Feb 7, 2013

ግጥሞች


የዘመኑ መስዋዕትነት
ከየት ነው አመጣጤ?
             ከዝንጀሮ አንትሮፖይድ መመረጤ
ወይስ
ከቀዳሚ «ሰብ=7»ዕ ፍጥረት
ከዱዳሌብ አፈር1 -ከኮሬብ እሳት2
ከአዜብ ነፋስ3 - ከናጌብ ውሃ4 ጥምረት፡-
እንደኔ ለኔ
ነባቢነትን5 ፣ልባዊነትን6 ፣ ህያዊነትን7
ተለግሼ -ውበትን ጨርሼ
ባጠፋችው ባጠፋነው ተከስሼ  
የኖርኩ ተመልሼ።
ይህ ከሆነ ማንነቴ
የኋላ መሰረቴ
ሞኝነት ቢመስል ውሸት ቢሉት ከናካቴ
እኔም ቂሉ ላረጋግጥ ብጥር
ለእውነትነቱ ብግር
ፍለጋን ብሞክር
 ላይጨበጥ ከውቂያኖስ
ላይዳሰስ ከህዋ ፋኖስ
ዘላለም መፈለጌን
በልቤ አኖረብኝ ።
ቢነግረኝ ትንሽነቴን
ባውቀው አፈጣጠሬን
አመንኩት ታናሽነቴን
ከሱ ለርሱ የርሱ መሆኔን።
መባከኑን ነፋስን መከተሉን
መቅበዝዙን ተውኩኝ።
ይህ አይደለም ጥያቄዬ አሁን ፡-
ማወቅ ነው  መዋጀት ዘመንን
መኖር ነው በተድላ በመጠን።
የዘመን መስዋዕትነት
ማሸነፍ ነው የስጋን ምኞት
መፈለግ ነው የነፍስን መሻት
ልባዊነት ለህያዊነት። 
                                                                                 ማስታወሻነቱ ፡- ህይወታቸው ላለፈው የግብጹ ጳጳስ አቡነ ሽኖዳ ይሁንልኝ።
                                                        ሰብ-አዊነት፡- ሰብ ማለት ፯ (7) ማለት ሲሆን ከ፯ቱ ባህርያት የተሰራ ማለት ነው።
                                                                                      ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ማራኪ98




ያፈንኩት ከተጻፈ
ያሰብኩት ከተቋፈ
ያመንኩት ከተረፈ
ያፈንኩት ከተጻፈ
አትላስ ተነሳፈፈ
በረሃን ቀዘፈ
ፋኖስ ተቆፈረ ውቅያኖስ ታቀፈ
አማዞን ታጠረ ጠፈሩም ተሰማ
ለቤም ተሞሸረች በሰላም አውድማ
 ሃሴቷን ጋለበች በኤዞጵ ከተማ
አርነቷን ያዘች በገነቷ ማማ።
                            (የመናገር ፣የመጻፍ፣ የማመን መብት ለሚሹ)
                                                                                                                                                               ቋራ 2000
ተጠምቶ የተኛ
መጠማትክን አትይ
ወዳልጋህ ስትሄድ
ፍላጎተህ ቢንር በደርስም ሰማይ ላይ
የነገዋን ስቃይ «ሃንጎቨር» ጸጸቱ
ጥርስ ማፏጨቱ
ጠዋት ጤነኛ ነህ
ስትነቃ ስትታይ
የዛሬ ደስታህ ነገም ቆሞ ይታይ።
                                   (He that goes to bed thirsty, rises healty)                                                                                                     ከሚለው አባባል የተወሰደ
አማርኛ አይዋሽም
Leave him not kill him.
Leave him, not kill him.
እንዳትለቁት ግደሉት
እንዳትለቁት ,ግደሉት።
ላንሴታ
ሆዴ አንቺን ሳይሆን
ጠፈር ተሸክሟል
ሃሳቤም ሳይቋጭ መፍትሄ ሳይፈትል
ከሰሜን ጫፍ ዋልታ ደቡቡን ሲያካልል
መች አገኘ ምላሽ አንቺን የሚመስል
ላንሴታው ቀለለ የሚዛኑ ወለል።




ሲኦል ባዶ ሆነ
ምድርን ለቅቄ
ብጓዝ ብዙ ርቄ
ሠይጣንን አገኘሁ
ሲፈትነኝ አየሁ።
ሲያምር አይ ውበቱ
ያ ጸጋ አንደበቱ
ምክንያት ስሌቱ።
ሊወስደኝ እቤቱ
ለያኖረኝ ከርስቱ
ሲያሳየኝ አንዳፍታ
ሲኦል ሚባል ቦታ።
ብቃኘው ከቅጽበት
ባተኩር ከርቀት
 ማንም ሰው የለበት
እንደውም ለዘበት
ኦና ሆኖ አየሁት።
ምነው ብዬ ብለው
ባዶ ሆኖ ሳየው
ስቆብኝ አረፈው
ለካስ ተቀይሯል
ምድር ሲኦል ሆኗል
ሲኦል ባዶ ቀርቷል።
                              (ከ ዊሊያም ሸክስፔር «hell is empty the devils are here» ከሚለው ሃሳብ የተወሰደ)
ጥቁሩ አንስታይን
                                                                   (የቅጠል ምስጢር)
«ትልቅ» ወንድም ሊቅ የሆነ
መላምት ንጽርርን የመጠነ
ሃይልን ለመፍጠር የባከነ
ባክኖም አልመነነ
መላምት «ባነነ»
E=mc2
 «ትንሽ» ወንድሙም ኖረ
ሊቅ ሳይሆን ደቂቅ የነበረ
የሰው ሀይልን ለማወቅ የቀሰረ
ቀስሮም አልቀረ ቀመረ
E > mc
እንዲህም አለ
“ዝንት አለም ብንጥር
እንኳን ሃይል ልንፈጥር
የራሳችንን ምግብ አዘጋጅተን አንጋግር፤
ፀሀይን አናስቀር-ቅጠልን አንሽር።
As the ultimate source of energy is the Sun, Plants utilize this Energy and transform it to the Living, non-living Things and for US! 



የደሊላ መምጣት
ያኔማ
በጥበብ ተሞለቼ ፤ በውበት ተለክቼ
ብቻየን ሰርቼ
ከዋክብትን ተወርወሩ ስላቸው -ሲወረወሩ
ጨረቃና ጸሃይን አብሩ ስላቸው- ሲያበሩ
ከግብጽ ምድር እስከ ቀይ ባህር
 ፈርኦንን ስደራደር
ባህርን ተከፈል ስለው -ሲከፈል
አለቱን ስፈለፍል
ጎልያድን በጠጠር ስጥል
ሁሉ የኔ ነው ስል
አሁንማ
አንቺ መጥተሽ ለአንዳፍታ
መልክሽ በጨረታ
እይታሽ ሲያመናታ
እንኳንስ ክንዴ ሊበረታ
እንኳንስ ተአምር ላበዛ
አለሁ ቁጭ አንዳልኩ
              ራሴን ሳልገዛ፡
                                                     ( በሱስና በተለያዩ በአለም ምክንታቶች ከቀደመ መንገዳቸው ለተለዩ) ደሊላ በአለም ትመሰላለች የሳምሶንን ሃይል በውበቷ ያስወሰደች ነበረች።
ሳምሶንም እነዲህ ብሎ ለመነ፡- እግዚእብሔር አምላክ ሆይ -እባክህ፡- አስበኝ አምላክ ሆይ፡- ይህን አንድ ጊዜ ብቻ፡-
አባክህ - አበርታኝ ብሎ እግዚአብሔርን ጠራ። ሃይሉንም አገኘ በመጽሐፈ መሳፍንት ፲፮


   ገለጻ ህይወት
ህይወት ወንዝ ናት
የት አንስታ የት እንደምትጥል የማናውቃት
ህይወት ዛቢያም ናት
ጧት ወጥተን
ማታ ገብተን
ይመሻል ይነጋል
በጋ ይከርማል
ይጸዳል ይመርራል
ህይወት እንደ ዑደት
ያንዱ ልደት ለሌላው ሞት
ትኩስም ናት አዲስም ናት
ዛሬን ቆመን የጨበጥናት
                                        አታምልጠን በጃችን ናት።         Today is the best day!



የኔ እንስስና
አሰብኩት
ባይኖር ህግጋቱ
ያምላክ ማንነቱ
ባይጠፋ ካሳቤ
ባይጻፍ በልቤ
ከብቶች ሲሳለቁ
በኔ ስብእና
ውሾቹም ሲበቁ
በኔ እንስስና። 
                                                                      «ኤሊስተር ክራውሊ»
ምጽኣተ ሰላም
ና ጌታ ና ጌታ
ሳትለያየን ማታ
 ምላሳችን ቆርጠህ በልባችን ፈንታ
በሆዳችን አዝነህ  ከነፍሳችን ቦታ
በደላችን ትተህ  ከምህረትህ ለዛ
     ና ጌታ ና ጌታ ኃጥያታችን በዛ።
ካለም ፍጻሜ በኋላ
ተወልጃለሁ
አድጌያለሁ
ያባቴን ክብር አቅልያለሁ
የናቴን አንገት ቀልቻለሁ
በሰው ሰልጣኔ ኋላ ቀርቻለሁ
በባቢሎን ቀንበር ለሞት ተይዣለሁ።
ሰርዶም ሆኜ እበቀላለሁ
ሞቼም ቢሆን እነሳለሁ
ላባቴ ክብር ለምዬ አንገት አሆናለሁ።
                                                       ውጫሌ ጅጅጋ 2005













ጥላዬ ነሽ
በሄድኩበት ለማትጠፊው
ጥላሆነሸ ለተሳልሺው
ቀን ቀን በርተሽ ለከበብሺኝ
ማታ ቆመሽ ለረበሽኝ
ካወቅሽ
ሁሌ ብርሃን ካለበት
አካል ከሌለበት
መንፈስ ከጸናበት
ገነት የገባሁ ለት
የለሽም።
አሊያም
ሁሌ ጨለማ ቤት
ሲኦል ያደርኩ ለት
አትኖሪም
ከጎኔ የለሽም
ዞሬም አላይሽም
ጥለዬ ነሽ ማለፍሽ አይቀርም።
                                                                                (በሳይንስ ፡-ጥላ የሚፈጠረው ብርሃንና ብርሃን የማያስተላለፍ አካል ሲገናኙ ሲሆን ሙሉ ብርሃን ወይንም ሙሉ ጨለማ ብቻቸውን ጥላ አይፈጥሩም) ፍቅር ለከበዳቸው።
ያዳም ምኞት
የትም ውሰዱኝ
ውቅያኖስ አስጥሙኝ
እንጦሮንጦስ ወርውሩኝ
በረሃም ቢቀብሩኝ
ኤልታሬም ቢረሱኝ
አትላስም አክርሙኝ
ሶፍ ኦመር ቢተውኝ
ከየትም ጠፈር ከየትም መሬት
በድኔን ግዴለም ያኑሩት
ብቻ ግን በለሷ ከማትበቅልበት
እባቡ ከማይወርድበት
«ልጅቷ» ብቻ ካለችበት።  
ምን አለፋኝ
                    አይቻልም አሉ
ብቸኝነት ኑሮ
ታሪኩም ከድሮ
ካዳም ተሞክሮ
ብቻውን በኖረ
ሳይችል ስለቀረ
ብቻም ካላማረ
በንቅልፉ ተቸረ
ስለዚህ ልተኛ ።
ታሪኩም ላይጣስ
ላይሻር ዳግመኛ
ቢቸረኝ ልተኛ።

ስኬት
ስኬት ለኔ
አይደለም ውድ መኪና መንዳት
ስኬት ለኔ
አይደለም ውድ ቤት መገንባት
ስኬት ጉዞ እንጂ የለዉምና ልኬት
ስኬት ለኔ አዲስ ነገር ማጣት።
ሁሉም ሆኖልና
ሁሉም ተፈቅዷልና
ሁሉም ግን አይጠቅሙምና
ቢኖረኝ እቁባት
ቢበዛ ጸጋ ሃብት
ቢተርፈኝም እውቀት
ስኬት ለኔ
አዲስ ነገር ማጣት።
                                              
                                              (Success is an endless journey and its provision is happiness)
                                                                                  (ኪሽ አይላንድ ኢራን 2001)
አንኳኩተህ የከፈትክልኝ
በተከበረው በር
ርስቱ የኔ መስሎኝ ነበር
ሲንኳኳ ብሰማ
ጆሮየን ሲያደማ
ማነው የመረኝ?
በምህረት የዳኘኝ?
ከሰው የቆጠረኝ
ከመንጋው የለየኝ?
ጆሮ ዳባ ብልህ
ልቤን ሰብረህ ገብተህ
በዋጋ ሸምተህ
በቃል አሳምነህ
በሞትክበት አክሊል በቀይ ሃር «ተውበህ»
ራት አብረህ በልተህ
የተቆለፈውን የገነት በር ከፍተህ
የሞት በርን ዘጋህ።
                                                                                       ማራኪ 99






ድንጋዮች ይጮሃ «» 1930
እኔም
በብዙ መንገዶች ብሄድም
ለብዙ ሃሳቦች ብማረክም
ለብዙ ስሞች ብሰጥም
ብቻዬን ባልሆንም በብዙ
በሰፊ ብሰፈርም
እነርሱም
አትጓዝ አትመስክር ቢሉ ቢናገሩም
ያ ሁሉ እኔነት
ያ ሁሉ ማንነት
ባይጓዝ ላሳቡ
ባይኖር ለጥበቡ
አለኝ አንድ ጥሪት
የኖረ ማንነት
እንደ ድንጋይ ጸንቶ
በእውነት በርትቶ
ባጠፋው በቀጠፍኩ ቁጥር እየዳኸ
ዘሎ እየጮኸ
ሚነግረኝ አፍ ፈቶ
 ድናጋነቱን ትቶ። 
                                          (ሉቃስ 1930 የቢታንያ ድንጋዮች ይጮሃሉ።)
ዘመን ሲሸሽ
ባልተዘመነበት ዘመን
የመንደሩ ዛፍ ነበርሽ
ዘመናት ሲከንፉ፤ መኪኖች ሲበሩ 
      ቆመሽ የምናይሽ።
ያስርሽ ምላስሽ እንደ ስር በርትቶ
ያቆመሽ ያ ግንድሽ በብል ምስጥ ፋፍቶ
ለስልክ እንጨት ጠቀምሽ።
ዘመን ግን ሲዘምን ጊዜ ሮጦ ቢሸሽ
የፈካው ቀን ጸሃይ በጽልመቱ ቢያመሽ
«ሴል ፎኖች» ሲበዙ እንቺ ቆመሽ ቀረሽ።
                                                                                          አረብ ኤምሬትስ, አቡድሃቢ 2001





 ያልታወቀው የበላይነት
ብሉይ እንደጻፈው
ከጥንት ጀምሮ ለአዳም ጉሮሮ
 የሆንሺው ሮሮ
ለነገስታት  ዘውድ የርስታቸው ጓሮ፤
ሀዲስ እንደ ጻፈው
ድንግሏ ካሰችው።
ነገር ግን ሄዋኔ
አሁንም ጥንት ያኔ
ሳየው ፍጥረትሽን
ሳጤነው ስራሽን
ለዚህ ሁሉ መንገድ መካሪ የሆንሽው
የሰራዊት ሰልፉ ለሆንሺው  መሪያቸው
አኖፊለስ ትንኝ የወባ በሽታን ምታስተላልፈው
የጉንዳን የንቦች ሲታይ ህይወታቸው
ድንጉላው ያዛዥ ነው ለንግስት ሚኖረው።
ሌሎችን ፍጥረታት ዞረን ካየናቸው
ሴቶች በላይ ናቸው።
                                             አሰላ 2004
በላዔ ቀን
ማታ ይሁን ህይወት
ለኔ ለምዋትት
አልጋየ ላይ ሆኜ
አምላኬን ለምኜ
ልቤን እንዲገዛት
ነፍሴን እንዲያነቃት
ለምኜ ለምኜ ተሰምቶ ጸሎቴ
የጠቆረው ፊቴ
ሲፈካ በቤቴ
በፍጥነት በጠዋት
ቢጠፋ በሌሊት
የዛ ሁሉ ጥማት
የደረሰው ጸሎት ሲቀር እንደ ዘበት፡-
ቀን ቀን አየበላሁ የምጾም በሌሊት። 
                                                             ባህር ዳር 2002
የሞት ቅጥረኛ
ሰሞኑን ሕልም አላለምኩም
ምክንያቱም አልተኛሁም
ፍቅርም አልሰጠሁም
ብዕርም አልቀሰርኩም። 
ይህን ሰሞን  ብዙ አሰብኩ
ሞቴን አስታወስኩ
ብሞትስ በማለት ተጨነክሁ።
በፍርሃት ተያዝክሁ
እንዳልሞት ብኖር ሰው ነኝ አልክሁ።
እየኖርኩ እንዳልሞት በጣም ፈራሁ
ሞቼ አንዳልሞት እጅግ ሰጋሁ።                                                           
                                                                            (ሳይሰሩ መኖር እየኖሩ መሞት  ነው)                                                                                                            ሶደሬ 2004
ብርቱ ታካች

አየሁ ገብረ ጉንዳን
በህብረት ሲሰሩ
አንበጣም ያለ ገዥ ባንድነት ሰበርሩ
አንቺም ሸረሪት ድር
ተግባርሽ የሚያምር
ምግባርሽ በምድር
አየሁ ውበትሽን
ሰራሽ ወጥመድሽን
ገነባሽ ቤትሽን።
እባክሽ ተመልከች
እኔን ሰነፍ ዘማች
እኔ ምስኪን ታካች
ተመልከች፡--
እንኳንስ ቤትና
መንገዴም የጠፋች
ወጥመዴም ለሰፋች
እንኳንስ መኖሪያ
ጎጆየም ለከፋች
እባክሽ አስረጂኝ ለኔ ብርቱ ታካች።
አንተ ብርቱ ታካች ወደ ገብረ ጉንዳን ሂድ መንገድወንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን። አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋን በበጋ ታሰናዳለች መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች። ምሳሌ 6፡6-8
      U.A.E.ሳርጃ ኤርፖርት ተርሚናል 2001
የፒራሚድ ጥላ
እኔስ ይገርሙኛል የቀድሞ ታሪኮች
ያባቶቻችን ሃይል የሰሯቸው ቤቶች
የቀየሱት መንገድ የቆሙት ሃውልቶች
የማየው እንስሳ
ባለክንፍ አንበሳ
ፈረሱ ባለክንፍ እነሱ ባለክንፍ
የጠለፉትስ ጥልፍ የቆሙለትም ሰልፍ
እኔስ ይገርመኛል
ከነርሱ ሌላማ «ሌላ ኃይል» ይኖራል።
ከመርሜድ - ሞንስተር
ከፎኒክስ - ቫምፓየር
ዳይኖሰር - ዩኒኮርን
ድራጎን - ከራድዮን
ሃሳባቸው ግሩም ሚስጥራቸው ሁሉም
እኔስ ይገርመኛል
ከነርሱ ሌላማ «ሌላ ኃይል» ይኖራል።
Description: Description: http://upload.wikimedia.org/wikipedia/commons/thumb/4/43/Phoenix-Fabelwesen.jpg/220px-Phoenix-Fabelwesen.jpg የፎኒክስ ወፍ Description: http://upload.wikimedia.org/wikipedia/commons/thumb/7/70/Oftheunicorn.jpg/220px-Oftheunicorn.jpgባለ አንድ ቀንድ ዩኒኮርን(ዋይልድ ኦክስ) በአንዳንድ የመፅሀፍ ቅዱስ ቦታዎች ተጠቅሷል። ዘኁልቅ 23፡22 እግዚአብሔር ከግብፅ አውጥቶአቸዋል ጉልበቱ አንድ ቀንድ እንዳለው ነው። በያቆብ ላይ አስማት የለም በእስራኤልም ላይ ምዋርት የለም-



በቅሎ መነኮሰች
በቅሎ ንኳ መነነች አለም በቃኝ አለች
በሁለት ዘር ተጣምራ ራሷ መከነች
ዘር አላይም ብላ በቅሎ መነኮሰች።

«ለመጻተኛ -ለግዞተኛ- ለጃንደረባ»
ምድር  ነው ስፋትህ
ጠፈር ነው ጥልቀትህ
እንደ ምድር ተጓዝ በጸሃይ ምህዋር
ሳትረሳ ዛቢያህን በራስህ ተሽከርከር
ፍካ እንደ ጸሃይ ሰፊ ነው መንፈስህ
ይዘርጋ በጠፈር ይመንጠቅ ሃሳብህ
ሳያስርህ አባዜ ሳትወድቅም በሰፈር
እንዳትሆን በግዞት በ «ሰው ሃገር - መንደር»።
ሀረር 2005 ከፈረንሳዊው ቤት
ፍሬ አልባ
እረኛው ተርቦ
በመንገዱ ቀርቦ
ሊበላ ቢመጣ
ቅጠል ብቻ እንጂ ፍሬ ከኔ አጣ።
                         ገርጂ ጊዮርጊስ (ማቴ 21፡18) ገላ 5፡22 የመንፈስ ፍሬዎች

                                                                                                                            
      ድህነት፡- ከሳሾችሽ የታሉ?

ቁጣሽን አታስፊ
በሰው አትከፊ
ምንም ብትገፊ
ህመመሽ ቢሰፋ።
ባደባባይ ጥለው እንደ ማርያም ቢያዩሽ
መቅደላዊት ሆነሽ ለፍርድም ቢያቀርቡሽ
የራስን ፍርድ ትተው
በሙሴ በህጉ በድንጋይ ሊወግሩሽ
ለራሳቸው እንጂ አንቺን መች ጠቀሙሽ?
በ«ራሳቸው ሃጥያት» ደብቀው ሊቀብሩሽ።
እንደ እጭ ተንቀሽ
እንደ ነውር ቢያዩሽ
አትፍረጂባቸው ይህን ላስታውስሽ፡-
ሁሉም አንድ አይደለም
በፍርድም በውነትም ሚመሳሰል የለም
ብቻ ግን ይኖራል መሪ ፈራጅ ዳኛ
የልብን ተረድቶ መላሽ ቀጥተኛ
የናዝሬቱ 'የሱስ መጣ ሰላምተኛ
ሊፈውስ ቁስልሽን
ሊሰማ ህመምሽን
ጠማማ ቀኖችን ሊደመስስልሽ
የራሱ ለያደርግሽ ፥ እንደ ማንነትሽ
ይቅርታን ሊቸርሽ
በፍቅር ሊያድንሽ። ብቻ ግን ተመለሽ
                                                                                   
                                                                   ሃሰብ፡- መፅሃፍ ቅዱስ ። ውርስ ትርጉም ከአሰፋ አለሙ Manacled የግጥም መድብል;-salvation
                                                           ከአትላስ- ቦሌ መድሃኒያለም።



ነፋስን መከተል
አንብበው አንብበው ባዶ ለሚሆኑ
በ-እውቀት ተሞልተው «ኦና» ለሚዘግኑ
ጥንት ዓለም ዝንት ዓለም ለሚንከራተቱ
በነፋስ መንገድ ስር ሁሌ ሚታክቱ
እወቀት ፍቅር አንጂ
ህይወት ፍቅር እንጂ
ሌላም አይደል አ-ት-እ-ሳ-ቱ።
                                                                                                        
                            
                                                   «ከተማው መብራት»
የምን ብልጭ ድርግም
ምንድን ነው ብርሃን የደመቀ ቀለም
ቢሆን በፈረቃ መብራት በየተራ
                      «ፋየር ወርክ» ቢንጫጫ አብሪ ትል ቢያበራ
ከዋክብት ቢጠፉ ጨረቃ ብትቀላ
ጸሀይም ብትደማ አለም ባያበራ
ካልሆንኩኝ ብርሃን ዘላለም በመቅደስ
«ልቤ ካላበራች» እሱን ስታወድስ
ያኔ ጨለመብኝ ለ«መብራቱ» ላልቅስ።                                                                                                                                                                             (ሁሉንም የሚገዛ ጌታ አምላክና በጉ መቅደስዋ ናቸውና መቅደስ በእርሷም ዘንድ አላየሁም። ለከተማይቱም የእግዚአብሔር ክብር ስለሚያበራላት መብራትዋም በጉ ስለሆነ፡- ፀሐይ ወይም ጨረቃ እንዲያበሩላት አያስፈልጓትም ነበር።) ዮሐንስ ራዕይ 21፡22-23













አዲሲቷ ኢየሩሳሌም

በምድር አሜኬላ፤
በአለም ከንቱ ተድላ፡-
በባቢሎን አጥር፤
ካመፃዋ ቅጥር -
ከገባሽ መንፈሴ፤
ካለሽ አንቺ ነፍሴ፡-
ውጪ ከመንደሯ፤
ተለይ ከምግባሯ
αΩ αΩ αΩ αΩ αΩ
 መጣች ተሸልማ፤
ወረደች ሙሽራ በቀደመው ክብሯ።
እንባዬን ልታብስ
ኀዘኔን ጩኸቴን ስቃዬን ልታድስ፡-
«አልፋና ኦሜጋ» የምንጭ ውሃ ሲፈስ።                         
                                                   ራዕዬ ዮሐንስ ፳፩፡ ፩-፯ (21፡1-7)

                                 

















                               በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጎዱም አያጠፉምም ፤ ወኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና። ኢሳ ፲፩፡፱







ቅድስቲቱም ከተማ አዲሲቷ ኢየሪሳሌም፥ ለባልዋ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወር አየሁ፡-…

No comments: