Mar 18, 2018

"ዩቶፕያ-UTOPIA”





በእያንዳንዳችን ነፍስ ውስጥ የምትቀመጥ ከተማ አለች፡፡ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የነገሠች አገር አለች፡፡ 


ይሕች ከተማ/አገር ወደ ዚህች ምድር ከመምጣታችን በፊት ሥንኖርባት የነበረች በመሆኗ መንፈሳቸውን እና ልባቸውን ያነቁ ግለሰቦች በጭላንጭል ሲመለከቷት እና ሲያስተውሏት፤ ከወንዙ እየቀዱ፤ ከተራራው ነፋስ እየቀዘፉ፤ ከጫካው ማር እየቆረጡ፤ ከአኗኗር ሥርኣቱ እየተቋደሱ ምስክራቸውን ይሰጡናል፡፡


መንፈሳችን እና ልቡናችን የደነደነው፤ አዕምሮ እና ልባችን የተቀየጠው እኛ ብዙኃኖቹ ግን ይሕ ቋንቋ አይገባንም፡፡ነፍስ እና ልብ ከነመፈጠራቸው እንኳ ዘንግተን፤ በአስኳላው ትምሕርት “ተምረን”፤ በቸልታ መዘውር ውስጥ እየተወዛወዝን እንገኛለን፡፡ -ያለ እውቀት!


ጠቢቡ ሠለሞን ከመሰከራቸው ምስክሮች ሁሉ “ነፍስ እውቀት የሌለባት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም” የሚለው በከፍታ ማማ ላይ የሚጻፍ ነው፡፡


ያለ እውቀት መኖር መወዛወዝ፤ ያለ ምርምር መኖር መደናገር፡፡ በሁለት ጽንፎች ተተብትበን ስጋችንን ተሸክመን፤ ሕይወትን እንደ ሲሲፈስ ስንገፋት እንኖራለን፡፡


 ወደ የትየለሌ እንነጉዳለንየማይነጋው ያለ እውቀት ነፍስን በሥጋ ሥላጨለምን በድንግዝግዝ ስለምንደናበር ነው!!


በቸልታ እንደመኖር ሌላ የሲኦል ተምሳሌት አይኖርም፡፡ ሌላ አለ ካላችሁኝ ነፍስ ያለ እውቀት ስትባዝን እንል ይሆናል፡፡


ቸልታ ambivalence በሁለት ተቃርኖዎች መካከል መኖር አንዱንም አለማወቅ ነው፡፡ ለሁለት ጌታ እንደመገዛት፡፡ ከአንድነት/ውህደት ይልቅ ለሁለትነት/ምንታዌነት ማጎብደድ ማለት ነው፡፡ ይህ የብዙዎቻችን የዘመን ሕመም ነው!!


ግለሰቦች በቸልታ ሲጠማዘዙ፤ የአንድ አገር ሕዝቦች ደግሞ በቋንቋ የማይግባቡ ከሆኑ፤ በታሪክ እና በሥነ-ልቡናቸው ሕብረትን የማይፈጥሩ ሲሆኑ…ለባሕል ለታሪካቸው ለሥነፅሁፍ ስራተ መንግስታቸው ስልት አኗኗራቸው ደንታ ቢስ ሲሆኑ  ያ ምድር አትጠራጠሩ -ሲኦል ነው፡፡


ገነት ሊሆን የሚገባው ምድር ሲኦል ማድረጋችን ላይ እንደሆንን ስንቶቻችን እንተማመን ይሆን?


በልሳን የማይታረቅ አገር፤ በደቦ የማይሠራ ሕዝብ፤ በሽምግልና እና በእውቀት የማይታዘዝ ፍጥረት መነሻውም መድረሻውም ሲኦል መሆኑ አይቀሬ ነው!


“ያቺ” ፍጽምና የሰፈነባት ከተማ እያልን የምናስባት “ምድር”፡፡ ከዚህ በፊት የጥንት አያቶቻችን የኖሩባትን አገር `ሠማይ ላይ` ከማሰሳችን በፊት ምድር ላይ ብትሆንሥ?” ለን የመጠየቅ ሙሉ አዕምሮአዊ መብትም አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ 


አዕምሮአዊ መብት ደግሞ የራስ ንብረት ነው፡፡ አእምሯዊ መብት ነጻነት ነው!! “ፈጠራ” ሆኖ ቢቀርብ እንኳ ፈጠራው ማስረጃ/መረጃ የሚሉትን ሣይንሳዊ ‹‹ዶሴዎችን›› ካቀረበልን እና በጥናት/አመክንዮ ከተደገፈልን የአገር ሐብት፣ መመኪያ እና መኖርያ <<ቅርስ>> መሆን ይቻለዋል! ቅርስ ጥበቃ ትልቁ መመኪያ ግንባችን ነው::


ፈጠራ ፡- አእምሮ፣ ልብ እና የነፍስን ንቃት የሚጠይቅ መሆኑ አልቀረም! ፈጠራ የነፍስ አውቀት ነው፡፡


ያቺን አገር ምድር ላይ ስንፈልጋት እና መጠሪያ ስሟን ስናስቀምጠው “ዩቶፕያ” እያሉ እንደሰየሟት የኋላ መጽሐፍት ይመሰክሩልናል፡፡  


()ቶፕያ! ማን ናት…? ለምንስ ይህ ስም ተሠጠ?


ይሕ ስም በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ አለ፡፡ ነጻነት፣ እውነት፣ ፍቅር እና አንድነትን ሚማጸን ልብ ውስጥ የተቀረጸ ስም ነው፡፡ በወርቅ የተለበደም ድርሳን ነው፡፡ በማኅተም ተክትሞ በምስጢር የተቀመጠ!!


ወደ ገሃዱ አማናዊ ለም (በስጋ) ስንገለጥ ከየት እንደመጣን ማወቅ ስንሻ ይሕ ስም እንደ ገደል ማሚቶ በልባችን መቃብር/ዋሻ ውስጥ ያስተጋባል፡፡ የሚሰማው ያደምጠዋል፡፡ የሚያደምጠው ይጠብቀዋል!!


አውሮጳውያን ከበርካታ አረመኔያዊ ሥርዓቶቻቸው ማግሥትክርስትናን ከተቀበሉ ማግሥት ከክርስትናም ከተራራቁ ማግሥት በጭለማው ዘመን ውስጥ በሚኳትኑበት ዘመን... ጥቂቶች የፈለቀው ዩቶፕያ የተሰኘ ድርሰት ከእንቅልፋቸው እንዳነቃቸው ይነገራል፡፡ ይሕ ስም/መጽሐፍ ከጭለማው ዘመን አራራቃቸው፡፡ ብርሓንን ሲሹ ይሕ ስም ከለላ ሆኖ ደረሰላቸው፤ መታደስን ሬነሰንስን ሲመኙ መጠጊያ አደረጋቸው፡፡ ኤጅ ኦፍ ኢንላይትመንት ሲማፀኑ መልስ ሆኖቸው ይህ ስም::-ዩቶፕያ!!


በእርግጥ ዩቶፕያ የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው (ከ1478 – 1535 የኖረ) እንግሊዛዊው ሰር ቶማስ ሞር ነውይባላል፡፡ ቃሉም በ1516 ዓመተ ምሕረት በዚህ ቃል ርዕስነት በተጻፈ እና ቆይቶ ለሕትመት በበቃው “ልብ ወለድ” መጽሐፍ የተገለጸ ነው፡፡ በርካቶች መጽሐፉ ተምኔት ነው ይላሉ፡፡

 

ዩቶፕያን በርካቶች ማማ በሰማይ ላይ ሲሏት ይደመጣሉ፡፡ በልብ ወለድ መልክ የተቀመጠች “ከተማ/አገር” በምድር ላይ ፍጹማዊ ከተማ ሆና የምትጠቀስ - ነገር ግን ምናባዊ የሆነች ናት የፍፅምና ተምሳሌት ደብተራ ናት ሲሉም ይነበባሉ፡፡ 


በርካቶች “ምናባዊ ናት ልትፈጠር አትችልም ብለውም ሲደመድሙ ጥቂቶች ግን ምድር ላይ የነበረች/መኖርም የምትችል አገር/ከተማ ነች ይሏታል፡፡


ኢትዮጵያዊቷ የመካነ ጥናት መምሕር የሆኑት ዶ/ር መስከረም ለቺሳ ይሕን ፈቃድ በመውሰድ ልቡናቸውን እና የነፍሳቸውን ጓዳ በመፈተሸ ይሕች የምናብ አገር የኛዋ ኢትዮጵያ ናት!” ሲሉ በመጽሐፍ መልክ አቅርበውልናል፡፡ 


እሳቸው ማለቴ የሐሳባቸውን ክብደት እና አክብሮት በማሰብ እንጂ በእድሜያቸው ለስጋ አንቱታነት ገና አልታጩም! ከዚህም በኋ እሷ እያልኩኝ እንድጠራ ይፈቀድልኝ!


ዶ/ር መስከረም ያሳተመችው መጽፍ (ኢ)ዩቶፕያ ይሰኛል፡፡ የትርጉም ሥራና የምርምር ማስታዎሻዎችን የያዘ ሲሆን፤ ‹‹ለእንግሊዝ መንግሥታዊና ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ምክንያት የኾነው፡ የመካከለኛው ዘመን፡ የኢትዮጵያ ሥርዓተ- መንግሥትና የሕዝቧ አኗኗር..››  ‹(ኢ)ዩቶፕያ›› ፤ ‹‹እውነተኛ ኅዳሴ ወይም ተሃድሶ ፡ ከምንታዌነት (dualism)፡ ወደ ተዋሕዶ (unity) የሚደረግ ኹሉን አቀፍ ኀብረተሰባዊ የንስሓ ጉዞ መሆኑን የሚያሳይ፤ ተጨባጭ እና ታሪካዊ ማስረጃ›› በሚል የፊት ገጽ ዝርዝር የቀረበው መጽሐፍ የታተመው በ2008 ዓ.ም ነው፡፡ ታድያ ይሕን መጽሐፍ ሳነብ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት የምስቅልቅል ዘመን ፖለቲካ፣ ማሕበረሳበዊ ሕመም እና ሥነ ልቡና ክስረት፤ መፍትኄ ቢሆን በሚል ካሰብኳቸው መጽሐፍት ውስጥ በቀዳሚነት የምጠቀሰው ነው፡፡


ዪቶፕያ/ዩቶፕያኒዝም ምንድን ነው…?

Utopianism” የሚለው ቃል፡ “Utopia” ከሚለው የግሪክ ቃልየተገኘ ነው ይላሉ ቃሉ በስፋት የተጻፈውና የተነገረው16ኛይቱ ክፍለ ዘመን አውሮፓ ሲኾን፡ አውሮፓውያን፡በወቅቱ፡ ከአስከፊው የጨለማው ዘመን Dark Age) ወጥተው ወደዘመነ አብርሆት Age of Enlightenment) ለመሸጋገርና የኅብረተሰባቸውን ኑሮ በኹሉም አቅጣጫለመቀየርና ለማሻሻል ሲነሱ የተፈጠረ አህጕርአቀፍ የለውጥሞገድ Continental movement) ነበረ። ለአውሮፓውያኑ ኅዳሴRenaissance) ዋና አንቀሳቃሽ የነበረው አስተሳሰብ፡ ይኸውዩቶፕያዊነትUtopianism ነው።

ዩቶፕያዊነት  በኹሉም የሰው ልጆች የኑሮ ዘርፎች ዙርያ፡አዲስና አዎንታዊ እይታ መያዝን የሚጠይቅ፡ ፍጹም የኾነ ታደስ መንፈስ ነው።

ሰው፡ ምድራዊ ሕይወቱን ከሰማያዊ ሕይወቱ ጋር የሚያስማማበትና በምድር የመኖሩን ትርጕምና ዓላማ፡ከፈጣሪው አግኝቶ፡ ራሱንና ማኅበረሰቡን በዚያ በተቃኘ ተግባራዊ ሕይወት፡ ከፍ ላለ ልዕልና የሚያበቃበት ጉዞ ነው። 


ይኽ ጉዞ፡ ብዙውን ጊዜ የሰው ልጆችን የግልና የጋራ ኗኗር አደጋ ላይ ከሚጥሉት ጽንፈኛ አመለካከቶችና ጥጎች እያወጣ፡ ወደሚያስማማው መካከለኛ አስተሳሰብና ተግባር የሚያመጣ የእርቅ/ተዋህዶ ጉዞ ነው። 


ሃይማኖትን፣ ተፈጥሮን፣ ሥነ-መንግሥትን፣ ምጣኔ-ሃብትን፣ ማኅበራዊ ሕይወትን፣ሥልጣኔን እና ባህልን ጭምር በተመለከተ፡ ግማሽ እውነት ይዘው እርስ በርስ የሚቃረኑ አስተሳሰቦችና ተግባሮች፡በዩቶፕያዊ አስተሳሰብ ይታረቃሉ።


በዩቶፕያዊው እይታ መሠረት፡ በግለሰብና በማኅበረሰብ፣በመንግሥትና በሕዝብ፣ በወንድና በሴት፣ በሃሳባዊውና በተግባራዊው፣ በዘለዓለማዊውና በጊዜያዊው፣ በሰማያዊውና በምድራዊው፣ በተፈጥሯዊውና በዘመናዊው፣ በገጠሬውና በከተሜው፣ በለውጥና በቀጣይነት፣ በተቀደሰውና በተራው ወዘተ... መካከል ያሉ የሚያስተጻርሩ ልዩነቶች በሙሉ፡ በተዛባ ሓሳዌና ምንታዌ (Dualist) አስተሳሰብ ምክንያት የሚመጡ ጠንቆች ናቸው። 

እነዚህን አንድ የሚያደርጓቸውን እውነተኛ የአስተሳሰብ መንገዶች በመለየት፡ በጥበብ በማረቅና ማስማማት ፍትሓዊ ማኅበረሰብ መመሥረት፡ የዩቶፕያዊነትUtopianism) እንቅስቃሴ ዋነኛ ግብ ነው። 


በዚህም ምክንያት፡ኅዳሴ/ተሃድሶ” እና ተዋህዶ” መካከል በዘመናችንየተፈጠረው ልዩነት በራሱ፡ የተዛባ ሓሳዌ አስተሳሰብ ያመጣውምንታዌነት መኾኑን እንረዳለን፤ ምክንያቱም፡ ያለተዋህዶ ተሃድሶ የለምና።


ዩቶፕያዊነት፡ በሰው ልጆች ውስጥ ያለውን ፍቅር፣ ሰላም፣ደስታ፣ እኵልነት፣ ፍትሕ፣ እና በጠቅላላው፡ መልካም የኾነውን ነገር ኹሉ የመፈለግ ዝንባሌን የሚገልጽ ቃል ነው። ይህ ጽንሰሃሳብ፡ የአውሮፓውያን የብቻቸው ሀብት አይደለም። እንዲያውም፡ አስተሳሰቡ የተገኘው ጨርሶ ከአውሮፓውያን ዘንድ አይደለም። ይልቁንም፡ የእግዚአብሔር አገር፣ የጠቢባን ምድር እና የዓለም ብርሃን ከኾነችው ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት መንፈስ ጋር የሚያያዝ ቃል፣ አስተሳሰብ እና ተግባር ነው።


በእርግጥ፡ “ዩቶፕያ” የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው፡ እንግሊዛዊው ሰር ቶማስ ሞር (1478 – 1535) ነው። ቃሉም፡ 1516 ዓመተ ምህረት፡ በዚህ ቃል ርእስነት፡የጻፈውና ያሳተመው “ልብ ወለድ” መጽሓፍ እንደሆነ እላይ ተመልክተናል “ልብ ወለዱ” አንዲት፡ “ዩቶፕያ” በተሰኘች ሩቅ "ደሴት" ላይ፡ ከሌሎች ራቅ ብለው የሚኖሩ “ዩቶፕያውያን” የሚባሉ ሕዝቦች፡ እንዴት፡ በእኵልነት፣ በፍቅር፣ በሃይማኖት፣በሥነ-ምግባር ልዕልና፣ በፍትሕ እና በደስታ እንደሚኖሩ፡በሰፊው የሚተርክ ሥራ ነው። 


በምዕራባውያን ምሑራን ዘንድ፡ “Utopia” የሚለው ቃል፡ ”‘Ou’ እና ‘Topos’ ከሚሉ ኹለትየግሪክ ቃላት የተውጣጣ ነው“ የሚል እምነት አለ። “Ou” ማለት፡ ”No” የሚለው የእንግሊዘኛው ቃል አቻ ሲኾን፡ “Topos” ማለት ደግሞ፡ ”Place” ማለት ነው። ስለኾነም፡ “Utopia” ማለት፡“‘Noplace’ ማለት ነው” የሚል ድምዳሜ አለ።


ያም ማለት፡ “የሌለ ቦታ” ወይም “እውን ያልኾነ ቦታ” እንደማለት ነው። እንግዲህ፡ እውን ስላልኾነ ቦታ በአንድ ግለሰብ የተጻፈልብወለድ፡” “በአህጕር ደረጃ የለውጥ ማዕበልን ያነሳሳል” ብሎ ለማመን ይከብዳል። ከዚያ ይልቅ፡ ቃሉ፡ ኢትዮጵያ” ጋር፡የትርጕም ብቻ ሳይኾን የታሪክ ዝምድናም እንዳለው መገመትየሚያስችሉ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ትለናለች ወ/ሮ መስከረም:: /ፒኤችዲ/


ከነዚህ መካከል አንዱን ብቻ ለመጥቀስ ያኽል፡ ራሱ “Utopia” የሚለው ቃል፡ምዕራባውያኑ ምሑራን እንደሚያምኑት፡ ”Eutopia” የሚል ደባል ቃል ያለው መኾኑና፡ የቶማስ ሞር “ልብ ወለድ ኋላ ርእሱ ተቀይሮ  “Utopia” ከመኾኑ በፊት፡ በመጀመርያ ”Eutopia” በሚል ስም ወጥቶ የነበረ መኾኑ፡ በታሪክ የሚታወቅ እውነታ መኾኑን መግለጽ ከበቂ ባላይ ነው 


”Eu” የሚለው ቃል፡ በግሪክ፡ “መልካም” ማለት ስለኾነ፡ “Eutopia” የሚለው ቃልም፡ትርጕሙ፡ “መልካም ቦታ” ማለት ይኾናል። ይህ፡ “ጦብያ” ከሚባለው የግዕዝ ቃል ከኾነው ኢትዮጵያ“ ሌላኛው ስሟ ጋር በትርጕም አንድ መሆኑን ልብ ይሏል


ዩቶፕያዊነት ወይም ኢትዮጵያዊነት “የሰው ልጅ ምድራዊ አኗኗር፡ መልካምና ገነታዊ መኾን ይችላል” ብሎ ማመንን የሚያስገኝ እውነት፣ እውቀትና መንፈስ ነው።  


በዚህ እምነት ላይ ያልተመሠረተ ተግባር፣ ሙያ፣ አገልግሎት፣ ወይም ኗኗር ኹሉ፡ ራስንና ሌላውን፡ ወደተሻለውና ወደቀናው ህልውና ለማምጣት ለሚደረግ ማናቸውንም ጥረት ኃይል ሊሰጥ የሚችለው እውነት ላይ ያልቆመ በመኾኑ፡ ፍሬያማነቱና ቀጣይነቱ፡ አስተማማኝ አይኾንም።


የዘመናችን የኢትዮጵያ/አፍሪካ ትውልድ፡ ዩቶፕያዊው እይታና አስተሳሰብ፡ በእጅጉ ያስፈልገዋል። የዩቶፕያዊነት እንቅስቃሴ ጠንሳሾች በነበሩት አውሮፓውያን አሳሾች ዘንድ “የካህኑ ዮሓንስ አገር” Prester John’s Land) ትባል የነበረችው ኢትዮጵያና በርሷ ተጽዕኖ ሥር የነበረችው መላዋ አፍሪካ፡ ይኽን ለአውሮፓ ያበረከተችውን ርእዮትና መንፈሳዊ ኃይል፡ ዛሬ፡በድጋሜ የራሷ ልታደርገው ይገባታል። 


ይህ፡ ከአምስት መቶ ዓመታት በፊት፡ በአውሮፓ ተካሂዶ እንደነበረው ያለ ታላቅና ሕዝባዊ የምርምርና የእውቀት ብርሃንን ይፈልጋል። ይህ ምርምር፡ “ዩቶፕያዊነት የኢትዮጵያዊነት አውሮፓዊ አቻ ትርጕሙ መኾኑን ዐውቆ፡ በዚያ ዙርያ የተጻፉ ጽሑፎችንናታሪካዊ ክስተቶችን እየመረመሩ፡ ወደትክክለኛ ኢትዮጵያዊ ማንነታቸው በመመለስ፡ የአሁኑን የኢትዮጵያ ትውልድ፡ ከፍወዳለ አስተሳሰብና ንቃተ ሕሊና፡ በትምህርት ማምጣትን ይጠይቃል።


አውሮጵያውያን ያለሟት ያቺ ምናባዊ አገር የእኛዋ ኢትዮጵያነች ብሎ ማሰብ በራሱ እብደት የሚመስላቸው ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ስያሜ እንኳ በመጠሪያነት ደረጃ የማፈሪያ እና የሽንፈት መሸሸጊያ በሆነበት በአሁኑ ዘመን፤ ብሔርተኝነት ማምለጫ እና ማጌጭያ በሆነበት እርኩስ ዘመን ፊት ቀርቦ ይሕንን ሐሳብ ማሰብ በራሱ "እብደት" መባሉ  የሚደንቅ አይሆንም፡፡


መጽሐፉ 348 ገጾች ሲኖሩት፤ ከገጽ 15- ገጽ 216 የሰር ቶማስ  የትርጉም ሥራ ሲይዝ፤ በቀጣይ ደግሞ የጸሐፊዋን በመጽሐፉ ላይ ያደረገችውን ጥናት ያካተተ ነው፡፡

ዩቶፕያን ኢትዮጵያ ነች ብሎ ማሰብ/መደምደም ከባድ ድፍረትን ይጠይቃል፡፡ ከማሕበረሰብ መገለለልን “ማበድን” ሊያስከትል ይችላል፡፡ ጠለቅ ያለን መሠረት እና በራስ የመተማመንን መንፈስንም ጭምር ይፈትሻል፡፡ የነፍስ እውቀትንም አብዝቶ ይሻል፡፡


በበኩሌ ከበርካታ ዓመታት በፊት ዩቶፕያ የሚለው ስያሜ ለምን ተሰጠ? ለምን የፍጹማዊ/ምናባዊ አገር ስያሜነት ተደርጎ ተቀመጠ? የሚሉ ጥያቄዎች በአዕምሮዬ ይመላለሱ ነበር፡፡ የነጮቹን መረጃ ብቃርምም፤ ወደ ነፍሴ ስለማላስጠጋው፤የልቤን የሚሞላ ሥራ እፈልግ ነበር፡፡ ዶ/ር መስከረም መቃረሜን ተገንዝባ አለውልህ! ያለችን ይመስለኛል:: የኔ ብጤ "መፃተኞች" ካሉ ማለቴ ነው፡፡


የቶማስ ር መማፀኛ ከተማን  “ዩቶፕያ” ድርሰት ስናነብ ፤ በተለያዩ ገጾች ውስጥ የገጠሪቷን ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿን በልቡናዬ እየሳልኩ ለመቆዘም አስገድዶኛል፡፡ ደጋግሜ እመሰጣለሁ፤ “ዮቶፕያበተባለችው የሰር ቶማስ ር ደሴት ይፈጸም የነበረው የአኗዋር ሥርዓት እና ልማድ በምድር ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገኘቱ የቆዬ ሕሊናዬ ከባዶ ካልተገለጠ ዐለም ሊስበው አይችልም፡፡ ያላየሁትን መሳል፡፡ ያልሳሉትን ማለም፤ ያልኖሩትን ማኖር እንዴት ይታሰባል? ዴዥያቩ እንደሚሉት አይነት ድንግዝግዝ አርምሞም አይደለም!! 


የቀደሞ ማሕበረሰባችንን አኗኗር በምናባችን መሳል የምንችለው የቶማስ ሞርን መጽሐፍ ስንመለከት ነው፡፡ ይህ ለዮቶፕያ ኢትዮጵያዊነት ቀደሚው ተገላጭ ምስክር ነው፡፡ 

ምንም እንኳ የመጽሐፉ ጸሐፊ ምናቡን ከእውኑ አገር ጋር ላለማዛመድ መድከም ቢጠበቅበትም፤ በተለያዩ ገለጻዎች እና ግርምቶቹ ግን ይሕች ምናባዊ አገር በአካል የተገለጠች የኛዋ ኢትዮጵያ መሆኗን ቢያንስ “በስውሩ የአዕምሯችን” ክፍል መስካሪዎቹ እኛው የኖርንባት በከፊልም የምናውቃት አያቶቻችን የተመላለሱባት የገጠሪቷ ኢትዮጵያ መሆኗ አልቀርም!


ዶ/ር መስከረምም ይሕንን በመገንዘብ በእያንዳንዱ ገጽ የተገለጸውን የአኗኗር ልማድ ከጥንት ኢትዮጵያኖች አኗኗር ጋር በማዛመድ፤ አሁን ርዝርራዡ ካለም እያጣመረች ጥናቷን እና መላምቷን በማቅረብ ምስክርነቷን አጽንታለች፡፡ 


በአሜሪካን ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋም /ለዚህ ጥናት የሚደጉም እርዳታ ሰጭ ባታገኝም/፤ በከፍተኛ መስዋእትነት ሌት ተቀን በመልፋት በትዕግስት እና በፈጣሪ እርዳታ መጽሐፉ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ለአንባቢ እንዲቀርብ ሆኗል፡፡ ነጮቹ ርዕሱን እንዴት እንደሚፈሩት መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ግለሰብ ሊያነበው እና ሊነጋገርበት የሚገባ ትልቅ ነው፡፡ በተለይ በተለይ አቅጣጫው ለጠፋበት ለአሁኑ ትውልድ!!


መጽሐፉ ጎደለው ብዬ የማስበው ነገር ቢኖር (በቅድሚያ) ከትርጉም ሥራው እኩል የጥናት ሥራው ሰፋ ያለ ትንተና ቢኖረውና ኢትዮጵያ በምን መልኩ ይሕንን ማሕበረሰባዊ የአኗኗር ስርዓት እንደጣችው ጥልቅ ታሪካዊ ዳሰሳ ቢያቀርብ የሚለው ሲሆን፤ የተለያዩ ሓይማኖቶችን ቀፈች አገር ዩቶፕያኒዝም የሚባለው አስተሳሰብ/መንፈስ የሓይማኖት ቅጥር ስብከት ብቻ ሆኖ እንዳይቀር(እንዳይተረጎም)፤ ሓይማኖታዊ ትርጓሜ ብቻም ሳይወሰን፤ ሰፊውን ማሕበረሰብ አሁን ካለን ነባራዊ/ተጨባጭ ፖለቲካዊ (በአራቱ ማእዘን ክፍል) እና ማሕበረሰባዊ ምዘና ከዳሎል እስከ ደጀን ተለክቶ የሚቀርብበት መንገድ ማሳዬት ቢቻል ይበጃል እላለሁ፡፡ (ቀጣይ ሥራም እንጠብቃለን ብዬ እገምታለሁ!)


ከቅን መንፈስ እና ከቀና ልቡና የሚነበብ ከሆነ እና ተጨማሪ ጥናት ምርምር እንዲሁም ትኩረት ቢሰጠው፤ በምርምር ተቋምም ሆነ በከፍተኛ ትምሕርት ተቋማት፤ ከለጋ ሕጻናት ጀምሮ ባሉ እድሜዎች እየተሠጠ አሁን ያለንበትን የሥጋ እና የመንፈስ እስራተ-ዘመን የሚያስወግድ መነበብ ያለበት፤ ሰፊ ጥናትን የሚጥቅ የ21ኛው ክ/ዘመን ቅርስ ነው ብል እያጋነንኩ አይሆንም፡፡


ኢትዮጵያዊ ከሆናችሁ… ኢትዮጵያን የምትናፍቁ ከሆናችሁመጽሐፉን ፈትሹት፡፡

“ዩቶፕያ” ማን ናት…የትሥ ናት? ለምትሉ ፤ ኢ(ዩ)ቶፕያ ምድር ላይ ናት፡፡ ያውም በመካከልህ… የረገጥካት መሬትህ ናት…!  

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር::


መልካም ንባብ!

No comments: