Mar 20, 2022

<የዘውግ ፖለቲካ ሥረ መሰረቶች>

(አጭር የመፅሐፍ ዳሰሳ)

•የመፅሐፉ ርእሥ:- የዘውግ ፖለቲካ ሥረ መሰረቶች

•ፀሐፊ :- መስከረም አበራ::

•የገፅ ብዛት 424: 
•ማንኩሳ ማተሚያ ቤት: 
•ዋና አከፋፋይ ጦቢያ:: 
•2013 ዓ.ም :: 



[መግቢያ::]

የጥናት ፅሑፍ፣ ንድፈ ሃሳባዊ እይታ ነው:: በችኮላ የተፃፈ አይደለም:: ብዙ ተደክሞበታል:: ወደ 400 የሚደርሱ የኅዳግ መዘክሮች ለዚህ testimonials (ምስክሮች) ናቸው:: 

የማንነትን ትርጉም ለመፈተሽ ምዕራፍ አንድ የዓለምአቀፍ አጥኚዎችን የጥናት ውጤቶቻቸውን እና መዛግብቶቻቸውን ከሥረ መሰረቱ ዋቢ አድርጓል:: 

ዘውግ፣ ኃይማኖት፣ መደብ፣ ባሕል  በአብዛኛው የማንነትን ብያኔዎችን ሲያግዙ እንደሚስተዋሉም እስከ ገፅ 62 ድረስ እናነባለን:: 

ፀሐፊዋ በእውቀት ጥማት ሥር በጥናት እና ምርምር እንዲሁም ለንባብ ባላት ብርቱ ውስጣዊ  መግፍኤ የተለያዩ ድንጋጌዎችን ወደ ሳይንሳዊ መዛግብት ማማተሯ በጉልህ የሚታይ ነው:: ለአንባቢም የሚበጀው ከስሜት የፀዳን የንድፈ ሃሳብ አረዳድ ታጎናፅፍለታለች:: ይህም ለአገራችን የወደፊት የተግባቦት ፖለቲካ ትርጓሜ እንደ በጎ አሻራ ( legacy) የሚሆን ነው:: በትውልድ ተስፋ የሚጣልበት በነፃነት የዜጎች ምሳሌ ነው:: 

[ጭብጥ::]

የዘውግ ሳይናዊ ትርጉሞች:- የሚለው ክፍል በገፅ 69  <<ሰዎች በተመሳሳይ ዘውግ ናቸው ማለት በጋርዮሽ የሚጠሩበት ሥያሜ አለ ማለት ነው>> ለእነዚህም ከአንድ ዘር ሐረግ የሚመጡ አፈታሪክ ያስፈልገዋቻል:: 

ለስምምነት እጅግ የሚያዳግተው ይህ አፈ ታሪክ ከእውነትነቱ ይልቅ ወደ ልብ ወለድነቱ የሚያመዝን በመሆኑ ከሳይንሳዊ ብያኔ የሚያርቀን እንደሆነ ትጠቅሳለች::

ምናልባት ለወደፊት የሚመጣው ተከታታይ ትውልድ ሳይንስን እንደ መነሻ መግባቢያ አውድ የሚወስዱት ከሆነ የዘር ሐረግን የሚፈትሹ የማስረጃ ውጤቶችን በመመልከት የዘውግን ጡዘት ሊያበርዱበት የሚችሉ እንደሚሆን አመላካች ይመስላል:: እንጂ አሁን ባለው የዘውግ አጣብቂኝ አመለካከት እውነት ኹሉ በዘውግ ልኂቃን ንግርቶች ተወስኗል:: Futile የመዳረቅ ክፍል እንጂ ተቀምጦ ለመደራደር አዳጋች ነው:: 

ማንነቶች ትገልፀው ወደ ተልያዬየእርከን ደረጃ ሲደርሱ በትኩረት የዘውግ ማንነት ጡዘት፣  ከቋንቋ ባህል እና ምጣኔ ሀብታዊ ሰልፍ ጋር ሲያዛመድ የዘውግ ፖለቲካን ይዞ ብቅ ያላል:: ከገፅ 84 ጀምሮ የዘውግ ፖለቲካ ጅማሮ በአፍሪቃ ርዕስ በስፋት ይከተላል:: 

በቡድን የሚኖር ማህበረሰብ እንዳለ ኹሉ በግለሰብ ልእልና ላይ የዳበረ እሴት ያለው ማህበረሰብ አይጠፋምና ፀሐፊዋ በዚህ ደረጃ የሁለቱን ማንነቶች አመጣጥኖ ማክበር እንዳለብን እና አንዱን ከሌላው ነጣጥሎ መሄድ እንደሌለብን ከጅምሩ ትመክራለች:: ገፅ 84::

ለአፍሪቃ የዘውግ ማንነት ፖለቲካዊ ይዘት የቅኝ ገዥዎች ድርሻ ሰፊ እንደሆነ ታትታለች:: በተለይ በግልፅ እንደሚታወቀው ቅኝ ገዥዎች በአፍሪቃ ምድር ላይ የከተማ መስፋፋትን እና የመደብ ቅርፅን በሚያሳልጡበት ወቅት አስቀድመው የበየኗቸውን የዘውግ ማንነቶች ይዞ ለመቀጠል እንደተገደዱም (እንድስገደዱ?)  ትናገራለች:: ይህንን ጉዳይ የቤተዘመድ መረብ ስትል በገፅ 86 ላይ እናነበዋለን::  በመፅሐፉ ዳሳሽ ምልከታ ምናልባት መረቡ እንደ ወጥመድ የሚተረጎም ሳይሆን አይቀረም:: 

በተፈጥሮ ሊካድ የማይችለው ዘውጌ ማንነት ልቦለዳዊ ትርክቶች፣ በጥቅም እና በቅኝ ገዥዎች መስመር የተበየነው <<ዘውጋዊ ማንነት>> ወደ ትምክህተኝነት እና ዋና አሳሳቢ ወደ ሆነው ብሄረተኝነት ትርጓሜ ያመራናል:: 

ምንም እንኳ የሥነ ፍጥረት ሳይንስ (biology) በሰው ልጆች መካከል የበየነው መከፋፈል የሰው ልጅን አንዲገዳደል ፣ እንዲጋጭ እንዲገለል ኢፍትሀዊነትንም እንዲያስከትል የሚያስችል ትርጓሜን እንደማያመጣ በገፅ 94 ተገልጿል:: 

እንደ አጠቃላይ <<ብሔርተኝነት>> በምድር ላይ  ያለው ዕድሜ ከዘመናዊው የዓለም ታሪክ ጋር መሳ ነው በሚል  ይወሰዳል::  ቃሉ በኢትዮጵያ ምናልባትም የሚታወቀው ግለሰቦች የመጡበትን የትውልድ ሐረግ ማለትም ዘብሄረ ዘጌ ፣ ዘብሄረ ቡልጋ ፣ ዘብሄረ ጎንደር በሚል ሲጠቀስ የሚስተዋለው ትርጓሜ ብሄር ከመነሻው natio ከሚለው የላቲን ቃል በቀጥታ ትርጉሙ የትውልድ ቦታ እንደሚል እንገነዘባለን:: 

ይህ እሳቤ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከነገረ መንግስት nation state ምስረታ ጋር ወደ ሰው ልጅ ታሪክምሆነ የእውቀት ቋት መግባቱን እናያልን:: ምናልባትም የብሄር ትርጓሜ እና የአውድ አገላለፅ ከእኛ አገር ተጨባጭ ታሪካዊ ሂደት አንፃር ሰፊ ትንታኔን እና መግባባትን የሚጠይቅ ነው:: 

ፕ/ር መስፍን በዚህ ዙርያ የኢትዮጵያ ታሪክ ምሁራንን አጥብቀው የሚሞግቱብት ርእሰ ጉዳይ ነው:: state, empire, nation እና መሰል ቃላት ወደ ነባራዊው ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ትርጓሜዎች ሲታዩ <<አቻ ፍቺ>> በትርጉም ደረጃ ስለሚፈልጉ ነው:: 

አውሮጳውያን በበየኑት የእነዚህ ቃላት ትርጓሜ መሰረት ከሩቅ ምስራቅ እና አፍሪቃ የረዥም ታሪክ ቁርኝት አንፃር እንዴት ይተያያሉ? የሚለው ጥልቅ ምርምን የሚጠይቅ ነው:: መስከረም ምናልባትም ይሄንን ጉዳይ በምን መልኩ እንደተመለከተችው ከገፅ98 ጀምሮ እስከ ገፅ 110 የነገዳዊነት ትርጉም ርእስ  ድረስ የምንዳስሰው ይሆናል::

እንደ ፀሐፊዋ ዝርዝር ሂደት በእንግሊዞች እና ፈረንስዮች ዲያሌክቲካዊ መርህ መስፈርት እንግሊዝ የነገረ መንግስት እሳቤ ጀማሪ ስትኾን፣ 

ፈረንሳይ የብሄርተኝነት እሳቤ አመንጭ ናት(ገፅ 99) :: በመፅሐፉ ዳሰሳ መሰረት የthesis እና antithesis ዓለም አቀፋዊ ደባ በዝርዝር ሊጠና የሚገባው ነው::

ከፈረንሳይ አብዮት ማግስት የነገረ መንግስት ትርጓሜን በብሔር እና መንግሥት በሚል አንጓ ተከፈለ:: በዚህ ርእስ ውስጥ የምናገኜው የብሔርን ፖለቲካዊ ፅንሰ ሃሳብ አጠቃላይ ውልደት ሲሆን በአንድ ነገረ- መንግስት የሚኖሩ ህዝቦችን የተለያዬ ባህል ያላቸውን ህዝቦች የሚገልፅ ቃል ነው:: 

እነዚህ ህዝቦች ፖለቲካዊ ማንነት ካለው "መንግሥት" ከሚባለው አካል ጋር ቁርኝት እንደሚፈጥሩ ተቀምጧል:: በመንግስቱና በብሔሩ መካከል ያለው ቁርኝት ብሄራዊ ተብሎ የሚገለፀውን ማንነቱን ከባህላዊ ልዩነቱ ሳያስቀደም በነገረ መንግስቱ ውስጥ የሚኖረው ትርጉም የብሄርተኝነቱን እሳቤ <<የሲቪክ ብሄርተኝነት> ስያሜን ያሰጠዋል::

እንደ መስከረም መፅሐፍ አገላለፅ የሲቪክ ብሄርተኝነት የመጀመርያ ቢሆንም በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ የተለዬ ቋንቋን መናገር፣ ወይንም የተለያየ ባህልን ከሚያስተሳስረው የዘመናችን የብሔርተኝነት ጭብጥ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ያሳያል:: ይህ ነጥብ በእጅጉ ውይይት የሚያስፈልገው እና በትርጉም ደረጃ ከአገራችን ታሪካዊና አሁናዊ እይታ ጋር ሊፈተሽ የሚገባው ያልነው ነው:: ምናልባትም ይህንን አጥንቶ አቅጣጫ ያስቀመጠ የልኂቅ ስብስብ ለቀጣዩዋ ኢትዮጵያ እጣፈንታ የበኩሉን የሚወጣ ባለውለታ ነው:: 

በቋንቋ እና በባህል የሚተረጎመው የዘውግ ብሄርተኝነት ከሲቪክ ብሔርተኝነት በተለዬ አንድ አይነት የሚናገሩ ህዝቦች ብሔር/ ዘውግ ተብለው መጠራት ጀመሩ:: እነዚህ ብሔሮች በጀርመን ምሁራን አመለካከት መሰረት ሃገርን የሚመሰርቱት ብሄረሰቦች ወይንም ዘውጎች ሰው ሰራሽ ሳይሆኑ ተፈጥሮአዊና መሰረታዊ ናቸው ብለው ያትታሉ:: እዚህ ላይ አሻሚ የሆነው የብሔር ቃል ወደ ብሔረሰብ አቻ ፍቺው ሆኖ መቅረቡ በጥንቃቄ ሊፈተሽ የሚገባው ነው:: ብሔር ምንድን ነው? ብሔረሰብስ? 

በገፅ 100 ላይ የምናገኜው የሲቪክ ብሔርተኝነት ቃል በ102 ገፅ ላይ "በሲቪክ ብሄረተኝነት" ቃል መተካቱ የትየባ ስህተት ወይንስ ብሄርተኝነት/ብሄረተኝነት ጋር ተመሳሳይ ትርጉም ነው የሚለው ግልፅ አይደለም::

ብሔር፣ ብሔርተኝነት ከዘውግ ስሜት ጋር ብቻ ታይቶ የሚቀርብ ባለመሆኑ ከፍተኛ ትኩረት እና ምርምርን የሚጠይቀው ለምንድን ነው ቢባል በሃገረ መንግስት ምስረታ ሂደት ውስጥ የራስን ሪፐብሊክ እስከ መመስረትን የሚያልምፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በመያዙ እንደሆነ በመፅሐፉ በገፅ 103 ላይ ይገኛል:: ብሔርና ብሔረተኝነት የሕልውና ጉዳይ ነው:: 

በአጠቃላይ ትንታኔ የብሔር ፅንሰ ሃሳብ ከመነሻው ጋር የሚስተዋለው የአገራችን ብሔር ትርጉም የአሮጳውያኑን የብሔር መስፈርት አሟልቷል ለማለት እንደሚያዳግት ትቀሳለች:: ይህ ድምዳሜ ስምምነትን ባላስቀመጠበት ሁኔታ የሃገራችን የበላይ ህግ ግን ያለ ርህራሄ መዝግቦታል:: ለዘውግ የሚቀርበው የህገመንግስቱ ትርጓሜ የማደናገርያ አካሄድ ምንጩ መሆኑን እናነባለን:: ይህ አካሄድ ኢትዮጵያን ወዳልነበረች ሃገርነት የመቀየር ኃይል እንዳለውም በዝርዝር ተቀምጧል:: ከላይ እንደጠቀስነው ይህ ኃይል አስቀድሞ በእንግሊዞች ሲታገዝ መቆየቱንም መዘንጋት የለብንም:: 

በአገራችን በሶስት ዘውግ ብሔርተኛ ልኂቃን(ኦሮሞ፣  ሱሜሊ እና ትግሬ) ዘንድ የሚቀነቀነው የመገንጠል ፍላጎት መኖሩን የምትጠቅሰው መስከረም ሁሉንም ዘውጎች ብሔር ብሎ የሚገልፀው ህገመንግስት ለምን እንደሆነ እንመርመር ትለናለች:: ጥናት አስፈላጊ መሆኑን የምታሰምረው መስከረም ዘውጎች በሕገመንግስታዊ አንቀፅ ብሔር ተብለው የመገንጠልን ለሃገረ መንግስቱ ቀቢፀ ተስፋ ማነገባቸው ሥሕተት ነው:: ገፅ 109::

በአሁኑ ሰኣት ያሉ የኢትዮጵያ ዘውጎች ወደ ፅንፉ የመገንጠል መውጪያ በር አለመታተራቸው (አለማናተራቸው) ከመነሻው ዘውጎችን በብሄር በይኖ ተገንጠሉ መባሉ የሥህተቶች ሁሉ ቁንጮ ማሳያ መሆኑንም ትሞግታለች- መስከረም::

ከዚህ ገፅ ቀጥሎም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬውን አጠቃላይ መዋቅራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስረ መሰረቱን ከአማራ ከኦርቶዶክ ቤተክርትስያን እና ከአማርኛ ቋንቋ ጋር የሚተሳሰረውን ትርክት በማስረጃዎች እና በታሪካዊ ክስተቶች እያጣቀሰች የግል እሳቤዎቿን ታጋራናለች:: 

የኢትዮጵያ ህገመንግስትም ይሁን መሰረቱ የሆኑለት የትግሬ ዘውግ ልኂቃንን ጨምሮ የኦሮሞ እና የሱማሊ ዘውግ ብሄርተኞች ከአንድ ዘውግ ጋር ባላቸው የትርጉም አይን ይመሳሰላሉ:: ምንም እንኳ የፖለቲካ አላማ በየዘመኑ የፖለቲካ ዘይቤ የሚለያይ መሆኑ ቢታወቅም (ገፅ 294) የኢትዮጵያ ነባራዊ የታሪክ ሂደትን የአንድ ዘውግ ተኮር ይዘትን ይዞ የተንከባለለ ሃገረ መንግስት እንዳልሆነ ትዘረዝራለች:: 

የአገዎች ሥርወ መንግስት በወንድማማቾቹ በላሊበላ እና በሃርቤ መካከል የተደረገው የሥልጣን ሽኩቻ ላሊበላ አማሮችን ይዞ በመሄድ ድል እንደነሳና ነገረ መንግስቱ ዘውግ ተኮር አለመሆኑን እንደ አባሪ ትጠቅስልናለች:: 

አማርኛም የቤተ መንግስት ቋንቋነቱን በአገዎች አፀና እንጂ በዘውጉ ልኂቃን ፍላጎት በጀት ተበጅቶለት እንዳልተስፋፋ ለማሳዬት ብዙ ርቀት ሄዳለች:: በተለይ ሚስዮናዊያን አማርኛን እንዲስፋፋ ከግእዝ በተቃራኒው የካቶሊክ እምነት በአማርኛ እንዲሰበክ በመሆኑ አማርኛን የአገሪቱ ዘውጎች መግባቢያ ቋንቅ አድርጎ እንደወሰደው ትሞግታለች:: በቅርብ ዓመታት የሚታዩ የብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎችንም ትላንት ከምናስታውሳቸው ፖለቲካዊ ቀውሶች ጋር እያዛመደች የምፍትኄውን ጎዳና ትቀይስልናለች::

[መውጫ::]

የመዳኛ መንገዱንም በአጭር ገለፃ ትደመድማለች:: 

የዘውግ ብሄርተኝነትን የሚቃወሙ ግለሰቦችም ይሁኑ ይድኑበት ዘንድ በዚህ መፅሐፍ ዙርያ ብዙ ውይይት ሊያደርጉ  እንደሚገባቸው እሙን ነው:: ይህ የተሰማው ግለሰብም ይሁን - ቡድን እንደ ዘውግ ፖለቲካ ስረ-መሰረቶች ዓይነት  የሃሳብን ጉልበት ተጠቅሞ በመፅሐፍ መልክ የበኩሉን አሻራ ይወጣል:: 

ከየሱፍ ያሲን <<ኢትዮጵያዊነት አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት >> መፅሐፍ ቀጥሎ ደጋግሜ ለማንበብ የምመርጠው  መፅሐፍ ነው::   

ኢትዮጵያችን ቸር ይግጠማት:: 

መልካም ንባብ::

ተስፋ በላይነህ:: 
መጋቢት 2013