Dec 4, 2017

ፕ/ር መስፍን የዲያቢሎስ ጠበቃ? በእንዘጭ እንቦጭ-የኢትዮጵያ ጉዞ መጽሐፍ ውስጥ፡፡





                                                                  ተስፋ በላይነህ


(እንዘጭ እንቦጭ-የኢትዮጵያ ጉዞ INZECH IMBOCh BOOK  by PRof Mesfin W/mariam )

በአሁኑ ሰዓት መጽሐፍ የማንበብም የመጻፍም ፍላጎቴ ወርዶ ነበር፡፡ ነገር ግን በመጠኑም ቢሆን “እንዘጭ እንቦጭን” ሳነብ ተነሳሳ፡፡ የሚኮረኩር መጽሐፍ ሲመጣ ከደነዘዝንበት፤ እየከነፍን፤ ከምንገኝበት የውድቀት ጉዞ እንድነቃ የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡ እንደ መብረቅ ነው፡፡ ያነቃቃል፡፡ በልቡናችን ሲጮሕ ይሰማል፡፡

ዋናው ችግራችን እየተንደረደርን ቁልቁለቱን እየተምዘገዘግን መጓዛችንን አለማወቃችን ነው፡፡ ተላምደነዋል፡፡ ሞቆናል፡፡ አይበርደንም፡፡ ተመችቶናል፡፡ አይጎረብጠንም…ተኝተናል፡፡ አናነብም፡፡ አንጠይቅም፡፡ አንወያይም….ይቀጥላል!!

ፕ.ር መስፍን ወልደማርያም ከ21ኛው ክ/ዘን መባቻ ጀምሮ በአስር ዓመታት ውስጥ በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ‹‹ብቻ›› ሶስት መጽሐፍትን አሰስነበቡን “መክሸፍ፣አዳፍኔ፣ እንዘጭ እንቦጭ!”
ሶስቱም መጽሐፍት መሰረታዊ ዳራቸው፤ ጭብጥና መቼታቸው፤ ሐሳብ ፍሰታቸው፤ መዳረሻ አላማቸው አንድና አንድ ነው፡፡
ይኄውም ኢትዮጵያ፣ ታሪኳ፣ በባህሏ ውስጥ ተቀብሮ የሚገኘውን የአገዛዝ ተራክቦ፤ ፍትህ/ህጋዊነት፣ እውቀት፣ ነጻነት እና ሥልጣኔ..!
ፕ/ር በመጽሐፉ ተደጋጋሚ ሲናገሩ እንደምንሰማቸው፤ በግልጽ ሲጠቅሱ የምናገኘውም ለዘመናት የኢትጵጵያ ሕዝብ ባሕርይ ከሆነው እና ቀስ ብሎ የተገለጠልኝ ከሚሉት የማድፈጥ ባሕርይ ነው፤ 

“ማድፈጥ ለጉዟችን ውድቀት መንስኤ፤ ለአገዛዝ እና ጨቋኝ መንግሥት መተካካት ምክንያት ሆኖ እንመለከተዋለን” ይሉናል  ፕ.ሩ፡፡

በበኩሌ መጽሐፉን የመንቀፍም ሆነ የመተቸት ፍላጎትም ይሁን አዝማሚያ የለኝም፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባሕል እና ሥነ-ባሕርይ እንደእሳቸው ተንትኖ ያቀረበ እና ለመፍትኄ ሐሳብ እንዲውል ተደርጎ የተጻፈልኝን ጽሑፍ አጥብቄ ከሚደግፉት ውስጥ የምመደብ በመሆኔ፤ መሰል መጽሐፍት እንዲበዙልን እማጸናለሁ፡፡ የእሳቸው ጥማት የአውቀት ጥማት ነው፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ቀያሪ መዘውር ግፊት ነው፡፡ ትምህርት መስሪያው እና መሳሪያው ነው!

 ሆኖም በመጽሐፉ የተረዳሁትን እና ያገኘሁትን (የማልስማማባቸውን) ሐሳብ በጥያቄ በማቅረብ እጥራለሁ!

1-ይሕ ማድፈጥ የተባለው ግኝት፤
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኝነትን በልቡ ይዟል፡፡ የሃይማኖት ሕጎችን በፍጹም ሙሉነት ተቀብሎ ይተገብራቸዋል ባንልም ባሕሉ ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ፈርሃ እግዚአብሔር ያለው/የነበረው ሕዝብ ነው፡፡ ይሕንንም ራሳቸው እንደመሰከሩት በሕግ አምላክ በሚል ልማድ፤ ሁለት የተጋጩ ግለሰቦች ማንም አልፎ ሂያጅ አገላግሎ ኩታቸውን ቋጥሮ ወደ ሸንጎ ይልካቸው ነበር፡፡ ይሕ ከሃይማኖተኛ ማሕበረሰብ የሚወጣ ልማድ ነው፡፡ በልቡ ሕግን/እግዚአብሔርን ከሚፈራ ማሕበረሰብ የሚወጣ ነው፡፡ ስለዚህ በሕዝቡ ልማድ እኔም እሳቸውን እንስማማለን ማለት ነው፡፡ የሃይማኖተኛ ማሕበረሰብ ደግሞ በልቡ የዝምተኛነት፣ ሚስጥር የመጠበቅ፣ የጭምትነት እና ከአመጻ ይልቅ በትዕግስት ለውጥን መጠበቅ ይቀርበዋል፡፡ 
ለውጥን መጠባበቅ በብዙ መንገድ ሊሆን ይችላል፡- 

አንዱ በጸሎት ነው፣ አንዱ በመቧደን ነው፣ አንዱ በቃወም ነው … 

አንድን ማሕበረሰብ የሙሉ ማንነት ስብዕና ማላበስ የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሰሜን ደቡብ ከምስራቅ ምዕራብ ለመቀራረብ በቀላሉ አይቻለውም፤ በለውጥ ጊዜም ይሁ ችግር ተከትሎት ይመጣል፡፡ ጥቂቶች ወደ ስልጣን ይሽቀዳደማሉ፣ ጥቂቶች ጎልተው ይወጣሉ፤ ጉልበተኛው ይገዛል፡፡

ዝም ያለ ሕዝብ ሁሉ ያደፈጠ ላይሆን ይችላል፡፡ ዝም ብሎ የሚጸልይ አለ፣ ዝም ብሎ የሚቃወም አለ፣ ዝም ብሎ የሚኖር አለ፤ ዝም የሚለውም ሁሉ ገዥ ለመሆን አልያም ጨቋኝን ለማንገስ አይደለም፤ ከዚህ መሐል አድፋጭ የለም ማለት ባንችልም፤ ሥልጣኑን የሚፈልጉ አድፋጮች ግን ትልቁን ሥራ እንደሚሰሩ እንረዳለን፡፡ አሜሪካም አብራ ማድፈጥዋ ኢትዮጵያዊ ሆና አይደለም!! ማድፈጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክል መጠሪያ መሆኑ ሊያወያየን ይገባል!!

ለምሳሌ ማድፈጥ የትዕግስት ሂደት ሆኖ ቢቀርብ እና ታግሶ የኖረ ሕዝብ እምቢ የሚልበት ጊዜ መድረሱን የሚያመላክትበት ጊዜ ሲደርስ ፤ ነገር ግን በለውጡ ሰዓት ጠበንጃ ያነገበ እና ሴረኛ ቡድን (የውጭ ሃይል) ሲጨመርበት የለውጡ አቅጣጫ መልኩን ይቀየራል፡፡

በተለይ በሶስቱ መንግሥታት የለውጥ ሂደት ስንመለከት፤አደፈጠ የተባለው ሕዝብ በለውጡ ዋዜማ ወቅት የራሱን ተቃውሞ አሳይቷል፡፡ 
1-በኃይለስላሴ ወቅት ሕዝቡ ወጥቶ በአደባባይ የመቃወም ባሕል/ልምድ ባይኖረውም ጥቂቶች ተቃውመዋል፡፡ በሰላምም የተዘዋወረ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ንጉሱ ከውጭ እርዳታ በሰማይ የሚበር ጉድ ማግኘታቸው ሥልጣናቸውን አቀዳጅቷቸዋል፡፡

2-በመቀጠልም የ1960ዎቹን የሕዝብ ማዕበል፤ የሰራተኛው ሰልፍ፤ የሙስሊሙ ሰልፍ፤ የባለታክሲው አድማ እና የወታደሩ እንቅስቃሴ እንዲሁም የተማሪዎች ድምጽ ከማድፈጥ ጋር ፈጽሞ መያያዙ ግራ አጋብቶኛል፡፡ የሕዝቡ ፍላጎት ሌላ አምባ ገነን መንግስት ለመተካት ሳይሆን መሳሪያ አልባ ሕዝብ መሳሪያ ካነገበ አንጃ ጋር በመገናኘታቸው ነው፡፡ ያም ሆኖ ዝም ብሎ የተገዛ ሳይኖር ወረቀት እና ብእር ይዞ በእሳት የተቆላው ሕዝብ ተቆጠሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡

3-በዘመነ ወያኔ 83 ዓ.ም ቢሆን እንኳ 15 ዓመት የመረረው የደርግ አገዛዝ፤ ደርግ የመወያየትን፣ የነጻነትን መስመር በዘጋበት ጊዜ በመሆኑ ያቺን አገር አይደለም ሕውሃት ሌላም ሊቆጣጠራት እንደሚችል ግልጽ ነበር፤ ያውም ሲአይኤ ተጨምሮበት!!

ወደ ኋላ ብንመለስ እንኳ ተፈሪ መኮንን በምዕራባዊያን እገዛ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ጳውሎስ ኞኞ በመጽሐፋቸው እንደዘገቡት አንብቤያለሁ፡፡(ይሕንን ጽሑፍ ስጽፍ በእጄ ምንም አይነት መጽሐፍ የማላገኝበት አጋጣሚ/ቦታ ላይ በመሆኔ የማቀርባቸው ጽሑፎች በሙሉ ርዕስና ገጽ አይገልጹም)
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠበንጃ ካነገበ አንጃ እና ከውጭ ኃይል ሴራ ጋር የሚላተም ህዝብ ነው፡፡ ሕዝብ መሳሪያን ይዞ አገዛዙን እንዲለውጥ ነው ወይንስ ሰላማዊ ተቃውሞ እንዲያደርግ..?
ለአገዛዞች መፈልፈል የኢትዮጵያን ሕዝብ (አድፋጭነት) ተጠያቂ ማድረግ በእጅጉ ያሳስባል፡፡ ያጠያይቃል፡፡ መሪ ሆነው አርአያ ሆነው ብቅ የሚሉ ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን በሚገድል ስርዓት ምን አይነት አገዛዝ ስር እንደሚሰድ ለሁላችንም የታወቀ ነው፡፡ በውጭው አለም በርካታ ሰላማዊ ሰልፎችን የሚያደርግ የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ምን ያሳየናል፡፡ አገር ውስጥ ሀሳብን በመጻነት የመግለጽ ጉዳይ የውሃ ሽታ ቢሆንበት እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም፡፡ በሔደበት ሁሉ እየተቧደነ ያቅሙን ይፍጨረጨራል፡፡ ፈቅዶ የሚሰደድ የለም፡፡ ፈርቶ የሚሰደድ እንዳለ ሁሉ፤ መከራና ችግር አላይም ብሉ የሚሰደድ እንዳለ ሁሉ፤ ጊዜውን ለማምለጥ የሚሰደድም አለ፤ እድሜ ልኩን በስደት ለመኖር ሳይሆን ጊዜው ሲለወጥ ወደ አገሩ ለመመለስ የሚመኝም አለ፡፡

"ከተመኙ ላይቀር ወንዝነት መመኘት.." በውቀቱ ስዩም::

 የተሰደደው ማሕበረሰብ በራሱ በገዥው ላይ የፈጠረውን ጫና መዘንጋት የለብንም፡፡ ሆኖም ይሄኛው ልማድ የሚበረታታ አለመሆኑን እደግፋለሁ፡፡ በ1985 የተገደሉት ተማሪዎች፤ በ1997 የተሰዉ ዜጎች…ከአድፋጭ ሕዝብ የሚወጡ ስሜቶች አይደሉም፡፡ የ1997ቱን ምርጫ ወቅት ብንመለከት እንኳ ኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያ ስሜቱን በሰላማዊ ተቃውሞ ሲገልጽ የመሪዎቹ አለመግባባት፣ የወያኔ ጭካኔ እና የአሜሪካ እጅ የለውጡን ማዕበል ማስቀልበሳቸው በራስዎ መጽሐፍ የተገለጸ ነው (አገቱኒ ይመስለኛል)፡፡ ይሕ ባሕርይ ከአድፋጭ ሕዝብ የሚገኝ ባሕርይ አይደለም፡፡

ምናልባት ምናልባት የታሰሩ መሪዎችን ለማስፈታት አሁንም ሰልፍ ቢወጣ የሚጠብቀው ጠበንጃ ካነገበ ኃይል ጋር ነው፡፡ እልቂት፡፡ ይሕንን በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡

በግሌ በተደጋጋሚ የገለጽኩት እና የማምነው፤ የኢትዮጵያ ታሪክ በቅርጽም በይዘትም የተቀየረው ከተፈሪ መኮነን ወደ ሥልጣን መምጣት ጀምሮ ነው፤ ይህም በዋነኝነት በውጭ አገራት እርዳታ እና ፍላጎት ወደ ስልጣን መውጣት በሰፊው የተለመደበት ወቅት ነው፤ በመለስም ዜናዊም ደርሷል በመንግስቱ ኃይለማርያምም እንደነበረ አልጠራጠርም፡፡
የኢትዮጵያን ሕዝብ በአንድ ቃል ማድፈጥ ብሎ መወከል ለውይይት የሚዳርግ ጉዳይ ነው፡፡ ፕ/ር መስፍን የኢትዮጵያን ሕዝብ የወቀሱበት በዚህኛው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በሴራና በተንኮል የተሞላ ሕዝብ ባለቤት አድርገው ይስሉታል፡፡ ከዚህ በፊት በአዳፍኔ መጽሐፋቸው ሁለት የሚጋጩ ሐሳቦችን ሲገልጹ ተመልክቻለሁ (ከዚህ በፊት የጻፍኩት ነበር) ይሄውም ምንድነው… “ሐሳብን የመግለጽ ጉዳይ በኢትዮጵያዊያን ምን ይመስላል” የሚለው ነው፡፡ በአንደኛው ሐሳባቸው መድረክ ላይ ወጥቶ ለመናገር የማይቸኩል ሕዝብ የሚሉትን በሌላኛው ደግሞ የመነጋገር እና ሐሳብን ችግር እንዳለብን ይጥቅሳሉ፡፡ ሁለቱን እንዴት አብሮ ማስኬድ ይቻላል?
የኢትዮጵያ ሕዝብ የውስጡን ስሜት ለመግለጽ አገዛዝን እና ጭቆናን እንዲሁም ኢፍትሃዊነትን ለመግለጽ ልምድ አለው፡፡ ቢችል በእረኛ፣ ቢችል በአዝማሪው ባይችል ደግሞ በቅኔ ሰምና ወርቅ ይገልጻል! ፕ/ር አሁንም  ጋር አሁንም የማልስማማበት ትልቁ ጉዳይ ቅኔ የመክሸፍ መነሻችን ነው ማለታቸውን ሲሆን፤ እንደውም ቅኔን በሐሳብ ነጻ የመሆንን ጥማት እና የተዘጋን በር መክፈቻ ቁልፍ ሳይንሳዊ ዘዴ አድርጌ እመለከተዋለሁ! ክርስቶስ በአብዛኛው ለሚጠይቁት መልስ የሚመሰተው በምሳሌ እና በምስጢር ነበር፡፡ ቅኔን አዕምሮ ያለው ብቻ ይከፍተዋልና!

ቅኔ ብርሃን ነው፡፡ ዝግ እይደለም… ጥልቅ ነው… ሰፊ ነው! የነጻነት ባሕርይ ነው! በተዘጋ አለም ውስጥ የመፍጠር ጸጋ ነው፡፡ ይሕንን ሐሳብ ደማሙ ብዕረኛ መንግስቱ ለማ በመጽሐፋቸው በሚገባ ይጠቅሱታል፡፡
2- በእንዘጭ እምቦጭ መጽሐፍ ፈፅሞ የማልስማማባቸው ሁለት ነጥቦች አሉ፡-
ሀ.  በገጽ 77 እንዲህ የሚል ሐሳብ አለ፡-
“አንዱ ሰው ኑሮውን በሙሉ ብቻውን ተሸክሞ ለመኖር ቢፈልግ ተንገዳግዶ ይወድቃል፡፡ የኑሮ ጣጣ ለአዳም ለብቻው በጣም ከባድ መሆኑን በመረዳት እግዚአብሔር ሔዋንን ፈጠረለት፤ ሔዋንም አዳምን ነጻ አወጣችው፤ ለኑሮው ጣጣ ሁሉ ኃላፊነትን ተቀብሎ ራሱን እንዲችል አደረገችው፤ ለራሱ ኑሮ ኃላፊነትን የተሸከመው በሔዋን ግብዣ ዕጸ በለስን በከላ በኋላ ነው፤ ትብብሩ አዳምንና ሔዋንን ከገነት ቢያወጣቸውም ራሳቸውን ችለው እንዲቆሙና የራሳቸውን ገነት እነዲፈጥሩ አደረጋቸው፤ የእግዚአብሔርም ዓላማ ይኸው ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ (ጥቅስ ዘፍጥረት 3/22-23)
(ልብ በሉ “ሔዋንም አዳምን ነጻ አወጣቸው” ይላል)
ይሕንን ገጽ አንብቤ ወደ ቀጣይ ገጽ መሄድ አልቻለኩም…! ለብዙ ቀናት ከራሴ ጋር ሙግት ውስጥ ነበርክሁ፤ ማመን አልቻልኩም፡፡ መቀበልም አዳገተኝ፡፡ ራስ ምታት ለቀቀብኝ፡፡ ጨለመብኝ፡፡ በእውነት ከእኚህ ሰው ይሕ አንደበት ወጣ…? ክርስቶስን፣ ክርስትናን መጽሐፍ ቅዱስን ያውቃሉ ያምናሉም ከምላቸው ሰው ይሕ አባባል እንዴት ወጣ…? ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ ሐቁን መቀበል ነው፡፡ እሳቸው በእርግጥ ይሕንን ብለዋል፡፡ በዚህም ያምናሉ፡፡ ዛሬም ብቻ ሳይሆን ከዚህም በፊት "ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው ሲፈቅድ ወይንስ ሲፈቀድለት?" በተሰኘ መጣጥፍ ይህንን ደግመውታል… ሔዋን ነጻ አውጭ መሆኗን ገልጸውታል!!

 በዚህ ወቅት ከርዕዮት አለሙ ጋር የተደረገው ቃለመጠይቅ በዩቲዩብ ተከታተልኩት) በድጋሚ መጽሐፉን ቀጠልኩት፡፡
በዚሕኛው መጽሐፍም ሆነ በመጣጥፉ ያልጠቀሱት ነገር ቢኖር ከሔዋን ጀርባ የነበረውን የክፉ መንፈስ አባት፤ የዲያቢሎስን ምክር እና ሴራውን ነው፡፡ ከእጸ በለሱ ውስጥ እውቀት ቢገኝም ሞት ያለበት እውቀት ነበርና ዘላለማዊ ባርነትን አስከተለብን! እንጂ ከሔዋን ነጻነት አልተገኘም!!
ይሕም ሔዋን በዲያቢሎስ ተመርታ በሰው ስጋ ላይ ሞትን አወረሰች፡፡ እጸ በለስ (ሞት) የእግዚአብሔር ዓላማ አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር አላማ ሕያው እንድንሆን እንጂ እንድንሞት አልፈጠረንም፡፡ ሞት የፈጣሪ ዓላማ ፈጽሞ አልነበረም፡፡ ከሕግ እንድንተላለፍ አይፈልግም፤ ባርያ ሆነን እንዳንኖር ሕግን አበጀልን/ምርጫን ፈቀደልን እንጂ፤ ዓላማው እጸ በለስ እንድንበላ እና ሕግን እንድንተላለፍ  ብሎም ሔዋን ነጻ እንድታወጣው አልነበረም፡፡ ፈጽሞ ይሕ አላማ ቢኖረው ኖሮ የክርስቶስ በስጋ መምጣትም አላስፈላጊ ነበር፡፡ ምክንያቱም ነጻነታቸውን እና ገነትን የመፍጠር ብቃት ቢኖረን የክርስቶስ መምጣት አላስፈላጊ ይሆን ነበር፡፡ ይህ የፕ/ሩ አባባል ለሄዋን ጠበቃ የቆመ ቢያስመስልም ዋናው ጉዳይ ግን የክፉው መንፈስ አለቃ የዲያቢሎስ ጠበቃ ሆኖ ሰውን ማሳሳት ነው! ፕ/ር ሆይ ለገጽ 77 ንስሃ ይግቡ! ተሳስተውም ከሆነ ደጋግመው ያስቡበት፡፡

(በዚህ ሐሳብ ዙሪያ ከዚህ በፊት አስተያት ለእሳቸው ሰጥቼ ነበር፤  በሌተር ደይስ ሴይንትስ/በየሞርሞን እምነት ተከታዮችም ዘንድ የእግዚአብሔር ዓላማ ይሕ ነው በማለት ቀኑን በሙሉ ስንከራከር ውለን ሳንተማመን ተለያይተናል-)
ከገጽ 77 በኋላ የመጽሐፉ ምክር እና ቁምነገር አዘል ሐሳቦችን እናገኛለን፡፡ ገጽ 77 ያጨለመውን ምናቤን ለመግፈፍ ግን አልተቻለውም፡፡ እውቀት ዲያቢሎሳዊ ሲሆን፣ ትምህርት ሰይጣናዊ ሲሆን….?
ፕ/ር መስፍን አፍቃሬ እውቀት፣ መራሄ እውነት በመሆናቸው አጥብቄ እደግፋቸዋለሁ፡፡ በግልጽ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለመወያየትም ሆነ ለማወያዬት መትጋታቸውንም አደንቅላቸዋለሁ፡፡ ሆኖም የገጽ 77 ጉዳይ አሳምሞኛል፡፡ አጠራጥሮኛል፡፡
ዲያቢሎስ ጠበቃዎቹ በዝተውለታል…! ከዲያቢሎስ የሆነን ትምህርት፤ ለዘመናት ቤተክርስትያን ስትታገለው ነበር፤ ኢትዮጵያም ስትትጋለው ከነበረው ዋነኛ ነገር ጥበብ አጥብቃ እየፈለገች ዲያቢሎሳዊ እንዳይሆን በመስጋት ነበር፡፡ ይህንንም በቀድሞ ነገስታቶቻችን ደብዳቤዎች ውስጥ መመልከት የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ለ.  በገጽ 115 እንዲህ የሚል ሐሳብ አለ፡-
…በውጭ መንግሥታት መሪዎች ዘንድ አጼ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸው ክብር ከሳቸው በኋላ የመጡት ወጠጤዎች በሕልማቸውም ሊያገኙት የማይችሉት ነበር፤ አጼ ኃይለሥላሴ እንደ ንግሥት ኤልሳቤጥ፣ እንደ ቸርችል፣ እንደኬኔዲ፣ እንደ ደጎል ዓይነት የዓለም ታላላቅ ሰዎች ጋር ሲገናኙ ይሰጣቸው የነበረው ትልቅ ክብር የሳቸው የግላቸው ሳይሆን በኢትዮጵያ ጥንታዊነት፣ በነጻነት ታሪክዋና በሃይማኖትዋ ያገኘቸው ነበር፡፡
እኔ በበኩሌ በዚህ ሐሳብ አልስማማም! እነዚህ መሪዎች በስልጣን ላይ እያሉ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ጥንታዊነት እና ሃይማኖተኝነት ቢረዳቸው/ቢገባቸው እና ግድ ቢሰጣቸው ከ1928 ጀምሮ የኢጣልያንን መውረር ከመደገፍ ጀምሮ፤ ንጉሱ ሥልጣናቸ ሲገባደድ… ወታደሩ ቁጥጥር ሲያደርግ… ያሁሉ የሕዝብ እልቂት ሲደርስ እና የደርጉ አለቃ በሰማይ እየበረረ ከአገር ሲወጣ ያገባኛል ይሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ብታሳስባቸው አሁንም የወንበዴዎች ቡድን የሥልጣን መንበሩን ባላመቻቹ ነበር፡፡ የመና የቀረው የእንግሊዙን ስብሰባ እርሶ እና ጎሹ ወልዴ የጮሃችሁለት ነበር፡፡  

ፕ/ር መስፍን ሰለ አለማዊ ማሕበራት፣ ድብቅ አጀንዳዎች እና ሚስጥራዊ ቡድናት አላማ ምን ያሕል ያውቃሉ? ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ብንወያይ ምናልባት ስለእርስዎ ያለኝን ሙሉ ሐሳብ የማውቅበት መንገድን ሊከፍትልኝ ይችላል፡፡ በርዎ ክፍት ስለሆነ እንደተለመደው ማንኳኳቴን ይጠብቁ..!

No comments: