Mar 16, 2013

ለፕሮፌስር መስፍን ወ/ማርያም እና ለዲቆን ዳንኤል ክብረት የቀረበ ሃሳብ፡፡













ለፕሮፌስር መስፍን ወ/ማርያም እና ለዲቆን ዳንኤል ክብረት የቀረበ ሃሳብ፡፡
       በላ ልበልሃ!                                                                                                                                
ያጤ ስርዓአቱን የመሰረቱን
አልናገረም ሀሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን››
              **   
ውሃ የሌለበት ጅረት
ሚስት የሌለችበት ቤት
ጀግና የሌለበት ጦርነት
እውነት የሌለበት ሙግት
ሁሉንም አይጠቀሙበት

ተጠየቅ!
አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ  ባህሎች፣ ወጎች ሰልጣኔ እና የታሪክ ሃብታም ነች፡፡ ከቀን ወደ ቀን፤ ከወር ወደ ወር፤ ከአመት ወደ አመት፤ ከዘመን ወደ ዘመን ስንሸጋገር ግን ይህ ሁሉ ሃብት ሲዳከም ሲቀዘቅዝና ደብዛው ሲጠፋ እያየን እንገኛለን፡፡ ብዙ ነገሮቻችን አሁን ላይ የሉም:: የጥንቶቹ ትክክል አልነበሩምና አሁን እየተጠቀምናቸው አይደለም ብለን ብንወስድ ካደጉ የተባሉ ሀገራት ግን የጥንት ታሪኮቻቸውን ከዘመናዊው ስልጣኔና ጊዜ ጋር በማጣመር የበለጠ ሲምዘገዘጉ፡፡ እያየን ነው ለምሳሌ እንግሊዝና ጃፓንን መውሰድ እንችላለን::
      የእንግለዝ ክሮዋዌል አገሩ የኢንዱስትሪ አገር እንድትሆን ያመቻቸው አብዮት ግቡን ሲመታ የጃፓኑ አፄ ሙትስሒቶም ሂቶም ጃፓንን ከመሳፍንት አገዛዝ ነፃ ሲያወጣ የኛው አፄ ቴዎድሮስም ተመሳሳይ አላማ ነበረው ታዲያ የትኛው ተሳካ?
      እንገሊዝ በ28 እጥፍ ትበልጠናላች የሚል እሳቤ አለኝ፡፡ 1ፓውንድ ለ28 ብርን በማሰብ፡፡ እንግሊዝ አሁንም የቀደመ ማንነቷን ከዘመናዊው ስልጣኔ ጋር በማዋሀድ ቀደምትነቷን እያሳየች ትገኛለች::  
አንዳንዴ  በቴሊቭዥን መስኮት የፓርላማቸውን ክርክር በምመለከትበት ወቅት አስተውላለሁ፣ እናዳዳለሁ፡፡  ብዙ ትምህርት እወስዳለሁ፡፡ በጣም የሚገርመው የፓርላማው አይነት ክርክር ሙግት በኛው አገር የነበረ በህዝቡ ዘንድ እንደ ባህል ሆኖ የሚሰራበት የታሪክ ክስተት ነበር፡፡ ተጠያቅ! ተብሎ የሚታወቀው ይህ ሙግት ስልቱን ቀይሮ በዘመናዊው ስልጣኔ ተደግፎ ህግና ደንብ ወጥቶለት ጊዜና ገደብ ተሰጥቶት ብንጠቀምበት የተሳካ ታሪክ አካል ያደርገው ነበር፡፡ አሁን ላይ ያለ ትውልድ ግን  ይህን ባህል አያውቀውም::  ይህንን የአደባባይ የችሎት ባህል ወይንም ልማዳዊ የአሞጋገትና የዳኝነት ስርዓት የዘመናዊውን ለውጥ ተፅኖ መቋቋም አቅቶት ከአደባባይ ገለል ማለት አልፎም ደብዛው የጠፋ የታሪክ አካል ሀኖ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ መክሸፍ የሚለው ቃልስ አያሰጠውም ትላላችሁ? የግሪክ ፈላስፎች ቀኑን ሙሉ ሽንጣቸውን ገትረው ሲወያዩና ሲከራከሩ ሃሳባቸውን ሲያፋጩ እንደነበር አንብበናል፡፡ ፍልስፍናው በክርክር /በሙግቱ/ ሲቀርብ ፈጣሪ አለ የለም የሚለው ከኾነ በተገለጠ እውነት ላይ መሟገት አዕምሮንና ጊዜን ማባከን ይመስለኛል፡፡ በተጨባጭ እውነቶች/በተረጋገጡ እውነቶች/ ላይ ግን መሟገትና መከራከር ግን ህዝብን እያስተማሩ ወደ አንድነት ወደ እውነት የሚያመጣ በመኾኑ ሊበረታታ የሚገባ ሃሳብ ይመስለኛል፡፡  
  ይህንንም በማሰብ ታሪኮቻችን ከሽፈው ይቅሩ ማለት ሳይሆን ያሉበትን በመፈተሽ የሚጠቅመውንና ዘመኑ በሚፈቅደው መልኩ እንድንጠቀምበት መቻል ታላቅነት ነው፡፡ ብዬ እገምታለሁ፡፡ የከሸፈን ወይም የጠፋን ታሪክ መደተሸ ወደ ታሪክ ስኬትም የሚመራ ጭብጥ ይኖረዋል፡፡
‹‹በላ ልበልሃ!
ያጤ ስርዓአቱን የመሰረቱን
አልናገረም ሀሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን››
እየተባለ ሁለት ከሳሽና ተከሳሽ የአሞጋገትና የአነጋገር ሰልትን የመቅሰሚያ፤ ህግና ዳኝነትን የመመሪያ፤ ከሹማምንትና ከመሳሰሉት ከፍተኛ ሰዎች ጋር የመተዋወቂያና ለዳኝነትም ሆነ ለሌላ ስልጣን የመመረጫ ቦታ ጭምር በመኾኑ ትልቅ ሰፍራ የነበረው ባህል ነበር::  
ልምድ ያላቸው በማህበረሰቡ ዘንድ የተከበሩ የሚባሉት ታሟጋቾች እንኳ ልምድ ከሌላቸውና ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸው ተመጓቾች በሚቀርቡበት ወቅት የባለ ብዙ ልምድ ተሟጓች ደካማ ተሟጋቹን በንቀት አይን በማየት እንዴት እንደሰደበው እንዲህ ሲል ሃሳቡን ይሰጣል::
ባለ ልበልሃ
ያጤ ሰርዓቱን የመሰረቱን
አልናገርም ሀሰቱን
ሁሌ እውነት እውነቱን

በሳማ ሲባላ ጣቱን የሚልሰው
አደባባይ ቆም አንድ የማይመልሰው
ሚሰቱ ስትቆጣው እጓሮ እሚያለቅሰው
አንተም ከኔ ጋር እኩል ሰው እኩል ሰው፡፡ በማለት ይናገራል፡፡
  ይህ ባህል በሰለጠነው ህዝብ ዘንድም አንደ ጥብቅና ስራ በመዘናዊ  መልኩ ሲቀርብ እናየዋለን፡፡ የአሜሪካ የዳኝነት ስርዓት መልኩን ለውጦ የቀረበ ይመስለኛል፡፡ ማትሎክ የተባለ ተከታታ የቴሌቪዥን ድራማን እያስታወሱ፡፡ በአንድ ወቅት አገራችን ይህንን ባህል ተጠቅማበት ነበር፡፡
  ተበደልኩ የሚል፤ ተጓዳሁ የሚል ለሹሙ ሄዶ ጉዳዩን በማስረዳት ተከሳሹ ይቀርብና በላ ልበልሃ እየተባበሉ  እውነትን ይዘው ይሟገቱ ነበር:: ከዛም በዳኛው ፈራጅነት በታዳሚው መስካሪነት ፍርድ ተፈርዶ ከሳሽ እስጥ ፈረስ ፣ ዋርዲት በቅሎ እስጥ፣ ዳማ ፈረስ እሰጥ፣ ቦራ ፈረስ እሰጥ፣ ሳሙና ፈረስ፣ እሰጥ ሻሽ የመሰለ ማር እስጥ! እያለ ተከሣሽም  ለፈረሰህ እገባ እየተባባሉ እስጥ-አገባ ወይንም ውርርድ ያቀርባሉ:: ተከሳሽም እሸነፋለሁ ብሎ ካሰበ /ጥርጥር ውስጥ ከገባ / ከሳሽ ውርርዱን ዝቅ እንዲያደርግለት ‹‹ውርርድህን አሰላስል›› ይለዋል፡፡ ይህም ማለት ለምሳሌ በቅሎ እስጥ ብሎ ከሳሽ ውርርዱ ተክሎ እንደሆን  ‹‹ፈረስ እስጥ›› በማለት ይለውጥላትና ተከሳሽም ‹‹አገባ›› ብሎ ለፈረስ ውርርድ የተተመነውን መቀጮ ይከፍላል፡፡ እስጥ-አገባ የሚለውም አባባል የመጣው ከዚህ ነው፡፡ ተከሳሽ ክሱን ካመነ ግን ‹‹አጉራህ ጠናኝ!›› ብሎ ሙግቱን ባጭሩ ይቀጨዋል፡፡
ባጉራህ ጠናኝ የተፈታ
መሀል አአዳውን የተመታ
የሚባለውም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ እንዲህ እየተባባሉ እውነትንና ፍርዱን የሚያገኙበት ባህል በዚህች አገር ነበር፡፡
  ወቅቱ እየሄደ የነበረውም ሙግት መልኩን እየቀየረ መሄዱ አለቀረም፡፡ በፈራጅና በተሟጋቾች መካከል ያለው ቅርበት፤ ሰውም ያለምንም ስራ አደባባይ ሙግት ብቻ ማየትን እንደ ትልቅነት ማየቱ እየተከሰተ በመምጠቱ እንደጉዳት የሚታይ ቢሆንም እውነትን የያዘ ህሊና ያለው ዳኛ እስካለና የሙግቱን ስርዓት የጊዜ ገደብና ደንብ ቢኖረው ጥቅሙ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህንንም ነጋድራስ ገብረ-ሕይወት ባይከደኝ ‹‹መንግስትና የህዝብ አስተዳዳር› የተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ በአገራችን ስለሚገኙ ብሄራዊ ችግሮች ውስጥ ሙግትን በሚመለከት ጽፈዋል፡፡ ስራን ትተው በክርክር በሙግት ብቻ መዋለን
 እንደችግር አስቀምጠዋል፡፡ ሆኖም በዘመናዊ አሰራር ቢቀርብና እውነትን ወደ አደባባይ የማውጣት ባህል፤ እንደበተ ርቱዕነትን፤ በራስ የመተማመንና ባህሉንም ከማስተላለፍ አኳያ ሊሰራበት የሚችል ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ዶክተር ሀይሌ ወልደ ሚካኤልም ‹‹የሞራል ውድቀት ዝንባሌ በትምህርት እድገት በኢትዮጵያ ላይ›› የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ ይህንን ሀሳብ በመደገፍ አቅርበው ነበር፡፡
   በዚህ ሙግት ወቅት በችሎት ይሰሙ የነበሩት የሙግት ግጥሞችና ምሳሌያዊ አነጋገሮች ጥልቀትና ውበት አሰተዋፅኦ ሳያደርግ እንዳልቀረ በመጠቆም ነገር ግን ሙግቱ እውነት የሌለው ከሆነ ስራ መፍታት በመሆኑ ጭምር እውነትን የሚያስገኝ ሙግት ( ክርክር) መታማመን ያለበት ሂደት ቢኖር ህዝብ ቢማርበትና ቢለወጥበት አጅግ አኩሪ የሆነ ባህል መሆኑ እያጠራጥርም፡፡
በለ ልበልሃ
ያጤ ስርእቱን የመሰረቱን
አልነገርም ሀሰቱን
ሁሉ እውነት እውነቱን!
ላምህ ብትወልድ ዛጎላ
ሚስትህ ብትላብስ ነጠላ
አንተ ብትለው እጥላ!
 አንደኛው ሲለው አደባባይ የማያዘወትረውና የኑሮ ደረጃው ዝቅ ያለም ተሟጋች
                በላ ልበልሃ ብሎ የተለመደውን ስንኝ ይከተልና
ላሜ ብትወልድ ዛጎላ
አውራውን አስመስል ብላ
ሚስቴ ብትለብስ ነጠላ
ቀን እስቲያልፍ ብላ
እኔ ብውል እጥላ
ያንተን ብጤ ነገረኛ ብጠላ!
በማለት የሆዱን ይመልሳል፡፡ በሙግቱ ወቅት ወቀሳ አሽሙርና ስድብ የነበረበት ቢሆንም ይህንን ለይቶ በማውጣት  በእውነትና በአመክንዮ ከዛም መተማመንን  በመያዝ መከራከር ግን ይቻላል፡፡ ስድብና አሽሙርን በማስቀርት፡፡
   ይህንን ባህል የተለያዩ የውጭ ፀሐፊያን ጠቅሰውታል፡፡ ዶናልድ ሌቪን ‹‹በዋክስ ኤንድጎልድ ( ሰምና ወርቅ) መጽሐፋቸው የጠቀሱት
‹‹ሙግት በአማራው ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ጉዳት ጠቅሰው አልፈዋል፡፡ ቻያናዊያን ይህንን ባህል አይጠቀሙበትም ነበር፡፡ ወደ ፍርድ ቤት መሄድን እንደጊዜም ሆነ ገንዘብ አባካኝነት ይቆጥሩት ነበር፡፡ በቻይና ባለጉዳዮች በሻይ ቤት ውስጥ ተሰብሰበው በመወያየትና በመደራደ በመካከላቸው ለተፈጠረው ቸግር መፍትሄ ይሹ ነበር፡፡ በማለት የፃፉ  ሲሆን ይህም ግን መልኩን ቀየረ እንጂ ተነጋግሮና ተስማምቶ ፍርድን ከማምጣት ጋር የሚለያይ አይመስለኝም::  ቀኑን ሙሉ ሲሟገቱ መዋል ጉዳቱ ግልጽ ነው፡፡ ቢሆንም ከላይ እንደጠቀስኩት ጊዜና ገደብ፤ ስርዓትና ደንብ ይዞ ግን መገልገል የሚጎዳ መስሎ አይታየኝም ::
      ጀርመናዊው ፕሮፌሰር ኢኖ ሊተማንም ከፍተሃ-ነገሥት እየተጠቀሰ ፍትኀ ርትዕ በሚሰጥባቸው ሽንጎዎች ( አደባባዮች) እየተገኘሁ የእስጥ-አገባን ሙግትና ፍርድንም በማዳመጥ ያስለፍኳቸው ቀናት ለኔ እንደገና ትምህርት ቤት እንደ መግባት ነበር ብሏል፡፡:      
 ጄነራል ቨርጂን ‹‹እኔ የማውቃት አቢሲኒያ›› The Abyssinia I know መጽሐፋቸውme በተሟጋቾች መካከል የሚደረገውን ሰርዓት ማራኪ መሆኑን፤ የነበረውን የቃላት አጠቃቀም በተሟጋቾች መካከል የሚደረግ የሰውነት እንቅስቃሴ ሳይቀር እጅግ ውብ እንደነበር ጽፏል፡፡ እንግዲህ አንድ አገር የኋላ ታሪኩን አጣርቶ በመያዝ ለአሁኑና ለወደፊቱ ትውልድ ጊዜው በሚፈቅደው ቴክኖሎጂ በመደገፍ ማንነቱን ካለቆና ካላስተላለፈ የታሪክ አስፈላጊነት የሚቀርበት እድል ሊከሰት ይችላል፡፡ የዚህም ፅሑፍ ዋና አላማ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የሚያጠነጥነውን ‹‹መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ›› መጽሐፍ ላይ በመመርኮዝ በወቅቱ ለተነሱት ክርክሮች ሀሳቦች  ላይ በመታዘብ ለምን ተጠየቅ! የሚለውን ባህላችንን እናስታውስበትም? በፕሮፌሰሩ መጽሐፍ በተቃራኒ  ገጽታው ላይ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች በማሰባሰብ ብንጠቀምበትስ የሚል ነው፡፡ በተለይ አስተያየት የሰጠውን ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን በማሰብ ይህ ገጠመኝ በታሪክ ትልቅ ስፍራ ሊኖረው እንዲችል በማሰብ ጥያቄውን ለሁለቱም ግለሰቦች አስተላልፋለሁ:: በዚህ ርዕስ ጉዳይ መጽሐፉን በማንበብ ያልተነጋገረ፣ ያልተገረመ፣ያልተበሳጨ፣ ያላዘነ፣ ያልተወያዬ፣ ያልጻፈ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ርዕስ ነው:: የዛሬውና የነገው ትውልድ ትልቅ መልስ የሚያገኝበት፤ ታሪኩን አውቆ ነገ ምን ልስራ ብሎ እንዲያውቅ ሃሳብ እንዲገበይ የማያደርገው በመሆኑ  ክርክሩ/ውይይቱ/ ቢሳካ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ይመስለኛል፡፡ ትልቅ ትምህርት የሚገኝበት ይመስለኛል፡፡ ምንም እንኳ ከሳሽ ተከሳሽ ባይኖርም:: ፈራጅ ዳኛ ህዝብ ሆኖ ሊያወያይ የሚችል አካል ቢኖርና ለታሪክ ትምህርት ቅርበት ያላቸው ምሁራን፤ የሚመለከታቸው አካላት፤ ማንኛውም ኢትዮጲያዊ ነኝ የሚል ግለስብ ቢሳተፍና ለህዘብ እውነቱ ቢቀርብ ለትውልድ ትልቅ አሻራ ሆኖ የሚያልፍ ተግባር ይመስለኛል፡፡ ስለ መጽሐፉ የካቲት 3 ቀን 2005 ዓ/ም በብሄራዊ ቲያትር የቀረበ ቢሆንም አጥጋቡውን ውይይት ማድረግ አልተቻለም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ከሽፏል ወይንስ አልከሸፈም የሚባል ነውን? በሚል ርዕስ በሁለት ቡድናት ቢካሄድ የሚኖረው ታሪካዊ አሰተዋጽኦ ትንሽ አይባልም:: በትንሽ ነገር ብዙ መስራት ይቻላልና፡፡ ይህ ትውልድ እውነት ይፈለጋል! እውቀትን የያዘ መረጃ የተደገፈ አንድ ሊያደርገው የሚችል ሀሳብ ይፈልጋል:: በታሪክ ውስጥ አንትና ይህን አደረገ:: ብሎ መፈራረድና ጥላቻን መፍጠር ሳይሆን በታሪካችን ከነበሩ ክስተቶች ለአሁንና ለነገ ማንነታችን በምን መልኩ ሊወሰዱና ትምህርት ልንቀስምባቸው እንችላለን? በሚለው ጉዳይ ላይ መወያየት የሚያወጣ ይመስለኛል፡፡ በቀላሉ ይህ የሙግት ( የመከራከሪያ ) ባህል ተጠየቅ በሚል መልኩ ቢዘጋጅ አንድም ባህልና ወግን ከማዳን አንጻር ሌላም እውነትን ነማስጨበጥ አንጻር ሊታሰብበት ይገባል፡፡
ውሃ የሌለበት ጅረት
ሚስት የሌለችበት ቤት
ጀግና የሌለበት ጦርነት
እውነት የሌለበት ሙግት
ሁሉንም አይጠቀሙበት
እየተባለ የሚመካከሩበት ሙግት ነበረን
ካያያዝ ይቀደዳል
ካነጋገር ይፈረዳል
አንድንተ ያለ ዘንገኛ
አይወለደም ሁለተኛ
ፍየል መንታ ትወልዳለች
አንዱ ለመጣፍ
አንዱ ለወናፍ
መጣፉ እኔ ወናፉ አንተ!
እየተባሉ አሽሙር የሚነጋገሩበት ነበር በአሽሙር መነጋገር መሰዳደብ ሳይሆን
መሪ የሌለበት መንግስት፤ እውነት የሌለበት ሙግት የሚለውን በመውሰድ ለእውነት እንኑር! በግል ሀሳብንና መልስን ከመመለላስ ተቀራርቦ፣ ተያያዞ ለህዝብ አርአያ ሆኖ በታሪክ ትልቅ ስኬትን መፍጠር ታላቅነትና አዋቂነት ይመስለኛል:: እንጂ ውስጥ ለውስጥ መጎነታተል፤ መተማማት የዚህ ዘመን የሚደገም መሆን የለበትም፡፡ ምንም እንኳ ጊዜው ተቀይሮ በጽህረ ገጽ፤በጋዜጦችና በመጽሔት ክርክርን መመላለስ አንደ ዘዴ መቁጠር ብንችልም፡፡ የራሱን የቻለ መነሻና መድረሻና ያለው መረጃ ሊኖረን ይገባል፡፡ ተቀራርቦ፣ ተነጋግሮ፣ ሰላምነወ አሳይቶ በደስታና በፍቅር  መለያየት የአገር ወግ ነው:: የአገር እድገት ነው፡፡ ከአያቶቻችን የወረስነውም ነው፡፡ ተመካክሮ ይቅር ተባብሎ መኖር መታደል ነው፡፡ ሰለዚህ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ከዲያቆን ዳንኤል ክብረት ጋር በተጠየቅ! ዝግጅት እንዲገኙና ሀሳባቸውን እንዲያካፍሉን በሁለቱም ወገን ሀሳብ ያለው ግለሰብ (ቡድንም ) ሀሳብን እንዲያካፍሉን እንዲያወያይና ከታሪክ እንድንማማር በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ አለምን የፈጠረ አምላክ ነው:: እንወያይ፣ እንመካከር፣ አንለወጥ!


  • ይህ ደብዳቤ ለሁለቱም ግለሰቦች የሚደርስ ይሆናል፡፡
  • ይህንን ዝግጅት ሊያዘጋጅ የሚችል አካል ይበረታታል፡፡





* ስለ በላ ልበልሃ /የጥንት እስጥ-አገባ ሙግት/ በሺበሺ ለማ የተጻፈቸውን ተጠየቅ! መጽሐፍ ቢያነቡ በእጅጉ ይማረካሉ፡፡ በዚህች ትንሽ መጽሐፍ ብዙ ይማራሉ፡፡
   (ተጠየቅ! ሺበሺ ለማ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት-1985)



የዚህን ጽሑፍ አዘጋጅ በtes_bel@yahoo.com
Tesfabelaynehh.blogspot.com ማግኝት ይችላሉ፡፡












Mar 12, 2013

ዲ.ዳንኤል ክብረት ከ‹‹ላይፍ›› መጽሔት ጋር አስደንጋጭ ቃለ-ምልልስ፡፡

‹‹የአከሱምንና የአቡነ ጴጥሮስን አይነት ሞራል ማጣታችን የታሪካችን ቁንጽል አካል ነው፡፡››
 ዲ.ዳንኤል ክብረት ከ‹‹ላይፍ›› መጽሔት ጋር አስደንጋጭ ቃለ-ምልልስ፡፡
በተስፋ በላይነህ
መክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ መጽሐፍ ለንባብ ከበቃ ወዲህ ብዙዎችን አነጋግሯል፡፡ ፕሮፌሰሩ በርግጥ ለዘመናት ተደባብሶ የተያዘን ሃሳብ ይዘው መቅረባቸው ምሁርነታቸውን፤ የተሸሸገውን በማውጣት ህዝብ እንዲወያይበት ማድረጋቸው የሚያስመሰግናቸው ነገር ነው፡፡ የ5ና የ3ሺህ ዓመታት ባለታሪክ አገር፤ ከሜሶፖታሚያ ከባቢሎን ከሮም ስልጣኔ ጋር እኩል ትራመድና ትታይ የነበረች አገር እንዲህ በአለም ኋላ ቀርና በድህነት አዘቅት ውስጥ መታየቷ አይደለም ከ80 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ቀርቶ አለም እንኳ የሚስማማበት ሀቅ ነው፡፡ ይህች አገር 30ና የአርባ ዓመት ባለታሪክ አደለችም፡፡ እንዲህ ስላጣኔያቸው ጣራ ደርሶ የምናያቸው አገራት መፈጠራቸው ሳይታወቅ ይህች አገር ነበረች፡፡ የገንዘብ መገበያያ ምንነቱን ሳያውቁ ይህች አገር ትገበያይ ነበር፡፡ የካም ህዝብ ቅኝ ግዛት ሲሰቃይ ተደራጅታና በሰው ግዞት ውስጥ መኖርን እንደ ህልውና ቆጥራ የታገለች አገር ኢትዮጲያ መሆኗንም አለም ያውቃል፡፡ /የአሁኑ ትወልድ በደንብ እያወቀው ባይሆንም/ የባቢሎንና የሮም ስልጣኔ የት እንደደረሰ ማየት እንችላለን፡፡ የኢትዮጲያ ስልጣኔ የት ደረሰ? የሌሎች ስልጣኔዎች እንኳ ወደሌሎች አገራት በመሸጋገር  ከባለታሪኩ ሂደት ባሻገር ተላልፎ አሁንም እያየነው እንገኛለን፡፡ ይህች አገር ግን የነበራትን ስልጣኔ አይደለም ለሌሎች አገራ ልታሸጋግር ለራሷ ህዝቦች እንኳ አላስተላለፈችም፡፡ ኢትዮጲያዊነት የትም ላይጠፋ ይችላል፡፡ ታሪክ አይፋቅምና፡፡ ለወደፊት ግን የዚህችን አገር ታሪክ በሚገባ ፈትሾ አሁን የት ደረስ? ምን ላይ ይገኛል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በታሪክ ውስጥ የተከሰቱትንን ማንኛውንም አሻራ በማጥናት የዛሬንና ለወደፊት ማስተላለፍ ታላቅነት ነው፡፡ እንግዲህ ይህቺን የታሪክ ባለሃብት፤ የስልጣኔ መነሻ  አገር አስከ አሁን የመጣችበትን ሂደት መርምሮ መሻሻል እና እድገት ካለ አጠናክሮ መቆየት ካለበለዚያም እየደበዘዘ የሚመጣ ከሆነ፤ ይባስ ብሎ ቁልቁል የሚወርድ ከሆነ መክሸፉ ግልጽ ነው፡፡ ታሪክ ከሸፈ የሚባለው ጠቅላላ ነገ የሚመጣውን ያጠቃልላል ማለት አይደለም፡፡ በፕሮፌሰሩም መጽሐፍ ይህንን አይጠቅስም፡፡ የትናንትናውን ታሪክ በመመልከት፤ እስከ አሁኑ ሰዓት ያለውን ፍጻሜ በማመዛዘን የትናንቱ ከዛሬው ሲነጻጸር ምን ላይ ደረሰ? ተሻሻለ ወይስ እንደ ግመል ሽንት ወደ ኋላ? ይህ ነው ትልቁ ጥያቄ!
 እስካሁን ከዳንኤል ክብረት ያየሁት ግን በመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ ሳይሆን መክሸፍ በሚለው ቃል ብቻ ነው፡፡ ቃልን መሰነጣጠቅ እና እዛው ለዛው በመሽከርከር ለውጥ ማምጣት አይቻልም፡፡ በአንድ ወቅት በዳንኤል ክብረት ጡመራ ላይ ያነበብኩት ነገር ትዝ አለኝ፡፡ ቀኑንና ርዕሱን ማስታወስ ባይቻለኝም የፍትሃ ነገስት ባለቤት የሆነችው አገራችን ከተለያዩ አገራት በተውጣጡ ህግጋት መደገፏን ያዘነበት ጽሁፍ ሁልጊዜም ከአዕምሮዬ አይጠፋም፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መለስ በፓርላማ የተናገሩትን በመጥቀስ አገራችን ህግና ደንብ ፍለጋ ከሌሎች አገራት መሄዷ  አሳዝኖት ነበር፡፡ ታዲያ ይህንና መሰል ሃብቶችን ይዘን መጠቀም አለመቻላችን አያሳዝንም? አዋቂ ግን የሚያደርገው ዝም ብሎ ወሬ መጠረቅ ሳይሆን ለተፈጠረው ችግር መፍትሄና ምሁራዊ ትንተና በማቅረብ ህዝብን ማወያየት፤ ችግሩን በማወቅ ምላሽ መፈለግ፡፡ ፍትሃ ነገስት ለምን ጥቅም ላይ አልዋለም? ያኔ የህጎች ሁሉ በለይ እንዳልተባለ አሁን ለምን ሊገለጥ አልተቻለም፡፡ ቀጣይነቱ ለምን አልዘለቀም? ይህ ክሽፈት ነው፡፡ ፍትሃ ነገስት ለምን ከሸፈ? ለምንስ ጥቅም ላይ መዋል አልቻለም? ብሎ በመጠየቅ የነገ ህልውናውን ለማስረገጥ መጠየቅና ምሁራዊ ትንታኔ ማቅረብ ግን ይቻላል፡፡ ፍትሃ ነገስት ለምን ከሸፈ? ማለት ግን የነገውን የፍትሃ ነገስት ጥቅም ላይ ማዋል አያከሽፈውም፡፡ እንደውም እንዲሳካና ነገ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚረዳው ጅማሬ እንጂ፡፡ ስለዚህ ታሪክ ከሸፈ ስንል አጠቃላይ የነገን ታሪክ መዳረሻን አያጠቃልልም፡፡ እስከ አሁኑ ሰዓት ያለውን ሂደትና ተጨባጭ ህልውና ግን ሊያመሳክርልን ይችላል፡፡ የኋላን በመፈተሸ፤ የት ደረሰ ብሎ ሁነቱን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡ ያለበትን ሁኔታም በግልጽ በማየት በመፈተሸ የነገን ጉዞ መተንበይ ይቻላል፡፡ ይህን ሁሉ ሃሳብ የተረዳሁት ከመክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ መጽሃፍ ውስጥ እንጂ መክሸፍ ከሚለው ቃል አይደለም፡፡ የኢትዮጲያን ታሪክም ስንመለከት እስከ አሁን የመጣንበትንና ያለንበትን በማጤን ከትናንትናው ጋር በማመዛዘን ትናንት አለም የሚያደንቀውን የእጅ ስራ ጥበብ ሰርተን ዛሬ ለሌላ አገር ስልጣኔ መሰጠቱ ከክሽፈት ሌላ ምን ስያሜ ያሰጠዋል? በዚሁ ክ/ዘመን እንኳ ኢትዮጲያዊነት ከየት ወዴት እንደተጓዘ መመልከት ይቻላል፡፡ በመጨረሻው የንጉስ ዘመን እንኳ ህንዶች የአሜሪካን ዜግነት ለማግኘት አማርኛ ሲማሩ፤ ኢትዮጲያኖች ምንም አይነት ገደብ ሳይኖርባቸው እንደ ህንዶች የተወሰነ ኮታ ሳይኖርባቸው ተፈቅዶላቸው መመላለስ እንደቻሉ ታሪክ መዝግቦታል፡፡ አሁን አይደለም እና መደበኛው ዜጋ ጳጳሳት የአሜሪካን ዜግነት እየያዙ ነው ተብለን በምንሰማበት ሰዓት ይህ የኢትዮጲያዊነት ስሜት እንዴት ተቀየረ? ነው ወይስ የድሮዎቹ ልክ አልነበሩም? እንደዛ አገርን መውደዳቸው፤ እንደዛ ለአገር መስዋዕትነት መክፈላቸው ልክ አልነበርም? አሁን ስንት ምሁራን ናቸው እየፈለሱ የሚገኙት? ለጊዜያዊ ስራ እንኳ ተልከው ጥገኝነት በመጠየቅና ስርዓትን ከመቃወም በግዞት መኖርን የሚመርጡ ሰዎች በየጊዜው እንደ አሸን እየፈሉ በምንሰማበት ሰዓት ካለፈው ሁኔታ ጋር ስናወዳድረው ከክሽፈት በላይ ምን ይገልጸዋል፡፡ ምክንቱን በማቅረብ መፍትሄ መውሰድ ግን የነገውን ሁኔታ አያከሽፈውም፡፡ የበለጠ እንድንጠነቀቅና እንድናስብበት ያደርገናል እንጂ! ብዙ ምክንያቶች ማቅረብ በተቻለ፡፡ ነገር መደጋገም ያሰለቻል እንጂ፡፡
  እጅጉን የገረመኝ ነገርም ይህ ነው፡፡ አንድ ስንት መጽሐፍ አነባለሁ ከሚለን ሰው ጋር ይህ ሃሳብ እንዲህ ማጨቃጨቁና አንድን መጽሐፍ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ ከሚል ሰው ይህን አይነት ምላሽ ማግኘቱ ያሳስባል፡፡ ያስቆጫል፡፡ ነገስ ማን ነው የሚገዛን ወደሚል ሃሳብም ይወስድና ያስጨንቃል፡፡ በ‹‹ላይፍ›› በሚባል በመጤ ቋንቋ በተሰየመ ‹‹መጽሔት›› ስር የዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ቃለ-ምልልስ ሳነብ እስኪ ምን ብሎ ደግሞ ተናገረ ለማለት ተዋስኩት፡፡ በነገራችን ላይ እነ ‹‹አዕምሮ›› ‹‹ጦቢያ›› ‹‹ሙዳይ›› በተነበቡበት አገር በውጭ ቃል ስያሜ መጠቀማቸው አያስገርማችሁም፡፡ ይህች አገር የስንት ቋንቋ ባለቤት ሆና ሌላ ባህርን የተሻገረ ቃል መፈለግ ከክሽፈት ሌላ ምን ሊባል ይችላል?  መቃጠል ነው!
 በዚችሁ ‹‹ መጽሔት›› ቅጽ 7 ቁጥር 102 መጋቢት 2005 እትም ስር ከገጽ 3 ጀምሮ እስከ ገጽ 5 ድረስ ከዲያቆኑ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በአንዳንድ ቃላት የትየባ ግድፈት እያገጣጠሙ ያነባሉ፡፡ በተለይ ወደ መክሸፍ ታሪክ በሚገቡበት ጊዜ ደጋግመው ሊያነቡት ይችሉ ይሆናል፡፡ እኔ በበኩሌ እየተቃጠልኩ ያነነብኩት ቃለ-ምልልስ ነበር፡፡
  ቃለ-ምልልሱ የሚጀመረው ስለ ስድስተኛው ጳጰስ ምርጫ ሂደትና በተያያዙ ጉዳዮች ነው፡፡ በዚሁ ጉዳይ ስር ያለኝ እውቀት ላይ ላይ በመሆኑ አልቀባጥርም፡፡ አንድ ሰው ስልሁሉ ነገር ሲቀባጥር ችግር ያመጣል፡፡ ሁላችንም በሁሉም ነገር የተካንን አይደለንም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ግን ብናተኩርና ብንካን ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ብዙዎችንም መለወጥና ግልጽ የሆነ መረጃና እውቀት መስጠት ያስችለናል፡፡ እኔም አንብቤ ወደ ገባኝና አስተያዬቴን መሰንዘር ወደምችልበት ሃሳብ ላምራ፡፡
  በቃለ-ምልልሱም ከቤተክርስትያን ወጣ እንበል በማለት በቅርቡ  በሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጅነት በቀረበው የመጽሐፍ ውይይት የሚለው ጥያቄ እናመራለን፡፡ በስፍራው ለምን አልተገኘህም ተብሎ የተጠየቀው ዲያቆን ይህንን ነገር ካነሳኸው እናውራ በማለት ይቀጥላል፡፡ ዲያቆኑ የሚለው በአስፈላጊው ሰዓት አልሰማሁም መልዕክቱ የደረሰኝ በሶስተኛ ሰው ነው ነበር ምላሹ፡፡ በመጀመሪያ ግን ከብርሃኑ ደቦጭ እንደሰማ ይነግረንና ከዛም ከአሜሪካ በተደወለ ስልክ ማለትም አርብ ዕለት ስለዝግጅቱ ሰማሁ ይለናል፡፡ ለማረጋገጥም የፌስቡክን መልዕክት እመለከተዋለሁ ይላል፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው በሚገባ ሳይነገረው ጽሁፍ ታቀርባለህ ከተባለ ችግር የለውም ማለት አንችልም፡፡ ችግር አለው፡፡ ነገር ግን በዝግጅቱ ቀርቦ ጽሑፍ ማቅረብ ባይቻል እንኳ ዝግጅቱ መኖሩን ከታወቀ ተገኝቶ መወያየት፤ ለህዝብ በግልጽ እውነትንና ሃሳብን ማስረዳት ከአንድ ኢትዮጲያዊ የሚጠበቅ ሃላፊነት ሊሆን ይችላል፡፡ ግዴታ ነው ብለን ግለሰቡን ማስገደድ ባንችልም በአሁኑ ሰዓት አሳሳቢ ለሆነ ጉዳይ፤ በተለይም ሃሳብ የሰጠን ሰው ከመመልከትም አልፎ ይዞት ለተነሳው ሃሳብ የጠራ መረጃና አስተያየት  መስጠት የሚያስችል መድረክ መሆኑን አንዘንጋ፡፡ እዚህ ላይ የግል ውርደት፤ ቂም፤ጥላቻ አይደለም የሚቀድመው ኢትዮጲያ ነች ቀዳሚዋ፡፡ ወደ ጦርነት እንኳ ተገድደን የሄድንበት ጊዜ እኮ ነበር፡፡ ይህ ደግም ከጦርነት ሺህ እጥፍ የሚበልጥ አጋጣሚ ትልቅ አገራዊ ጥቅም የሚያሰጥ መድረክ ነበር፡፡ በሃሳብ ለመወያት፤ እውነትንና እውቀትን ለማፋጨት የቀረበን ታሪካው አጋጣሚ መኖሩን እያወቅን አልተጋበዝኩም፤ ህጋዊ ማህተም ያለው ደብዳቤ አልደረሰኝም ብሎ ማመካኘት፡፡ በበኩሌ የተቃጠልኩበት ወሬ ነበር! በግድ መገኘት አለብህ እያልኩ አይደለም ዲያቆን- እያልኩ ያለሁት ስንትና ስንታ መነጋገሪያ የሆነ ሃሳብ ቀርቦ እስቀድመህም ያገባኛል ብለህ ሃሳብ መስጠቱ፤ ለፈጠንክበት ርዕስ ውይይቱ ምሁራዊ ሆኖ በግልጽ መቅረቡን አመካኝቶ መቅረት ለፍርድ የማይመች ውሳኔ ነበር፡፡ ከመጀመሪያው ሲጀመርስ በጽሁፍህ ላይ ሃሳብ ለመሰንዘር ማን ጋበዘህ? ኢትዮጲያዊነት አልነበረም? ይመለከተኛል ብለህ አልነበረም? ነው ወይስ ይጻፉልን የሚል በህጋዊ ማህተም የተላከልህ ደብዳቤ ደርሶሃል? ከአንድ አንባቢ ነኝ ባይ ኢትዮጲያዊና ከአንድ መንፈሳዊ ነኝ ባይ አማኝ የማልጠብቀው ገጠመኝ ነበር ለኔ፡፡ በወቅቱም በጣም የማከብረው የታሪክ ተመራማሪ ብራሃኑ ደቦጭ እንኳ አልተጋበዝኩም! ለምንስ ሰማያዊ ፓርቲ አዘጋጀው በማለት የሰነዘረከው ቡራ ከረዮ እጅጉን አስገርሞኛል፡፡ይህንን የመሰለ ዝግጅት ኢህአዴግ ያቀርበዋል ብለን እንጠብቅ ነበር? ለምንስ አንድ ያልታወቀ ድርጅት ወይንም መንግሰት ወይንም ግለሰብ አያዘጋጀውም? ዋናው ጉዳያችን ከቀረበልን ርዕስ ላይ ነው እንጂ ሌላ ጭቅጭቅ ወስጥ ምን አስገባን? በጣም ገርሞኝ ነበር በወቅቱ፡፡ ይህችን አገር የሚመራት እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ነው? ክሽፈት! ለነገሩ በሰዓቱ አርቲስት ደበበ እሸቱ አሳማኝ መልስ ሰጥቶናል፡፡ የአፍሪካን ኳስ በደሌ ቢራ ለምን አስተላለፈው ተብሎ ይጮሃል እንዴ? እኔ ከቢራው ምን አለኝ? ከኳሱ እንጂ በማለት መልሶልናል፡፡ እግዜር ይስጠውና!
 ይቀጥላል ሁለተኛው ጥያቄ፡- ‹‹በመጽሐፉ ዙሪያ ለሰጠኸው ሃሳብ ምላሽ አለመስጠትህን ጠጠር ከወረወሩ በኋላ ዝም ማለትህን ከመጀመሪያው የሰጠኸው አስተያዬት ትክክል አለመሆኑን የሚያመላክት አይደለም?›› ለተባለው ጥያቄም ምላሹ በይበልጥ ያቃጠለኝና አንድ ጣሳ ውሃ ያስጠጣኝ መልስ ነበር፡፡ በስንቱ ልቃጠል አለች…
  ‹‹እንኳን አነስተኛ የገጽ ብዛት ያለውን መጽሐፍ ይቅርና ብዙ ሲ/ሺ ገጾች ያላቸውን መጻሕፍት አነባለሁ፡፡›› በማለት የመለሰው በእጅጉ ገርሞኛል፡፡ ከመገረምም አልፎ አበሳጭቶኛል፡፡ ለዚህች አገር ብዙህ ሺ ገጽ መጽሐፍ ማንበብ ምን ይጠቅማታል፡፡ ያነበቡትን በትክከለኛ መልኩ ተረድቶ ህዝብን ካልለወጠ! ብዙ ሺ ገጽ መጽሃፍስ ማንበብ እውቀት ሆኖ ነው? በአንድ ስንኝ እንኳ ስንት ሃሳብ እያስተላለፉ፤ በ30 ሴኮንድ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ስንት ሰው መለወጥ የሚያስችል ማስታወቂያ እየሰተሰራ ባለንበት ዘመን ብዙ ሺ ገጽ ያለው መጽሐፍ አነባለሁ! ብሎ ማውራት ለኔ እንደ መልስ የሚቀርብ አልነበረም!
  የፕሮፌሰሩንም መጽሐፍ ባልከን መሰረት ደጋግመህ አንብበኸዋል እንበል፡፡ ደጋግሞ ማንበብስ አውቀት ነው? ይገርማችኋል በጣም የምወዳት የወንድሜ ልጅ አለች እድሜዋ 8 ነው ስሟን ያወጣሁላት እኔው ነኝ ብሌን ታባላለች፡፡ከቄስ ትምህረት ቤት የተማረችውንና የሸመደደችውን የግዕዝ ንባብ ሁልጊዜ ትልልኛለች፡፡ ትርጉሙን ግን አንዱንም እንኳ አ.ታ.ው.ቀ.ው.ም! ደጋግሞ ማንበብ ዋናውን ጭብጥ ካልያሳዘን ለምን እንደሆነ ተጎልቶ የሚወራው በኔ በኩል አልገባኝም፡፡ እባካችሁ የገባችሁ ካላችሁ አስረዱኝ! በተደጋጋሚም ዲያቆኑ የሚያነሳው ክሽፈት በሚለው አርዕስቱ ብቻ ነው፡፡ ለመጽሐፉም ክሽፈት የሚለው ርዕስ መሰጠቱን ከላይ ጠቅሰነዋል፡፡ የነገን ሂደት የሚያጠቃልል ሳይሆን እስካለንበት ጊዜ ያለውን የሚያመላክት ነው፡፡ አንድ ነገር ሲቋረጥ ከሸፈ ልንል እንችላልን ነገ ግን ከተስተካከላና በደረሰበት የክሽፈት መጠን ልክ ማሳካት የምንችልበት ሆኖ ቢነበብ እመርጣለሁ፡፡ ይህንንም ርዕሱን ከማንበብ ሳይሆን መጽሐፉን ደጋግሞ ማንበብም ሳይሆን አንዴ አንብቦ መረዳት የምንችልው የመጽሐፉ ጭብጥ ሲገባን ነው፡፡
  ሌላው ተብሎ የቀረበውም ከ41 ዓመታት በኋላ ጸሐፍቶች ሲሞቱና አልጋ ላይ ሲወጡ ጠብቀው መጻፉን እንደ ትልቅ ህጸጽ መታየቱ ደንቆኛል፡፡ መጽሐፉ ለህትመት እንዲበቃ የታሰበው በደርግ መንግስት እንደነበር ሰምቻለሁ አልከን፡፡ እሳቸውም ተናግረውታል፡፡ ይህንን እንደ ምክንያት እንውሰድና በዚህ ወቅትም መቆየቱ ምናልባት ከሽፏል የተባለው የኢትዮጰያ ታሪክ ይሳካ ይሆናል ተብሎም የተጠበቀ አጋጣሚ ሊሆን ይችል ይሆናል፡፡ እሳቸው አስበው ባያደርጉትም ጠቢበኛው ለሁሉም ጊዜ አለው ብሎ መናገሩን እናውቃልን፡፡ ያኔ ለመጻፍ ተሞክሮ በሳንሱር ምክንያት አለመታተሙን እንደ ችግር ብንወስደው እንኳ ፕሮፌሰሩ በኢህአዴግ አገዛዝ ስር ሆነው እኔ የማውቀው 4 መጽሐፍትን ጽፈውልናል፡፡ እነዚህም መጽሓፍት የኢትዮጲያን ታሪክ በከፍተኛ መልኩ ሊመሩ የሚችሉ ሃሳቦችን ይዘዋል፡፡ በተለይ በ80ዎቹ የተጻፈችን ኢትዮጲያ ከየት ወዴት? የምትወለው ትንሽ መጽሐፍ በሚገባ ብትነበብ ስንት ለውጥ ባየን! አልተነበበችም እንጂ! ከዚህችም መጽሐፍ በኋላ የክደት ቁልቁለት፤ መንግስት ፖለቲካና አገዛዝ እንዲሁም አደጋ ያንዣበበበት የአፍሪካ ቀንድ ምሁራዊና ለዚህች አገር ጉዞ አመላካች መጽሐፍት ነበሩ፡፡ በተገቢው አልተነበቡም፤ ቢነበቡም አልተገበርናቸውም እንጂ! እሳቸውም እነዚህን ሞከሩ የተሳካ ነገር አላዩም፤ ለውጥ አልመጣም ስለዚህ አሁንም በቃኝ ብለው አልተቀመጡም ታሪክ አያቆምምና፡፡ መክሸፍ እንደ ኢትዮጲያ ታሪክ በሚል ርዕስ አጠቃለው ማውጣታቸው እንደውም ዘገየ ሳይሆን ትክክለኛውን ጊዜ ጠብቆ ወጣ የሚባልለት አገጣሚ ነው፡፡ ሳይጽፉት የሰው ልጅ ወደ ማይቀርበት ጸጥታ ቢሄዱስ? ይህ ነበር ሊታሰብ የሚገባው፡፡ የጊዜ ሰጭና ነሺን አምላክ የምናመሰግንበት ገጠመኝ ነው እንጂ!
ሌላኛው ቅጥል እርር ብግን ያስደረገኝ መልስ ደግሞ ይኸውላችሁ፡፡‹‹መስፍን? በቁጣ ስሜት ለእኔ መልስ ማለት ለጻፉት ጽሑፍ ምላሽ ያልሰጠሁት አንደኛ ለእርሳቸው አክብሮት ስላለኝ ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም በዚህች አገር ላይ…›› ምናምን ማናምን ምናምን….ጉድና ጅራት ወደ ኋላ ነው አለ ያገሬ ሰው! ጎበዝ ሁለት ሰዎች እኮ በሃሳብ ደረጃ ሲወያዩና ሲመላለሱ ሁልጊዜም በሃሳባቸው ላይ መመላለስ እንጂ ከግለሰብ አክብሮትና ማንነት ላይ ምን አገኛኘው? እንደ አይሁድ አዋቂ እንደ ፈሪሳዊያንና ሰዱቃዊያን ህግና መጽሐፍትን ተርጓሚና የተከበረ ማን ነበር? ነገር ግን እውነተኛው ክርስቶስ ‹‹መከበር አለባቸውና›› ብሎ ዝም አላለም፡፡ እስኪገርፉት፤እስኪተፉበት፤ እስኪሳለቁበት፤ እስኪሰቅሉትና እስኪሞት ድረስ እውነትን ሰበከ! ተሰቀለ ነገር ግን እውነት ይኸው 2ሺ ዘመናትን አስቆጠረች፡፡ ክርስቶስ እውነትን ባይናገር ኖሮ እውነትን ባይሰብክ ኖር ዝም ቢል ኖሮ እኛ እንዲህ አንቆምም ነበር፡፡ ክርስትናም የሚያስተምረን የድቁናም ሆነ የሌላ ማዕረግ የምታበቃን ክርስቶስን መሪና ተምሳሌት አድርጋ ነው፡፡ኢትዮጲያም ለዘመናት ያጣችው ይህንን ነው፡፡ እሱ ንጉስ ነው! እሱ የተመረጠ ዘር ነው! እሱ የተከበረ ነው በማለት ስንት እውነት ተቀብራ ቀረች? ስንት ሀቅ ለተውልድ ሳትተላለፍ ቀረች? አሁንም ያውም ከዚህ ትውልድ ‹‹ስለማከብራቸው ዝም አልኩ›› ማለት ሌላ 3ሺ ዘመን እንድንመለስ የሚያደርግ ምላሽ በመሆኑ ሊታረም ይገባል፡፡ ነው ወይስ ምላሽህ ስድብ ብቻ ነበር? ከመሳደብ ዝም ይሻላል ከሆነ ሌላ ነገር ነው፡፡ ነገር ግን እውነትና እውቀት አለን ብለን ዝም ማለት ትልቅ ክሽፈት ይመስለኛል! በበኩሌ ፕሮፌሰሩ ሁለተኛ ምላሽን በመዝሙር 115 አያይዘው እስኪጽፉ ምላሽህን ጠብቄ ስለነበርና ያልመለስክበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል ብዬ የጠበኩትን ያክል ያገኘሁት መልስ በጣሙን አሳዝኖኛል፡፡ መልስ አትስጥ በማለት ምክራቸውን ለግሰውኛል ያልከውንም ስቄበታለሁ! ሲጀመር ለመጻፍ ስትነሳሳ አትጻፍ አለማለታቸውም ደንቆኛል፡፡ ለአገር እድገት ለታሪክ መሳካት ዝም ብለን ውስጥ ለውስጥ ከመገፋፋት እውነቱ ይውጣ! እንወያበት! እውነት ደግሞ ሁልጊዜም አንድ ናት፡፡ ይህች አገር ኋላ ካስቀሯት አንደኛው ምክንያትም ይህ ነው፡፡ ደፋፍኖ አለባብሶ ማለፍ፡፡ ረመጡ ይጎዳናል!
 ‹‹ስለ ቤተ መንግስቱ›› ወሬም ሲነሳ ይህንን ታሪክ የሚያውቁት 6 ሰዎች ብቻ ናቸው የተባለው መልስም ከላኞይቹ መልሶች ጋር አይለይም፡፡ ስድስትም ሰው ይወቀው ስድሳም ይወቀው አንድም ይወቀው እ.ው.ነ.ቱ ይውጣልን! ዋናው ቁም ነገሩ እውነትን ማጋለጥና ለህዝብ በማቅረብ እንማርበት፤ አንወያይበት እንለወጥበት! ይህ ነው ትልቅ እድገት የሚያመጣው፡፡ የተፈጸመው ነገር በግለሰብ ደረጃ የሚቀርብ ከሆነ ብዙም ላይጠቅም ይችላል፡፡ በታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ የሚያመጣና በተለይም ከመጽሐፉ ጋር የሚገናኝ ከሆነ የእውነቱ ሰዓት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ፕሮፌሰሩም በጤናና በህይወት እያሉ ይነገረን፡፡ ካለበለዚያ በሚስጥርና በድፍንፍን መጥቀሱ ተንኮል ሊያደርገው ይችላል፡፡ እውነት አትደበቅም!
  ‹‹የአከሱምንና የአቡነ ጴጥሮስን አይነት ሞራል ማጣታችን የታሪካችን ቁንጽል አካል ነው፡፡ ይህንን በማንሳት ብቻ ታሪካችንን ከሽፏል ማለት አንችልም›› የሚለው መልስ ወደ መጨረሻ የሚመጣው መልስ ነው፡፡ ስሜቴን በመቆጣጥር ለዲያቆኑ ጸሎቴን አቀረብኩ! ምን ነካው ዲያቆን በማለት፡፡
ይታያችሁ ለአንድ አገር እድገት መሰረታዊ ከሚባሉት ነገሮች ውስጥ እጅ ስራን ወይንም ጥበብን ስልጣኔን የሚያመላክቱ እሴቶች ከህሊና ወይንም እውነተኛነት ስሜት ጋር ተዋህደው ሊፈጠር የሚችለውን ትውልድ ማሰብ ከዛም አልፎ ጥቅሙን መገንዘብ አይደለም ከአንድ አንባቢ ጸሐፊና ዲያቆን ከተባለ ሰው ይህንን አይነት መልስ መስማቴ ወደ መጨረሻው ውሳኔዬ ወደስዶኛል፡፡ አንድ ሀገር በጥበብ ስልጣኔን ይዛ፤ እውነተና የጽድቅ መስዋዕትነትን ብታዋህድበት የት በደረሰች! በአሁኑ ሰዓት አገራችን ያጣቸው ደግሞ አንዱን ብቻ ሳይሆን ሁለቱን ነው! ይህ ደግሞ የክሽፈቶች ታላቅ ክሽፈት! የጥበብ ስልጣኔ የሌለው ትውልድ ከዛም አልፎ የጴጥሮሳዊነት ሞራል የሌለው ህዝብ ሲጨመርበት -ህዝብ ከአራዊትነት አልፎ ድንጋይ የሚሆንበት ክሽፈት አይደለምን?
 ፕሮፌሰሩም አንድ የተሳካ ታሪክ ፈልጌ ማግኘት አላችልኩም ላሉት ሃሳብም ዲያቆኑ ‹‹አልፈለጉም›› ብሎ ነበር  የመለሰው፡፡ በነገራችን ላይ በብሔራዊ ቲያትር የመጽሐፉ ውይይት ላይ ይህንን ሃሳብ እርሳቸው መልሰዋል፡፡ ሲመልሱም ምናልባት ‹‹የኢትዮጲያ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ወደ ጦርነት በጋራ ሆ! ብሎ መዝመትን እሳካሁን አይቻለሁ፡፡ ይህ ያልከሸፈ ነገር ነው ብለዋል፡፡ ሌላም ፈልገዋል በግላቸው ማግኘት አልቻሉም፡፡ ዲያቆንም እገምታለሁ ብሎ አንድ እንኳ የተሳካውን የታሪክ አካል ሊገልጽልን አልተቻለውም! የተሳኩ ታሪኮች አሉን ብለን የምናስብ ከሆነ በምሳሌ ተንትኖ ማስቀመጥ፡፡ ይህ ነው ምሁራዊ ውይይት፡፡ ሌላው ወሬ ነው!
 ‹‹የኢትዮያን ህዝብ ተረድቼዋለሁ የማትለው ልዩ ሕዝብ ነው፡፡ አንድን ጉዳይ በቃ ጨርሷል ስትለው ብድግ የሚል፤ ተኝቷል ስትለው የሚነሳ ከ97 በፊት የነበረውን 97 ላይ ለምንድን ነው ብድግ ያለው ለሚለው ያንን እንኳ ተንትኖ የሚነግርህ የለም፡፡›› በማለት ቃለ ምልልሱ ያበቃል፡፡ ጋዜጠኛው በራሱ ይህንን ሃሳብ አሜን ብሎ መቀበሉ ገረመኝ፡፡ እዪት እንግዲህ ተናጋሪውን፤ እዩት ጠያቂውን፡፡ ታዲያ ይህች አገር በነዚህ ነው እንዴ የምትመራው? አዘንኩ! አፍክን ስትከፍት ጭንቅላትክን አየውህ የሚል አባባል አስታወስኩ፡፡ ጌታ ሆይ ከዚህ ዘመን አውጣን! እውነትህን ግለጥ! ‹‹ማውራት ጥበብ የሆነባት አገር›› የሚል የኤፍሬም ስዩም ግጥም ትዝ አለኝ፡፡ ለካ እኔም እያወራሁ ነው… አምላክ ሆይ እውነትን እንድናወራ እንድንመሰክር እርዳን፡፡የኢትዮጲያ ህዝብ ያጣችው እውነትን ይዞ የሚመራት መሪ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ አምላኩን ይፈራል፡፡ እርስ በርሱ ይዋደዳል ግን አንድ አድርጎ በልዩነቱ የሚመራው እውነተኛ መሪ ይፈልጋል፡፡ ግን በማንም ሲመራና ሲዘበትበት ሲወራበት እያየን ነው፡፡ አምላክ ሆይ እውነተኛውን መሪ ስጠን! ብናወራው አያልቅም!
ቸሩ ቸር ያቆየን!
 


ፍቅር ከዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር_FIKIR EZIH BOTA FEGEG BILO NEBER-Ephrem Seyoum


ፍቅር ከዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር፡፡
/የአለማችን ረዥሙ የግጥም መድበል/
በተስፋ በላይነህ
  የጥበብን ሃይል የምናውቀው የተደበቀን ምስጢር ወደ ገሃድ ማውጣቱ፤ የተሰወረን አዚም፤ የጠፋን መንገድ በማመላከት መስመር ማስያዝ መቻሉ፤ በጦር በሰይፍ እንኳ የቀረበን ፍርድ ለእውነትና ለእውቀት ወግኖ መገኘቱ ከዛም ለትውልድ ቅርስ ሆኖ መዘከሩ ነው፡፡
ምንም እንኳ ጥቂት ሃጥአን ብዙዎችን ነፍሳት የማጥፋት ሃይል ቢኖራቸውም፤ ጥቂት ወይንም አንድ እውነት አለምን እንደሚገዛም አይተናል፡፡ በዚህ እውነት ስር የሚወጡም በርካታ የጥበብ ስራዎች ብዙዎችን የመለወጥ ሃይል ሲኖራቸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ብዙ ነገሮች ጠፍተውብን፤ መድረሻው ርቆብን፤ ማረፊያው በጠጠር ተደግፎ በአሜኬላ ታጥሮ፤ ፍጻሜው ታክቶን የምንንከራተት ስንቶቻችን ነን? ‹‹አፋልጉን›› በሚል ጩኸት የምናሰማ ብዙዎቻችን መሆናችንን ቤት ይቁጠረው፡፡ በዚህ የጩኸት ዓለም ውስጥ እውነትንና የጠራ እውቀትን ማግኘት ከባድ በሆነበት ዘመን እውነትና እውቀት የለችም ብሎ እጅን አጣጥፎ መቀመጥ ከሰውነት ተርታ የሚያስወጣን በመሆኑ መቼም ቢሆን ለእውነት መታገል ይኖርብናል፡፡ ‹‹አፋልጉን!›› እያሉ የመጮኽ ትግል ::
      አሜሪካኖች ለየት ያለ የሙዚቃ አቀንቃኝ ብቅ ካለች /ካለ/ በአለማችን አስገራሚዋ/ው የሙዚቃ አቀንቃኝ ብለው መጮኽ ያዘወትራሉ፡፡ ሌላኛውን ዓለም ሳያዩ ፣ ሳይወዳደሩ በአለም አንደኛ! ማለት ይወዳሉ:: ይህም ትልቁ የንግድ ሴራቸው ነው::  እኔም በእነርሱ ንግድ አለም ሥርዓት አይደል ያደኩት::  አዎ!  በአለም ረዥሙ የግጥም ስንኝ በሚለው ጩኸት ርዕስ ስር የኤፍሬም ስዩምን  ‹‹ፍቅር እዚህ በተፈለገ ብሎ ነበር›› የሚለውን የግጥም መደበል በአለም አንደኛ ረዥሙ የግጥም ስንኝ ለማለት ተገደድኩ፡፡ እውነት ነው በአለም ረዥም ግጥም ስንኝ ማነው ቢባል ማንም ይወራረደኝ ፍቅር ኢዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር የሚለው ግጥም ነው ኤፍሬም እነርሱ ባይጽፉትም ፤ አነርሱ ባያነቡትም እኔ ግን  አንብቤ ፅፌዋለሁ ትችላልህ! ኤፍ፡፡
      ኤፍሬም ስዩም “ሶሊያናን” የግጥም ሲዲ በ 1998 ሲያቀርብልን ለግጥም የስነ ጥበብ ዘርፍ ከፍተኛ ትርጉምና ዋጋ ያስጠበት ዓመት ነበር፡፡ ተፈጥሮ በለገሰችው ስልቅልቅ  ጉሮሮ፤ ቅላፄ፣ ዐርምሞና ምሳጤ  መሰረት የተለያዩ ሃሳቦችን በያዙ ግጥሞች ወደ ትልቅ ባህር ወደ ሚወሰዱ ዜማዎች ታጂቦ አስከመኮመን፡፡ ግጥምን ልክ አንደ ሙዚቃ ስራ ወስደን በቤተሰብ መሃል እያዳመጥን የምንወያይበትን መድረክ ከፈተልን፡፡
      ግጥምን በድምፅ በማሰማት እነ ሎሬት ባለ ቅኔ ፀጋዬ ገ/ መድህን  ፣ እና  አበባው መላኩም ሞክረውልናል ታገልም ሊካተት ይችላል፡፡ ሌሎችም…
   መዚ ቃል ( የብርሃን ክንፎች) ለኤፍሬም ቀጣይ ስራው ነበር፡፡ በ 2004 ዓ/ም የለቀቀው ይኸው ስራ አሁንም ጥበብ የጋለ ብረቷን ለኩሳው በ 2005 ዓ/ም ‹‹ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር›› በሚል ርዕስ ለየት ባለ አቀራረብ በሚስብ ይዞታ በሰማያዊ መደብ ሁለት  ተበአትና እንስት የአዕዋፍ ፍጡራን በፍቅር ማዕድ ተቆላልፈው ተስለው በነጭ ቀለም ዳርቻ ስር ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር የሚለውን መድበል እንኳችሁ አለን ኤፍሬም::  የሸፉኑን  ሥዕል አልፈን አንድ ገጽ ስናልፍ በጥቁርና ነጭ ቀለም የተጣለ የገጣሚውን ከደረት በላይ ምስል  እናገኛለን፡፡  አንድ ፈላጊ የሚመስል አትኩሮ የሚያይህ ሰው ይመለከትሃል፡፡፡ በመጠኑም ቢኾን  እንደ ግጥም ለማንበብ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ይዘህ ልትቆይ ትችላለህ፡፡ ትገልጣለህ “ተበረከተ” ለሶልያና የሚል ጽሑፍ ታገኛለህ  በሶልያና ፍቅር እንደተነካ በግልጽ ማየት ችያለሁ::  ፍቅር ደግ ነገር ነው! ከዛም ስትገልጥ ማውጫው ላይ በግጾች አምድ ስር ሀ፣ሐ፣ሠ፣ኀ እና በሚሉ ፊደላት ለየት ያሉ ሃሳቦችን እናያለን፡፡ በብዛት የለመድነው በሮማን ቁጥር ሊኸን  ይችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት የገጽ ዉጥሮችን በግዕዝ ቁጥር ማየት አልተለመደም፡፡ ይስማዕክ ወርቁ የቀንድ አውጣ ኑሮ የግጥም መድበል ላይ ገጾች በግዕዝ ቁጥር መፃፋቸውን አድንቄ ነበር፡፡  አሁን ደግሞ በፊደል ማየቴ ደስ አለኝ፡፡ ነገር ግን ሌሎች የግጥሞች ገጾች የቀረቡት በህንድ/አረብኛ  ቁጥር  በ1 2 3 ተጽፈዋል፡፡ በግዕዝቁጥር ቢጻፉ ኖሮ የመድበሉን ውበት በጣም ሊያሳምሩት እንደሚችሉ አሰብኩ፡፡  
      ትገልጣለህ የግጥሞቹ ማውጫ  ያልቅና ባደ ገጽ ታያለህ፡፡ በጣም የስነ-ጽሁፍ አድናቂ  ፍልስፍናም ነካ የሚያደርገህ ኮኾነ ባደ ገፁን ልታነበው ትችል ይኾናል፡፡  ባደ መኾኑን ሳትገነዘብም ታልፍ ይኾናል ይሆናል፡፡
የምስጋናው እፍል ይከተላል፡፡ ቤተሰቦችንም ለማመስገን ያቀረበውን ምክንያት በጣም ወድጃዋለሁ፡፡‹‹የእናንተን ለእናንተ መናገር ራሴን በራሴ ከማክበር እኩል ስለሚኾን በልብ ከልብ ለልብ›› ይላል፡፡ ለገፀ ሀ ደግሞ  ከዛው ይህችን መድበል ሕይወት የዘራበትን ሰው ዘሚካኤልን ያመስግነዋል፡፡ እኔም በበኩሌ እጅጉን አመሰግኜዋለሁ፡፡ እንዲህ ሰው በጣፋበት ዘመን ስው ሲገኝ ያሰደንቃል፡፡ “ዘ” ብድራቱን የላይኛው ይከፍልህ፡፡ ከዛም ስንገልጥ በገጽ ሠ ላይ የምናገኘውን የዚህን መጽሐፍ ትልቁን ክፍል ነው::   ጠማረ አሚን የሚለውን እናገኛለን፡፡
 ‹‹ሁላችንም የግላችን የሆነ sound truck አለን ያ sound track ያለፈ ጊዜያችን የአሁን ማንነታችን ነው፡፡ እያለ ሕይወትን በሙዚቃ እያዋዛ እያመሳሰለ የህይወታችን መሰረት የሆኑትን አሁን ቅድም ዛሬ ትላንት አምና ካቻምናን ያስቃኘናል:: ያለፈው ሕይወታችን በአሁንና በነገ ማንነታችን ላይ ያለውን ተጽዕኖ ምላሽም ያስቃኘናል::    
      አራተኛው አንቀጽ ላይም …ትናንሽ የሸክላ ጭረቶች የሙዚቃውን ጣዕም ይረብሹታል… ከሙዚቃ  ሐዘንተኛ መንፈስ ይልቅ ባለዋቂ ጥፍሮች የተቧጨሩ የሸክላው ጀርባዎች…ዜማውን ያበላሹታል፡፡ አንድ ወዳጄ ውብ እኔነቱን ብዙ ምርጥ ዜማዎችን በማንነቱ ላይ እንደተሸከመ ራሱን በራሱ ለመስበር ሲሞክር ሞክሮም ተሰባብሮ  ስብርባሪው ተለቅምና ታሸጎ ወደ ዘላለም ፀጥታ ሲጓዝ ተመልክቼአለሁ፡፡ በዚህም ከታላላቆች መስበር የታናናሾች ጭረት እንዲጎዳ አስተውያለሁ፡፡ የምትለውን አንቀጽ ውበቷ ጎልቶ ታይቶኛል፡፡ ቀሪውን ጦማረ አሚን /እውነተኛ-የታመነ ደብዳቤ/ ሃሳብና ይዞታ እስከ ገጽ ተ ድረስ ያንብቡ፡፡ ብዙ ይማራሉ፤ ብዙ ያስባሉ፤ ብሉ ይጠይቃሉ ይመራመራሉ፡፡ምናልባት ፀጥታ የሌለበት  ስፍራ ወይንም ህሊናዎን ሰብሰብ አድርገው ካለነበቡት ምን ለማለት እንደፈተለገ ሊያገኙት ስለማይችሉ በትህትናና በትዕግስት ኢኒዱያነቡት እመክራለሁ፡፡
       ይቀጥላል በ ኀ ገጽ  ደግሞ ‹‹ዋዜማ›› በሚል ርዕስ ስር ከደመና ልትቀዳ ተራራውን ወጣች የሚል የመዝገቡ ተስማን አድባር ስዕል አስታወስኩት በማለት  ህልሙን ይነገራናል …ህልም…ከዛም የዮፍትሄን ስለት ጠቅሶልን ህልሙን ለመፍታት ሊተረጉምልን ይተርክልናል፡፡      
    ‹‹ቅደመ ታሪክ›› የሚል ግጥም ይጀምራል፡፡ ያንብቡት! የግጥሙም የመጨረሻ ስንኝ እንዲህ ትላለችበ ግርጌው ላይ በ29 -02 2004 ተጻፈ ይላል፡፡
   ‹‹ታዲያ በዚህ አገር የፍቅር ማደሪያው የትኛው ልብ ነው?›› ብሎ በመጠየቅ በገንዘብና በቪላ ተደልላ ለሄደችበት ሴት የተፃፈ በማስመሰል ረዥሙ የግጥም ወንዝ ይፈሳል፡፡
      ገጽ 1 ‹‹ዕለተ ቅዳሜ ፒያሳና ቦሌ››  በቃ ከዚህ ጀምሮ እስከ ገጽ 100 ድረስ አንድ የግጥም ሃሳብ ያነባሉ::  ለዚህ ነው በአለም ረዥሙ  የግጥም ስንኝ በማለት በአለም ድንቃድንቅ መዝገቦች ስፍራ የሸለምኩት፡፡ ከአንድ ታሪክ ከአንድ ቅዳሜ ተነስቶ አዲ አበባን የአዲስ አበባን ሰዎች ወጣቶች ሴቶች ልጆች ኢትዮጵያን የምናይባቸው ግጥሞች ቀርበዋል::  በተለይ ከመጀመሪያው ገጽ የቀረቡት ----የቤት ልጅ ( ፀጉሯን የምትሰራውን እፎይ ብላ ተቀምጣ ያረፈቸውን የፒያሳ ልጅ ከቦሌ ቀለማት ቆነጃጅት ጋር  ያነፃፀረበትን ወገን ስቄበትም ተደንቄበትም አልፌዋለሁ፡፡ 
ለአራት ሰባት ምግብ አዘው፤ በጋዜጣ ምናምን ነገር ያየዙትን ወጣቶች ‹‹ቀኑ ቅዳሜ ነው›› ያለበትን ምክንያት ወድጄዋለሁ፡፡
      በአንዳንዱ ገጽ የተለያዩ ግጥሞች የሚመስሉ ስንኞች በተለያየ ርዕስ ስር ቢቀርቡም  እርስ በርሳቸው የተያያዙና የተደጋገፉ አንዱን ካለነበብን የሌላኛው የማይገባን ግጥሞች ናቸው፡፡ ምናልባት እንደ ሌሎች የግጥም መድበሎች ከመሃል አንድ፤ ከዳር አንድ እያደረግን የምናነበው ከኾነ አይገባንም፡፡ በአብዛኛው ሁሉም ማለት ይቻላል በ 21 -04-2004 እስከ 29 -04 2004 ባሉት ቀናት ውስጥ የተጻፉ መኾናቸውን በግርጌ ማጣቀሻቸው ማየት ይቻላል፡፡ ኤፍሬም ስዩም  በዚህ የግጥም ስራው አንዲት የወደዳት ያፈቀራት አብሮ ትኖር የነበረችን ሴት  እያስተዋወቀ ለሌላ ባል የተሰጠችውን ፍቅረኛውን የበለጠ ሃብት ፈለጋ ወደ ሌላ ወንድ ጋር ሄዳ የምታሳልፈውን ሕይወት ከጓደኛዋ ከጎረቤት ከሰራተኛ እና እራሱም የሚያየውን እየጠቀሰ ይተርክልናል፡፡ ምናልባት ትግስተኛ አንባቢ ካልሆኑ በዚህ ዘመን ደግሞ ‹‹ምን ያለ ፍቅር ነው›› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ የዋዛ እንዳይመስላችሁ፡፡ በገጽ 87 ላይ በምናገኛት ‹‹ደባል ታቦት›› የግጥም ስንኝ ብዙ ልንማር ብዙ ልናውቅ ብዙ ልንለወጥበት የምንችልበትን ሃሳብ በአዲስ ቀን  01-03-2003 ወደ ኃላ በመመለስ ያቀርብልናል፡፡ አዲስ ቀን ነው፡፡ ምናልባት ግን 2003 ዓ/ም በስህተት የተገለጸ ሊሆን እንደሚችል ገመትኩ፡፡ ምክንያቱም በገጽ 87 የምናየው ‹‹መቼም›› የተሰኘችው ግጥም የተጻፈችው በ02-03-2004 በመሆኑ፡፡
  ከዚህ በገጽ 91 ስንበት በሚል ያቀረበው ግጥም የዚህ ሁሉ ታሪክ መገባደጃ በመሆን ቻዋ !! ይላታል፡፡ ‹‹ሁሉም ከንቱ ነበር›› የሚለው ቀጣይ ግጥም በገጽ 92  ይቀርብልናል፡፡ አራት ጊዜ አንብቤዋለሁ፡፡ ወድጄዋለሁ! የመጣሁበትን ጉዞ ሁሉ አሳረፈኝ፡፡ አስተማረኝ መክረኝ እንድጠይቅ አደረገኝ፡፡ ተባረክ ኤፍሬም!
 ለዚህ ዘመን ለዚህች አገር ለዚህ ትውልድ ለሽማግሌ ለነገስታት የተጻፈ ግጥም፡፡
ህልማችን መተኛት
ህልማችን መጠጣት
ተሰብስቦ ማውራት ማውራት ማውራት ማውራት-- ---
አዎን በዚህ ሀገር
ሁሉም ከንቱ ነበር፡፡
ሽማግሌው መውራት
ወጣቶቹ ማውራት
ነገስታቱ ማውራት
ማውራት ብቻ ጥበብ ሕይወት የሆነበት
እርስ ኢትዮጲያ ናት፡፡
ያንብቡት! ከዚያ በገጽ 97 ላይ ሐያሲ በሚል የግጥም ስንኝ የግጥሙ ፍሰት ይቋጫል፡፡ በ 30 02- 2004፡፡
     በገጽ 101 መውጫ ወዳሻችሁ በሚል ርዕስ የተጻፈን ደብዳቤ ከምጠብቀው በላይ በእያንዳንዱ መስመር እፈልጋት የነበረችውን የመድበሏን ዋና ገጸ-ባሕርይ ‹‹ምንም›› አጥብቂ እንድፈልግና ያቀረበበትን የአፋልጉኝ ርዳታ በምልክተ ያስቀመጠበትን ‹‹ዘይቤ›› ከሚገባው በላይ ለመረዳትና ልጁንም በማድነቅ ምነው ፅሑፍ ባለለቀ አስብሎኛል፡፡ እነዚህ 4 ገጾች የጸሐፊውን ልዩ ችሎታ ያሰዩ ሃሳቦች የተሰነቁበት ልዩ ክፍል ነው፡፡
  በዚህ ዘመን የምንፈልገው ጸሐፊ ከራሱና ከፈጣሪው ጋር ተጣልቶ እኛንም የሚያጣላን፤ ውዥንብር ፍልስፍና ሳይኾን በብዙ መንገዶች በስነ-ጥበባዊ ወዝ እያዋዛ ራሳችንን አገራችንን ፈጠሪያችንን ፈልገን ለለውጥው የምንነሳበት ሀሳብ የሚጠቁምን ነው፡፡ ጥበብ ከሰይፍ ከጦር የበለጠ ሀይል አላት ያልኩበት ምክንያትም ይህ ነው፡፡
      ጸሐፊዎች- ገጣሚዎች ስነ-ጽሑፍ ሰዎች ከዚህች ስራ ብዙ ሊማሩ ይገባል፡፡ አንባቢያን ከዚህ መጽሐፍ  ብዙ ነገር ትፈልጋላችሁ፡፡ እናትን ፈልጎ ለማግኘት ቢያንስ ወደ እውነት  ፍለጋ መንገድ የምትመራ ድንቅ መጽሐፍ፡፡ ኤፍሬም ስዩም በእውነት ትችላለህ! የራስን ፍለጋ ጨርሰህ እርፍትህን ሽተህ ሌሎች እንዲፍልጉና እንዲያርፉ ለማድረግ መሞከርህ ያስመሰግንሃል፡፡ እውነትን እንድንይዝ እውቀትን ጥበብን እናገኝ ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን፡፡ እናታችን ጠፍታለች ጭራሽ ደግሞ መገኛዋ ጠፍቶ ላትገኝ ስትዋትት ከማየት ፍለጋው ይጠንከር፡፡በማንም እጅ ስር ተይዛ ሲያሻቸው ሊጨብጧት ሲያሻቸው ሊገነጣጥሏት የሚሹ ሀይሎች አሉና ሁላችንም እንታደጋት፡፡ እናታችን ጠፍታለች፡፡ አፋልጉን ከጠፋች ልክ 38 አመቷ፡፡