Jul 31, 2013

… and be sure your sin will find you out! Num: 32:23






ደወል!

… and be sure your sin will find you out! Num: 32:23

If you do not do well, sin lies at the door. Gen 4:7

…ኃጥያታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ…ዘኁልቅ 32፡23

ተስፋ በላይነህ

“አቤልም በግ ጠባቂ ነበረ፤ ቃየንም ምድርን የሚያርስ ነበረ፡፡ ከብዙ ቀን በኋላም ቃየን ከምድር ፍሬ ለእግዚአብሔር መሥዋዕትን አቀረበ፤ አቤልም ደግሞ ከበጎቹ በኩራትና ከስቡ አቀረበ፡፡ እግዚአብሔርም ወደ አቤልና ወደ መሥዋዕቱ ተመለከተ፤ ወደ ቃየንና ወደ መሥዋዕቱ ግን አልተመለከተም፡፡ ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ፡፡ እግዚአብሔርም ቃየንን አለው፡- ለምን ትናደዳለህ? ለምንስ ፊትህ ጠቆረ? መልካም ብታደርግ ፊትህ የሚበራ አይደለምን? መልካም ባታደርግ ግን ኃጢያት በደጅ ታደባለች ፈቃድዋም ወደ አንተ  ነው ፡- አንተ ግን በእርስዋ ንገስባት፡፡” ዘፍጥረት 4፡2-7

   አ. ማ፡ አጽህኖተ ማስታወሻ /P.S- Post script/ አንተ ግን ግን በእርስዋ ንገስባት! ነገር ግን ቃየን በኃጥያት ላይ መንገስ አልቻለም፡፡ ወንድሙን  ጠራውም ወደ ሜዳ ወሰደው፡፡ አቤልንም ገደለው፡፡ የመጀመሪያው ግድያ ተፈጸመ፡፡ በንዴት በቅናት ተነሳስቶ ወደ በቀል አመራ፡፡ ኃጥያት ላይ መንገስ አልተቻለም፡፡ ለኃጥያትም ተገዛ! ማንም አላየኝም ብሎ አስቦ ነበር፡፡ የኅሊናው ደወል ግን ይጮሃል! እግዚአብሔርም “የወንድምህ የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮኻል፡፡” አለው፡፡  ቃየን ተረገመ፡፡ ተቅበዝባዥ ኮብላይ ኾነ!

 ቃየንም ለእግዚአብሔር መለሠ  አለውም፡- “ኃጥያቴ ልሸከማት የማልችላት ታላቅ ናት፡፡ እነሆ ዛሬ ከምድር ፊት አሳደድኸኝ ከፊትህም እሰወራለሁ በምድርም ላይ ኮብላይ ተቅበዝባዥ እሆነለሁ የሚያገኘኝም ሁሉ ይገድለኛል፡፡” ሲል ተናዘዘ፡፡ ይህ የህሊና ደወል ነው፡፡ ኃጥያት ትከታተለናለች!

  ሰንቶቻችን በህሊና ደወል ተቅበዝብዘናል? ስንቶቻችን ኮብልለናል? ስንቶቻችን ደወሉ ይጮኽብናል? ከተጫማነው ጫማ እሰከ ተከናነብነው ልብስ፤ ከያዝነው የኪስ ስልክ እሰከ ምንዘውረው መኪና… ስንቶቻችን ለኅሊና ነጻነት እንኖራለን? የኅሊና ደወል ከሐዲስ ሳህሌ- ከሱጴ ቦሮ ምድር! /በዓሉ ግርማ/

ደወል-1

  ወድ መባል የሚያንስበትን ‹‹ካዲላክ›› መኪና ይነዳል… ገንዘቡ በየት በኩል… እንዴት አድርጎ… በመቼ እንደገባ ለማስታወስ ጊዜ አጥቷል… ባማረው መንገድ እንደ ጉድ ይነዳዋል… ወደ ተቀጣጠረበት ጎዳና እያመራ ነው… መኪናውን ‹‹ፓርክ›› ለማድረግ አልተቸገረም…በጣም የተከበረ ነው! አንዲት ጥላሸት የተቀባች የምትመስል ሴት… በሚንቀጠቀጥ እጇ ለልመና ዘረጋች… አለማዬት ቢችል መታደል ነበር… አለማየት ግን አይችል!፡ አለመስማት ቢችል ግልግል ነበር…! አይን ቢታወር… ጆሮ ቢደፈን ግን ከኅሊና ደወል ማምለጥ አይቻልም! የሚነዳው መኪና የተገዛው ከዚህች አዛውንት ጎሮሮ ተሰንቅሮ እንደኾነ ኅሊናው ብቻ ያውቀዋል! ድሀ ሲያይ ያንገሸግሠዋል፡፡ ደወል..!

ደወል-2

  የማይፈልገው የስልክ ጥሪ ነበረበት… ስልኩን ማጥፋት ግድ ሆነበት፡፡ አጠፋ…! አገር ሰላም- ታክሲ ውስጥ ገባ፡፡ ወደ ማምለጫው ስፍራ እያመራ ነው፡፡ ባልጠበቀው መልኩ የስልክ ደወል ይሰማል… ማመን ግን አልቻለም፡፡ የስልኩ ጥሪ ልክ የራሱን! ልቡ ደነገጠ… ኪሱ ውስጥ ገባ፡፡ ስልኩ ‹‹ኦፍ››  ነው፡፡ ወዲያውኑ ግን ሌላኛው ሰው ‹‹ሄሎው›› አለ፡፡   እፎይታ! የሌላ ሰው ስልክ ነበር፡፡ መንገዱ ለጊዜው ሸሸ… አዕምሮው ሰላም ግን ማረፍ አልቻለም! ከኅሊና ደወል ማምለጥ አይቻልም፡፡ ደወል…!

ደወል-3

በጫት ቤት ውስጥ ተቀምጠዋል፡፡ በጠራራ ፀሐይ ቤታቸው ደምኗል፡፡ በጢስ ታፍኗል፡፡በለጋ ወጣትነት እርጅና እና ተስፋ የመቁረጥን “ጸጋ ለብሰዋል”፡፡ በጢስ ውስጥ መተያዬት ቢከብድም፤ በድንግዝግዝ ይደባበቃሉ፡፡ ድብብቆሽ! እየመሸ ሄደ፡፡ መብራት ይብራ ተብሎ በራ፡፡ ደነገጠ፡፡ ድንገት የሚያውቀው ሰው እንደዳይኖር በጣም ሰጋ! ትልቅ ስጋት፡፡ በፍጥነት የበራ አይኑን አሽከረከረ፡፡ የሚያውቀውን ሰው ፍለጋ፡፡ ሁሉንም አማተረ፡፡ ተመስገን! የሚያውቀው ሰው የለም፡፡ ድንጋጤው ሸሸ፡፡ ውፍ!! ሲጋራ በላይ በላይ! የኅሊናው አባቱ ግን ተደነቀሩበት…! የስጋ እናቱ ተላተሙበት…! ሌላ የማይሸሹት ድንጋጤ…! የማያመልጡበት ጩኸት! ደወል…!

ደወል-4

‹‹ከፍቅረኛው›› ጋር ይዝናናል፡፡ በልዩ ስፍራ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፡፡ ልጅቷ የባለጠጋ ልጅ ናት፡፡ ባለጠጋ ቤተሰቦቿን ተማምኖ በትዳር ሊተሳሰር ይፈልጋል! “ሃብት እና ባለጠግነት ከአባቶች  ይወረሳሉ፤ አስተዋይ ሚስት ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ናት” የሚለውን አባባል ከተረት ለይቶ አላየውም፡፡ ከእግዚአብሔር ያገኛት ሴትማ ገንዘብ ፍለጋ…ባለጠጋን ፍለጋ ሸሽታዋለች! አሁን ያለው ከማያውቃት ሴት ጋር ነው! ባለጠጋ ለመኾን…! በበቀል ሀሳብ እርሱም ሊበቀል ይሁን… ያጣውን ለማግኘት… ከባለተረኛ ልጃገረድ ጋር ተቀምጧል፡፡ ያሉበት መዝናኛ ራድዮኑ ተከፍቷል...! ፍቅረኞች ይገባበዙበታል…! “ፍቅር እና ገንዘብ” የሚል ሃሳብ ለውይይት ቀርቧል፡ የመረጋጋት ስሜት አይታይበትም…! ይቅበዘበዛል…! መወያያ ርዕሱ ‹‹ምቹ›› አልሆነለትም፡፡ በጣም ረዘመበት… የ 5 ደቂቃ ንግግር ለዚህ ብላቴና ዝንት አለም ሆነበት! አንቆራበጠጠው…! አንገሸገሸው…! “ኤጭ!” ብሎ ጮኸ፡፡ “ምንው?” አለች ‹‹ፍቅረኛው›› “አይደብራቸውም እንዴ? ቀኑን በሙሉ አንድ ርዕስ ብቻ መጮኽ?” ሲል ተደመጠ፡፡ የተረዳው አልነበረም፡፡ “ኧረ” አለች በመገረም፡፡ “ እኔ ደግሞ አልሰማሁትም ነበር፡፡” ስለ ምን ነበር ዝግጅቱ ስትል መለሰችለት፡፡ ራድዮኑን ማንም የሚሰማው የለም… የሚጮኸውም ራድዮኑ አልነበረም፡፡ ደወሉ ከውስጥ ነው! ከኅሊና ደወል ማምለጥ ዘበት ነው!

ደወል-5

  ከቤተ ክርስትያን አገልግሎት ከራቀ ዘመናት ነጎዱ…! የቅዳሴ… የማሕሌት… የሰዓታት… ዜማ ከሩቅ ይሰሙታል…! ከአሃዱ/ከእሁድ/ እስከ ሰኑይ/ሰኞ/ ደወል አልጠፋም፡፡ ደወል ለእግዚኦ… ደወል…ለቅዱስ ቅዱስ! የቤተ ክርስትያኑን ደወል ሰምተው “አሐዱ” ለማለት ሲሯሯጡ ይመለከታል፡፡ ባለፉት የጉብዝና ጊዜያት ይህንን ደወል የሚደውለው እርሱ ነበር…! ሙዳይ ምጽዋት ወደ ግሉ ካዝና አድርጎ ከተያዘበት ዕለት ጀምሮ ከቅጥሩ አርባ ክንድ ማለፍ ተስኖታል…! እንደ ንዑስ ክርስትያን ለመሳለም… በረከት ሊሳተፍ ቀረብ ሲል መጽዋቾች  የሚጥሉት ሙዳይ ሳንቲም በተቀበለ ቁጥር ጩኸቱ አላስቆም፣ አላስቀምጥ፣ አላስቀርብ ስላለው እግሬን ይስበረው ብሎ ቀርቷል፡፡ በርቀት ደወሉ ይሰማው ጀመር…! ከቤተክርስትያን ደወል ሽሽት…! ሀገር ተሻገሮ… ወንዝ አቋርጦ… ወዝ ወደ ሚቆረጥበት መንደር ተሳፈረ… እዚህ ደወል የለም! እዚህ አሐዱ..እግዝኦ…ቅዱስ ቅዱስ የለም፡፡ ለርሱ “ረብሻ” የለም! ጸጥታ! ሰማዩ በጠራ ቁጥር፤ ከዋክብት በተደረደሩ ቁጥር፣ ጸሐይ በጠለቀች ቁጥር… ወፎቹ ሲንጫጩ ግን ከኅሊናው ደወል ማምለጥ አልቻለም! ከውስጠኛው ደመል ለመራቅ የት ይግባ? የዚህኛው ደወል የባሰ ነው!

ደወል-6….ደወል-7…8….9

  ባለስልጣኖች ለህዝብ ይደሰኩራሉ… በርካታ አዋጆችን ተንተርሰዋል…! ረዣዥም የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ከትረዋል…! “ሙስናን እንዋጋ…!” በትልቁ ተጽፏል… የኅሊናው ውጊያ ግን ከተለጠፈው ደርቷል፡፡ ስፍር ቁጥር የሌላት፤ የማትታይ ኅሊና ግን በየጊዜው ትደውላለች…! ትላልቆቹ የማስታወቂያ ሰሜዳዎች የውስጣቸውን ጩኸት ለማካካስ የተሰቀለ ነው፡፡ ኅሊና ካልፀዳ… ወሬ ቢንጋጋ ምንም ጥቅም አለው? የማስታወቂያ ሰሌዳዎች ሙስናን ሊያቆሙት አልቻሉም፡፡ ማቆሚያው የውስጥ ሰሌዳ እንጂ መች ከውጭ ነው? …

 ሰዓሊው ሳያስበው የለቀለቀው ‹‹አብስትራከት›› ስራ በታዳሚዎቹ ተደንቆለታል…! ተጨብጭቦለታል፡፡ ነገር ግን ለርሱ ምጸት ሆኖ ይሰማዋል፡፡ በስንት ምርቃና እንደተገኘ… ለምን እንደሳለው፣ እንዴት እንደሳለው  እርሱ ብቻ ነው የሚያውቀው፡፡ ጥበብ የጫት ውጤት ሲኾን አይወድም! ግን እንጀራ ከጥበብ በለጠች! ደወሉ ከቀለማቱ ጋር ተዋህደው በጠበጡት! …

  የሚጠጣው ውድ ‹‹የአልኮል›› መጠጥ ለመለኪያ የተከፈለባት ዋጋ የእናቱን ማጀት ትሞላለች፤ የልጆቹን ወተት ታነጣለች… ግን በላይ በላይ ይታዘዛል! የውስጡ ደወል ስካር እና ‹‹የሞንታርቦው›› ድለቃ እየመሰለው “ድገሚ!” እያለ ያስቀዳል… ቆነጃጅትን እያሻሸ ይጋብዛል…! ሲነጋ ከስካር ሲተያይ… ከድለቃው ሲለያይ ደወሉ ግን አልተለየውም! ህመም…

  ብዙ ‹‹ዕልፍ›› ደወሎች፡፡ ብዙ ሺ ጩኸቶች ተረግጠዋል! ብዙ እውነቶች፣ ብዙ ሃቆች፣ የስንቱ ደም ይጠራናል፣ የብዙ ንጹሃን ነፍሶች በእስር ቤት ታጉረዋል፡፡ ደወሉ አላረፈም! ጊዜው ለፀፀት፣ ለይቅርታ እና ለንስሃ ነበር፡፡ ይቅር ሳንባባል ጊዜው ይነጉዳል…! በሕይወት መቆየት ከኅሊና ንጽህና ለመፈወስ ነው፡፡

  ኅሊናን ሳንንከባከብ፤ ኅሊናን ሳናስተምር፣ ኅሊናን ሳናዳምጥ- ፖሊሲ-ስትራቴጂ- ትምሕርት- ሚዲያ-ደንብ… ሁሉ መደበቂያ ናቸው፡፡ ህጻናት ከስር መሰረታቸው የኅሊናን ምንንት ሳይገነዘቡ፤ ኅሊናን እየደለሉ፤ በቁመት ብቻ የሚያድጉ ከኾነ በኋላ የሚለጠፍላቸውን መመሪያ እና ደንብ ለማንበቢያ ብቻ እንጂ ለመተግበሪያ ቦታ የላቸውም፡፡ በኅሊና ደወል ጩኸት ሳይሆን በኅሊና እጦት ተጠምተዋል፡፡ የኅሊና ዋጋ አልተነገራቸውም እና! ህጻናት የከደበ ሚካኤልን ተረትና ምሳሌን እንኳ እንዲያውቁት እየተደረገ አይደለም፡፡

  ልቡሰ ጥላችንን ባዶ እያደረግን መኖር ‹‹ፋሽን›› ሆኖ ተዋህዶናል፡፡ /ልቡሰ ጥላ፡ የዳኛቸው ወርቁ አደፍርስን ያስታውሷል/  አዕምሯችን ለወረት የሚታክት ሲሆን ከሰውነት ሚዛን እወጣን ነው፡፡ አንዴ ቆም ብንል፤ ደወሉን ብንሰማ ይበጃል!

  ራስን መሸወድ፣ ራስን ማሳመን፣ መሸንገል እና መደለል የሚቻልበት ዘመን ደርሰን ይኾናል፡፡ በዘመናት የማይለወጠው፤ ሰማይ ምድር ቢያልፉም ቃሉ ግን የማይልፈው፤ ልናመልጠው፣ ልንሸገው፣ ልንክደው፣ ልንደበቀው አንችልም! ደወሉ እርሱ ነው፡፡ ደዋዮቹ የእርሱ ናቸው፡፡ ነጋሪቶቹ፣ ሙሾዎቹ፣ እምቢልታዎቹ፣ ዋሽንቶቹ ይጮኻሉ… አንዴ ቆም ብለን ልናደምጥ ይገባናል! ለይቅርታ እንድንዘጋጅ፡፡ ይቅርታ ደግመን እንዳንሳሳት ቃል መግባት ማለት ነው፡፡

ቃየን እና አቤል አንድ ቢሆኑ ይህ ሁሉ አይደርስም ነበር፡፡ አሁን በእኛ መካከልስ ሰንት መለያየቶች ነግሰዋል፡፡ ስንት ተቃውሞዎች ተበራክተዋል….ስንት ደወሎች…? አንድነት ርቆናል! ማናለብኝነት፣ ማሽሟጠጥ፣ ማፌዝ ተስፋፍተዋል፡፡

  ለኃጥያት መገዛት በስንፍና፣ በንዴት በቂም በበቀል ሊሆን ይችላል፡፡ ከኃጥያት መሸሽ ይበጅ ነበር፡፡ ለኃጥያት ግን ከተገዛን የኅሊና ደወሉ አያድርስ ነው! ተመልሶም እንደሚያገኘን አንጠራጠር፡፡ ንጹህ ኅሊና ዕረፍት ነው! ካሆነ ግን ማምለጥ አይቻልም፡፡  መጽሐፉም እንዲል “… እግዚአብሔርን ትበድላላችሁ ኃጥያታችሁም እንዲያገኛችሁ እወቁ!” ዘኁልቅ 32፡23፡፡

ቸሩ ቸር ያቆየን!



 
 

Jul 25, 2013

የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት




Prof_Mesfin-wolde maRiyAm
“የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት” የፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም የመጨረሻ ቃል?

እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም ሉቃስ ፯፡፴፪

ተስፋ በላይነህ

  ሰሞኑን የክረምቱ ብርድ ሃይሏል፡፡ ዝም ላለ ህዝብ “ሬሳ ያስመስላል”፡፡ ሌሊቱንም የሚዘንብባቸው ቀናት በዛ ይላል፡፡ የሌሊት ሰላም ይናፍቃል! ጸሐፊዎቻችንም መጽሐፍ እያወጡልን ነው፡፡ መሪዎቻችንም ዝም ላለው ህዝብ ህግጋት እያወጡልን ነው፡፡ በዚህ አመት በርካታ መጽሐፍት የወጡ መሰለኝ፡፡ በርካታ ህግጋትም ጭምር፡፡  የባለፈውን ዓመት መጽሐፍት አሰባስቦ ያስተዋወቀን የዛጎል ቤተ መሐፍትን አመስግኑልኝ፡፡ እንዳለ ጌታ ከበደ ነበር አስተባባሪው፡፡ ባለፈው ዓመት መሪዎቻችን በሞት መተካካት ላሳየን ሞትን አስታውሱልኝ! ሞት ግን አይመሰገንም፡፡ ሞት ሲከበር  ካየን ግን ቆየን፡፡

 ዘንድሮ ጥቂት የማይባሉ መጽሐፍት ወጥተውልናል፡፡ መጽሐፍ አዙዋሪዎቻችን ተሸክመውት የሚዞሩት ነገር ያሳዝኑኛል፡፡ ህዝቡም ተሸክሞት የሚዞረው ሸክም ያሳምመኛል! አንዲት መጽሐፍ ለማንበብ ተሸክመን መዞር  የከበደን ሰዎች እጅግ በዝተናል፡፡ አንዲት እንጀራ ለማግኘት የምንንከራተት ሰዎች ተበራክተናል! በረከትም አጥተናል! መጽሐፍ አዟሪዎቻችን ግን በጀርባም በፊት ለፊትም ይዘውታል፡፡ ተሸክማ ይዞራሉ! መሪዎቻችን እንጀራ መሬቱን ተሸክመውታል! ተሸክመናቸው እንኖራለን!

 ከአንዳንድ መጽሐፍ አዟሪዎች ጋር የመግባባት እድል አጋጥሞኛል፡፡ በእውነት ያስደስታሉ፡፡ መጽሐፍ ከሚያነብ ሰው ጋር ማውራት እንዴት ደስ ይላል? ምንም በሃሳብ ባንግባባ የሌላውን መጽሐፍ ሃሳብ በማምጣት ያግባባናል፡፡ አንባቢ በሃሳብ ያፋጫል፡፡ ጦር መወራወር፣ ሰይፍ መማዘዝ የለም፡፡ በሃሳብ ብቻ መወያየት፡፡ ይህ ትልቅ ስልጣኔ ነው! ሰው ማለት ይኼ ነው! ከመሪዎቻችን ጋርም የመተዛዘብ እድል አጋጥሞኛል፡፡ ከመጽሐፍ አዟሪዎች ጥፍር እንኳ አይደርሱም! መሪዎች ያነባሉ/ ንብ ማንባት/ ፡፡ መጽሐፍ አዟሪዎች ያነባሉ/ ንባብ/ ባ ሲጠብቅ፡፡ አሊያም ያነባሉ እንባ!/ ባ ሲላላ/ ይህ ኢትዮጵያ ነውና!

 ታዲይ በዚህ ክረምት ሰሞኑን ከእጄ የሰነበተች መጽሐፍ “መልክዐ ስብሐት” ትሰኛለች፡፡ በዓለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት የተሰናዳቸው ይህች መጽሐፍ ስለ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚአብሔር ማንነት የ27 ሰዎች የግል ዕይታን አቅርቦልናል፡፡ የሃሳቡን አምንጪ ዓለማየሁ ገላጋይ አመስግነናል፡፡ መልክአ እና መልክዐ አንድ ናቸው? ሕያው ስብሐት /ገጽ 129/ ፣ ጋሽ ስብሐት አንድም ሶስትም ነው! /ገጽ 256/ እንዲሁም ስብሐት ለአብ /260/ ርዕስ አሰጣጣቸው ከመስመር ያለፈ ኾኖ ታይቶኛል!

  ሰው የግል አስተሳሰቡን ይዞ በተወሰነለት የእድሜ ገደብ የኪራይ ምድሩን ለቅቆ ሲሄድ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የማንነቱ አሻራ ተተክሎ ይቀራል፡፡ ዘላለማዊ ሰው የለም፡፡ በኖረበት ዘመን “ሰው” ለመኾን ግን ያደረገው ሙከራ ማንነቱን ይገልጸዋል፡፡ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር የራሱ የሆነን ማንነት ይዞ የኖረ መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቀዋለን፡፡ ስለ ስብሐት ለአብ የምንነጋገርበት ሃሳብ ባለመኾኑ በዚሁ ልተወው እና “ሰው መኾን” ወደ ሚለው ፍሬ ሃሳብ አመራለሁ፡፡

ሰው እና ሞት የሚባሉት ነገሮች አይነጣጠሉም፡፡ እየኖርን ሰው ለመሆን እንጥራለን፡፡ ሞት ግን አይቀርልንም፡፡ ስለዚህ ለማይቀርልን እጣ ፈንታ ከመጨነቅ ወይንም ከመታገል በተሰጠን የመኖር እጣ ፈንታ መታገል ይበጀናል፡፡ ትግል ሰው ለመሆን! በተወለድንበት መሬት የምንሞትለት ዓላማ አለን፡፡ የምንሞተውም ለዓላማችን እና ለማንነታችን ነው! ማንነት ምንድን ነው?

 መልክአ/ዐ ስብሐትን እያነበብኩ “የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት” የምትል አንዲት ጥሑፍ አገኘሁ፡፡ እጅጉን ከማረኩኝ ጽሑፎች ተርታ መድቤያታለሁ፡፡ ከባድ ሃሳብ እና ከባድ ሸክም ለዚህ ትውልድ ያዘለች ነች!

  በዚህ ዓመት በቁጥር መግለጽ ባልችልም በርካታ መጽሐፍት ወጥተዋል፡፡ ኧረ ለመኾኑ በየጊዜው የሚወጡትን መጽሐፍት የሚመዘግብ አካል ማን ነው? ምናልባት የኢትዮጵያ ደራሲያን ማሕበር? መጽሐፍ አዟሪዎች…? መሪዎቻችን ድህነት ቅነሳ ላይ ናቸው ብዬ ነው፡፡  አላውቅም…! መጽሐፍ ሳይቆጥሩ ድህነትን መቀነስ ድሀን ለመቀነስ ይመስለኛል፡፡ /በነገራችን ላይ በፓወር ግዕዝ አማርኛን ሲተይቡ ኮምፒውተር ላይየጥያቄ ምልክትን በቀጥታ ማግኘት ስለማይቻል ኹሌም እናደዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያኖች መጠየቅ አይወዱም ተብለን ይኾን?/

  ከትንሽ የመጠን እና የገጽ ብዛት ያላት የደሳለኝ ዳቼ ፡ የመለስ አስተምህሮተ ጥቅሶች መጽሐፍ እንስቶ እስከ ዘውዴ ረታ የአጼ ኃይለሥላሴ ታሪክ ትልቅ መጽሐፍት ታትመው ወጥተውልናል፡፡ በብዛት አነጋጋሪ የነበረች “መክሸፍ እንደ… ኢትዮጵያ ታሪክ” ትመስለኛለች፡፡

  የስብሐት ለአብን መልክ ያሳየችን መጽሐፍ ለየት ትላለች፡፡ ባለፈው ዓመት በሞት የተለየንን ስብሐት ገብረ እግዚአብሔርን ለማስታወስ የተጻፈች ነች፡፡ አስታውሱ “በሞት የተለዩንን ለማስታወስ…!”

ታዲያ ይህችን መጽሐፍ እያነበብኩ መሃል ላይ ከግል ጡመራ ሰሌዳ ያገኘኋት ጽሑፍ ሃሳቤን ይዛው ሄዳለች፡፡ “የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት” ብዙ እንድናስብ የምታደርግ አጭር ጽሑፍ፡፡

 ሰው ሲሞት በሌሎች ዘንድ ማንነቱን ማስተዋስ እና ስራዎቹን ለቀሪው ትውልድ ማስተላለፍ የተለመደ ነው፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይ ስብሐት በህይወት እያለ አስነብቦናል፡፡ መሰል፡፡ ኢህአዴግንም ከስሶልናል! /ጥያቄ ምልክት ስላጣኹ ነው!/ መልክዐ ስብሐት ከሞት በኋላ በተለያዩ ሰዎች ዘንድ የተውጣጣ ሃሳብ ነው፡፡

 ሰው በህይወት እያለ “የተውጣጣ ሃሳብ” ሲያገኝ ደስ ይላል፡፡ ምናልባት ስብሓት በህይወት እያለ ብዙ ተብሎለት እርሱም ብዙ መልሷል፡፡ መታደል ነው በህይወት እያሉ ጣጣን ጨርሶ መሞት…! ስንቶቻችን

 ሳንሞት ጣጣችንን ጨርሰናል? ስንቶቻችን ጣጣችን ከህይወታችን በልጦብናል? ስንቶቻችን ህይወት ጣጣ ሆኖብናል? የምንኖረው የምንሞተውስ ለምን ጣጣ ነው? መሪዎቻችንም በማውጣጣት ሃሳብ ቢያምኑ ምንኛ መታደል ነበር ጥያቄ ምልክት፡፡ ከቃል አጋኖ ጋር፡፡

  ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምን ሳስብ የኢትዮጵያን ታሪክ በልዩ አይን እንድመለከት እና በተፈጠረው ታሪክ አጋጣሚ ከስህተት መማር ወይንም ከስኬት መሻሻልን እንድወስድ ያስገነዝበኛል፡፡  መጽሐፍትን ጽፈዋል፡፡ ሃሳባቸውን ያለ ፍረሃት ለዘመናት ገልጸዋል፡፡ እውቀት የእድገት መሰረት መሆኑን አበክረው አስረድተዋል፡፡ ጦርነታ ትልቁ ጠላታቸው ነው፡፡ ባንዳ ኮርቶ አርበኛ ሲሰቃይ እና ሲረክስ ሲያዩ እርር ድብን ይላሉ፡፡ መንፈሳዊነት መሳሪያቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት መገለጫቸው ነው፡፡ ጣጣቸውን ጨርሰዋል!  ልብ በሉ የህይወት መሰረቱ ጣጣን መጨረስ ነው!

 የስልጣን ጥማት አለባቸው እያሉ የሚያስወሩ ቡድኖች አሉ፡፡ ስልጣን የሚፈልግ ሰው እንዲህ እውነትን ብሎ ሙጭች አይልም! ጣጣ አያበዛም! ስልጣን የሚፈልግማ ወላወይ በመኾን ባለተረኛን መንግስት ከነታሪክ ስህተቱ አሜን ብሎ መቀብል ነው፡፡ ስልጣን ፈላጊ ናቸው ብዬ መቀበል አልችልም፡፡ በደርግ ዘመንም «ታዲያ እኛን ምን አድርጉ ትሉናላችሁ፣ መሳሪያው ያለው እናንተው ጋ አይደለም እንዴ?» የተባለን አባባል ወደ “በለው፣ ጨርሰው” አስተሳሰብ በመለጠፍ “ስም የማጥፋት” ወንጀል ሲሸመት አይተናል፡፡ የሁሉንም የግል ማንነት ለፈጣሪ ፍርድ እንስጥ፡፡ ነገር ግን የእኚህን ሰው ማንነት በሚገባ አውቆ ፍርድ ከመስጠት በፊት የጻፏቸውን መጽሐፍት አንብበን እንዲሆን የግል ምስክርነቴን አስተላልፋለሁ፡፡

 በእጄ ከገቡ መጽሐፍት “አትላስ” ስለ ኢትዮጵያ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ በስዕል ይዘረዝራል፡፡  እንጉርጉሮ  በ1967 ዓ.ም የወጣ የግጥም መድብል ነው፡፡ እውነትም እንጉርጉሮ! በተለይ በመቅደሙ ላይ የተቀመጠው ሰሜት ነኪ አገላለጽ ለብቻው ነው፡፡ እውነት ፕሮፌሰሩ ስሜትን ‹‹የማንጎርጎር›› ስጦታ አላቸው፡፡    ከቆሜ አየዋለሁ እስከ ህያው ኢትዮጰያ የተቀመጡት ግጥሞች ለስሜት ከስሜት የቀረቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ከየት ወዴት…? ደግሞ 1986 ዓ.ም የወጣች ስትሆን ትንሽነቷ ቶሎ ቶሎ ጨርሱኝ ግን ደጋግሙኝ ደጋግሙኝ ትላለች! ከነፍጠኛ አተረጓጎም እስከ ጴጥሮሳዊነት አመለካከት ውስጣዊ መንፈስን የሚነካ ግሩም ጭብጥ ይዛለች፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ፍቅርን የገለጸበት መንገድ ማንም አልገለጸበትም፡፡ መስፍን ወልደማርምም ኢትዮጵያዊነትን የገለጹበት አገላለጽ ልዩ ነው፡፡  የክደት ቁልቁለት ሁለት መጽሐፍን ይዟል፡፡ ገረፍ አደረግሁት ግን አላነበብኩትም፡፡  አገቱኒ  ሌላኛው ለየት ያለ አቀራረብ ያለው መጽሐፍቸው ነው፡፡ የህይወት ታሪካቸውን ለመጠቆም ሞክረውበታል፡፡  ታሪክ የለኝም! ብለው ይነሳሉ… አንድ “ወሬኛ ናቸው” ብሎ የመለሰላቸውን ሰው በቁጣም አልተቀበሉት! አዎ ወሬኛ ነኝ ብለው ይመልሱና ወሬ ሃሳብ መግለጽን ከያዘ፣ እውነተኛ እና በእውቀት ከተደገፈ ወሬ ከብረት እንደሚበልጥ ያስረዱታል፡፡ በመጠኑም ቢሆን የልጅነት ጊዜያቸውን አስቃኝተውናል- በአገቱኒ ተምረን ወጣን፡፡ ክፉ ቀን ደግ ነው! ምርጫ 97ን እና የኢትዮጵያን የወደፊት ሁኔታ ለማመላከት የቀረበ ጭብጥ ወደ መጨረሻ እናገኛለን፡፡ “አደጋ ያብዣበበበት አፍሪካ ቀንድ” ይከተላል፡፡ ስለ አፍሪካ ቀንድ የኋላ ታሪክ ፣ ያለበትን ሁኔታ እና የወደፊት እይታ ለማመላከት የቀረበ መጽሐፍ፡፡ የአፍሪካ ቀንድ በ20 ዓሜ,ት ውስጥ ከ 5 ሀገራ ወደ 10 ተሸጋግሯል፡፡ ስለ አረብ አገራትም ብዙ ጽፈውበታል፡፡

  ከዛም በያዝነው ዓመት መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንደርሳለን፡፡ መጽሐፉ መታተም የነበረበት ቀድሞ ቢኾንም ጊዜውን ጠብቆ 2005 ወጣ፡፡ ብዙዎቹን አነጋግሯል፡፡ ያስቆጣቸው ነበሩ! ሃሳቡንም የተጋሩትም በርካታ ናቸው፡፡ “የከሸፈ ታሪክ እንጂ ታሪክ ይከሽፋል…?  በሚል አገላለጽ የተጀመረው ሃሳባዊ ውይይት ያስደስት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ እንዲህ በሃሳብ ብንወያይ፤ የሃሳብ የበላይነት ባህል አድርገን ብንቀጥል ልዩ ነበር፡፡ ያም በጊዜው ከሸፈ!?

  ለዓመታት በመጽሔቶች እና በጋዜጦች በበርካታ ሃሳቦች ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን አስነብበውናል፡፡ አሁን ደግሞ በወርድ ፕሬስ እና በዘመነኛው ፌስ ቡክ ገጽ አልተለዩንም፡፡ እድሜ መጨመር ቢቻል ለእርሳቸው በጨመርኩ ያልኩበት ቀን ነበር፡፡ ነገር ግን የእድሜ ባለቤት ፈጣሪ ነው! እድሜና ጤና እንዲሰጣቸው መለመን የእኔ ፈንታ፡፡ ታዲያ በዚህ ክረምት አንድ ጽሑፍ በድረ ገጽ እንደ ተለመደው አስቀመጡ፡፡ ከአድን ጊዜ በላይ አንብቡኝ አንብቡኝ ይላል፡፡ የሚወለዱበት፣ የሚሞቱለትና የሚሞቱበት መሬት አስተማሪ ጽሑፍ ነው፡፡ እንድታነቡልኝ እጋብዛለሁ! ሳንሞትም ሳናኖርም ኖረንም ሞተንም የምንሸከመው ጥሑፍ፡፡

ታዲያ ሞት የሚባለውን ነገር በዚህ ጽሑፋቸው መግለጻቸው የመጨረሻ ቃል!? ብዬ እንዳስብ አደረገኝ! ጽሑፉን አንብቤ ስጨርስ ለሰዓታት ስሜቴ ይርገበገብ ነበር! እውነት ምንድን ነው? መኖር ምድን ነው? የምንሞተው ለማን ነው? እየኖርን መሞት እንዴት ያለ ክፉ ደዌ ነው? መሬት ምንድን ነው? ኮምፒውተሬን ወደ እንግሊዝኛ ለወጥኩና ብዙ ጥያቄ ምልክቶችን አስቀመጥኩ…!

ሰው መሆኔ ቀርቶ፣- አስከሬን ስባል፣

እወቁልኝ ይህን ብቻ፣- የገባኝን ያህል

ሞክሬ ነበር ሰው ለመሆን፤

ኑዛዜ ከምትል አንዲት የግጥም ስንኝ ቀንጨብ አድርገው በለሆሳስ ሹክ አሉኝ፡፡

መሬት አልነበረኝም በሕይወቴ

መሬት አልፈልግም፤ አሁን በሞቴ

አቃጥሉልኝ ሬሣዬን፤

አመድ እስኪሆን፤

አዋሽ ውስጥ ጨምሩልኝ አመዴን፤

አመዴ

ከአዋሽ ይቀላቀል ከዘመዴ

ይቺን አትንፈጉኝ አደራ

አመዴ እንኳን እንዲኮራ …

 ይህ ግጥም የምንወደው ሰው በሞት ሲለየን ከምናለቅሰው በላይ የሚያስለቀስ አባባል ነው፡፡ በስሜት አልቅሻለሁ!

  ሬሳ የማቃጠሉ ተግባር በቁሙ የተጎዳውን ደሀ ሲሞት ደግሞ መድረሻ እንዳያሳጣው የደሀ ሬሳ ለማቃጠል የሚያስፈልገው ወጪ ‹‹ድህነትን ለመቀነስ›› ከሚለው በጀት ወይም እርዳታ ቢወጣ ችግሩን ሁሉ ያቀላጥፈዋል፤ ደሀውም እየተደሰተ ይቃጠላል ወይም ችግሩ አብሮት እንደሚቃጠል እያወቀ ይደሰታል። ይኸኛው ደግሞ ይገርማል፡፡

ሰው እየኖረ ሲሞት ያሳዝናል፡፡ ለአኗኗሩም ሳይጨነቅ ለአሟሟቱ ይጨነቃል፡፡ ለምን ለሰውነቱ ሳያስብ ለበድን ሬሳው ያስባል!?  

ሰው እየኖረ ቢስማማ፣ ቢረዳዳ፣ ቢከበር፣ ቢከባበር፣ ቢደሰት እድል ፈንታው ነበር፡፡ አምላክ በምድር ሁሉን መሬት ሰጠን! ነገር ግን በመሬቱ ሰው ከሰው ሲበላለጥበት አንዱ ሲጨፍርበት እንደኛው ይኮራመትበታል፡፡ ድሀው መሬቱን ሲልስ ‹‹ሀብታሙ›› ጫማው ይላስበታል…. የሚትበት መሬት እና የሚሞትለት መሬት ማጣት አለመታደል ነው!  

  የምድሩ መሬትስ አልኾነም ፈጣሪ ግን ነፍሳችንን በግዛቱ ያድርግልን! በዚህች መሬት እውነትን ያለ፣ እውቀትን ያለ፣ ሃቅን ያለ፣ ሀገርን ያለ፣ መሬትን ያለ በመንፈስ ድሀ ሲኾን ታዝበናል፡፡ በመንፈስ ድሀ መኾን ብጹዕነት ነው! በህይወት ሳለን መስማማት፣መሰማማት ያሻለናል! በህይወት ሳለን መደጋገፍ መተቃቀፍ ይበጀናል! በህይወት ሳለን መከባበር መመካከር ይቀልለናል! እኚህን የሞራል አባት ግን አልሰማናቸውም! አልተመከርናቸውም! አልዘሀርናቸውም! አላከበርናቸውም፡፡ ከሞቱ በኋላ ሙሾ ማብዛት ግብዝነት ነው! ከተሞተ በኋላ ነጋሪት መጎሰም ለማደንቆር ነው! በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 7፡ 32 /፯፡፴፪/ የክርስቶስ ቃል ትዝ አለኝ፡፡

እንቢልታ ነፋንላችሁ አልዘፈናችሁምም፤ ሙሾ አወጣንላችሁ አላለቀሳችሁምም

  ድንጋይ ከመኾን ይሰውረን! ፈጠሪ ሰው አርገን! ፈጣሪ ለመሬት ልሳን ያድርገን! የኢትዮጵያን ልሳን የሚሰማ መሪ ላክልን! ፕሮፌሰሩንም የሰማቸው የለም! እርስዎ ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ አያፍሩም ኢትዮጵያም እርስዎን ስላፈራች አታፍርም፡፡ ልሳኗ ነበሩ! ሰሚ ግን አልነበረም…

ቸሩ ቸር ያቆየን!


ስንት ዳዊቶች በጎልያዶች ወድቀዋል…?






ስንት ኢትዮጵያኖች ለጥበብ ተጠምተዋል…?
ስንት ዳዊቶች በጎልያዶች ወድቀዋል…?
በተስፋ በላይነህ
ይህ የአንድ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ነው፡፡ የአንድ ኢትዮጵያዊ እንጅ የኢትዮጵያ ታሪክ ግን አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ታሪክ አላት፤ ይህ ልጅ ግን ታሪክ የለውም፡፡ ከባለታሪክ ሀገር “አልቦ ታሪክ” ïነን ስንገኝ ያሣዝናል፡፡ ኢትዮጵያ የታሪክ መዘክር ናት፡፡ ኢትዮጵያኖች ግን ታሪክ አልባ እየïኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያኖች ታሪክ አልባ ከïኑ ኢትዮጵያስ ታሪካዊነቷ ምኑ ላይ ነው? ህዝብ ታሪክ አልባ ሲïን ሀገር ምን ትïን? ይህ ግን የአንድ “ታሪክ አልባ ኢትዮጵያዊ ታሪክ” ነው፡፡ በዚህች ሀገር ጥበብ በብርቱ ትፈለግ ነበር፡፡ ጥበብን የሻተች ንግስት ወደ ጠቢበኛው ለምስክርነት የተዘከረች ሀገር ነች፡፡ ለጥበብም ለመፍረድ የምትነሳ! ህዝቦቿ ግን በጥበብ መሪነት ሲጓዙ አልታዩም፡፡ ሲገዙም አልተሠሙም! ህዝቦቿ ግን ጥበብ አልባ፣ ታሪክ አልባ፣ ሀገር ለልባ ሲïኑ እየታዘብን ነው…. ዳዊት ይባላል ባለታሪኩ፡፡
የአስረኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ ወደሚቀጥለው የትምህርት ደረጃ ማለፍ አትችልም ተባለ፡፡ ቤተሰቦቹ ብዙ ይጠብቁ ነበር፡፡ ሕይወት አንድ ቀጥተኛ መንገድ አለመïኗን ሳያስተምሩ ለአንድ ትልቅ ቦታ ይመኙታል፡፡ ከህፃንነት ጀምሮ በርካታ መጽሐፍትን አስነብበውታል፡፡ ከ “ኬጂ” ጀምሮ የሚያቀላጥፈው እንግሊዘኛ ቋንቋ አሁን ከፍተኛ ተናጋሪ አድርጎታል፡፡ ሶስት ተጨማሪ ቋንቋዎችን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ አሉ የተባሉ መጽሐፍትን በቤቱ አሟልቷል፡፡ ያነባል…. ሙዚቃ ያደምጣል… ፊልም የቀረው የለም… አሥረኛ ክፍልን በእንደዚህ ጉዞ ፈጽሟል፡፡ አባቱ “የፖለቲከኛ እስረኛ” ናቸው፡፡
ህይወት “ማለፍና መውደቅ” መïኗን ባነበባቸው፣ በተመለከታቸው እና ባደመጣቸው መጽሐፍት ፊልሞች እና ዘፈኖች ተምሯል፡፡ ነገር ግን- ነገር ግን ለአስረኛ ክፍል መውደቅ መከታ አልïኑለትም፡፡ የባስ የወደፊት ህይወቱን አጨለሙበት፡፡ በየሙዚቃው በየፊልሙ የሚያያቸውን የአልባሣት፣ የመጓጓዣ፣ የመኖሪያ እና የመዋብያ ንዋያትን የሚያገኘው ተምሮ ጨርሶ በሚያገኘው “ገንዘብ” እንደïነ ተነግሮታል፡፡ ካልተማረ እነኚህን ኹሉ የግሉ ማድረግ አይቻለውም፡፡ ቆነጃጅት ሴቶችን ማማለል የሚቻለው እነኚህ ሲሟሉ እንደïነ ተማምኗል፡፡ አሁን ግን እነኚህ ነገሮች የሉም ህይወትም የለችም!
ለሣምንታት ከቤተሰቦቹ ተገልሎ ቆይቷል፡፡ ማንንም ማነጋገር አይፈልግም፡፡ ከጆሮው በሠካት ማፅናኛ ብቻ ቀኑን በሙሉ ይገፋል፡፡ ይጮኻል ዘፈኑ… ይጮሃሉ ዘፈኖቹ… ይጮኻል መሣሪያው… መጽናኛው “ሙዚቃ” ብቻ ነበር፡፡
ከህፃንነት ጀምሮ አብራው ያልተለየች ልጅ አለች፡፡ ዘፈኑ በሙሉ ለእርሷ ነው፡፡ ህይወት በሙሉ ለእርሷ ነው፡፡ ሲፈልግ ያሞግሳታል… ሲያሻው ያብጠለጥላታል… ካሠኘው ያመልካታል… ከመጣበትም ይቃወማታል፡፡ ይኽ ሁሉ የሚነገረው በዘፈኑ ነው፡፡ ዘፈኑ ቀኑን በሙሉ ከጆሮው አይለይም…! ዘፈኑ “ሮክ” ነው፡፡
በደመነፍሥ ይራመዳል፡፡ መሄጃ የለውም ግን ይጓዛል፡፡ ሃሣብ የለውም ግን ይጨነቃል፡፡ ሰሚ የለውም ግን ያወራል…! ምናልባት ስሜቱን ተረድታ፤ በቀዘቀዘው ማንነቱ ውስጥ ገብታ የምታሞቀው አብሮ አደግ “ጓደኛው” ሚልካ ትኾናለች፡፡ የሚያደምጠው ሙዚቃ ናፍቆቱን ቀስቀሰበት፡፡ እንደውም ወደርሷ እንዲሄድ ገፋፋው… ጉዞ ወደ ሚልካ፡፡
I miss you miss you. Don’t waste your time on me you already the voice inside my head. I miss you. Miss you….እያለ ይዘፍናል፡፡ ሜልኮል በአእምሮው ውስጥ ትጮኽበታለች፡፡ ናፍቆት “በልቡ” ይወዛወዛል፡፡ ሄደ ማየት አለበት፡፡
ዝናቡ ከዛሬ ውጪ የሚዘንብ አይመስልም፡፡ ሠማይ ተከፍቶ የሚዘጋም አይመስልም፡፡ ይዘንባል! ዳዊት ወደ ሚልኮል እየሄደ ነው፡፡ ዝናቡን በትከሻው ተሸክሞታል፡፡ ቤታቸው ፊት ለፊት ደረሰ፡፡ ባለፎቅ መኖሪያ ቤት ውስጥ ፊት ለፊት የሚያየው በመስኮት ሜልኮልን ነበር፡፡ ዝናቡ አስገርሟት “በሣቅ” ትመለከታለች፡፡ ያዘነው ዳዊት ስልኩን አውጥቶ መደወል ጀመረ… አነሣችው…
ሄሎ ዴቭ…
ሄሎ…
እንዴት ነህ?
አለሁ…
በጣም ጠፋህ በሰላም ነው?
አለሁ አንቺስ ምነው አልደወልሽም? እደውልልሃለሁ… ሣይጨርስ ተቀበለችው
አይ ዴቭ ሰሞኑን እኮ ክፍለ ሃገር ሄጄ አልተመለስኩም፡፡ ዳዲ ዘመድ ምናምን እያለ የሚጨርሥም አይደለም፡፡ ስንመለሥ አገኝሃለሁ….
ማመን አልፈለገም፡፡ መጠየቅም አልፈለገም፡፡ ማረጋገጥ ግን አለበት….
ታዲያ አሁን ቤት አይደለሽም? አለ በፍርሃት አንደበት…
አዎ! ክፍለ ሃገር ከሄድኩ ቆየሁ፡፡ በማለት የመስኮቷን ነጭ መጋረጃ ፈታች፡፡ ነጭ መጋረጃው ክፍለ ሃገር ሸኛት… ነጭ መጋረጃው ዳዊትን ጥቁር አለበሠው፡፡ ዝናቡ በመብረቅ ታጀበ፡፡ ዳዊት እንደ ጨው ሟሟ፡፡ የግቢውን ረዥም አጥር ኮረንቲ መጠጣት አሰኘው…ዝናቡም ዳዊትን አጥቦት ይዞት ጎረፈ፡፡ Jump to fire የሚል ዘፈን ቀጠለ… (ሰባት ዓመት…..)
ከሰባት ዓመት በኋላ ዳዊት አልተመለሠም፡፡ የሚዘልበት እሣት አላገኘም ልቡ ግን እሣት ይተፋል፡፡ ሲጋራ… ሬት ሲጠጣ ይውላል… ቅጠሉ መምረሩ እንደጣፋጭ ïነለት፡፡ 7 ዓመት መቃም… ሠባት አመት መጨስ… ከ97 ጀምሮ!
“ታላቁ መሪ” ሞቱ የሚል ወሬ ይሠማል፡፡ ዳዊት እንኳንሥ መሪውን ሱሪውን በስርዓት ለይቶ አያውቅው… አያወልቅምም! ቀይ ደም ቀርቶ አረንጓዴ ደም “ከልብ ስሩ” ይረጫል! ፀጉሩ አያቱ ከሚፈትሉት ፈትል በይበልጥ ተፍተልትሏል፡፡ ጡንቻው እናቱ ከምትለብሰው ነጠላ በይበልጥ ተሸብሽቧል… የብብቱ ጠጉር መነኩሴን ያስመንናል… ታጋይን ይሸሽጋል… አርበኛን ያስኮበልላል… ለዳዊት ፀሃይ ጠልቃ አልወጣችም… ጨረቃ ሞልታ አልተገመሠችም… ከዋክብትም ረግፈዋል… “ነጋ ጠባ ሰኞ አመት ሙሉ ሰኔ…!” ዳዊት ተፈርዶበታል!(ፊያሜታ)
ዳዊት ኢትዮጵያዊ ነው! ስንት ዳዊቶች ሣይኖሩ ሞተዋል? ስንት ኢትዮጵያኖች ሣያድጉ ረግፈዋል…? ስንት ኢትዮጵያኖች በጩኸት ደንዝዘዋል? ስንት ኢትዮጵያኖች ተሸሽገው አድፍጠዋል..? ስንት ድንጋዮችስ ተጠርበው፣ ተውበው ህንፃ ኾነዋል? ስንት ዳዊቶች ተውበው፣ ተጠርበው፣ ተቀብረዋል…? ስንት “ኮብሎች” ተፈልጠው መንገድ ኾነዋል…?  ስንት ጉብሎች ተጠልፈው መንገዱ ጠፍቷቸዋል…? ስንት ጀግኖች…? ስንት ጠቢባኖች ተሠደዋል…? ስንት ታሪክ አዋቂዎች በመንፈስ ተኮላሽተዋል…? ስንት እውነት ፈላጊዎች  ታስረዋል…? ስንት ነፍሳት ተነጥቀዋል…? ስንት “ሜልኮሎች” በዳዊቶች ተሣልቀዋል….? ስንት ዳዊቶች በጎልያዶች ወድቀዋል…? ስንት ኢትዮጵያኖች ለጥበብ ተጠምተዋል…? ኢትዮጵያ ሆይ ስንት…? ፡-(
www.tesfabelaynehh.blogspot.com
ቸሩ ቸር ያቆዬን!

Jul 11, 2013

የይስማዕከ - "ክቡር ድንጋይ"ን እንዳነበቡኩት

“ውሻ መሪ”…ውሻ ትውልድን ይፈለፍላል…!
የፖለቲካ ትግል በአሉባልታና በመንደር ወሬ? የይስማዕከ “ክቡር ድንጋይ” ወደ ምን ሊያመራን ነው? የንጋት ኮከብስ ማን ነው?
ተስፋ በላይነህ
A DOG IS CHANGED IN TO MAN?

  የስነ ጥበብ ሰው በስነጥበብ ሥራው ሲቃዥ፤ደራሲ ተደራሲንን ጭፍግግ አድርጎ ሲይዝ፤ታዳሚ ከጥበብ ትዕይንት የድርሻውን “እውነት” “ጥበብ” እና መፍትሄ ሳይሰንቅ ከተመለሰ ወዮለት ለዛ የጥበብ ሰው!
  በደብዛዛ ልቡና፣ባልጠራ ብዕር፣ በማይተጋ መንፈስ የተተየበ የሥነ ጽሁፍ ሥራ ያስነውራል፡፡ በተለይ “ጊዜ እና እውቀት” ፈስሶበት ተብሎ ተደራሲን በጥበብ ጥም ደዌ ሲሰቅዝ ማየት የአስርት ዓመታት የኋላ ታሪካችን  አሳባቂ ነው፡፡ የአንድ አገር የሰነ-ጥበብ ሙያ ሲዋዥቅ፣ባለሙዎቹ ነጻነት ሲያጡ፣ ጥበበኞቹ በንዋይ ሲደለሉ፣ በፍርሃት ቆፈን ሲርበተበቱ፣ በፖለቲካ ርዕዮት ዓለም ሲደቆሱ፣ ስነ-ጥበቡ “ፕሮፓጋንዳ” ሲነዛበት፣ በአሉባልታ የመንደር ውሬ ሲልመሰመስ ማየት የአንድ አገርን መዋዠቅ ቀጥተኛ አመላካች ነው! ወደ ዚህ ሃሳብ ያስገባኝ የስማዕከ ወርቁ “ክቡር ድንጋይ” የሁነቶች ልቦለድ /የሃሳቦች ልቦለድ/ ሥራ ነው፡፡ 
2013 BOOK BY THE `AUTHOR`
   
  ብላቴናው ቀላል አይደለም፡፡ 7 ሥራዎቹን በማይታመነው የእድሜው ቁጥር ጉድ አስብሏል፡፡ ኾኖም ግን ዘመኑ ትውልድን በለጋነት እየቀሰፈ፤የሰብዓዊነትን ሕልውና እያኮላሸ፤የሰውነትን ድርሻ ጥልቅ ሀይል እየቀበረ እያሽካካ ነው እንጂ ክርስቶስ በ12 ዓመቱ ስንት የአይሁድ ሊቆችን አስደምሟል? በሀገራችን የነገሱት ነገስታት በሥንት አመታቸው ታሪክ መዝገብ ውስጥ ተከትበዋል? ልጅ ተፈሪ በ13 ዓመቱ ከአባቱ ባገኘው ሥልጣን ወደ ዘውድነት የሚያመራውን ካባ ተከናንቧል፡፡ ነጋድረስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ በምኒልክ ዘመን…ለገሰ ዜናዊስ “ወገኑን”አርነት ሊያበስር በ19 ዓመቱ አልተሽቀዳደም? ኧረ ስንቱ…! የሌሎችን ግለ-ታሪክ ለታሪክ መዘርዘር ለየግላችን እንተወው፡፡
      ነገር ግን በአንድ አገር ውስጥ ትኩስ “ወጣት” እያለን ሲኮላሽ ማየት ውርደት ነው፡፡ይህ ብላቴና ከተኮላሸ ትውልድ ውስጥ ገንኖ ቢወጣ ያስመሰግነዋል፡፡ መግነኑ ግን በንኖ እንዳይቀስፈው ወዮለት!
“ክቡር ድንጋ”ን እንዳነበቡኩት
በአስማት ቃላት፣ በጥቁር ውሻ እና በድንጋይ የተከበበ ሽፋን የደራሲውን ስም ይዞ ይታያል፡፡ /በአንድ የሆሊውድ ፊልም አባት ወደ ውሻነት ሲቀየር ያየሑት ፊልም ትዝ አለኝ፡፡/ ሽፋኑ በአንድነት ተሾመ ቢሰራም “ዲዛይኑ” የራሱ የደራሲው ነው፡፡ ደራሲው በዘመነኛው የስነ-ጽሁፍ ታሪክ ለዚህች አገር ትልቅ ስም አለው፡፡ ይህ መኾኑም ያለንበትን ደረጃ ማሳየት የሚችል መረጃ ነው! /ያለንበት በቂ ነው አይደለም የሚለው ጥያዌ እንዳለ ሆኖ/
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ 2005 ዓ.ም በግዕዝ ተጽፏል፡፡ ከዚህ በፊት በዚህ ቁጥር አጻጻፍ ተነስቶ የታዘብነው ውዝግብ ነበር፡፡ 2005 በግዕዝ ሲሳፍ እንዴት ነው? የመ.ይትባረክ ገሰሰን መጽሐፍት ማገላበጥ ግድ ይለናል፡፡ ለ”ክቡር ድንጋይ” መጽሐፍ ዶ/ር አድማሡ መሸሻ እና ገዛኸኝ ጸጋው ሀተታ እና ፍተታ ሰጥተዋል፡፡ ለፍተታው መልካም ንባብ! መባሉ መጀመሪያ መቅረብ የነበረበት አስተያየት ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን የቀረበልን መጽሐፉን አንብበን ከጨረስን በኋላ ነው፡፡
የምናምነው የምንጠራጠረውን ነው፡፡ የምትል አንዲት መጽሐፍ የሚወጣላት ዐረፍተ ነገር በገጽ5 እናነባለን፡፡ ለራሴ ብዙ ጥያቄዎችን በመስጠት አሰላሰልኩ፡፡ በህይወታችን ማንን እናምናለን? ማንን እንጠራለን? ጥርጣሬ ያለበት እምነት ዋጋ ቢስ ነው! የምንጠራጠረውን ካመንን እምነታችን ከንቱ ነው! እምነት የሰናፍጭ ታክል ብትደቅም ምልዕነቷ ግን ዝግ ነው! የቅንጣት ጠብታ ታክል ጥርጣሬ በውስጧ አታስተናግድም፡፡ የዚህ ብላቴና እምነት ግን በትልቅ ጥርጣሬ እንደተሳካች ናት፡፡ ትልቅ ጥያቄ ምልክት በገጽ 5!
የዚህ አባባል ንድፍ በገጽ 6 ላይ ቀርቧል፡፡ በዚህ ጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን የአስማት ቃላት በሞመከር ለሚመጣው ችግር ደራሲው ተጠያቂ አይደለም፡፡ ይለናል! አቤቱ… እኛን በማጠራጠር ሊያሳምን የሚሞክር ሙከራ ነው ለማለት ዳዳሁ፡፡ የዚህ “አስማት ቃል”   ማሳሰቢያ በገጽ 169 ተደግሟል፡፡ የአስማት ቃሉን ግን ከገጽ 144 በቀር  በመጸሐፍ ውስጥ አይገኝም፡፡ ምናልባት ከመጽሐፉ ሽፋን ላይ የተጻፈውን ከሆነ? ነገር ግን ልጁ የዋዛ አይደለም… ሁለተኛ መጽሐፌን ሰረቁኝ ብሎ አስወርቷል… “ሥራዎቹ የበዓሉ ግርማ ናቸው”ን ዱብዳ ዜና …. ሌሎች ሌሎች…አሁንም በዚህ መጽሐፍ ለተደራሲያን ምክንያታዊ አክብሮት እና በስልታዊ ተዘዋዋሪ አጽንዖት እንዲታሰር ያስገድደናል…. በካፒታሊዝም ብልጠት የተነደፈ ጸሐፊ ይህ ነው ትርፉ!
ከዚህ መጽሐፍ ተምሬአለሁ፡፡ ብዙም ተማርሬያለሁ! ልብወለድ ነው? ወይስ ታሪካዊ መጽሐፍ?  መጣጥፍ? እያልኩ አነበው ጀመር፡፡ የስነ-ጥበብ ጥማቴን ለመወጣት ጊዜዬን ሰጠው… በአንድ መጽሔት የወጡ ሃሳቦች ተደገዋል… ልጁ የፖለቲካ ምሬቱን በልቦለድ ስም ይለጥፋል፡፡ አይተ ስብአት ነጋ ገጸ-ባህሪ ተሰጥቷቸው እናያለን /ገፅ 64/፡፡ ይሄ ልጅ የሰውን የፖለቲካ ጥማት በየመንደሩ የሚወራውን አሉባልታ ስብስብ ለታሪክ ምስክር እንዲሆን እየሞከረ ይኾን? ጠ/ሚኒስትሩ ከህመማቸው  ጀምሮ እስከ እለተ ሞታቸው የዜና እወጃ ከዚያም የቀብር ስነ-ስርዓት በኢትዮጵያ የነበረውን ጊዜ ሊያስታውሰን ይሞክራል… ክረምቱን ተገን በማድረግ የሙት አመቱን ሊያሳስበን ይሆን? እያልኩ በግድ ማንበቤን ቀጠልኩ…
በአስማት ወደ ውሻነት የተቀየረው መሪ ገጸ-ባህሪ እና ሩጫው ከደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል ወደ መሀል ኢትዮጵያ ወደ ቤተ መንግስት ይነጉዳል… በየቦታው የሚሰማውን አሉባልታ ወይንም ምሬት ከዚያም አልፎ በሀገራችን የሚታየውን የገሀድ ገፅታ ሊያሳየን ደፍሯል፡፡ ከአይሱዚ መኪኖች ፍጥነት እስከ የሴቶች መደፈር… ከሥጋ ቆራጭ አስፈሪነት እስከ ትውልድ በጫት በሲጋራና በአልኮል መነደፍ…የገዢው ቡድን (ፓርቲ) ስርዓት…..አድርባይ የ”ፓርቲው” አባላትን ያስቃኘናል፡፡ አንዳንዴም የሚነግረን ተምሳሌታዊ መረጃ ጸሐፊው ይህንንም አውቃለሁ እያለ ይመስላል፡፡
የብልግናን (ጸያፍ ቃል) በመጠቀም ድርሰቴን በመብረቅ በማጀብ አነጋጋሪነቱን ለማወጅ “ግልጽ ነኝ!” ያክል ድፍረት ነው የተሰማኝ… በገፅ 30 ላይ የተጻፈው አባባል የመጽሐፉን ይዘት በሁለት አሀዝ እንዲዋዥቅ አድርጎብኛል፡፡ እንዲሁም ከእንስሳ ጋር የሚደረግን ግንኙነት ያቀረበበት አባባል ወይም ስነ-ጥበባዊ መልዕክት እንዲሁም መፍትሄ በቂ ምላሽ አላስገኘልኝም፡፡
 ጸሐፊው የጥንቷን ኢትዮጵያ አጥብቆ ይመኛታል፡፡ የነበረንን ታላቅነት በአፈ-ታሪካዊ ሀተታ እያዋዛ ሊያስታውሰን ይዳዳል፡፡ የካፒተሊስትን አሰቃቂ ሸክም ሊያሳየን ይሞክራል፡፡ ለኔ ግን ራሱ ከካፒታሊስት የባሰ ጨካኝ ርዕዮተ ኣለም አራማጅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡
ካፒታሊዝም “የትም ፍጭው ዱቄቱን አምጪው!” አይነት የሰግብግብነት ኑፋቄ እንዳለው ሊያስተምረን ይዳዳውና ይህች አገር የምታድገው ህቡዕ ቃል (በአስማት እያለ በሚጠራው) መተት እንደሆነ ሊያሳየን ሲሞክር አይኑን አያሽም፡፡
 በገጽ 7 “የእውነቱን የማይኖር የእውነቱን የማስቅ፣ የእውነቱን የማያለቅስ ትውልድ ይህንን አስቸጋሪ ሀቅ እንዲያይ አይገደድም” ከሚል አባባል ጀምሮ ዘመኑን የሚቃኙ በርካታ ሀተታዎችን በማስቀመጡ  መልካም ሆኖ ሳል  በጸሐፊው ፍላጎት ይህ ትውልድ ወደ አስማታዊው “ጥበብ” እንዲመለስ አስማተኛ ትውልድ እንዲፈጠር ይሽቀዳደማል፡፡
ስለውሻ፣ ስለ ሰው ባሕርያት፣ የእንስሳን እና ያውን ወሲባዊ ግንኙነት፣የሰውን ሳይንሳዊ ትንታኔ፣ ስለአመጋገብ እና ታሪክ ከጎግል የቀዳው መረጃ መሆኑን ጠርጥሬለሁ፡፡ የ“ዣንቶዣራ” ዓይነት አፃፃፍ አሳይቶናል፡፡ በዣንቶዣራ ውስጥ ስለ ፍሪሜስን፣ቴምፕላርስ፣ አሉሚናቲ ታሪካዊ አመጣጣቸው እና ምልክቶቻቸውን የጎግል ፍብርኮች ነበሩ፡፡ ሰውየው ዓለሙን ሁሉ ልብ-ወለድ አድርጎ፤ምትሃታዊ ትውልድ ፈጥሮ ፈሪ ጸሐፊያንን አበራክቶ አዋቂነቱን በልቦለድ መድረክ ማቅረብ መፈለጉ ምን ነካው አስብሎኛል? እባክህ ተገለጥልኝ!
ቻይናዊያን ስለ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን አመለካከት አሳይቶናል፡፡ በገጽ 33 ያ ቻይናዊ የኢትዮጵያኖችን የስራ ጥላቻ ለማስተላለፍ ሞክሯል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያዊያን ስራ ወዳድ ያልሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? ተብለን ስንጠየቅ ምላሹ ሊቀርብልን ይገባ ነበር፡፡ ገበሬው አመቱን ሙሉ አስቦ፣ ዝናብ ጠብቆ፣ ክረምቷን አርሶ፣ አርሞ፣ ጸሉቶ የሚያገኛትን እህል ላልዘራው እና ላላረሰው ወስዶ ሲገብር ምን ያህል ተስፋው አይታጨድ? ምን ያህል በስራው አይለግም? ዛሬ ልደታ፣  ነገ አቦ ከዛም ስም እየጠራ ስራን ማቅለሉ ታይቶን ይሆን? አሁንም ሴቷ መራዛማ አመድ ተነስንሶባት፣ ቀኑን ሙሉ ከአህያ ሳትተናነስ ስትሸከም ውላ ክብሯን እያጣች የምታገኘውን ገቢ ለአንድ ቀን ምሳ አጠራጣሪ እየሆነባት “ያለችበት አግባብ” እያለ እንዴት በስራ አትለግም? ፈረሱ ተላልጦ  ተሸክሞ፤ መሪውን እና ጋሪውን እየጎተተ  እየታየ ያለው  የማን ህዝብ ነው?  /በገጽ 50 የተገለጸውን ተምሳሌታዊ አቀራረብ አድንቄዋለሁ/
ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እለተ ዕረፍታቸው ከታወጀበት ቀን አንስቶ እስከ ቀብራቸው የነበረው ጊዜ ስንት ቀን ነበር? በገጽ 3 ሀተታ ላይ “ይስማዕከ በተፈጥሮ በተለገሰው ክህሎት ሲፈልግ አንዱን ሴኮንድ የዘላለምን ያህል ያረዝመዋል፤ሲያሻው ዘመንን ጠቅልሎ በአንዲት ሰኮንድ ውሥጥ ይከተዋል” በማለት አምልኮታዊ ስብዕናን ያለብሰው አሰትያዬት ሰጪ… ነሐሴ 2004 ግን ለኢትዮጵያ ዝንት አለም አልነበረችምን? በዚህ መጽሐፍ ላይ ግን በሩጫ ታልፋለች! ደራሲው ወደ ገጽ 191 ለመድረስ ነካ ነካ አድርጎ አልፏታል፡፡ ነካ ነካ ያደረጋት እንደው ፖለቲካዊ ለዛ ለማሳደር እንጂ ሌላው አልመስልህ አለኝ..!
ከዚህ መጽሀፍ ምን እንረዳ? የኋላን ታሪክ አንድንማርበት፣ ኢትዮጵያ በመሪዎቿ እንደዋዠቀች፣ ጥቂቶች የሚያወሩባት የሚመራመሩባት ሀገር እንዳለችን፣ የተደበቀ ጥበብ እንዳለ፣ ከህይወት መማር እንዳለብን የሚጠቁሙ አንቀጾች አሉት፡፡ በገጽ 41  የተጠቀሰቸውን አባባል  እንዳለ   ላቅርባት፡፡
“ህይወት እንደ ካርቱን ፊልም ቀለም ዘቅም በሰጣቸው ስዕሎች ተንቀሳቃሽነት ጀብድ የሚፊጸምባት የህልም አለም አይደለችም፡፡ ለመሄድ የራስን ቋንጃ፣ ለመዞር የራስህ ጋንጃ፣ ለመወሰን የራስን ፍርጃ፣ ለመንዳት የራስን አቅም፣ ፍሬን ለመያዝ የራስን ቅልጥም ትጠይቃለች” ሌላም ሌላም መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህንን ካልክ ለምን ሙሉ በሙሉ አድናቆትህን ችረህ አትዘጋም እዳትሉኝ፡፡ ልጁ እኮ የ“ዴርቶጋዳ” ጸሓፊ ነው! ሰው እየደገ ሲመጣ፤ እየተሻሻለ ይሄዳል፣ የበለጠ ይጠነክራል የበለጠ ያይላል እንጂ…. ይደበዝዛል?  መጽሐፍ በሽያጭ ብዛት ፣በገጽ ብዛት ብቻ አይደነቅም፡፡ ምን ተማርኩ? ምን አሳየኝ? ምን የማላውቀውን አስተማረኝ? ምን ለወጠኝ? ምን አንዳስብ አደረገኝ? ምን ጭብጥ አገኘሁበት ተብሎ ይመዘናል…! በቅዠት ብቻ ተለውሶ የሚወራጭ ከኾነ በእኔ እምነት መጽሐፍ ነው ብዬ መጥራት ያዳግተኛል፡፡ ዝና ሊገኝ ይችላል፤ ስምም ሊስፋፋ ይችላል፤ ገንዘብም ሊከማች ይችላል ነገር ግን ሰውን  ወደ ተሻለ ስብዕና መቀየር ካልተቻለ የጥበብ ትልቁን ትርጉም ያመክነዋል፡፡
በክቡር ድንጋይ ውስጥ አስማተኛ እንድንኾን…ሀገራችን “የንጋት ኮከብን” መተት እንድትከተል ጸሐፊው ሊያሳምነን ይሞክራል፡፡ ደራሲው በመጽሐፉ ውስጥ የባዕዳን ርዕዮተአለም ፍልስፍናዎችን ማለትም ካፒታሊዝምንና ሶሻሊዝምን አጥብቆ ይኮንናል፡፡ ታላቅ ክቡር ተብሎ በተገጸው ቃል አማካኝነት አስማታዊ ሃይልን ይዘን እንድናድግ ይወተውተናል፡፡ ለመኾኑ የንጋት ኮከብ ማን ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ የንጋት ኮከብ ተብሎ የተሰየመው የዳዊት ዘር ስር እየሱስ ክርስቶስ ነው! /ራዕይ 21/ ኾኖም ዲያቢሎስንም በንጋት አጥቢያ ኮከብ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡/ኢሳ 14/ ፡፡ በዚህ ደራሲ አገላለጽ የንጋት ኮከብ ማን እንደኾነ የግላችንን መላምት ለመውሰድ እንገደዳለን፡፡ ይኸውም የሰውን ልጅ ከሰውነት ተርታ ወደ ውሻነት ከዚያም ወደ ዘንዶነት እንዲሁም ወደ ፈለግነው ፍጥረት እንድንለወጥ የሚያደርገን የአስማት “ጥበብ” ከዲያቢሎስ እንጂ ከክርስቶስ እንደማይኾን እንተማመናለን፡፡ በአስማት ሃይል ምጣኔ ሃብት ይደግ፤ ሀገርም ትልማ ቢባል ከካፒታሊስቶቹ ፍልስፍና በምን ተለዬ? “የክቡር ድንጋይ” ደራሲ ግን ለዚህች ሀገር ከካፒታሊስቶቹ በተለዬ በአስማታዊ ጥበብ ሊገዛት ይፍጨረጨራል… የባሰ አታምጣ! የህንጻ ጥበብ አስማት ከተባለ የሰለሞን ጥበብ ከምን ሊመደብ ይችላል? በዲያቢሎስ ተመርቶ መኖር እና ዲያቢሎስን መርቶ ገዝቶ መኖር አንድ አይደሉም፡፡ /ሰለሞን አጋንንትን ገዝቷል/
ውሻው ወደ ቤተ-መንግስት ይሮጣል… ጉዞው  ቤተ-መንግስት ላይ አይፈጸምም፡፡ የውሻው ሩጫ ወደ ባለቤቱና ወደልጆቹ ይቀለበሳል፡፡ በአስማታዊ ሃይልም ከውሻነት ወደ ዘንዶነት ይለወጣል… “በንጋት ኮከቡም” መሪነት ወደ “ሰውነት” ይቀየራል፡፡ ባለቤቱን እና የቀድሞ ጓደኛውን በምሕረት ይሸኛቸዋል… “ለባዶ ሰው በቀል ትርጉም የለውምና… ያለውን ሀተታ በሙሉ ለአንባቢያን በመተው
ልጆቹንና መጽሐፍቱን ይዞ ይሄዳል… መጽሐፍት እና ልጆች ትልቅ ሐብት ናቸው፡፡ እውነት ነው፡፡ የመጽሐፍቱ ይዘት ግን ሊመረመር ይገባል… አጥፊም አልሚም መጽሐፍት አሉና!

ሰው ወደ ውሻነት እየተቀየረ ነው….ሰው ወደ አውሬነት እየተለወጠ ነው… ይህ ደግሞ የኾነው “በመሪዎቻችን” ውሻነት ነው…! ጸሐፊያን መሪዎቻችን ናቸው! “ውሻ መሪ እና ውሻ ትውልድ ቀስ በቀስ ይታያሉ…! ይስማዕከ ከውሻነት ወደ ሰውነት እንድንቀየር አጥብቆ ወትውቶናል፡፡ ሰው ከኾን በኋላ ግን ምን አይነት ሰው እንደምንኾን የወሰደው አማራጭ የሚያስተዛዝብ ነው…. መጽሐፉን ያንበንቡት እና የግልዎን ድምዳሜ ይያዙ፡፡