Aug 29, 2017

Habtamu Alebachew 4th book_ Talaku_Tekarno


የቄሳር መንፈስ “በታላቁ ተቃርኖ” መጽሐፍ፡፡

ሀብታሙ አለባቸው ዛሬም ብዕሩን እና ብራናውን አጣምሮ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ቅኝት ለመቃኘት ሞክሯል፡፡  ቅኝት በመቃኘት ይታዘዛል፡፡ ጥሩ ቃኚ ጥሩ ዜማን እንደሚያወጣ እሙን ነው፡፡ ሀብታሙ በቅኝቱ ጥሩ ዜማን አውጥቶ ይሆን አይሆን እንደ አዳማጮቹ የሚወሰን ይሆናል፡፡ በበኩሌ ያልተደፈረውን የቤተመንግስት ጓዳ፣ ያልተደፈረውን የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እና ያልተለመደውን የኢህአፓ ዘመን ድብብቆሽ ባለፉት ስራዎቹ ለመቃኘት መሞከሩን ወድጄለታለሁ፤ የነበሩኝን አስተያዬቶችም በወቅቱ የሰጠኋቸው አጭር ጽሑፎች በቂ ይመስሉኛል፡፡

ዛሬ በወፍ በረር መቃረም የፈለግኩት “ታላቁ ተቃርኖ” የተሰኘውን ስራውን ነው፡፡ በእርግጥ ይሕንን መጽሐፍ ማኄስም ሆነ ጥናታዊ ዳሰሳ ለማድረግ አቅሉም አቅሙም ኖሮኝ አይደለም፡፡ ሆኖም እንደ አንባቢ እና ባገር ጉዳይ ላይ ለመሳተፍ/ለመጠየቅ/ እንዲሁም የግል አስተያዬትን ከመስጠት የተፈጥሮ መብትና/ግዴታ ከመሆን አንጻር ስለመጽሐፉ ጥቅል ሐሳብ የተሰማኝን ለመተው ነው፡፡

በበኩሌ የምስማማበት ጉዳይ (ከሌሎች ጋር አለመስማማት እንዳለ ሆኖ) የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ችግር ከአንድ ነጠላ መንግስት እና “ሬዥም” ጋር ማያያዙ የውድቀታችን መነሻ ነጥብ ነው፡፡

በዚህም አግባብ ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያ ታሪክ ማጠንጠኛ “የትክተት ነጥብ” ሆነው ሲወሰዱ፤ ልንወጣው ወደማንችልበት እና ሸክማችንን የሚያበዙ ጋሬጣዎችን ይሰበሰባሉ፡፡ ሌላኛው አስከፊ ችግር ጋሬጣዎች መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን ጋሬጣውን የምናስወግድበት እሾኩ ላይ ይሆናል፡፡

ሀብታሙ አለባቸው የዚህ ምሳሌ ማሳያ ሆኖ የሚቀርብ ይመስለኛል፡፡ በመጽሐፉ ሽፋን የመሃል ኢትዮጵያን እና የሰሜን ጫፍ ድንበርን እንደ መነሻ በማድረግ “ታላቁ ተቃርኖ”ን በማመልከት፤ “አጼ ምኒልክ ሠርተውት ያለፉት ነገር በትክክል ምንድን ነው?” ሲል አጼ ሚኒልክን ምስል አስቀምጦ እናየዋለን፡፡ በእርሱ አተያይ እና ጥልቅ ምርምር የኢትዮጵያ መሰረታዊ ችግር የተገለጸው ወይንም የተጠቀለለው በአጼ ሚኒሊክ ዘመነ መንግስጥ እና ከዚህ ወዲህ ነው ማለት ነው፡፡

ይህን መሰል የምሁራን ቅኝት (ቅዠት ላለማለት)፤ ከ1960ዎቹ የምዕራባዊያን እና የምስራቁ ዓለም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ውዥንብር በፈጠራቸው አስተሳሰቦች(የያ ትውልድ አባላት)  ኢትዮጵያን ቀርጸው (የፈጠሯት እስኪመስል ድረስ) የዘመናችንን ትኩሳት እና የወደፊት እጣፈንታችን በየመቶ አመት ታሪክ ብሂል ውስጥ ይቀብረናል፡፡ ይሕ በራሱ የታላቁ ተቃርኖ አንኳር መነሻ ነው፡፡ (የኢትዮጵያ የመቶ አመት ታሪክ ክርክር ሐሳብ በእነ ዮሐንስ አድማሱ፣ እሸቱ ጮሌ፤ ፈቃደ አዘዘ እና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ተችተው የተነሱበትን ዘመን ያስታውሷል)

የፖለቲካ ድንበር እና የአገርን ማስተዳደር ቅርጽ መልኩን ቀይሮ የምዕራባዊያን ጣልቃ ገብነት በተስፋፋበት ዘመን ላይ ቆመን፤ መፍትኄም ይሁን የጥናታችንን ዛቢያ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ብቻ ሆነን ስናንዣብብ “የታላቁ ተቃርኖ” መነሻም መድረሻም እንደሚሆን አስባለሁ፡፡

“የኤርትራ” ችግር እና “የደቡብ ቅራኔ” በምኒልክ መጀመሩን እንደ ፖለቲካዊ ትንታኔ አድርጎ መነሳት የሃብታሙ አለባቸው እና የመሰሎቹ የፖለቲካ ልሂቃን ውድቀት መሆኑ የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ (ግል እይታዬ) ነው፡፡

የዳዕማት ሥልጣኔ አንድምታው ምንድን ነው? የአሁኑ ትውልድ ምን ያሕል ያውቀዋል? የአክሱምን ሥልጣኔ ማን አቆመው?  ማን መራው? ማን ማን ገበረ? የትኛው ሕዝብ በየትኛው ህዝብ ትስስሩን ፈጠረ? በምን መንገድ ከየት ወደዬት? ሕዝብ በምን ተለያዬ?  በምን ተሳሰረ? ፤

የዛጉዌ ሥልጣኔ ከየት የት ይደርስ ነበር? የውጭው ዓለም በወቅቱ በምን መልኩ ይረዱት ነበር? በዚህ ወቅት የደቡቡ ይዞታ በምን መልኩ ይተሳሰር ይተዳደር ነበር?

የመካከለኛው ዘመን የይኩኖ አምላክ መንግሥት ከደቡቡ ጋር የነበረው ትስስር? የሸዋ ነገሥታት እና ቀሪው ማሕበረሰብ የነበራቸው ገጽ፤ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ ሶማሌ ድንበር ድረስ ሄደው የገነቡት ልማት፣ ጥፋት፣ የትዳርም ይሁን የማስገበር/የመገበር ታሪካችን፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እስከ ቀይ ባሕር እና ህንድ ውቅያኖስ ወይንም የአፍሪካ ቀንድ ጫፍ መታዬት፤ የልብነ ድንግል ንጉሳዊ ስም አጠራር በራሱ የሚሰጠው ትርጓሜ፤ የምስራቁ ዘመቻ ወደ ሰሜን ያመጣው ለውጥ፤  ለምላሹም የተሰጠው አጸፋ (አሉታዊም አዎንታዊም የአገር ግንባታ ሂደት..)

የእነሰርጸድንግል ታሪክ፤ የጎንደር ነገሥታት ከደቡቡ በተለይም ከኦሮሞው ሕዝብ ጋር የነበራቸው ትስስር፤ የየጁ መሳፍንት በጎንደር ዘመን የነበራቸው ሚና፣ ኦሮምኛ በጎንደር የነበረው ቦታ፤ ባሕረነጋሽ/ኤርትራ የነበረችበት ሁኔታ(ይዞታ)፤

የአጼ ቴዎድሮስ አነሳስ፣ ዘመኑ የጠየቀው መስፋፋት ምክንያት፤ ለምን አጼ ቴዎድሮስ?፤ በዘመኑ የነበረው የግዛት አወሳሰን እንዴት ይገለጽ ነበር?፤ ነው ወይንስ “አቢሲኒያ”ን ቀርጸን ማነብነብ ይቀልለናል? …

(እዚህ ላይ ትልቅ የሚዘነጋ ሐሳብ ይታየኛል፤ ይሄውም የአጼ ቴዎድሮስ ዜና መዋዕል ከታቢ እና ምጡቅ ግለሰብ አለቃ ዘነብ የኦሮምኛን ቋንቋ ማጥናታቸው፤ ብሎም መጽሐፍ ቅዱስን በኦሮምኛ ለመተርጎም ማሰባቸው፤ አስበውም መተግበራቸው በምን መልኩ የሚታይ ሐሳብ ነው?)

በአጼ ዮሐንስ ዘመን መባቻ ላይ የተደረገው የባዕዳን ወረራ እና ተጽዕኖ፤ ሃይማኖታዊ ርዕዮተ ዓለም ለምን?  የባሕረ ነጋሽስ ይዞታ፤ የሂወት ውል፤ የምዕራባዊያን ቅኝ ግዛት ዘመቻ፤ የፖለቲካ አስተሳብ ዘመቻ፤ የመንግሥታት ትብብር ሐሳብ፤ የዘመናዊነት ትርጓሜ፤ … ወዘተ

እንዲህ እንዲህ እያልን ጥናታዊ ምርምር፤ የታሪክ ጥናት የሚጠይቀውን መነጽር እየተጠቀመን “ታላቁ ተቃርኖ” በሚል ሐሳብ እያላወስን፤ የኢትዮጵያን ችግር ነቅሰን እናውጣ ቢባል አዕምሮየንም ሆነ ስሜቴን የሚገዛ ጭብጥ የማገኝ ይመስለኛል፡፡

ዋናው ሀብታሙ አለባቸውን የምሞግትበት ነጥብም ይሄው ነው፤ ከእዘኒህ ጭብጦች ውስጥ ነበር የአጼ ምኒልክን ቦታ ፈልቅቀን በማውጣት ወዳለንበት ደረጃ ደርሰን ተቃርኖንም ይሁን የግጭት መንስኤዎችን አልያም ስኬቶችን ልንገልጽ የምንገደደው፡፡ ከአንድ ትልቅ ሰፌድ ውስጥ አንዱን ሰንደዶ አውጥቶ የሰፌዱን ሕልውና አድርጎ መውሰድ በሰፌዱ እና በሌሎች ሰንደዶዎች ላይ የሚሰራ ደባ ሆኖ መታሰቡ አይቀሬ ነው!

ኤርትራ ከምኒልክ በፊት የኢትዮጵያ ግዛት የሆነችበት እና ያልሆነችበት ጊዜ በታሪክ ተፈትሾ ሲጠና፤ የደቡቡን ይዞታ እና ትስስር ቅድመ ታሪክ ጥናት ሳናደርግ፤ ምኒልክን መነሻም መድረሻም ማድረጉ ትልቅ የታሪክ ሸፍጥ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ምኒልክ ሳይፈጠሩ ኤርትራ የነበረች እና ለበርካታ ነገስታት የድልም የውድቀትም የስኬትም የክሽትም ማጠንጠኛ ሆኖ የዘለቀች በመሆኗ፤ “ኤርትራ” “ኤርትራ” የምንለው የምዕራባዊያኑ እርኩስ መንፈስ ወርሶን ለመግባቢያነት የምንጠቀምበት የቦታ ስም ብቻ ሳይሆን ለውድቀታችን የተበተብነው የቄሳሩ መንፈስ አዚም /አዙሪት/  ነው፡፡ ደቡቡንም በመቶ አመት ውስጥ የተፈጠረ መልክዓምድራዊ ይዞታ እስኪመስል ድረስ፤  ስለ ሺሕ አመታት የኢትዮጵያ ታሪክ ሂደት እያወራን ቦታና የሕብረተሰብን ፍልሰት ሳናጤን፤ የጥንቱን ስያሜ በዘመነኛ “ሰካራም” ስያሜ እየሰጠን፤ በአሁኑ ትርጉምና ዘመን አመጣሽ መቀመርያ መመዘን፤ የውድቀታችን መነሻ እና የታላቁ ታቃርኖ ክስተት መደምደሚያው/መፈጸሚያው/ ነው፡፡

ሀብታሙ አለባቸው በመጽሐፉ በርካታ አገር ውስጥ እና የባዕዳንን ሰም እየጠቀሰ፤ የሐሳብ ክርክሩን ለማጠናከር ሲሞክር እናስተውላለን፡፡ የምሑራኑን ሐሳብም እየጠቀሰ ለ“ታላቁ ተቃርኖ” መፍትኄ ‹‹ፋይዳ የሌለው›› እና ‹‹ያለው›› እያለ ሲገልጽ እናስተውላለን፤ በተለይም ከአገር ውስጥ ገብረሕይወት ባይከዳኝን እና ፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ማስተዋላችን አልቀረም፡፡

በበኩሌ ፕ/ር መስፍን መልደማርያምን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ባሕል እና ፖለቲካ ትንታኔ አረዳድ ላይ በአንድ እና በሁለት መጽሐፎቻቸው ዙሪያ ላይ ብቻ በማተኮር አጠቃላይ ሐሳባቸውን ሲተችም ይሁን መፍትኄ የለውም ብሎ መነሳቱ በሰፊው ጸሐፊውን ያስገመግመዋል፡፡ “አዳፍኔ” ይሕንን አላስቀመጠም ብሎ ወደ ፍርጃ መውረድ ጸሐፊው የተልዕኮ ማስፈጸሚያ አንደበት መያዙን ያጎላበታል፡፡ (አንባቢ ሆይ በሀንታሙ አለባቸው መጽሐፍ ውስጥ ከበርካታ ምሁራን ሐሳቦች በመጡ መደምደሚያዎችን ስናጤን፤ “መስፍን ወልደማርያም በዘመናቸው ያልጠቀሱት ሐሳብ (መፍትኄ) ይሄ ነው” ብሎ የሚያሳየኝ ሰው ካል ለመቀጣት ዝግጁ ነኝ!- ፕሮፌሰሩ ከጻፏቸው መጽሐፍት ውስጥ እንደዋቢ የጠቀሳቸው ከሶስት አለመብለጡን ያጤኗል!)

መጽሐፉ የበርካታ ምሁራንን ሐሳቦች በቁንጽልም ቢሆን መያዙ ምሁራኑ ተሰባስበው እንዲመካከሩበት እና እንዲወያዩበት የኢትዮጵያን ትልቁን ቁልፍ ችግር ለመያዝም እና የተዘጋብንን ደንቃራ አስተሳብ ለመክፈት፤ ብሎም ቁልፉን ለእያንዳንዱ ዜጋ ሰጥቶ ወደ ብርሃናማው “የታሪክ አቅጣጫ”  እንደንዘልቅ ያግዛል ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ጸሐፊው ለመማርም ይሁን ለመታረም ዝግጁነቱን ሲያሳይ እና በአካለ መንፈስ ሲገኝ ብቻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

መጽሐፉን በተደጋጋሚ እየተመለስኩ ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ምርምራዌ ሂደትን ለመከተል የታሰብ ከመሆኑ አንጻር አሁንም ልዩ ትኩረት እና አንጽንዖት ተሰጥቶት ሊታይ የሚገባው ነው፡፡ እንደ መቋጫ ሁለት ነጥብ ብቻ ላንሳ፡፡ አንደኛ የኔ የአስተሳሰብ አድማስ ልኬት በእጅጉ የተወሰነ መሆኑን ወይንም በሌላኛው ጎን የጸሐፊው ሐሳብ በኢትዮጵያ ታሪክ እና ፖለቲካ ዙሪያ አዲስ አስተሳሰብን ይዞ ስለመጣ ለመረዳት አዳግቶኛል፡፡ በበኩሌ ጸሐፊው (ለእኔ) ይሕንን የፈጠረበት ምክንያት  ምንድን ነው ብዬ ሳብብ አንዳንድ ነጥቦችን ማስቀመጥ ይኖርብኛል፡፡ በተቻለኝ መጠን በማሳጠር በሦስት ነጥቦች ብቻ ላጠቃልል፡፡

  1. የኢትዮጵያን ችግር ከአጼ ምኒልክን ጋር አቆራኝቶ መነሳቱ እና የመፍትኄ ሐሳቡንም እዚያው ዙሪያ በማድረጉ
  2. በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የባዕዳንን ተልዕኮ እና ጫና ራሱን የቻለ ሰፊ ግምት የመያዙን ያክል ጸሐፊው ጥናቱን በዚያ ላይም ባለማድረጉ
  3. አሁንም በምሁራን እይታ ይቀርቡ የነበሩ ቃላትንን ለምሳሌ፤ ብሔር፣ አገር፣ ሐገረ መንግስት፣ ስልጣኔ፣ ባሕል፣ መንግስት ሬዥም…. ወዘተ መሰል ቃላትን አጠቃቀማቸውን ከነልዩነታቸው ለማስረዳት ቢሞክርም በተለያዩ ገጾች ላይ ግን ራሱ ሲዳክርባቸው መመልከታችን አልቀረም፡፡

ሶስቱን ነጥቦች በመያዝ ሌላ አንድ ረዥም ትንተና የሚያስፈልገው ጽሑፍ ይዞ ብቅ ማለት ይቻላል፡፡ ለጊዜው ይብቃን፡፡

ታላቁ ተቃርኖ በባዕዳን አስተሳብ የተቃኘ የምሁር እይታ መሆኑን መካድ አልችልም፡፡ የገብረህይወት ባይከዳኝን ሐሳቦች ላይ አተኩሮ ሚዛኑን እሱ ላይ መድፋቱን ሲገልጽ እናየዋለን፡፡ የሌሎችንን ባዕዳን አስተሳሰቦች/ጥናታዊ እይታ/ ከውስጣዊ ታሪካችን ጋር እያነጻጸሩ ለመግባቢያነት መቀመጡ ላይ ውስጤን ሲኮረኩረው በተደጋጋሚ ተይዣለሁ፡፡

የበርካታ ምሑራንን ሐሳቦች ጥናታዊ ስራ እና የምርምር ውጤቶችን ደርድሮ በጫት የታገዘ ጽሑፍ እንዳይሆን  ጸሎቴን አድርሼ፤ በመጽሐፉ ዙሪያ የወጡ አስተያየቶችን ለማንበብም ሆነ ለመሳተፍ ዝግጁነቴን ጀምሬያለሁ፡፡ መጽሐፉ አሁንም በተደጋጋሚ ሊመረመር እና ሊታይ ሚገባው መሆኑን ግን የሚክድ አንደበት የለኝም፡፡

  Article:- by Tesfa Belayneh. 

No comments: