Feb 7, 2022

ሚተራሊዮንን

ሚተራሊዮንን እንደቃረምኳት!
 
(ተስፋ በላይነህ።)



እንደተለመደው ነው። ተመሳሳይ መነሻ ጭብጥ፥ መሰረታዊ ፅንሰ ሐሳብ፥ የተራቀቀ የጉዞ ሰልፍ። እንደተለመደው ነው! 

እመጓ፣ ዝጎራ እና መርበብት በተመሳሳይ አውድ፥ በተያያዘ ይዘት እና ገፅ ባህርይ፥ ውስጣዊ ማንነታችንን /በስነልቦና ውቅር አንደበታችን ላይ/ የሚስተዋለውን ‘ደዌ’ ታሳቢ በማድረግ፤ ያለንን ከሌለን፥ የሌለንን ካለን ጋር በተቃርኖ ስሌት እያዋዛ፤ የነበርንበትን ካለንበት ፥ ያለንበትን ከነባራዊው ዓለም እንዲሁም ከመጭው እኛነታችን ጋር በማስተሳስር የአሁንን ወርቃማ እድል ፈልቅቀን እናጌጥበት ዘንድ ይማፀናል። እንደተለመደው ነው። 

ስሌት እና ብልጠት ‘መድኃኒቶቻችን’ እንደማይሆኑ በገፅ 251 ላይ የአብዛኞቻችን ገፀ ባሕርይ ሆኖ ዋጋ እያስከፈለን እንደሆነ ያመላክተናል። እንደተለመደው! 

ሚቶሎጂ ነው። ምናልባትም ሃይማኖታዊ፥ በሚያስደንቅ ሁኔታም ሳይንሳዊ ነው። በልማዳዊ አስተሳስባችን ላይ የሚዘወተሩ ተግባራትን ከሳይንሳዊ ፅንሰ ሐሳቦች ጋር እያጣመረ አጭር መግለጫ ጥሎ ያልፋል። ስዎች ተነግሯቸው ካላመኑ በተግባር ሊማሩ ግድ ነው። <<the law of Effect>> ገፅ 250።energy deception ገፅ 219። ስለ ውሃ memory ገፅ 186 አይነት ዝርዝር ምሳሌዎችን መጥቀስ እንችላለን። 

የሚተራሊዮን ውበት ጥልቅ ድረስ ከሚደርሰው ሕመሟ ጋር ተስፋን እና ቀቢፀ ተስፋን በአንድ ማዕድ እንድንሳትፍም ያደርጋል። እንደ ሀገር ያሉንን ሁሉ፥  ጥልቅ ባህር ድረስ እየቃኜ ሲያስቆጥረን፥ ባዶ ማዕድ ላይ ለመዝገን እርስ በርሳችን የሚያነካክሰንን ወስጠ መሰረት ዳሰሳም ያደርጋል። እንደተለመደው ነው።   

አንዳንዶች እመጓንም ይሁን ሌሎች የዶክተር ዓለማየሁ ዋሴን መፅሐፍት እንደ ቅዥት እና አጉል የመንጠራራት ‘ምናባዊ ዴሉዥን’ አድርገው ይቆጥሯቸዋል። የሌለንን እና ያልሆንነው እኛነታችን እየለጠጠ በባዶ ሙሊት 'የተወጠረ ፊኛ' አድርገውም ይገልፁታል። ምንም ማድረግ አይቻልም፥ እንደተለመደው ነው። 

ይህንን ሐሳብ ለመሟገት ጥንታዊ የብራና መፅሐፍትን ጥልቅ ዳሰሳ አድርጎ፥ ዘመናዊ ከሚሉት ሳይንሳዊ ትወራዎች እና ጥናቶች ጋር እያስተሳስሩ መወያዬት የወግ ነው። 

ሚተራሊዮን ልክ እንደ ቀደሙት የደራሲው ስራዎች ጉዞን፥ ቁፋሮን፥ ተፈጥሮአዊ ፀጋዎችን መዳሰስ፥ ምርምር ጥናቶችን ማቅረብ፥ ራስን መገምገም፥ ችኩልነታችንን እና ስግብግብነታችንን፥ ጥራዝ ነጠቅነታችንን እና ቆሞ ቀርነታችንን በዋና ገፀ ባህርይው አምሳያነት በራሱ ላይ ሰይሞ የችግሮቻችንን ምንጮች በቅደም ተከተል ያስቀምጣል። የችግርን ምንጭ ወደ ሌላው ሃይቅ ከመቀሰር ይልቅ ወደ ራስ ወንዝ መሻገርን ይመርጣል። ሰከላ ግሽ ዓባይ ላይ የነበረው ትዕይንት ለዚህ ገላጭ ነው።  

262 ገፆች ያሉት መፅሐፉ ልክ እንደ ጣፋጭ ማዕድ ቶሎ በልቼው ቶሎ በጨርስኩት የሚያስብል አይነት ነው። 

የኢትዮጵያን ብልፅግና አጥብቆ ይሻል። የብልፅግና መርህ /ፍኖቱንም/ ሳይሰስት ከእነድክመታችን ፥ ከእነ ጉልበታችን ፤ ከእነ ነውራችን ፥ ከእነ ጌጣችን በዝርዝር ያሰናዳል። እንደተለመደው ነው!

አይሁድ፣ እስልምና እና ክርስትና ሃይማኖቶች በኢትዮጵያ እንዴት ተቆራኝተው እንደሚኖሩ፤ ነቢል በአባይ ውሃ ላይ ያለውን ቁጭት፥ የአይሁድ እምነት መሪ የሆኑትን አባ ዮናታንን ከገዳማዊያን አባቶች ጋር ያስተሳሰረበት ዘዴ ለዚህ አመላካች ነው። 

የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ቀለማዊ ገፅታዎች በምን ሕብረት እና ሕብረቀለማዊ ትስስር ለመግለፅም ገፅ 259 አይነተኛ የሰበዝ አካል ነው። 

‘ጎንደሬ ፈትሎ ዶርዜ የሸመነው፥ ጥልፉን አክሱማይ ጠለፈው? አማሴን?፥ ዐይነ ርግቡን ማን ሰጣት? አፋር ሱማሊው? አንጠረኛው ማን ነው ሽናሻው? መንበሯስ ከጅማ ምድር የበቀለ ነው ሲል በወፍ በረር ያስተሳስረናል።’ 
 
ውሃ፣ ማዕድናት እና እፅዋት ፀጋዎቻችን ላይ መሰረታዊ የሃይማኖት ንባቦችን፥ ከሳይንሳዊ መላምቶች እና ሀተታዎች ጋር በማጣመር ፍንጭ ሰጪ ገላጭ መፅሐፍ በመሆኑ፤ የማይነካካው የመንግስት ተቋም ዘርፍ ባለመኖሩም ፥ የዘመኑ የብልፅግና መሪዎች ዘንድ ሊዳረስ የሚገባው ዘመንን የሚዋጅ ገፀ በረከት ይመስለኛል።  

በተለይም ለ22ቱ የመንግስት ካቢኔዎች መፅሐፉ ይዳረስ ዘንድ በስጦታ መልክ እንዲቀርብ የሚያስችል የአስተባባሪ [ኃላፊነት] ብወስድ ምርጫዬ ነው። 

በአጭሩ ለሚተራሊዮን በቀረበው ምርቃት መተርጉማን ቃላት እንሰነባበት። 
 
ውሃ፣ አፈር፣ ዕብን/ድንጋይ -ማዕድን/፣ እሳት፣ ንፋስ፣ ዘር እፅዋት የወለድሺው ይውለድሽ ፥ ይስማሙልሽ. . .! በሚል በደርዝ ተቀምጠዋል። 

እንደተለመደው ከድንቁርና ግርሻ የሚያነቃ፥ ለኔ ብጤ ድውያን ፈውስ ነው! እንደተለመደው ነው። 

መልካም ንባብ!

No comments: