በጣም አሳፋሪ መልስ ነበር፡፡ አቶ ተስፋዬ ንጉሴ ማናቸው ለተባለ ጥያቄ የዚህ ቁመት ፣ የዚህ አይነት መልክ ፣ ስራ፣ እድሜ፣ ውልደት እያልን መዘረዘር እንችላለን በፕሮፌሰሩም መጽሐፍ ገጽ 50 ላይ አገርን የሚገልጽ በደማቅ የተተነተነ በቂ መረጃ ነበረልዎ፡፡ የተቀመጠልንን ሃሳብ ሳያነብቡ ባለመስቀመጦት እዘንኩ፡፡ አገር ማለት የመሬት ፣ የህዝብ ፣ የመንግሰት የሶስቱም ህብረት መሆኑን ጠቅሰውልናል፡፡ አላነበቡትም ካነበቡትም አልገባዎትም፡፡
ይቀጥላል ጉድ! በትዕምርተ ጥቅስ ያስገቧችውን ቃላት ሳያስረዱን የአክሱምን ሐውልት የላሊበላን የጎንደርን ቤተ-መንግስት የድንጋይ ሰራ ጥበብ ክሽፈት የተነሱትን ሃሳቦች የገለጹበት ሃሳብ አሳዝኖኛል፡፡ ደራሲው እነዚህን የገነባ እጅ ( ትውልድ ) ሰፊው ህዝብ በደሳሳ ጎጆ ቤት መኖሩን ማሳሰባቸው ያሳዝናቸው እኝህ ምሑር የነዚህ ሃውልቶች ደንጋዮች ክሽፈት ኢትዮጵያን ታሪክ ክሽፈት እንዳማይገልጽ የጠቀሱት የድንጋይ ስራ ጥበብን ከማጣጣልዎ አልፎ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው ደምድመዋል፡፡ ጎብኝዎች ይህችን አገር ለማየት የሚመጡት እርስዎን ለማየት ሳይሆን አነዚህን ድንጋዮች ለማየት እንደመሚጡ የሰረዙበት ሃሳብ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን ለውጭው አለም ከሚያስጠሯት እሴቶቻችን በቀዲሚነት የሚጠቀሱት ናቸው፡፡ አነዚህን የገነባ እጅና ትውልድ ጥበብን ለሰፊው ህዘብ ሳይማርበት መሰረታዊ ነገር ከሚባሉት አንዱ የሆነውን መጠለያ በመግንባት መኖር አለመቻላችን ያሳዝናል፡፡ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሌላ የክሽፈት ታሪኮች አሉ፡፡ ይጠቀሰ ቢባል እንኳን ሌሎች የታሪክ ጥበብ ክሽፈቶች አልተገለጹም ላሉት ጥያቄና በአረንጓዴ ምልክት የመታለፍ ክሽፈት ነው ብለው ያስቀመጡት ሀተታ በመጽሐፉ ገጽ 22 ና 23 ገጽ 25 እና በገጽ 67-73 በአጠቃላይ በዝርዝር የተቀመጡ 36 የክሽፈት ታሪኮች ቀርበውሎታል፡፡ በየመጽሐፉም አንዳንድ አንቀጾች ጭምር እግር ኳሳችንን ሳይቀር የጠቀሱልን ትልቅ ክብርና ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሰው ናቸው፡፡ ይህንንም አላነበቡትም ቢያነቡትም አልገባዎትም፡፡
በሌላኛውም አንቀጽ ያልተጠቀሱ የጥበብ ታሪኮች በማለት ሌላ ውስጠ ወይራ ሃሳቦዎን የዘከዘኩበት ( ያስበቀብዎት) መረጃ በ 7ኛው አንቀጽዎ ላይ እናገኘዋለን፡፡ የኦሮሞ ገዳ ስርዓት ባለመቀመጡ ፣ የወላይታ ፣ የሲዳማ ፣ የመሳሰሉት የጥበብ (ስልጣኔ) ታሪኮች ለምን አልተገለጹም በማለት ጠይቀዋል፡፡ የመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ ወደሌላ ሃሳብ ይዘው ለመሄድ ያደረጉትን ሃሳብ ተረድቻለሁ፡፡ ምናልባት በመጽሑፉ 29 ገጽ ላይ ያልከሸፈ ሀይማኖት የለም ፣
‹‹ዮዲት ከሸፈች፤ አባ አስጢፋኖስ ከሸፈ፤ አህመድ ኢብራሂም ከሸፈ፤ ሱሰንዮስ ከሸፈ፤ ዮሐንስ ከሸፈ እያሱ ከሸፈ፤ መንግሰቱ ከሸፈ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ሁሉንም ቅንጫቤ ይዛለች››
በሚለው አንዲት የተልባ ፍንጣሪ የምታክል አንቀጽ ውስጥ ባለመስቀመጣቸው እንደ አስተያየት የሚገለጽ ሃሳብ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይንም ለምን እንዳላስገቡት መጠየቅ ይቻላል፡፡ ሆኖም በመጽሐፉ ስለ ሃይማኖት ዘርና የእምነት ስርዓቶች ክሽፈት የማይዘላብድ መጽሐፍ ባለመሆኑ የሃይማኖት እምነት ወይንም ባህላዊ ስርዓቶች ለምን ከሸፉ የሚል ጭብጠን ያልያዘ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምናልባት ከዚህ በኋላ የአሮሞ ገደ ስርዓት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? ከሸፏል ወይስ እየተሳካ ያለ ስርዓት ነው? ብሎ የሚጠይቅ ሃሳብ የያዘ መጽሐፍ እንድንፈልግና እንድንጽፍ የሚያደርግ መጽሐፍ መሆኑን በጭራሽ አልተገነዘቡትም፡፡ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ባለበት ሥርዓት ማንነት ባጠቃላይ ታሪክ ከሽፏል ወይስ ተሳክቷል ብሎ እንዲመረመር የሚያደርግ መጽሐፍ በመሆኑ ሊታሪክ ሊቀመጥ የሚችል ቁልፍ ነው፡፡ ምናልባት የንቡረዕድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ ተከታታይ መጽሐፍት የኢትዮጲያ መክሸፍ (እንዲህ ለመዓት፣ለቁጣ ለበሽታ የተጋለጥነው) የእግዚአብሔርን ሕልውና በመዘንጋታችን ነው በማለት ያስቀምጣሉ፡፡ ከእርሳቸው ውጪ የክሽፈታችን መንስዔና ምክንያት ያስቀመጡ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚዳስስ ምሁራዊ መጽሐፍ እንድንጠብቅ የረዱ ፋና ወጊ ናቸው፡፡ ቀናና ሚዛናዊ ሆነን ልንወስደው የሚገባ መጽሐፍ ነው ባይ ነኝ፡፡ቢሆንም ማዕረጋቸው ፕሮፌሰር ሆኑ እንጂ ባለ ሁለት አይን ሰው ናቸው፡፡ ባለአራት አይን የሚያስብል ማዕረግ ላይ አልደረሱም፡፡ ለእያንዳንዳችን ያልተጨረሰ የቤት ስራ የሰጡ አባት ናቸው፡፡
ምኑ ተነካና! ይቀጥላል መንደርተኝነት በሚለው የመጽሐፉን ሃሳብ በመጥቀስ መንደርተኛነት ሊያሰጠው የማይችለውን የፕሮፌሰሩን ገጠመኝ አስቀምጠዋል፡፡አሜሪካ ሄደው ‹‹ስምዎ ማርያም ነው›› ብላ ስለተናገረች ሴትና ‹‹ስሜን እንቺ ነሽ እንዴ የምትነግሪኝ እንዴ›› በማለት ያቀረቡትን ምላሽ መንደርተኛ ብሎ መስጠት ትልቁ ክሸፈትዎ ነው፡፡ በአለም-አቀፋዊነት መድረክ በምንገኝበት ወቅት ማንነታችንን ባህላችን አመጣጣችንን ለአለም መግለጽ መንደርተኝነት ከተባለ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ ጫላ የተባለ አንድ ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ሄዶ ሰሙ ቻላ ( Chala ) ቢባል ቻ ሳይሆን ጫ እንደሆነ እስኪገባቸው ድረስ የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ በዛውም ማንነቱን ቋንቋውን ( ፊደሉን ) ለአለም አያስተዋወቀ መሆኑ መንደርተኛ አያስብልም፡፡ አንድ ሰሜን ኮሪያዊ ደቡብ ኮሪያዊ ነህ ብትለው ምናልባት በኑውክሌር ቦምብ ሊያፈነደህ ይችላል፡፡ ምናልባት አንድ ቻይናዊን ጃፓናዊ ብትል ሊበሳጭብህ ይችላል፡፡ ይህም እንኳ የተለመደ ነው፡፡ የፕረፌሰራችን አጋጣሚ ግን ከእነዚህ ይለያሉ፡፡ በኢትዮጲያዊ ስማቸው በአሜሪካዊ ስም ስለተጠሩ ለማሰረዳት መሞከራቸው መንደርተኛ ናቸው ብለው መለጠፈዎት በቀይ ምልክት ሳይሆን በዝረራ የከሽፉበት ቦታ በመሆኑ በዝረራ የወደቀ ደግሞ ተስፋው ሌላ ዕድል ነው፡፡ በሌላለ ጨዋታ ቢመጡ ያወጣዎታል፡፡ ፕሮፌሰሩም የ80 አመት ባለጠጋ በመሆናቸው የድሮውንም ኢትዮጲያው ባህርይ አንዳለባቸው መገመት አይከብድም፡፡እንዲህ አንዲህ እያለ አንቀጾች በበዙ ቁጥር ክሽፈቱም በዛው ልክ የበዛ ጽሑፍ በመሆኑ አባካችሁ መጽሀፉንም ይህንን ጥራዝ-ነጠቅ ፅሁፍ ለታሪክ ይቀመጥና ታሪክ ራሱ ይፍረደው፡፡ትውልድ ራሱ ይፋረደው፡፡
አንድ ገጠመኝ በማስቀመጥ ላጠቅልል፡፡ በዚሁ ዕለት ከብሔራዊ ቲያትር ዝግጅት በወጣንበት ሰዓት የተለያዩ ሰዎች የግል ጥያቄዎቻቸውን ለማቅረብ ከቲያትር ቤቱ ሕንጻ ግቢ ጀርባ ተሰብስበው ነበር፡፡ ከተሰበሰቡት ሰዎች አንድ ቦታውንና ቅድሚያ እድሉን ያገኘው ጀብራሬ ፕሮፌሰሩን እንደ ዜና መዋዕለ ወይም ገደል ታሪክ ፀሐፊ አሳቸውን እንደ ንጉስ አድርጎ ይፎክርላቸዋል፡፡ ‹‹እርስዎ ልዩ ሰው ነዎት ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በየጊዝው ንቁ በመሆን የሚያደርጉት ተሳትፎ እና ትግል አርዓያ እንዲሆኑ የሚያስችሎት ውለታ ነው፡፡ ትልቅ ሰው ነዎት፡፡ አድንቀዎታለሁ!›› ቀጠለና መጽሐፉ ውስጥ ያለውን ጭብጥና የታሪኮቻችንን መክሸፍ እንደ አስተያዬት ምን ይሉናል? በማለት ለመጠየቅ ሲወራጭ ይቅርታ አንዴ ብለው ፕሮፍ አስቆሙት፡፡ “እንደዚህ ከመንዘባዘብህ በፊት መጽሐፉን አንብበከዋል?” ብለው ጠየቁት፡፡ መልሱ ምን ቢሆን ጥሩ ነው “አላነበብኩትም” ማለቴ “አልጨረስኩትም” ብሎን እርፍ! በቃ ጨረሻለሁ ብለው የሌላውን ጊዜ በመሻማት ደበበ እሸቱ በያዛት ቀይ ሃሽባክ ጥለውን ገቡ፡፡ ያስፍራል መጽሐፉን ሳያነብ ለምን መጣ ለምን መጣ? መምጣቱስ ባልከፋ ሳይነብ ሃሳብና ጥያቄ መስጠቱ አሳዘነኝ፡፡ ካሳፋሪ ገጠመኞቼ ማስታወሻ በቀዳሚነት መዝግቤዋለሁ፡፡
ሳናነብ ወይም ሳይገባን ዋና ጭብጥ ሳንይዝ ቡራ ከረዩ ማለት ራስን ከከበሮ ክብር የሚያሳንስ በመሆኑ አባካችን ( እኔንም ጨምሮ) እናንብ! ስናነብም መሰረታዊ በመሆኑ ሃሳቦች ላይ ሃሳብ እንስጥ፡፡ የመጽሐፉን ዋና ይዘትና ጭብጥ ለማየት እንሞክር፡፡ ሰለዚህ አቶ ተስፋዬ ንዋይ ለነበረን ጊዜ እያመሰገንኩዎት ይህንን በመጽሐፉ ላይ ያላነበቡትን ሰዎች ነጭ መጋረጃ ለማልበስ መሞከርዎት ያነበቡትንም ቀይ መጋረጃ ለመጣል የሞከሩት ሙከራ አልተሳካሎትም፡፡ስለመጽሐፉ ከተጻፉት ትችቶችና አስተያየቶች /በቀዳሚነትት የከሰረ ትችት ዝርዝር ቆጥ ላይ በክሽፈት አንደኛ ያስቀምጦታል፡፡ በዚኽኛው መጽሐፍ ላይ የተደረገው ክሽፈትና ሰህተት በሌላ አንዳይደገም፡፡ ከስህተት መማር ከክሽፈት መዳን ነው፡፡ በስህተት መኖርና ስህተትን መደጋገም ግን ከክሽፈትም ሁሉ ታላቅ ክሽፈት ነው፡፡ ቸሩ ቸር ያቆየን፡፡ የግል ሃሳብ ካሎት
tesfabelaynehh.blogspot.com ጦማር እና tes_bel@yahoo.com
ኢ-ሜል ይላኩ፡፡

3 comments:

gashawmelesse said...

Though the topic doesn't concern me, I really want to appreciate you man!

Thumbs up!
GASH GASHAW

https://tesfabelaynehh.blogspot.com/ said...

Gashiti Thank you very much! Which topic, is that may be you are far from this land? you may be involved if you were here...any way keep in touch!

Unknown said...

Please try to write the writer's name first...Tesfaye Niway not Tesfaye Niguse.Then we can talk about other things.Concomitantily, you tried to support the argument of the Tesfaye On the issue of 'mendertenya'.I think u should read the critic again, forfeit the book!!!