Jul 19, 2015

ወሪሳ የውድቅት ፈለጎች



ወሪሳ የውድቅት ፈለጎች

ተስፋ በላይነህ


ዓለማየሁ ገላጋይን በአጫጭር ሐሳቦቹ ያወቀው፤ ጣዕሙን ያጣጣመውና የልብ ምት ሕመምን በጣጫፍና ከሽን ባሉ ቃላቶች አዋዝቶ፤ ጠበሉን ሲረጨን- በረዥሙ ስንተነፍስ…የዕለት ተዕለት ስብራቶቻችንን ሲጠግንል፣ የንዋይ ምታቶቻችንን በፍቅረ ቢጽ ሲያስታምምልን  የነበረ ጸሐፊ ነው፡፡ አምደኞቹ የተሰበሰቡበት “ጀምዐ” ለሕብረተሰቡ ልብ ምትም ሆነ አዕምሮ ልጓም ቀና አስተሳሰብ ቀማሪ ስለነበሩ በእነ “አምበርብር” ስርዓት ውስጥ አልተፈለጉም፡፡ (አምጰርጵር የወሪሳ ድርሰት ውስጥ አምባገነን ገጸባሕርይ የተላበሰ ግለሰብ ነው)፡፡
እንግዲህ “ወሪሳን” ያነበበ ማንም ሰው፤ አስቀድሞ ዓለማየሁ ገላጋይን ማወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ የዓለማየሁ ገላጋይ አጫጭር ጽሑፎችንና ሕመሞችን፣ ሐሳቦችንና ፈለጎችን መገምገም የሚኖርበት ይመስለኛል፡፡ “ወሪሳ”ን ለመረዳት በርካታ ዓለማየሁ ገላጋዮችን ሰባስበን ብርሓን ፈላጊውን አንዱን ለይተን ለመመልከት መጣር የሚኖርብን ይመስለኛል፡፡ አሊያም ሌላ እይታ -እኔንጃ!
የዚህ አስተያዬት ጸሐፊ አመለካከት፤ ወሪሳን ለመገምገም ደፋር አስተያዬት ሰጪ በመሆንና የግል አረዳዱን ለማካፈል እንጂ ትክክለኛ አረዳድ ይሕ ነው ብሎ አይገዳደርም፡፡
‹‹ወሪሳ››ና ‹‹እሪ በከንቱ›› የተረት አገሮች!?
በወሪሳ መጽሐፍ ውስጥ በርካታ የተረትና የምሳሌ መጠቁሞች አሉ፡፡ ይሕም በዬ ቤቶቻችን ይነገሩ የነበሩና ምናልባት አብዛኛዎቹ ከአገልግሎት ውጭ እየሆኑ ያሉ የሚመስሉ ተረቶች የወሪሳን መጽሐፍ ምሶሶ አጭቀው ያቆሙት ናቸው፡፡ ቀላል የሆነ ናሙና ብንወስድና በየሶስት ገጽ አንድ ተረት ቢኖር- በ280 ገጾች ውስጥ ወደ 80 የሚጠጉ ተረቶች ይኖሩናል፡፡ መጽሐፉ ተረቶችን ለማቆዬት ያደረገውን ሚናና ትጋት ሳንጠቅስ ማለፍ አንችልም፡፡ ወደ ሰማንያ የሚጠጉት ተረቶች ሰማንያ የተላያዩ ሐሳቦች መያዛቸውንና በእያንዳንዱ ሐሳብ ውስጥ ጎልቶ የሚወጣውን የማሕበረሰቡ ፍልስፍና (አረዳድ) በተረት መልክ ማስቀመጥ የጸሐፊውን ብርታትና ለሰፊው ድብቅ ማሕበረሰብ ያለውን ቅርርብ የሚያመላክት ሆኖልኛል፡፡
ተያይዞም ተረትና ታሪክ ላይ ብቻ የሻገተ ማሕበረሰብ በራሱ ምን ያክል እንደሚበከልና ነገን የማዬት ኃይሉም ምን ያክል እንደሚጨነገፍ በዚሁ መጽሐፍ ሲጠቀስ እናያለን፡፡ ገጽ 207
“ለመጀመሪያ ጊዜ የኋልዮሽ በተረት መጓዜን ትቼ ወደፊት ያሰብኩ መሰለኝ፡፡ ወደፊት ማሰብ ጭንቀት ይበዛዋል፡፡ መወላወል ያጋጨዋል፣ መድረሻ ይጠፋዋል፡፡ ተረት እና ታሪክ አደጋ የሌለባቸው ጥርጊያዎች ናቸው፡፡” ይሕ አባባል ለአንድ ማሕበረሰብ ውክልና ሆኖ ሲጠቀስ ያ ማሕበረሰብ አደጋ ላይ መሆኑ ብቻ ሳይሆን አደጋውም መዳኛ የሌለው ንጉደት ላይ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ዓለማየሁ ገላጋይ ከአገር ሰማይ ጠቀስ ተኮር ድልድዮች፣ ሕንጣዎችና ግንባታዎች ይልቅ የጤናማ ማሕበረሰብ ጉርብትና፣ ሰላምና ነጻነት የሚሸት መንደር ምስረታ ላይ ሲቆዝም በብዛት ተመልክቸዋለሁ! ኋላንና ነገን ተመልክቶ ዛሬን ማስተካከል ላይ ሲታመም የኖረ፣ መንፈሱ የተሰበረ መነኩሴ፣ ማማ ላይ ቆሞ ሕዝብ ሆይ ስማ- ንጉሥ ሆይ አድምጠኝ ሲል ሰሚ አጥቶ ቆቡን የጣለ መነኩሴ ይመስለኛል ዓለማየሁ ገላጋይ!  በጫንቃው የሠዎችን ሕመም አዝሎ የሚዞር ደራሲ፡፡ የካዛንቺሱ ዶስቶቪስኪ…
‹‹ወሪሳ›› ላይ መመልከት የቻልኩት ነገር ቢኖር፤ በግርጌው ላይ የተጠቀሰውን የውድቅት ፈለጎችን ነው፡፡ ፈለግ ሲነሳ ደግሞ የሠው ልጅ ብርሓንን ይፈልግ ዘንድ የታጨ ፍጡር ከመሆኑ ባሻገር፤ የብርሓን ፈለጎች በተሠኘው ተቀዳሚ የጽሑፍ ስራ ጋር ማያያዝ የሚኖርብንም መስሎ ይታየኛል፡፡ ከተሳሳትኩ እታረማለሁ!
በብርሓን ፈለጎች ውስጥ የቀረበልን ማሕበረሰብ ቀስ በቀስ ያሳዬውን ተፈጥሮአዊ የሰው ልጅ የለውጥ ሂደት፤ አባጨጓሬ ወደ ቢታቢሮ…..ብርሓናዊ ሕልም… ብላቴናው ገጸባሕርይም የብርሓን ዱካዎችን በሰመመንም ይሁን በድንግዝግዝ እየተመለከተ፤ ልቡ ብርሓንን ስትሻ የሚያሳይ ሥራ እንደነበርና፤ ይሕ ፈለግ ወደ ውድቅት መተላለፉን፤ በብርሓን ፈለግ ኃሰሳ፤ የግንፍሌ ቤቶችና ሰዎች ድብልቅልቅ ድባብ ወደ ወሪሳና ወደ እሪበከንቱ በተሰኙ መንደሮች መቀየሩ ሳያንስ፤ በወሪሳና በእሪበከንቱ የምናገኛቸው ሰዎች አውሬ፣ ሰው በል መሆናቸው፤ የሰው ልጅ ከሰብአዊ ጸጋው ተነጥቆ ወደ ሞጭላፋ አውሬነት ማንነት መቀየሩ፤ ስም የለሽ ፍጡር ሆኖ መታየቱን የተንጸባረቀበት ስራ ይመስለኛል ‹‹ወሪሳ››!፡፡
በዚሕ መጽሐፍ ውስጥ ታሪክ ወደ ተረትነትና ወደ መዘበራረቅ መቀየሩን በተደጋጋሚ እንመለከታለን፡፡ በገጽ 194 ላይ የታገቱት “ወንጌላዊ“ እንግሊዞች መድፍ ስሩ መባላቸውና፤ የእንግሊዛዊያኑም ምስል ኳስ ተጫዋቾች ያውም “መድፈኞቹ” ሆነው መገኘታቸው፤ የወደፊት እኛነታችን ታሪክ አልባና ውሸት የሞላ ማንነት ብቻ ይዘን የምንታይ የአውሬዎች ስብስብ ስንሆን ታልሞ የተዘራና የተለቀመ የሐሳብ  ሥራ ይመስላል ‹‹ወሪሳ››፡፡
ኢትዮጵያ በቅኔ እሴቷ የምትታወቅና ከክፍለዘመናት የዘለሉ ድንቅ ስራዎች ባለቤት መሆኗ፤ ቅኔ ካለው የተመስጦ ጥልቀት ሐሳብ ገለጻ አንጻር በተጨማሪም፤ ዱላ የያዘን ጉልቤ ገዥ መመከቻና ማምለጫ ሆኖም የቆዬ ብሒል እንደሆነም መገንዘብ ይቻላል፡፡ አሁን አሁን ይሕ የቅኔ ባሕላችንና የባለዱላ ገዥ ጉልቤዎች ሲበራከቱ፤ ይሕንን ጻፍክ ተብለሕ የሚደርሰውን መከራና ሰቆቃ ወሪሳን በመሳሰሉ መንደሮች ምናብ ፈጥሮ፤ አምበርብርን የመሰሉ ጉልቤዎችን ከደምና ከመንፈስ ሸክላ አበጅቶ ለሕዝብ ማቅረብ የተጠናበት ስራ ይመስለኛል- ‹‹ወሪሳ የውድቅት ፈለጎች››፡፡
ፓርቲዎች በመንደር ስም ሲመሰራረቱና ሲጎነታተሉ፤ ሲነታረኩና ሲገነጣጠሉ፤ ሌብነት ከስራም አልፎ ጀግንነት ሲሆን! አምበርብርን የመሰሉ ግለሰቦች በማሕበረሰባችን ተፈርተው፣ ተሞካሽተው፣ ተከብረውና መገባደጃው ላይም ራዕያቸው ጎልቶ “ስዩመ እግዚአብሔር”ነትን በግዝት መወከላቸው… ፍቅር እስከመቃብር ገጽ 531…
ጸሐፊው የፈጠራትን የምድር ውስጥ ውጥንቅጧ የተዛባባትን መንደር ሕልው አድርጎ ብራና ሸራ ላይ ሲቀባልን፤ “ዴዣቩ” የሚሉትን አይነት የምናባዌ ቅዠት “ምች” እንድንመታ ያደርገናል፡፡ የት ነበር የማውቀው ይሕንን ሥም- ታሪክ? የት ነበር የማውቀው ይሕንን ግለሰብ- የትነበር የማውቃት ይሕችን መንደር ? የት ነበር የሰማሁት ባክህ ይሕንን ምናምን….? እያልን ገጽ በገጽ መሯሯጣችን አይቀርልንም፡፡
.
.
.
ከዚሕ የበለጠ አንባቢ መጽሐፉን አንብቦ የራሱን አረዳድ ተመርኩዞ የራሱን ቢል የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ከዚሕ በላይ ከደሰኮርኩ ሌላ ቅዠት ውስጥ ገብቼ አንባቢን እንዳልሰባብር ፈቃድ ይሁን! ባለፈው እንደገለጽኩት ወሪሳ አቶሞክ ቦንብ ሆናብኛለች! ገና ያልተብላላች..
ሥለ ‹‹ወሪሳ የውድቅት ፈለጎች›› ብዙ መጻፍ ይቻላል፡፡ ዓለማየሁን ይዘን በጋራ ብንፈሳፈሰው የተሻለ ይመስለኛል፤
ሆኖም በእሪ በከንቱ የውድቅት ራዕይ ሲያንሰራራ፤ ትንሳዔ ሙታን ሲበሰብሱና አውሬነት ራዕይ ሆኖ ሲቀርብ…
“እሪ በከንቱ ሕዝብ ደሜ ባንተ ላይ ነው” ስል ልቋጨው ይሆን እኔም?

No comments: