Apr 29, 2014

ኦሪት ዘሌዋውያን 19




ከደሙ ጋር ምንም አትብሉ አስማትም አታድርጉ፥ ሞራ ገላጭም አትሁኑ።
27 የራስ ጠጕራችሁንም ዙሪያውን አትከርክሙት፥ ጢማችሁንም ዙሪያውን አትቍረጡት።
28 ስለ ሞተውም ሥጋችሁን አትንጩ፥ ገላችሁንም አትንቀሱት እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
29 ምድሪቱ ከግልሙትና ከርኵሰትም እንዳትሞላ ሴት ልጅህን ታመነዝር ዘንድ አታርክሳት።

ወደ ገላትያ ሰዎች 5

ወደ ገላትያ ሰዎች  5



1   በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።
2   እነሆ፥ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ። ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም።
3 ሕግንም ሁሉ እንዲፈጽም ግድ አለበት ብዬ ለሚገረዙት ሁሉ ለእያንዳንዶች ደግሜ እመሰክራለሁ።
4 በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል።
5 እኛ በመንፈስ ከእምነት የጽድቅን ተስፋ እንጠባበቃለንና።
6 በክርስቶስ ኢየሱስ ሆኖ፥ በፍቅር የሚሠራ እምነት እንጂ መገረዝ ቢሆን ወይም አለመገረዝ አይጠቅምምና።
7 በመልካም ትሮጡ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ?
8 ይህ ማባበል ከሚጠራችሁ አልወጣም። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ ያቦካል።
9-10   የተለየ ነገር ከቶ እንዳታስቡ እኔ በጌታ ስለ እናንተ ታምኜአለሁ፤ የሚያናውጣችሁ ማንም ቢኖር ግን ፍርዱን ሊሸከም ነው።
11 ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ገና እስከ አሁን መገረዝን ብሰብክ እስከ አሁን ድረስ ለምን ያሳድዱኛል? እንኪያስ የመስቀል ዕንቅፋት ተወግዶአል።
12 የሚያውኩአችሁ ይቆረጡ።
13 ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ ነገር ግን በፍቅር እርስ በርሳችሁ እንደ ባሪያዎች ሁኑ።
14 ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።
15 ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱና ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ።
16 ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።
17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።
18 በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም።
19 የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ዝሙት፥ ርኵሰት፥
20     መዳራት፥ ጣዖትን ማምለክ፥ ምዋርት፥ ጥል፥ ክርክር፥ ቅንዓት፥ ቁጣ፥ አድመኛነት፥
21 መለያየት፥ መናፍቅነት፥ ምቀኝነት፥ መግደል፥ ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው። አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።
ወደ ገላትያ ሰዎች  5
22     የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፥ ደስታ፥ ሰላም፥ ትዕግሥት፥ ቸርነት፥ በጎነት፥ እምነት፥ የውሃት፥ ራስን መግዛት ነው።
23     እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም።
24     የክርስቶስ ኢየሱስም የሆኑቱ ሥጋን ከክፉ መሻቱና ከምኞቱ ጋር ሰቀሉ።
25     በመንፈስ ብንኖር በመንፈስ ደግሞ እንመላለስ።
26     እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ።


Apr 28, 2014

ከአብዮት በፊት ትንሳኤ!!

ከአብዮት በፊት ትንሳኤ!!
ተስፋ በላይነህ
አንዳንድ ጊዜ /ሁልጊዜም ሊሆን ይችላል/ ታዋቂ ጸሐፊ መሆን ዕዳው በታዋቂነት ልክ ሲከፋ ይታያል፡፡ አያያዙን እና አጻጻፉን የተረዱትን ጸሐፊ ሁሉም ወገኖች አበጥረው የዩታል፤ አንደኛው ወገን እንደ ሚሳኤል ሲፈሩት ሌላኛው ወገን ደግሞ ለአብዮታቸው ፋና ነው፡፡
የዩክሬን የቀለም አብዮት ሳይቀሰቀስ ስለ ቀለም አብዮት የሚናገሩ ታዋቂ ጸሐፊያን ከቅርብ ዓመታት በፊት የተቀሰቀሰውን የአረብ አብዮት በመጥቀሳቸው ወደ ዘብጥያ የወረዱትን ልንዘነጋቸው ፈጽሞ አይቻለንም፡፡ አሁን አሁን የምሰማው ዜና ደግሞ እነኚህ ጸሐፊያን ጋዜጠኛ ሆነው ሳለ የጋዜጠኛነትን ሙያ በማያሟላ መልኩ እየተጠቀሙበት፣ ከሽብርተኛ ቡድናት ጋር ተለጥፈው እየነገዱ መሆኑን ተደርሶበት “ፍትህ” እንዳገኙ ሲነገረን ነገን ማሰብ የሌለበት ክህደት ነው፡፡
አብዮት /ሪቮሊዩሽን/ እምቢተኛነት፣ ዓመጽ የሚለውን ትርጉም የሚደመድም ቃል ነው፡፡ ዓብዮት እና አብዮት በእጅጉ የሚለያዩ ሐሳቦች መሆናቸውን ከአማርኛ ፊደላት አጠቃቀም ደንብ ባሻገር የሚፈጥሩትን የቃላት ትርጉም ልዩነት ሊጤን ይገባዋል፡፡ አበየ- እምቢ አለ፡፡ መታበይ- ከሚለው ስርወ ቃል ጋር የሚያስተሳስረው ፍቺ ቢኖረውም ቅሉ፤ ልክ እንደ ‹‹ነጩ ፈረስ›› ታሪክ የሚየዛምደው ትንታኔ ያስፈልገዋል፡፡
የነጭ ፈረሱ ታሪክ ከየት መጣ ብትሉኝም በምናባችሁ አንድ የሚያምር የደለበ ነጭ ፈረስ ተመልክታችሁ ባማረ እና በተሽቆጠቆጠ ሰረገላ ተውቦ ወደ ሰርግ ሲወስዳቸሁ አስተውላችሁ ተመለሱ፡፡
አሁንም እንደገና ልጓም አልባ የምናብ ፈረሳችሁን አስፈንጥራችሁ ያንን ነጭ ድልብ ፈረስ ተመልክታችሁ ጦር እና ጋሻ ያነገበ ወታደር በጥሩር እና ሰይፍ ተሞሽሮ ወደ ጦርን ሲጋልበው አስተውሉ፡፡ አንድ ፈረስ ለሰርግም ለጦርነትም ሲያገሰግስ ተገንዘቡ፡፡
አብዮትም እንደዛው ነው፡፡ ከአብዮት ይልቅ ትንሳኤን እናፍቃለሁ፡፡ እርግጥ አብዮት ወደ ለውጥ ይወስዳል፤ ወደ እልቂትም፡፡ ወደ ሞት ይወስዳል፤ ወደ ትንሳዔም፡፡ ጋንዲም አብዮተኛ ነው፣ ስታሊንም አብዮተኛ ነው፣ ደርግም አብዮተኛ ነው፣ ኢሕአፓም አብዮተኛ ናት፤ ሔዋንም አብዮተኛ ናት ማርያምም አብዮተኛ ናት፤ ዲያቢሎስ አብዮተኛ ነው፤ ክርስቶስም አብዮተኛ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ አብዮተኛነታችን በማን ላይ፣ በምን ላይ እና ወደ ምን እንደሚወስደን አስቀድሞ አቅጣጫውን ማስመር እና መንገዱን ማሳመር ነው፡፡ ክርስቶስ ታዋቂነቱ በድፍን እየሩሳሌም ተሰምቶ ነበር፡፤ ከዚያም አልፎ ወደ ሌሎች ቦታዎች ተሰራጭቷል፡፡ ያውም ጡመራም ሆነ ማሕበራዊ ድረ-ገጽ፣ ማስ ሚዲያ /ምሕዋረ ዜና/ ባልነበረበት 0ኛ ዘመን፡፡ ለሞት ያበቃው የታዋቂነቱ መጠን ጭምርም እንደነበር ልብ እንበል፡፡ ሆኖም ሰይፍ ሲመዙበት ሰይፍን ከለከለ እንጂ አላስተባበረም፤ ጥፊን ሲቀበል ተደገመ እንጂ አልተገዳደረም፡፡ መንገዱን፣ አቅጣጫውን፣ መዳረሻውን እና ውጤቱን በአይኑ ይመለከተው ነበር፡፡  አብዮቱን/ዓብዮቱነትንም “የሚያደርጉትን አያውቁም እና ይቅር በላቸው…” በማለትም ፈጸመው፤ እንጂ 60ዎችን ለጥይት እራት አስደርጎ ፍትሕን አላዛባም፡፡ ለዚህ ነው ስኬታማ አብዮት ሆኖ ዘመናትን የተሻገረው፡፡ የትላንትናው የደርግ አብዮት እንኳ ‹‹ግንቦት ሃ.ያ. ደርግ የወደቀበት›› ተብሎ በመሰየም ብሔራዊ በዓል በመሆን ተቀብሮ ቀርቷል፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም እጅግ የሚወዱት ቃል እንደነበር እና ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ በጣም የተጸየፉት ቃል እንደሆነ ሲናዘዙ በብዕራቸው ያስቀመጡበት ሐቅ አሁን ግልጽ ይሆንልናል፡፡
ታዋቂ አይደለሁም፡፡ ታዋቂ መሆንንም በመሻት አልጽፍም፡፡ ከዚህ በፊት ልክ እንደ አሁኑ ታዋቂ ሳልሆን በአንድ ስሙን መግለጽ በማልፈልገው ‹‹ጋዜጣ›› ስለ አብዮት ጽፌ ነበር፡፡ ለኢትዮጵያ ምን አይነት አብዮት ያስፈልጋታል? የሚል አንድምታን የያዘ ሲሆን ከብዙ ዝርዝር በኋላ አንዳንድ ወቅታዊ ክስተቶችን በማስታወስ ምሳሌ አቅርቤ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- ታክሲ ለመጠበቅ የምንይዘውን ሰልፍ ምንም አይነት ረብሻ  እና የትራፊክም ሆነ የጊዜን መሸራረፍ ሳንፈጥር በተሰለፍንበት አሰላለፍ ወደ ፊት በእርምጃ ብንሄድ መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከእንቅልፉ ሲነቃ በህግ ህሊናው ያሳትምበት ነበር፡፡ /ሕሊና መች አለው እንደማትሉኝ እርግጠኛ ነኝ!!/
የስጋ ውድነት እንዲህ በአፍሪካ በቀንድ ከብት 1ኛ ከምትባል አገር ሲጫወትብን ስጋ ገዝቶ አለመብላት የሚለውን አብዮት ብንጠቀም ለጥቂት ጊዜያት ከመጮህ የማያቋርጠውን ወስፋታችን ታግሰን ለዘላቂው እኛነታችን እና ክብራችን፣ሃይላችን እንዲሁም ጥያቄዎቻችን ምላሽ መስጠት የምንችልበት ዘዴ መሆኑን ለመግለጽ ሞክሬ ነበር፡፡ ግን ታዋቂ ስላልሆንኩ አዋቂው መንግስትም ሆን አዋቂው ህዝብ አላወቀብኝም፡፤ “ተመስገን!” ብታወቅ እና ቢታወቅብኝ ኖሮ አሁን ደግሜ ባልጻፍኩትም ነበር፡፡ ብታወቅ ኖሮማ አሁን የት እንደምገኝ እናንተም ታውቁታላችሁ፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ከተለያዩ ቦታዎች ያሉ አዋቂዎቼ/ እኔን በግል ዝምድና እና ወዳጅነት የሚያውቁም/ ሰዎች “እባክህ የምትጽፈውን ነገር አቁም!” የሚል ግልጽ ኢ-ህገመንግስታዊ ምክራቸውን ገልጸውልኛል፡፡ ትንሳኤ ናፋቂ መሆኔን የተረዱት በየቀኑ የምጽፈውን ጽሑፍ ካነበቡ እና ከተረዱ በኋላ ነው-ዝምታቸውን ለግሰው ዛሬስ ምን ጻፍክ በማለት የሚጠይቁኝ፡፡ መጻፍ እንዲህ ቀላል ነገር እንዳለሆነ ደግሞ ቢረዱት የተሸለ ነበር፡፡
በህገ-መንግስቴ አንቀጽ 29 መሰረት ተጠቃሚ መሆኔን ካለመረዳታቸውም ባሻገር ከፈጣሪ የተቸረኝ ምዕራፍ እና ቁጥር/አንቀጽ/ ሊጠቀስ የማያስፈልገው ጸጋ መሆኑን ልብ አላሉትም፡፡ ልብ የት አለና!? “ልብማ ቢኖራት..?” እንዳለችው ውሻ ተገላቢጦሽ እንደይተረክብን ‹‹ልብ እንላለን!››፡፡ ልብማ ቢኖረን የሚለው ለኔ ለጸሐፊው ነው? ወይንስ ለተናጋሪዎቹ? ልብ ቢኖራቸውማ ይህንን አይናገሩኝም ብዬ ነው ማሰብ እና ማሳሰብ ያለብኝ፡፡ እነርሱም በመጻፌ ልብ የለውም እያሉ ተርተውብኛል፡፡ ትክክል ሊሆኑ ይችላሉ… አልታበይም!!
የተገላቢጦሽ ምድር ውስጥ እንዳለን ግን ልብ ይሏል!! 
የዩክሬን የቀለም አብዮት ወደኛ “አብዮተተስፋ” ምድራችን ሲነዘነዝብን ሰነባብተናል፡፡ ራሺያና ዩክሬን ከሚነዛነዙት በላይ ወደኛ ምድር በቀለም አብዮት የሚነዛነዙት አይለዋል፡፡ ታብየዋል፡፡ በቅድሚያ የዩክሬኑን የቀለም አብዮት ለመዘገብ የበቃው መንግስት? ወይንስ የቀለም አብዮት ናፋቂ ወገን?  ይህንን ለመመለስ ደግሞ የኢትዮጵያ አብዮት የተቀለበሰው በደርግ እና በኢሕአፓ ንዝንዝ ሆኖ ማን የመጀመሪያዋን የጥይት ድምጽ አሰማ ወደሚለው 40 ዓመት ያልተፈታ ጥያቄ ይከተናል፡፡ መንግስትም ሆነ ሌላኛው አንጃ የቀለም አብዮት ብሎ መነዝነዙ ለእኛ “ቱርካዊያኖች” የሚያመላክተው መንግስት የቀለም አብዮትን አጥብቆ እንደሚፈራ እና እንደሚጠባበቅ ሲሆን ሌላኛው “ኢሕአፓ” ደግሞ አብዮት እንደናፈቀ የሚያሳብቅ የልጅነት ጨዋታ ይመስላል፡፡ የልጅነት ጨዋታ ደግሞ አጀማመሩ እንዲያ እንዳልተሽሞነሞነ ሲቆይ ግን አቅጣጫው እና አጨራረሱ እቃቃ ፍርስርስ ዳቦው ቁርስርስ እይነት ‹‹ወግ›› ‹‹ልማድ›› ቢቻል አመል እና ሱስ ብለው ያስደስተኛል፡፡
ኢትዮጵያ አብዮት ያስፈልጋታል? ኢትዮጵያ አብዮት በዓብዮት ያስፈልጋታል፡፡ ነገርግን ከምንጊዜውም በአለም ታይቶ የማይታወቅ አብዮት ከማስፈለጉም በሻገር የሚደርሰውን የእቃቃ ፍርስርስ ልማድ በከፍተኛ ሁኔታ ከማጦዙም በላይ ዳግመኛ የማትመለስበት መደናበር ውስጥ እንደምትዘፈቅ ለመገመት ነብይ በድንግል ማሕጸን ውስጥ ገብቶ ተጸንሶ ተወልዶ እስኪነግረን መጠበቅ የለብንም፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አብዮት እየሸተተን ከሆነ አብዮቱ የሚያስከትለውን መፈራረስ አስቀድመን ልናሸተው ይገባናል፡፡ ይህን ስል ‹‹ፈሪ›› የሚሉኝ አዋቂዎቼ ብቻ ሳይሆኑ አብዮትን በከፍተኛ ደረጃ እያሸተቱ የሚገኙ ወገኖቼም ጭምር ናቸው፡፡ ሲጀመር አብዮት ያስፈልገኛል ብሎ የሚያስበው ህዝብ በእጅጉን ከማያስበው አንሶ በመገኘቱ፣ የአብዮትን ፋይዳ፣ አስፈላጊነት፣ አካኄድ፣ መንገድ እና መዳረሻ የማይረዳው ሕዝብ የትየለሌ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ አያበቃም አብዮት ያስፈልጋል  ብለው ከሚሟገቱት ወገኖቼ ውስጥም ባልታወቅ እና በታወቅ ምክንያት አብዮቱን ለግል ጥቅም ማዋላቸውን እንደሚጎዳኙት ልብ ልንል ይገባናል፡፡ አብዮት ማስፈለጉን በየማያውቁት ወገኖች መበራከት፣ እያወቁትም ለዝርፊያ፣ለእልቂት፣ “እኔ በነበርኩበት ዘመን ሰላም ነበር አሁን ግን አብዮት አብዮት ብላችሁ በጠበጣችሁን” እስከማለት  የሚሞክሩትን በመቁጠር ከዛም ባሻገር “ከመንግስት” ጎን ሆነውም ቤንዚን እና ክብሪት በነጻ የሚያድሉትን ወገኖች አጥብቀን ልንገነዘባቸው የሚገቡን ናቸው፡፡ በሶስቱ መሪ ምክንያች ኢትዮጵያ አብዮት ሊዘገይባት፣ ሊብላላላት እና ሊመከርባት እንደሚገባ እንረዳለን፡፡ አሁንም አብዮት ናፋቂዎች ሁለቱ ወገኖች በተለይ አንደኛው ይህንን ድምዳሜ እንደ ካድሬነት አሊያም ፈሪነት አድርጎ ሲፈርጀው ገላጋይ የለውም፡፡ ትዕግስት ፍርሃት አይደለም! ክፉን በመልካም መመለስ ፍርሃት አይደለም… ወ.ዘ.ተ!
እስካሁን የተከሰቱት አብዮቶች እና አብዮተኞች ዋነኛ መገለጫቸው መነሻ /መካሪያቸው/ እና መዳረሻ/ ግባቸው/ ተለክቶ ነው፡፡ የኄዋን አብዮተኛነት ከዲያቢሎስ ምክር የተገኘ ነው፡፡ የዲያቢሎስ አብዮተኛነት ከእኔነት መታበይ የመጣ የክፉ የአብዮተኛነት አነሳስ ነው፡፡ የጋንዲ አብዮተኛነት የነ ማኦ፣ የነ ቼጉቬራ ፣የስታሊን የመንግሰቱ ኃ/ማርያም አብዮት እና አብዮተኛነት እዲሁም መሰል አብዮቶች በጥቂቱም እንኳ መነሻ ቢኖራቸውም መዳረሻቸው ግን ታሪክ ፍርዱን አስቀምጦ እየተመለከትናቸው ነው፡፡ ከሳጥናኤል እስከ ዩክሬን የቀለም አብዮት ድረስ የተደረደሩት አብዮቶች እና ብቅ ጥልም ያሉት አብዮተኞች በጥቅሉ ሌላ አብዮት እንድናፍቅ አሊያም በክፉ ዳርቻ አብዮትን እንድንጠላ ያደረጉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሃል በዘመናት መካከል የተደረገው አብዮተኝነት በትንሳኤ ተቀይሮ ግቡን ያሳካው እርሱ መሲህ ሆነው ክርስቶስ እሱን ብቻ ነው!!
ውድ ሙስሊም እህትና ወንድሞቼ እየደረጉት ያለውን ሳምታዊ ሶላት ጠገግ አብዮት አጀማመሩን ብናስታውሰውም/በጭጋግ ብንመለከተውም-ችግራችንም ሆኖ ስለማንጠይቅ…./ አጨራረሱን አልደረስንበትም፤ ሆኖም ከሚዘከርለት ውስጥ አንዱ እየሆነ መሄዱን ለመመስከር እንደምንታደል ፈጣሪ ይርዳን፡፡ ምናልባት ስብከት ባይሆንብኝ እና በቀናነት ቢታይልኝ ትንሳኤ የምትለዋን ቃል በፍልስፍና ደረጃ እንኳ ለመጤን ብትሞከር በእጅጉ ስኬታማ የምንሆንበት ብርሃን የሚበራ ይመስለኛል፡፡ ከእኔ ሃሳብ በቀር በሚል ማነቆ አልገዳደርም፡፡ ለእኔ ግን “በእኔ በቀር ወደ እርሱ የሚመጣ የለም፣ እኔ መንገድ እውነት ትንሳኤም ነኝ” ሚለው መፈክሬ መነሻዬ እና መዳረሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአብዮት በፊት ትንሳኤ አጥብቆ ያስፈልጋታል!! የትንሳኤው ጉዞ ክፉን በክፉ አትመልሱ፣ ግራ ጉንጭህን የመታህን ቀኝህን ደግሞ ስጠው አና መሰል አንቀጾችን የያዘ ሲሆን መዳረሻውም የሚሰሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው!! የሚል ነው፡፡ ግቡም ትንሳኤ/ እንደገና መወለድ፣መታደስ ዘር ፍሬ ሆኖ ማፍራት-ማበብ ነው፡፡ ከዓመት በላይ ታሽጎ የኖረ የስንዴ ዘር እንደምን ተዘርቶ ሊበቅል ቻለ? የትንሳዔ ምስጢር የገባው ብቻ የሚመልሰው ነው፡፡ ከአብዮት በፊት ትንሳኤ!!  
ዓመታትን ቆይቶ ለዘርነት የሚበቃው ስንዴ የተመረጠው ከንጹህ ዘር ተለይቶ እንክርዳድ እንዳይኖረው ተበጥሮ ነው፡፡ ተበጥሮም በጥንቃቄ ተይዞ ነው፡፡ ነቀዝ እንዳያፈራ ተጠብቆ ነው፡፡ እንክርዳድ እና ነቀዝ ለመጪው ዘር/ትውልድ/ ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው፡፡ እንክርዳዱ ቂም ነው፡፡ ጥላቻ ነው፡፡ ጎሰኝነት፣ እብሪት፣ ጠባብነት እና መሰል እርግማኖች ናቸው፡፡ ነቀዙ ደግሞ ያው የውጭ ሃይላት ናቸው፡፡ አብዮት ለእነርሱ መርዛማ እጅ ዋነኛ የጅብ መስኮት ነው፡፡ ጅብ በቀደደው የሚገቡት ውሾች ደግሞ ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡ እንክርዳድ እና ከነቀዝ የጸዳ ስንዴ/ አብዮት/ ወደ ትንሳዔነት ለመሸጋገር የበቃ ይሆናል፡፡ የሚከተለውም ንጹህ ዘር የሚያብብ የሚያምር አዝመራ ነው፡፡ ትንሳዔ አለው፡፡ ለዚህ ነው ከአብዮት በፊት ትንሳዔን ከአብዮት በኋላም ትንሳዔን የምንሰብከው፡፡ ከአብዮት በፊት ትንሳዔ- ለኢትዮጵያ!! 












                      

Apr 27, 2014

“የካሳ ትንሳዔ” በጥሩየ ልብስ



“የካሳ ትንሣዔ” በጥሩየ ልብስ
የጥሩ ሰው ልብስ???
*****
ከዚህ ልብስ መሐል- ስጋ ከሌለበት
አጥንት ካልቆመበት-ታሪክ ካልጻፈበት
የሚታየኝ መንፈስ- ጥሩ ሰው አለበት፡፡

 ካሳ አባ ታጠቅ ተዋቡን ሲሸኛት
በግሸን ተራራ እንደ ግማድ ቀብሯት
ሲመለስ በዚያን ወቅት ባዶነት ተሰምቶት፤
ከራሱ ከጥላው ከመኳንንት አልፎ
ከዛፉ ከምድሩ ደርሶ ተኮራርፎ
 በሰሜን በደቡብ ሲዘምትበት ቀፎ
 ባይተዋር እዳይሆን የሰው ሰው አሰኘው!
ወጣነት ባንዴ ሰው መሆን ኣማረው፡፡

ጥሩነሽን አይቶ በውበት ቁንጅና
ያባቷንም ግዞት፣ የጥሩየን እድሜ ከቶ ሳጠና
አገባት በዚያ ቀን ጥሩነሽ "ውቢቷን"
ሊያደርስ አንድነቱን ሊረሳም ተዋቡን፡፡
*****
ዑል ዓለማየሁ ካብራክ ቢገኝለት
ሩቅ ነበር ቴዲ መች ቅርቡን አየበት?
ናፒር ሲታይ ማዶ
ከሰሜን  ተዋዶ በካሳ ማግዶ
በጎጃም ተሰዶ
ሰተት ብሎ ገባ ናፒር እንግሊዙ በግብር ተላምዶ!!

ወሩ ሁዳዴ ነው- ሰሙነ ህማማት
ትንሣዔ መስሎታል በባሩድ  ሰው መሞት…

መቅደላ አሽካካች፣ እንግሊዝን ይዛ
ሲወረስ ጨፈረች ቀረች እንደዋዛ፡፡
ፈጠኑ ጌቶቹ የድርሻውን ያዙ
እጣ ተጣጣሉ፣ በቀሚስ በዘዱ ወርቁንም አበዙ

ብራናው ይከመር፣ ሽሩባውም ወዙ
ይሂድ ወደ ቤቱ ሸኙት ዕዳ ግዙ፡፡
******
ዕዳውን የገዛው ካፒቴን ስፒዲ
ባሻ ፈለቀ ነው አበሻው እንግዲ….
ጥሩየን ልዑሉን ወርቁን ይዘውታል
ለንግስት ሊያሳዩ "የጸሐይ መውጫዋን"
ጥሩየ አማጠች ዳዊቷን ሰደረች
ሞቷን አሳጠረች በዳዊት መዝሙራት ቀብሯን አሳረገች…
ባህር ሳትሻር -አገሯ ላይ ቀረች!!
 በበፍታ ቀሚስዋ ታሪክዋን ከተበች፡፡
.
.
ልዑሉም በዛበት የሙትነት መንፈስ
ደስታ የት ይገኛል በደት ሆድ ሲብስ..?
******
አሁን፡-

የጥሩየ ልብሷ ይታየኛል ፤ ባዶ መስሎ ውስጡ
የጥበቡ ማማር አወይ ጉድ ለምስጡ
ምስጥ እንደው ይበላል ስጋን ያፈራርሳል
ምስጢር መች ቀላል ነው በማንስ ይፈታል?
ያልተፈታ ምሥጢር ያለልተቀቁወዋጨ ፊደል
ያልተሳካ ታሪክ ያልተሳለ ምስል

በጥሩዬ ቀሚስ በጥሩዬ ሐብል፡፡
******
ካሳ ለምን ሞተ፣ ጥሩየስ ምን አለች?
ስደት አልቀናትም ሞቷን በዝታ ሻተች፡፡
ለምን ተቀበረ ገብርየ በወኔው ?
ታንጉት እንዴት ብላ ምስጢሯን ታካፍለው...
የነጭ እባብ ልክፍት አገሬን ሲያስታመው?

ባዶ አይታይም ዜሮም ወሰን የለው
በጨርቁ ገመድ ውስጥ መንፈስ ታሪክ አለው!!
ባዶ ነው አትበሉኝ አልቦ ታሪክ አገር
በዮሐንስ አንገት ይታየኛል ትንቢት የኑዛዜ ቀመር፡፡
መልሰህ ትከለው የኢትዮጵያን አንገት
ራዕዩ ታላቅ ይሻገራል ጉንደት…
ባዶ ነው አትበሉኝ የዚህ ጥበብ ግጥም
በባደዶ ነው አትበሉኝ የጥሩ ቀሚስ የጥሩየ ሕመም፡፡
-
ለመርዛማው እባብ ይዣለሁ ቀጥቃጩን መድህን የአለም
ካልሞቱ ካልሄዱ ካልተሰው ባለም ያ ትንሳሣኤ የለም!
***
"የካሳ ትንሣዔ" ይዘከር በዓለም...
                             ቀሚሱን እዩት  ውስጡ ማንም የለም!
Tsefa B. MiYAZiYA 6- On Tewodros's death Ann.


Apr 26, 2014

ኑ! “ቤት” እናፍርስ… “ገንፎ- ቁጭ!”

ኑ! “ቤት” እናፍርስ…
“ገንፎ- ቁጭ!”

                                                                                                Tesfa B.
እንጉርጉሮ- ሽለላ እና ፉከራ ተሰማ፡፡ ከራማ የነፍሳት ጩኸት እንደተባለው… ከዚህም ከዚያም ዝምታ ተሰማ፡፡ ከራማ ለተሰማው ጩኸት ነጻ-ውጪ ተሰየመ፡፡ ስለምን የአጋዚያን/ነጸ-አውጭዎች/ መልክ ተቀየረ? እነዚያ ህጸናት ሲጨፈጨፉ እነዚያ የሰማይ መላዕክት የት ነበሩ? ለካስ አጋንንት የሰለጠኑበት የፍዳ ዘመን ምስክር ነበር!
ግጥሞች ተገጥመዋል፡፡ ቤት መትተዋል፡፡ የኛ ጥያቄ “ግጥሞቹ ሲገጠሙ የት ነበራችሁ?” የሚለው ይሆናል፡፡ ሐሳቦች ሲታለሙ- ድርሰት-ቲያትር ሲሆኑ የት ነበራችሁ? አሁን እንዴት “ትወናውን አቁሙ! አፍርሱ!” ትሉናላችሁ? ትላንትናም አይደል እኒያ ሁለት የአንድ እናት ማሕጸን ክፍዮች- የአንድ አፈር ብቃዮች ቃታ ተሳስበው እጃቸው ሳይፈታተል ለአገናነዝ ሳይመቻቹ ወደ ግብዓተ መሬታቸው ያሸለቡት-የተቀበሩት-የሞቱት? በአንድነታቸው መሬት ላይ ተጨካከኑበት!!  
ቤቶች ይሰራሉ፡፡ ቤቶቹ ሲሰሩ የት ነበራችሁ? ስንትና ስንት ባድማ እና ቀዬ አልፈን ካሳ የተመዳደብንበትን መንደር፤ ደቦ የተለጋገስንበት ሰፈር፤ ጥል ያፈረስንበት ቅጥር፤ ጉማ የበላንበትን አድባር ጥለን መጥተን፤ መንደር ስንመሰርት የት ነበራችሁ? ከ3 እና ካራት እንዲሁም ካስር በመቶም የሚመለስ ቤትም ሆኖ በሆነ… በሺዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ስንገነባ፣ እንጨት ስንለቃቅም፣ እሳት ስናቀጣጥል፣ እራት ስንበላ፣ ብርሃን ስንከራይ፣ ደቦ ስንመላለስ፣ ጥል ስናበርድ፣ አድባር ስንመሰርት የት ቆያችሁን? ለምንስ እያላያችሁ አያችሁን? እያያችሁ አላያችሁን? ስለምን አፍርሱ አላችሁነ? እኛ ነነ ጥፋተኛ? ምን አረግነ? ምንስ በደልነ?
ገንፎን አስቀምጠን- ገንፎን ተቀምተን ምን ልንውጥ እንስማማለን? ገንፎውን በቅቤ እንዳናቦካው ከብቶታችንን ሸጠን ቆርቆሮ ገዛነ-መሬቶቻችንን ለልማት ተውነ- ማገር አቆምነ ጭቃ አቦካነ-ደማችን አቦካው “ገንፎ ቁጭ” ብለን ስም ሰጠነ…. ስለምን አፍርሱ አላችሁነ?
ካህናቱ መሳሪያ ሲገዙ ተመለከትን፣ አሙሃይ እልፍኟን ሰፍራ መቃብር ምሳ አዘጋጀች፣ ነግቶ የሚመሻሸው ነገር እንዳይወልድ ህጻናት በት/ቤት መዝሙራቸው ዝማሬ ያሰሙን ከጀመሩ ሰነባበቱ፤ መንግስት እና ህዝብ “ቲካ ቲካ” “የእንቁልልጭ” ሒሳብ ከተወራረዱ መሬቱን ደም ለቀለቀው! አፈሩን ስጋው አበከተው! አገሩን ቁራ አበላሸው…
ቁራነት፣ቂምነት፣ቂልነት አገሩን እንዳያበላሸው ባገሩ ባህል እና ወግ ቢሸመጋገሉ መልካም ነው፡፡ ሰባት ቤት ገንብቶ ገንፎ ቁጭ የተቀመጠ ካለ ስለ ሰላሙ አምላክ ብሎ ሰላምን ይመዝን፡፡ በኋላ በራሱ ባያገኘው በልጁ አያጣውም! ለልጆቻችን ቁልቁለት አናውርሳቸው!!
በጥበብ ካልተፈታ የታሰረው ገመድ ውሉም አይገኝ፡፡ የ44ሺ ነፍሳት ጩኸት ዕዳ አበሳ ነው፡፡ መሸናነፍ ጨዋታውን አይመልሰውም፡፡ “መንግስት ተሸንፎ ለምርጫ አሳብቦ ማረን” ቢባል፤ “ህዝብ ህገወጥ ሆኗል አፍርሱ!” ተብሎ ለማሸነፍ ቢነሳ ማንም አይጠቀምም፤ በቀዳዳው ሾልከው የሚነጉዱት ሸክሞች የትየለሌ ይሆናሉ!!
ጥበበኛ መሪ መፍትኄ አያጣም… ፍቅር ጥበብ አለው -ጥበብ መፍትኄ… መፍትኄው ሰላም “ገንፎ-ቁጭ”
“የብሔር ብሔረሰብ” ነጋሪት ከተጎሰመ ጀምሮ- አመጸኛው የሰው ልጅ ከበጎው ክፉን፤ ከክፉውም በጎውን እየወሰደ ሰው ከሰውነቱ በላይ ጎሳን እያጎነ፣ እያገነነ እኩል ነን ሲል ተደመጠ፡፡ እኩልነቱንማ ፈጣሪ መች ነፈገው? ሰው በፈጠረው ወሰን ተለያይቶ ተነካከሰ እንጂ! አሁን “ቅማንት-አማራ” በሚል መስመር ህገ-መንግስታዊ ጥያቄ ተነስቶ መልስም የለም ጥያቄም አላቆመም፡፡ በፍቅር አልተመላለስንም፡፡ ማንም ከማንም አይበልጥም-አያንስምም፡፡ ባልተረጋገጠ ሃሳብ አመጽ ሲወለድ-ዱላ እና ብረት ስልጣን ያገኛሉ፡፡ ደም ይፈላል… ሜዳ ላይ ይፈሳል… አጥንት ይዝላል… ስጋ ይተላል፡፡ ዛሬ ይለጠጣል፤ነገ ይጠፋል፡፡
 ፍቅር ግን ያሸንፋል፡፡ ፍቅርን አልጨበጥናትም… አንድነትን አልሰበክናትም… ኢትዮጵያን አልከፈልናትም…..!
ተጻፈ፡- በጎንደር ከተማ በተልምዶ “ገንፎ ቁጭ” ተብሎ በሚጠራ ሰፈር “የጨረቃ ቤቶች” ይፍረሱ-አይፍረሱ በሚል መጉረምረም ለተነሳ ሃሳብ…
በአማካይ ከ 40 ሺ በላይ ነዋሪዎች 10 አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተሰርተዋል፡፡  “እስካሁን ይሕ ሁሉ ህገ-ወጥ ቤት ሲሰራ ማን አይዟችሁ አሏቸው?” ትልቁ የህዝብ ጥያቄ ሲሆን፤         “በህገወጥ መንገድ ቤት ሰርቶ መኖር” ደግሞ ህግ አልባነት መንግስትን ስለሚያስወቅሰው ይሕ ደግሞ ሌላኛው ችግር ነው፡፡ 
የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በፍቅር ይፈታ ዘንድ እንማጸናለን፡፡ ዝምታው ሰላም አይመስልም፡፡ ክፉ ዝምታ ሰላም አይመልስም፡፡ ረመጥ፡፡ ለልጆቻችን የመቆራረጥ እና የመተላለቅ ታሪክ አናውርሳቸው… አንድነታችንን ስበኩልን… የትላንትና ታሪክ “የድካም ስህተቶች” ዛሬ እንዳያሳውሩን… ከትላንት እንሻል! ዛሬ እንለወጥ ነገን ብሩህ እናድርግ…
“የአኖሌው ሐውልት” ከሩቁ ይጣራል… እንደ እፉኝት ልጆች ስብዕናችን ለመቀየሩ መስካሪ ሆኖ ተገንብቷል፡፡ ለግንብማ ማን እንደ ባቢሎን?? !
በጥበብ ጫፍ፣ በሰላም ሰልፍ፣ በፍቅር ክንፍ በርሮ መጥቶ የጭለማውን ርጋታ በበትር መትሮ የሚለያይልን ወደ ብርሃኑ የሚያሸግርልን “ሙሴ” ያስፈልገናል፡፡
ጥበበኛ መሪ ያሻናል!! ፍቅር ይሳሳናል…ጩኸቱ እንዲህ ይላል “ሰላም!!” በናንተስ?

ቅጅ
v ለተከበሩ ካሳ ተ/ብርሃን
v ለፐ/ር መስፍን ወ/ማርያም
v ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ
v ለአብርሃ ደስታ
v ለከንቲባ
v ለአፈንዲ ሙ
v ለአምባሳደር ዘመነ ካሰኝ


እውነት በዚህች አለም

***እውነት በዚህች አለም***

“ሳራ” ከስራ ወደ “ሳር” ቤት፡-
በተማሪዎች ማመላለሻ ውስጥ እንገኛለን፡፡ አንዲት የ8ኛ ክፍል ውብ ተማሪ- ኢትዮጵያዊ ውብ ቀለም፤ ወደ ከተማው ታማትባለች፡፡ ከገጠር ከመጣች 4ኛ አመቷን ግንቦት 20 ላይ ታከብራለች፡፡ መሄድ መሄድ አሰኝቷታል፡፡ ከተማው ለእርሷ- የውበት መደምደሚያ የእውነት መቋጫ መሆኑን ትካዜዋ እና የአይኗ ሳቅ አሳባቂ ነው፡፡ ማስቲካዋ ከሜይሊ ሳይረስ የአምልኮ ዝማሬ አልፎ  ለሾፌሩ የአስረሽ ምቺው ሩምታ ነው፡፡ ከተማውን ታማትባለች፡፡ መሄድ መሄድ ያሰኛታል፡፡ ከተማው የእውነት መስሏታል፡፡ ዓለም የእውነት መስሏታል፡፡ ዓለም እውነት እየመሰላቸው ስንቶች ተሸኝተዋል? ስንቶች ተሰጥተዋል፡፡ ስንቶች ነፍሳቸውን አጉድለዋል፡፡ ጸሐዮቻቸውን ዐጨልመዋል… ከአለም ምን ይገኛል? እኔም የሌላኛውን ጠርዝ መስኮት ተደግፌ ወደ ውስጠኛው ከተማ ተምዘግዝጌ ይህንን እውነት መሳይ የጥጥ ፈትል ባዘትኩ… እውነት እምነት ነው፤ በፈተልነው ልክ የምንለብሰው…በዘራነው ልክ የምናጭደው፡፡ በበግጥም ፈተልሁት- ልበሱት፡፡ በቅኔ ዘራሁት-አጭዱት!! እነሆ….

አውነት በዚህች አለም
እንዲህ ተቀልማ በጽልመት ተቃርማ
በጠዋት ታጅባ- በብኩን ቀን ታማ…
በፍጥረት ግብግብ በአንድ አይነት መንጋ
በጎልያድ ቁመት በዳዊት ጽኑ ልብ በጨቅላነት ለጋ
በውሸት ብልጥነት- በእውነት ሞኝነት- ሌሊቱ ሊነጋ!!
ሲወጡት ሲወርዱት የመንጋት የመምሸት
የመወለድ መሞት በድንግዝግ ማየት
እውነት ማለት? እውነት ማለት?
እውነት በዚህች አለም
በጨለማ መሃል ጸሐይ እንደማትቆም
በጥቁር ህዝብ ዓለም ነጩ እንደማይተም
መዳረሻው ያው ነው የሁሉም ቀይ ደም!!
የጥላ መፈጠር የልዩነት ቀለም
የጸሐይ ክበቧ የኦርዮን ጠልሰም
በማንም አይቆምም በማንም አይደምቅም!
የምድር ፍጥረታት እነኚያ የቆሙት
እኛን ሊያደምቁ ነው ሌት ተቀን ሚዞሩት..!?
አንቺ ታናሽ ሴት ልጅ- ውበትሽ ሚያስፈራ
ለስጋና ለነፍስ ህይወት የሚዘራ
በመስኮቱ ዘልቀሽ ስታይ ከተማውን
አዲስ ዓለም መስሎሽ ስትሰጭ ትካዜውን
ተመስጠሸ ነበር ልታይ ከተማውን
አማትበሽ ልትገቢ ልትሸጭ ማንነትሺን
ወንዝ ልትሻገሪ ሊከብር አባትሽ ልትከፍይ ስጋሽን…!!
የባቡሩ መንገድ፤ የቀለበት ጉዞ፤ የህንጻው መደቀን
የምጣኔው ማደግ የህዝቡ መሰልጠን
ዕዳ ነው ይህ አለም ፍርሃት ሰቀቀን-
ማበድ ነው መቅበዝበዝ ዘመኑ መሰይጠን!
በውስጥሽ ሳታይ ሳትመለከቺ ያን ውብ ውበትሽን
የግዜር ውብ ፍጥረቱ ዓርዓያ ገጽሽን
ሳትመሰጪበት-ባንቺ ውስጥ ያለውን ረቂቅ አምሳሉን
የመኖር የመሞት የመሄድ የመምጣት የህይወት ሚስጥሩን
ተመለሽ… ተመለሽ ካሳብሽ ፈቀቅ በል ትካዜ
በኋላ ሞት አለው የማያልቅ ኑዛዜ!!
እውነት በዚህች አለም
እንደ ጤዛ በርታ ወዲያው የምትጨልም
እንደ ውብ አበባ ወዲያው የምትከስም
እንጉዳይ ስስ ቀለም- ብናኝ እንደ አረም
እንዳትጎዳኚው ክፉ ይህ አለም!!
አብሪ ነሽ ለአለም- በራስሽ ክበብ ስር እልፍ ለዝንት አለም
እንዳትቆራኚ ከዚህ የወረዛ የትንፋሽ ልም ቀለም
ታይቶ የሚጠፋ ውብ መሳይ ቅል አለም!!
ውብ ከተማ አለልሽ ወደ ውስጥ ሲታለም…

                                                     *ተስፋ በላይነህ*

Apr 7, 2014

በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን!

በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን!
በተስፋ በላይነህ

ክፍል -1
   ይህንን ጽሑፍ ስጽፍ ለብዙ ቀናት ተሟግቻለሁ! “ጽሑፉንስ ጻፈው ግን አደራ እንዳታወጣው!” ይለኛል አንደኛው ተሟጋች፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ በስም ማጥፋት ወንጀል!” ተብለህ እነዳትከሰስ፡፡ ሌላኛው ተሟጋች ደግሞ “አንተ ምን ባይ ነህ የሰው ስም ጠቅሰህ አንድ የባለ ረዥም ባለታሪክን አገር ታሪክ መክሸፍ ከጥቂት የግለሰቦች ስብዕና ጋር አያይዘህ የምትለጥፈው” ይለኛል፡፡ ሌላኛው ደግሞ “ኧረ እባክህ አርፈህ ተቀመጥ!” ብሎ የተለመደውን ምክንያት የለሽ ክርክር ያቀርብና ሊሞግት ይቃጠዋል፡፡
  ምክንያት የለሽ ሙግት ደግሞ ከሰነፎች ልብ የሚፈልቅ ኢትዮጵያን ለዘመናት ያቆረቆዘ የታሪካችን ውድቀት ምክንያት ነው ብዬ ለመወሰን ተገድጃለሁ፡፡ በተለይ “ተማርን” በሚሉት የኢትዮጵያ ዜጎች/ መሪዎች/፡፡ ያለምክንያት ተሟግቶ አለማመን፣ አለመተማመን፣ መሸነፍን አለማመን ማሸነፍን ብቻ ማመን ደግሞ ሌላኛው ደዌ! ክፉ መርዛማ ደዌ ነው! የመክሸፍ ሸክሞቻችን ናቸው፡፡
አንድ ፈላስፋ እንዲህ አለ፡፡ “እውነትን ከያዝህ ለክርክር አትቸኩልም፣ ከተከራከርክ ግን አትሸነፍም፡፡” ድንቅ አባባል! በብዛት የሚከራከሩ ሰዎች ውሸተኞች ናቸው፡፡ ሁሉም እውነተኛ ቢሆንማ ክርክር የሚባል ነገር አይፈጠርም ነበር፡፡ አንድ ውሸት ግን ስትመነጭ በብዙ እውነቶች ውስጥ ተደንቅራ ታከራክራለች፡፡ እውነተኞች ግን አሸናፊ እንደሚሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡፡ ለክርክር አይቸኩሉም፤ ከተከራከሩ ግን አይሸነፉም፤ እውነት አትሸነፍም! እውነትን ለማወቅ ደግሞ አውቀት ያስፈልጋል፡፡ እምነትም እንደዚሁ፡፡ እውነት እና እውቀት ያንድ ሳንቲም አንድ ገጽታ ናቸው፡፡ በሌላኛው ገጽታ እምነት አለ፡፡ የሚታየውን ተራራ አይቶ መኖሩን ማወቅ እውቀት ላያስፈልገው ይችል ይሆናል፤ መኖሩንም መተማመን ይኖርብናል፡፡
ውሸት ተጋንና፣ ተበራክታ፣ ተደላድላ ተቀምጣ ስትታይ፤ ቀስ በቀስ እውነት ለመምሰል የምታደርገውን የውሸት ህይወት የሚመለከቱ እውነተኞች ዝም ማለት አይችሉም፡፡ በተፈጠረው የውሸት ህይወት ምክንያት ብዙ ፍጥረታት ውሸቱ እውነት መስሏቸው ተቀብለውት ስለሚኖሩ እውነተኞች ይነቀፋሉ፡፡ ተከራካሪ ይባላሉ፡፡ ነገረኛ፣ አደናጋሪ፣ ጠብ አጫሪ ተብለው ይፈረጃሉ፡፡ እውነትን ለማሳየት ሲሉ ብቻ ከብዙ ምድራዊ ጥቅማጥቅሞች ይገለላሉ፡፡ በጥቂት ሰዎች ዘንድ ግን ይታወሳሉ፡፡ ይህንን ምድር የሚገዙት እና የሚመሩት ግን ውሸተኞች እንጂ እውነተኞች ስላልሆኑ አለም የምትመራው በውሸተኞች መሆን የጀመረው ዓ/ም ተብሎ ከታወጀበት ዕለት ይመስለኛል፡፡ ክርስቶስ ሲወለድ ጀምሮ ያለውን ጊዜ ዓ/ም ብለን የምንጠራው ላመኑባት፣ ለተከተሏት እና ለተገበሯት ብቻ ነው፡፡ ንጉሱ ክርስቶስ ጌታ ቢሆንም፤ የዚህ አለም ገዢ ግን ሰውን እንደ መልኩ እና እንደ አሻራው ለያይቶት ይገኛል፡፡ ብዙኃኑ   በተንኮለኞች እና በውሸተኞች እንዲመራ አድርጓል፡፡ አለም የምትመራው በውሸተኞች ነው፡፡ ይህንን ካላመናችሁ፤ ይህንን ጽሑፍ ባታነቡት እመርጣለሁ፡፡ አለም የምትመራው በጥቂቶች እጅ መዳፍ ተጨፍልቃ፤ በተንኮል እና በሸፍጥ  በተመረዙ ሴረኞች፤ በሆዳሞች እና የሰውን ልጅ ሰብዕና ለማኮላሸት ሌት ተቀን በሚንደፋደፉ ሸረኞች ነው፡፡ ይህ እንደሆነ ካልተገነዘቡ ይህንን ጽሑፍ እንዳያነቡት፡፡ ካመኑበት እና ከገባዎ ግንማንበብዎን  ይቀጥሉ፡፡
እየቀጠሉ ከሆነ አምነውበታል ማለት ነው፡፡ ሳያምኑበት የሚቀጥሉ ከሆነ እየዋሹ ነው ማለት ነው፡፡  ራስዎን አይዋሹ፤ ራስን መዋሸት ዋነኛው የክሽፈታችን ምንጭ ነው፡፡ ራስን መዋሸት አንድም ካለማወቅ ነው አሊያም ከተንኮል ነው፡፡
የዚህን ጽሑፍ ርዕስ የመረጥሁት ባሳለፍነው ዓመት በወጣ መጽሐፍ ላይ ለተሰጠ ምላሽ ሲብላላ ቆይቶ ለመጠጥነት የደረሰ “መጠጥ” ነው፡፡ እውነተኛ መጠጥ በጊዜ ሲብላላ ጣፋጭ ይሆናል፡፡ አንድም መድሐኒት፤ አንድም አስካሪ!
እውነት እንደሚያሳምም ባሳለፍናቸው የስራ ጊዜያት ሳንገነዘበው የቀረን አይመስለኝም! አውነት ያሳምማል! ለውሸተኛሞች አውነት አስካሪ መጠጥ ነው! እውነትን ለሚሹ ግን መድሐኒት፡፡ እውነተኛው ክርስቶስ በአንዳንዶቹ እንደ “ጋኔላም” ለምን ታዬ? ለአንዳንዶቹ ደግሞ ትንሳዔ ለምንስ ተባለ?  እውነትን በአይነ ልቡናቸው ስላሳያቸው አይደለም የስቅላቱ መንስዔ?!
መጽሐፉ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፤ ብዙዎችን አነጋግሮ አልፏል፡፡ ታዲያ ላለፈ ነገር ምን አስጨነቀህ? ምንስ አስቀባጠረህ እንዳትሉኝ እሰጋለሁ፡፡ ካላችሁ ደግሞ ይህንን ጽሑፍ መቀጠል የለብዎትም ብዬ ካሳሰብኩዎ አንዱ ነዎት ለማለት ይዳዳኛል ፡፡ መጽሐፉ ከወጣ ከ365 ቀናት በላይ ከማሳለፉም በላይ፤ ዲ/ን ዳንኤል በጡመራው የሰጠውን አስተያየት በማየት የተሰጡትን አስተያየቶች ብዛት እና ይዘት ስንመለከት ዝም እንደንል አይገፋፋንም፡፡
ቀጣይነት የሌለው ውይይት፤ ቀጣይነት የሌለው ሃሳብ መተማመኛ የሌለው ውይይት “ክሽፈትን” እንደሚያስከትል ግልጽ ነው! “መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ” የነገሰበት ምክንያት ነው የውይይታችን መሠረት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መክሸፍን እንደምን ተሸከምነው!? ሰባኪው ሰለሞን በዘመኑ እንዲህ ሲል መሠከረ፡-
ከጸሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ እርሱም ከገዥ የሚወጣ ስህተት ነው፤ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ፡፡
መክብብ 10፡6
   የትላንቱ ታሪክ በዛሬ ተዘግቦ፣ በዛሬ ተጠንቶ፣ ተወያይተንበት የጠራ እውነት ላይ ካልደረስን ውሸታሞች ነን ማለት ነው፡፡ አሊያም የተጣራ ታረክ በዘጋቢው አልደረሰንም ማለት ነው፡፡ አሊያም አልተደማመጥንም፡፡ የኳስ ጨዋታ ዘጋቢ የተሳሳተ ዘገባ ቢዘግብም፤ ኳስ ጨዋታው አልተካሄደም ብሎ ቢዶልትም፤  ተጫዋቾች የተራገጡበት አውላላ ሜዳ ከተገኘ፤ ሜዳው ቢጋጋጥ፤ ቢላላጥ ከጨዋታው ተመልሰው የተገኙ ተጫዋቾች ቢገኙ፤ ተጫወትን ብለው ቢዘግቡ ሆኖም ዘጋቢ የተባለው /“ኮሜንታተር”/ አሁንም ጨዋታው አልተካሄደም ብሎ ቢያነበንብ… ኳስ ጨዋታው እና ዘጋቢው ምንና ምን ናቸው፡፡ የኳስ ጨዋታ ዘጋቢው ከዘመናት በኋላ የዘገበውን መረጃ ብናገኘው ከትክክለኛው የኳስ ጨዋታ ጋር ባይገናኝ እና ትውልድ ግን የሚሰማው ይህንን የተሳሳተ መረጃ ቢሆን… ይህንን ሃሳብ ከታሪክ ዘገባ እና ዘጋቢዎች/ጸሐፊዎች/ ጋር አገናኝተው የራስዎን ሃሳብ ይውሰዱ እና ይመራመሩበት፡፡ ልታግዙኝም ትችላላችሁ፡፡ /ወደኋላ እንመለስበታለን፡፡/
  ትላንት እኮ ነገ ነበረ፡፡ ነገር ግን ዛሬ ከሆነ በኋላ አልፎ ደግሞ ትላንት ሆኖል፡፡ ቀናትን በነገ፣ በዛሬ እና በትላንት መከፋፈሉ እንደ እኔ እይታ ከስህተት ለመማር ብቻ ይመስለኛል፡፡ አንድ አባባል አባባል እጅጉን ይማርከኛል፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“የምጽአት ቀን ለምን እንዲህ ረዘመ?” ሲባል
“ለንስሃ!” የሚል መልስ ያስደስተኛል፣ ያረካኛል፣ ያሳምነኛል፣ ያጽናናኛል፡፡ ምክንያቱም ከዛሬ ስማር ለነገ የተሻላ ስለምሆን ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ አልፎ ትላንት ሲሆን  ከዛሬው ትላንትና እንድማር ስለሚረዳኝ ዛሬ ላይ መሆኔ እድለኛ ነኝ! ዛሬ የንስሃ ቀን ናት! ዛሬ የመዳን ቀን ናት! ነገ የምጽአት ቀን ናት ምክንያቱም ማንም ስለ ነገ እርግጠኛ የሚሆን የለምና፡፡ ሞት መቼ እንደሚወስደን ስለማናውቅ ፤ እንደ ሌባ ባልታወቀ ሰዓት እንደሚመጣ ተነግሮናል፡፡ ዛሬ ማለት ደግሞ አሁን ማለት ነው፡፡ ተደጋጋሚ አሁን /ንስሃ/ ማግኘት ምንኛ መታደል ነው! እነዚህ ተደጋጋሚ ዛሬዎች ደግሞ ትላንትን አሻሽለው ነገን ፍንተው አድርገው ካላሳዩን እነዴት የተሻሉ ይሆናሉ? ስለዚህ አሁን የትላንቱን የምንጨነቅበት፣ የምንዋጋበት፣ የምንጨቃጨቅበት እና ቂም የምንያያዝበት ሳይሆን የምንማማርበት፣ የምንወያይበት፣ የምንለወጥበት እና ንስሃ የምንገባበት ስህተታችንን የምንናዘዝበት ሊሆን ይገባል፡፡ “ትላንት ያልዘራው ዛሬ አይበቅልም፤ ዛሬ ያልተዘራው ነገ አይበቅልም” በ“መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” /ገጽ 51/፡፡
በዚህኛው አንቀጽ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የዛሬ ዓመት ለወጣ ጽሑፍ አሁንም ምለሽ ለመስጠት ተገድጃለሁ፡፡ ያስገደደኝ ቂም አይደለም፡፡ ያስገደደኝ ጥላቻ አይደለም፡፡ ያስገደደኝ ክርክር መውደድ አይደለም፡፡ ያስገደደኝ አውነትን ማምለኬ ነው፡፡ የማመልከው አውነት ራሱ ይፍረድብኝ፡፡
 ለ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍ ምላሽ በርካታ አስተያየቶችን አንብቤያለሁ፡፡ መጽሐፉንም ባንዴ በማነብነብ ሳይሆን ቀስ እያልኩ ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ አሁንም ነገም አነበዋለሁ፡፡ ለመጽሐፉ ከተሰጡት አስተያየቶች ደግሞ በርካታ ተከታዮች ያለው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የሰጠው ትኩረቴን ስቦታል፡፡  ጦማሪው ወደ 27ሺ የሚጠጉ ወዳጆች/ላይክ/ እና ከ4 ሚልዮን ጡመራውን/Blog/ እንደጎበኙት አብስሮናል፡፡ ስለመጽሐፉ አስተያየት በሰጠበት ጽሑፍ ስርም ቢያንስ ከ120 በላይ አስተያየቶች ተሰጥተዋል፡፡ እያንዳንዱንም ለማንበብ ሞክሬያለሁ፡፡ ስለመጽሐፉ የተሰጡት ምላሾች ጥቂቶች ናቸው፡፡ ሳያነብ አስተያየት የሚሰጠው ብዙ ነው፡፡ አንድ ሰው እንግዲህ 120 ሰዎችን  የመያዝ እድል አለው፡፡ ይህ ለኔ መሪ/ ገዥ/ ነው፡፡ ራስን መምራት ከመመራቶች ሁሉ ከባድ እና ታላቅነት ነው፡፡ አባት/ የቤተሰብ መሪ/ ቀጥሎ በመሪነት ደረጃ ትልቅ ድርሻን ይይዛል፡፡ 4 ሚልዮን ጊዜ ሰው የተከታተሉት፤ እና በአንድ ጡመራ ገጽ ብቻ ከ120 በላይ አስተያየቶችን የያዘ ደግሞ ትልቅ መሪ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እንዲህ አይነት እድልን ያገኙ መሪዎች/ገዥዎች/ ደግሞ ለአንድ ማህበረሰብ እና አገር መለወጥ ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡ 
በአገረ አበሻ ልምድ ውስጥ ነገሮች በአይን ከመታየታቸው ውጭ በሚነገሩት እና ባልታዩ ምክንያቶች አማካኝነት ውሸት ሳትታሰብ ነግሳ የቆየች ይመስለኛል፡፡ በአይን ከነበረው እና ድርጊቱ ከተፈጸመበት ሰው ይልቅ ያልነበሩት ሰዎች ብዙ ሊያወሩ ይችላሉ፡፡ ሳይታይ የሚወራ ነገር ደግሞ እንደ አሁኑ ፓርላችን /99.9/ ውሸት ነው፡፡ አደራ ሰዎች ፓርላማውን ውሸት አላልኩም! ፓርላማውን የጠቀስኩት ለ99.9 ለምትለዋ መረጃ ብቻ ነው!
ታዲያ በነዚህ ቀናት ውስጥ መጽሐፉን ሳነብ፤ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የጻፈውን ምላሽ ሳነብ እና የተሰጡ አስተያየቶችን ስመለከት ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ ከውስጤ ጋር ተሟግቼ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡ የተገደድኩበትን ምክንያት ከላይ ለመጥቀስ ሞክሬያለሁ-ከቶም የጽንፈኝነት የጨለምተኝነት እና የጥላቻ ሆነው እንደሰይተረጎሙ፡፡
ከዲ/ን ዳንኤል ምላሽ ውስጥ በጣም ግራ የተጋባሁባቸው ሃሳቦች ነበሩ፡፡ በመሰረቱ የዲ/ን ዳንኤል ምላሽ ልክ እንደፓርላማው/99.9/ ያህሉ አስቂኝ ነው፡፡ አደራ አሁንም ፓራላማውን አስቂኝ አላልኩም! ፕ/ር መስፍንም በምላሻቸው በነጥብ በነጥብ አስቀምጠውታል፡፡
ከላይ ጀምሬ የተውኩትን የኳስ ጨዋታ እና የዘጋቢውን ትስስር በማስታወስ ልመልስዎ፡፡ የጠቀስኩት ዲያቆን ዳንኤልም ለምሳሌነት ስለጠቀሰው ነው፡፡ አንዲህ ሲል፡-
ታሪካችን ከሽፏል ብንል እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት?
ለእኔ ይህ አካሄድ አንድ ሰው ሌላ ሰውን የገደለበትን ዜና የሠራውን፣ ለዜናው ትንታኔ ዜና ያቀረበውን ጋዜጠኛና ተንታኝ የግድያው ወንጀል አባሪ ተባባሪ፣ ወይም ደግሞ ለግድያው ምክንያትና መነሻ አድርጎ እንደማቅረብ ነው፡፡ ዘጋቢውን ‹ወንጀለኛ› ማለትና ዘገባውን ‹የወንጀል ዘገባ› በማለት መካከል ልዩነት አለ፡፡ ዘጋቢው ወንጀለኛ የሚባለው የሠራው ዘገባ ሕግን የተላለፈ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ዘገባውን የወንጀል ዘገባ የሚያደርገው ግን ስለ አንድ ስለተፈጠረ ወንጀል የቀረበ ዘገባ ከሆነ ነው፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን የታሪክ አዘጋገብና የታሪክ ጥናት ለብቻው ቢተነትኑትና ያም ትንተና የታሪክ አጻጻፋችንና አተናተናችን የተሳካ ነው ወይስ ያልተሳካ? አስመስጋኝ ነው ወይስ አስነቃፊ? ተመስጋኝ ነው ወይስ ተነቃፊ? የሚለውን ቢተነትኑት እስማማ ነበር፡፡”
በሚል ሃሳብ ለመተንተን ከሞከረ በኋላ የዝናብ መዝነብን ከሜትሮሎጂ ባለሙያ፤ የሂሳብ ኦዲተር ባለሙያን ከድርጅት ትርፋማነት-ኪሳራነት፤ የእግር ኳስ ዘጋቢን ከኳሱ ውጤት ጋር በማያያዝ በማቅረብ የታሪክ ጸሐፊ ባለሙያን ከታሪክ ስኬት እና ክሽፈት ጋር አቆራኝቶ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡ በማለት መቀመጡ የአስተያየቱ ትልቁ ስሕተት ነው፡፡ ይህንንም ቢያመን እና ለ4 ሚልዮን ተከታዮቹ ቢያሳውቅ አሸናፊው እርሱ ነበር፡፡
የመጀመርያው የታሪክ ክሽፈትና ታሪክ ጸሐፊዎች እንዴት ነው የተገናኙት? የታሪክ ክሽፈትን ለማሳየት የታሪክን ሂደት ተከትሎ አንድን ሁነት ከየት ተነሥቶ የት እንደደረሰ በመተንተን፣ ያም ሁነት ከሽፎ ከሆነ የከሸፈበትን ምክንያት ማቅረብ ሲገባ ታሪካችን ከሽፏል ብንል  እንኳን ‹የከሸፈውን ታሪክ› የጻፉት ወይም ያጠኑት ምሁራን እንዴት ነው ከታሪክ ክሽፈት ጋር ሊገናኙ የቻሉት? ሲል ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል፡፡
   ከፕሮፌሰሩ መጽሐፍ ከገጽ 41 ጀምሮ እስከ ገጽ 54 ድረስ ዲያቆን ዳንኤል ለጠየቀው ጥያቄ ማብራሪያ የሚሰጥ መልስ ይዘዋል፡፡ ሁነት ምንድን ነው፣ የታሪክ ሁነት ምንድን ነው፣ ታሪክ መጻፍ ዓላማ አለው ወይ? በሚሉ ሦስት መሰረታዊ ነጥቦች አጥጋቢ በሆነ በጥልቅ ምርምር እና ፍልስፍና ተውበው ተጽፈዋል፡፡ በገጽ 43 የተጻፈውን ሃሳብ ጥልቅ ምርምር እና አስተማሪ ይዘት ያለው ፍልስፍና ተቀምጦ ሳንረዳው የመጽሐፉን ገጽ ብንቆጥር ማነብነብ ብቻ እንደያዝን ተደርጎ እንዲቆጠርብን እናሳብቃለን! የሚያንገበግበውም ይህ ነው፡፡ ቢያንስ 4 ሚልዮን ህዝቦች ይህንን ጥልቅ ምርምር እንዳያነቡት ሆነዋል፡፡ ቢያነቡትም እንዳይረዱት ሆነው፡፡
ክፍል 2

ታሪክን ልንቀበል ከምንችልባቸው ዘዴዎች ውስጥ የታሪክ ጸሐፊዎች ድርሻ በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ የጠጠረ ድንጋይን መካድ ስለማንችል በተጨባጭ የሚገኙ ቀዳሚ መረጃዎች/ ፕራይመሪ ሪሶርስስ/ እንደ ታሪክ ነጋሪ፤ አስተማሪ መስካሪ ሆነው ይቆጠራሉ፡፡ ልሳን አበጅተው ግን በዚህ ወጥቶ በዚህ ገብቶ እንደዚህ ባለው መንገድ አድርጋችሁ ስሩኝ፣ አፍርሱኝ፣ ለውጡኝ፣ ተማሩ፣ ከትላንት ተሸላችሁ ተገኙ እያሉ ሊያስተምሩን አይቻላቸውም፡፡ ይህንን ማድረግ የሚችለው ታሪክ ዘጋቢው ነው፡፡ የዜና መዋዕል  አይነት የታሪክ መዝጋብ፣ ለትውልድ ትውልድ አስተማሪ እና ከታሪክ ተሸሎ እንድንገኝ የሚረዳን ቁልፍ ነው፡፡ የታሪክ ዘጋቢው ግን ትክክለኛ ዘገባ ካልያዘ፣ አስተማሪ የሆነ የሃሳብ መንገድን ካልጠቆመ፣ ታሪክ በተሳሳተ አቅጣጫ እንዲጓዝ እና ዛሬ ከትላንት እንዲሻል፤ ነገም ካዘሬ የተሻለ እንዲሆን የሚያደርጉት ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን እየታወቀ፤ አንድ የእግር ኳስ ዘጋቢ ተጫዋቶቹ በሚሰሙበት ሜዳ እንደ ደጋፊ /ቲፎዞ/ እየዘገበ ሚያጫውት በጨዋታው ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል እያወቅን፤ ኳስ ዘጋቢ የኳስ ጨዋታውን ሲዘግብ ለውጤቱ ስኬታማነት የሚረዱ ሃሳቦችን እየጠቆመ ቢያጫውት ለሚደረገው ጨዋታ እንኳ ለውጥ ባያስመጣ ለቀጣይ ጨዋታዎች መሻሻል አይነተኛ እና ቁልፍ ሚና ሊጫወት እንደሚችል በመዘንጋት ዲ/ን ዳንኤል የኳስ ዘጋቢን ከእግር ኳስ ጨዋታ ስኬት/ውድቀት ጋር ማነጻጸሩ በግላጭ የአስተሳሰብ ጥልቀቱን ያሳየበት ነጥቡ ነው፡፡
በፕሮፌሰር መስፍን መጽሐፍ የተጠቀሱት የታሪክ ምሁራን እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ዘጋቢ አድርጎ መውሰድም ተገቢ አይደለም፡፡ የእግር ኳስ ዘጋቢ/ኮሜንታተር/ በወቅቱ የነበረ ሰው ሲሆን እነዚህ የታሪክ ምሁራን ያቀረቡት ጽሑፍም ባልነበሩበት ዘመን የመዘገቡትን ድርሳን ነው፡፡
ጸሐፊያን የትላንትን ታሪክ መቀየር ፈጽሞ ባይችሉም፤ በተደራጀ እና በተጠና አዘጋገብ እና ለትውልድ ማስተላለፍ ስራ ላይ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖራቸው ፕሮፌሰሩ አስረድተውናል፡፡ ተፈጥሮም አስተምሮናል፡፡
ደቀመዛሙርት ትክክለኛወን ትምህርት ከመምህራቸው ባያገኙት፣ ባይቀበሉት፣ ባይጽፉት፣ ባያስተላልፉት እና ክርስትና በዓለም ቢጠፋ ተጠያቂው ማን ነው?  ሰባኪያን በአንደኛው ክ/ዘመን አልነበሩም፡፡ ሆኖም ግን ለ21ኛው ክ/ዘመን ሚያስተምሩት ት/ት ምን ያክል ወሳኝነት እንዳለው ለሰባኪው ዲ/ን ዳንኤል ክብረት የምነግረው እኔ አይደለሁም፡፡
የታሪክ ዘጋቢ ትክክለኛ መረጃን ባያቀርብ፤ ያቀረበውም መረጃ ከታሪክ እንድንማር፤ ከትላንት ልንሻሻል የምንችልባቸውን ነጥቦች ባይጠቁምልን የታሪክ መጻፍ ዓላማው ምንድን ነው? የታሪክ ህልውናስ ምኑ ላይ ነው?
በዚህ ምክንያት የታሪክ ቅብብሎሹ ይበጣጠሳል ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አሁን የተፈጠረው “ብሔር ብሔረሰብ” አሁን ያሉ ምሑራን ባስቀመጡልን አረዳድ እና አተረጓጎም በመቅረቡ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ እና  አስተሳሰብ በተቀመጠልን የታሪክ ምሁራን/ዘጋቢዎች አሊያም መሪዎች ተጽዕኖ መሆኑ እየታወቀ፤ የተፈጠረው የታሪክ ምሑራን አረዳድ/አተረጓጎም ከአገር ግንባታ አጠቃላይ ገጽታ አንጻር የተለየ ሆኖ ቀርቦልን ቢሆንም ጥቅሙን እና ጉዳቱን ማመዛዘን እንችላለን፡፡ ይህ በአደባባይ የሚያሳየን የታሪክ ምሁራን በታሪክ ላይ የሚኖራቸውን አሻራ ነው፡፡
ገበሬው ትላንት የዘራውን ዘር ለዛሬ ሲያስተላልፈው ዘሩን እንዲበቅል ከማስተላለፉ በተጨማሪ የአዘራሩንም ሁኔታ፣ የአበቃቀሉንም ሁኔታ፣ የተሻሻለ መንገድን እየጠቆመ ካልመጣ የነገው ዘር ዘሪ ከትላንት የተሻለ ምርት፣ ከዛሬ የተሸለ ውጤት ሊያገኝ ይከብደዋል፡፡ የነገው ዘር ዘሪ በራሱ ፈልጎ የሚዘራውን ዘር ከዛም ተተኪው ዘር ዘሪ ሌላ የራሱን ዘር ቢዘራ፤  ሁሉም የራሱን ዘር እየዘራ ቢቀጥል፤ የመጀመሪያው ዘሪ ለመጪው ዘሪ አልተጨነቀም፤ የዛሬው ዘሪ ከትላንትናው ዘሪ አልተማረም፤ የነገውም እንደዚሁ፡፡ በኢትዮጵያም ታሪክ የምናየው ይኽንን ነው፡፡ አንዱ ይነሳል ሌላኛውን ይደፈጥጣጣል፤ ይበጥሰዋል፤ ያከሽፈዋል…. መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የቀረበውም ይኸው ነው፡፡
የሚገርመው መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ተብሎ የቀረበው የመጽሐፍ ታሪክ በዋናነት የያዘው ሐሳብ አጀማመሩ በምዕራፍ አንድ ላይ መክሸፍ እንደ… ተብሎ ሳይሆን መክሸፍ በ… ተብሎ ተቀምጧል፡፡ ዲያቆኑም ይህንን ገጽ አላየውም ወይንም አይቶት አላስተዋለውም አሊያም እያየዬ በተንኮል አልፎታል፡፡ ማን በቀናነት ይዬው? መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ እና መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ በጉልህ ይተያያሉ፡፡ መክሸፍ በ….እና መክሸፍ እንደ.. ተብለው መቀመጣቸው ዲያቆን ዳንኤል ለጠየቀው ትልቁ ጥያቄ መልስ ነበር፡፡ ታሪክ ይከሽፋል ለሚለው ጥያቄ ፕሮፌሰር መስፍን በግልጽ ቋንቋ ለማስረዳት ከመጣራቸውም ባሻገር መክሸፍ በኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርዕስ መጽሐፋቸውን ጀምረዋል፡፡
ዲያቆን ዳንኤል እንዲህ ብሎ ጻፈ
አንድ መሪ
ለመሆኑ የገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ የብላታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ የአለቃ ሐዲስ ዓለማየሁ፣ የአቤ ጉበኛ፣ የበዓሉ ግርማ፣ ቤታቸው የት ነው? የት ነበር የጻፉት? ረቂቃቸው አለን? የጻፉበት ብዕር አለን? ምን ሰየምንላቸው? በምን እናስታውሳቸዋለን? ለመሆኑ የኢትዮጵያን የድርሰት ጉዞ የሚያሳይ አንድ ሙዝየም እንኳን አለን? የሺ ዓመታት የሥነ ጽሑፍ ታሪክ የምንደሰኩር ጀግኖች ሥነ ጽሑፋችን ከየት ተነሥቶ የት ደረሰ? የድርሰት ጉዟችን ከየት መጥቶ የት ደረሰ? የዕውቀት አባቶቻችንና እናቶቻችን እነማን ነበሩ? እስካሁን ምን ያህል ደራስያንን አፍርተናል? እነማን መቼ ተነሡ? እነማንስ ምን ሠሩ?
ፕሮፌሰር በመጽሐፋቸው አጥብቀው የከተቡት ይህንን ሐሳብ ነበር፤ ዳንኤል ክብረት አጥብቆ የተከራከረበት ሐሳብ ይህ ነው የተከራከረውም መጽሐፍ ደግሞ የፕሮፌሰሩን ነው፡፡
ይህ ሁሉ ሀሳብ እና ተጨማሪ አስተማሪ፣ አስደማሚ፣ አመራማሪ ጭብጥ ያላቸው ዓበይት እና ንዑሳን መዘክሮች ተቀምጠው በተሳሳተ መንገድ መጽሐፉን መረዳት፤ ያልተረዱትን ማሳሳት፤ የተረዱትንም ማወናበድ፤ ከዚያም “በመሪነት” ትልቅ ዕድል ይህንን ድርጊት መፈጸም ትልቅ የታሪክ ክሽፈት ሸክም ሆኖ መገኘት ነው፡፡ የዚህ ጥሑፍ ሐሳብም በኢትዮጵያ ታሪክ የመክሸፍ ሸክሞቻችን ነው!
የመክሸፍ ሸክሞቻችን እነማን ናቸው?
በግለሰብ ደረጃ አሊያም በቡድን የተወሰነ ጥያቄ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ታሪክ ይሰራል፣ታሪክ ያበላሻል፣ታሪክ ያሳካል፣ታሪክ ያከሽፋል፡፡ መሪዎቻችን የተቀበሉት የመሪነት እድል በጠበንጃ መሆኑ ትልቁ የመክሸፍ ሸክሞቻችን መንስኤያት ናቸው፡፡ በመሪነት ደረጃ ያሉ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድናት ስህተታቸውን በመጀመሪያ ደረጃ ሊገነዘቡት በተገባ፤ ክልተገነዘቡትም የሚገነዘብ ግለሰብ.ቡድን እንዲኖር የመፍቀድ ስርዓትን ማሰልጠን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለቱ በሬዎች ሲዋጉ የሚጎዳውን እንገንዘበው፡፡ ሰዎች ሊዋጉበት የሚገባቸው ቀንድ አልተሰራላቸውም፣ ጭንቅላታቸው የሚዋጉበት ጠፈጥሮአዊ ጸጋ ነው፡፡ ይህም ቀንድ ሊያስበቅል ሳይሆን አንዱ አንዱን ሊጎዳው ሳይሆን በሀሳቡ አሳምኖት ሊተማመኑ፤ የወሰደውን ርቀት ተጉዘው ሰው መሆናቸውን እንዲያሳን ነው፡፡ ሰው እንዲማር ነው፡፡ ሰው እንዲሰለጥን ነው፡፡ ዲያቆን ዳንኤል እና ፕ/ር መስፍን “ሲዋጉ” እጅግ በጣም ተደስተን ነበር፡፡ በታሪካችን ላይ “እየተዋጉልን” ነው ብለን ተደስተን ነበር፡፡ ሰው በሃሳብ ሲዋጋ አንዱ ወገን እንዲሚያሸንፍ እና እንደሚተማመኑ የተፈጥሮ ግዴታ ነው፡፡ ይህ ባይንማ ከመጀመሪያውኑ መዋጋት ባልተፈጠረ ነበር፡፡ ሐሳብ ተሰነዛዝሮ በቀጥተኛ በሐሳቡ ላይ ተወያይተው መዳረሻ ያለው ሐሳብ ያስፈልጋል፡፡ በሁለቱም ሰዎች ጥላ ስር ሆነው ያሉ ሰዎች በእጅጉ ይጠቀማሉ፡፡ ኳስ የሚጫወቱ ቡድኖች ሶስት እድል ይዘው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይታወቃል፡፡ ፕሮፌሰር መሰፍን  እና ዲ/ን ዳንኤል ወደ ሜዳ ሲሄዱ “ጨዋታው” ማርኮን ነበር፡፡ ውጡቱን ግን አላየነውም፡ ማን አሸነፈ? ማን ተሸነፈ? እንዴት እኩል በእኩል ወጡ? ያሸነፈውን ማንኛውም ሰው በራሱ አረዳድ እና አተረጓጎም ሊዘይደው ይችል ይሆናል፤ ያ አይደለም ብቸኛው እና ትልቁ ጭብጥ፤ ትልቁ ጭብጥ እንዴት ተስማሙ? የትኛው አካል መሸነፉን አመነ? በመሸነፉ ምን ተማረ? ምን አስተማረ? ምን ውጤት ተገኘ?
በታሪካችን ብዙ ውጊያዎች ተካሂደዋል፡፡ ያሸነፈው ማን እንደሆነ አልተነገረንም! ከመሸናነፍ ምን እንደተገኘ አላወቅንም… ሌላ ውጊያ ለመጠንሰስ እንነጋገራለን…. ውጤቱ መክሸፍ ነው!!
ይህም አንድም አላዋቂነት አሊያም ተንኮለኝነት፡፡ አላዋቂ እንዳንላቸው የአዋቂነት መልክን ይዘዋል፤ ተንኮለኛ እንዳንላቸው ቅቤ ምክርን ለማንጠር ተዘጋጅተዋል፡፡ እንደነዚህ ያሉ መሪዎች ኢትዮጵያን ለዘመናት መርተዋታል፡፡ የከሸፈ ታሪክ ሸክሞቻችንም እነርሱ ናቸው፡፡ አምነው አይቀበሉም፤ ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም፤ የመሪነት ቦታውን/ዙፋኑን ግን ይዘውታል፡፡ አይለቁትም፤ እንኳንስ ከዙፋናቸው ሊለቁ ከራሳቸው አላዋቂነትም ለመላቀቅ ፍንጩም የላቸውም፡፡ የያዙዋቸውን ተማሪዎችም/ተከታዮችንም/ እንዳሳሳቱ እንደገዘቱ ይኖራሉ፡፡ በመሪዎች ስንፍና የሚመጣ  ስህተት ክፉ ነው፡፡ ሰለሞንም የመሰከረው ይህንን ነው፡፡
ከጸሐይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ እርሱም ከገዥ የሚወጣ ስህተት ነው፤ ሰነፍ በታላቅ ማዕረግ ተሾመ ባለጠጎች ግን በተዋረደ ስፍራ ተቀመጡ፡፡
መክብብ 10፡6